Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow "ኦባማ ካሸነፉ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ...
"ኦባማ ካሸነፉ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ... E-mail
Wednesday, 01 October 2008
Image
ዶናልድ ፔይን
"ኦባማ ካሸነፉ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያበቃል"

ዶናልድ ፔይን
"የሚስተር ፔይን አካሄድ ጤነኛ አይደለም"
የኢትዮጵያ መንግሥት

በጌታቸው ንጋቱ

የአሜሪካው ኮንግረስ አባል ዶናልድ ፔይን ባራክ ኦባማ በምርጫ ካሸነፉ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደገና እንደምታጤንና መንግሥታትም በፀረ ሽብርተኝነት ትግል ስም አሜሪካን የሚያሞኙበት ጊዜ ያበቃል ሲሉ ተናገሩ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት "ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ይዘዋል" የሚላቸው የሚስተር ፔይን አካሄድ ጤነኛ እንዳልሆነ ገለፀ፡፡

የኤች.አር 2003 አርቃቂና እንዲጸድቅ በጆርጅ ቡሽ አስተዳደር ላይ ግፊት በማድረግ የሚታወቁት ዶናልድ ፔይን በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚካሄድና ይህም እጅግ እያሳሰባቸው እንደሆነ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ለተሰበሰቡ ኢትዮጵያውያን ገልፀዋል፡፡ ዶናልድ ፔይን ከምርጫ 97 ወዲህ በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ አስከፊ መሆኑንና ባራክ ኦባማ ከተመረጡ ይህንን ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡

ዶናልድ ፔይን በዋሸንግተን ዲሲ ኢትዮጵያውያኑን የሰበሰቡት ለፓርቲያቸው ዕጩ ባራክ ኦባማ የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ሲሆን ኢትዮ-አሜሪካውያን ለኦባማ ድምፃቸውን እንዲሰጡም ጠይቀዋል፡፡ "በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁልጊዜ ያሳስበኛል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያንና የአሜሪካን ግንኙነት የሚያስተካከል ሕግ ማርቀቃችን ይታወቃል፡፡ ባራክ ኦባማ ወደ ስልጣን ሲመጡም የወጣው ሕግ ይፀድቃል፤ ኦባማ ካሸነፉ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያበቃል" ብለዋል፡፡

ዶናልድ ፔይን በውጭ ባሉ ኢትዮጵያውያን ተቃዋሚዎች ዘንድ ተወዳጅና ተሰሚነት ያላቸው ሲሆን፣ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰሩም ተቃዋሚዎቹ ያምኑባቸዋል፡፡ ዴሞክራቶችን በማሳመን የኤች.አር 2003 ሕግ በኮንግረሱ እንዲጸድቅ ያደረጉት ፔይን በቅርቡ ደግሞ ከሌላው የዴሞክራት አጋራቸውና የሴኔት አባል በሆኑት ሩሥ ፌይንጎልድ ተመሳሳይ ረቂቅ ሕግ በኢትዮጵያ ላይ ተዘጋጅቷል፡፡ ምንጫ 97ትን ተከትሎ የተረቀቀውን ሕግ የኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ በሙሉ የሚቃወመው ሲሆን፣ ዶናልድ ፔይንም የአክራሪ ተቃዋሚዎች ጠበቃ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ይገልፃል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የረቂቁን ሕግ የተቃወመ ሲሆን በዴሞክራት ፖለቲከኞች እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችም በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሻክር እንደሆነ ይገለፃል፡፡

ዶናልድ ፔይን በአሁኑ የዋሽንግተን ዲሲ ንግግራቸው ለተቃዋሚ ኢትዮጵያውያን ታላቅ ተስፋና ቃል የመግባት ያህል ነው የተናገሩት፡፡ ዴሞክራቶች የመንግሥትነት ስልጣን ከጨበጡ የኢትዮጵያ ጉዳይ በሌላ ዓይን እንደሚታይ ገልፀዋል፡፡

"በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ አደገኛ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት አይከበርም፡፡ ይህ በጣም ያሳስባል" የሚሉት ዶናልድ ፔይን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ደርሰዋል የሚሏቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ገልፀዋል፡፡ በስብሰባው ላይ ለተገኙት ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸውን መቆርቆር የገለፁት ዶናልድ ፔይን "በኦባማ አስተዳደር የሰብዓዊ መብት እየተጣሰ አይናችንን አንጨፍንም፡፡ አንዳንድ መንግስታት ሽብርተኝነትን እንዋጋለን ብለው ሊያጭበረብሩንም አይችሉም" በማለት የኢትዮጵያን መንግስት ወርፈዋል፡፡

በዶናልድ ፔይንና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ያለው ግንኙነት የሻከረ ነው፡፡ ከዕለት ወደ ዕለት እየተሻሻለ ከመምጣትም ይልቅ በዴሞክራቶችና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ጤናማ ያልሆኑ ምልልሶች በየጊዜው ይሰማሉ፡፡ እንደ ዶናልድ ፔይኔ ፍላጎትና ዕምነት የሪፐብሊካኖቹ አስተዳደር በባራክ ኦባማ ተሸንፎ ዴሞክራቶች ስልጣን ከጨበጡ ይህ ሁኔታ ወዴት ያመራል ለሚለው "እንደ ቡሽ አስተዳደር በፀረ ሽብርተኝነት ትግል ስም የኦባማ አስተዳደር አይሞኝም፡፡ ሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ ሽብርተኝነት በመከላከል ስም ሲታፈኑ የኦባማ አስተዳደር ዝም ብሎ አያይም" በማለት ምላሽ ይሰጣሉ፡፡

ኤስ-3457 የሚባለው የሴናተር ፌይንጎልድ ረቂቅ ሕግ በቅርቡ መቅረቡን ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግሥትና የአሜሪካ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላት ፍጥጫና የቃላት ጦርነት ተጧጡፏል፡፡ ኤች.አር 2003 ሊጸድቅ ነው በተባለበትና ኮንግረሱ ባሳለፈው ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት ረቂቅ ሕጉ ከኢትዮጵያና ከአሜሪካ ዲፕሎማሲ አይበልጥም ብሎ ነበር፡፡ የአሁኑን የፌይንጎልድ ሕግ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት መረር አድርጎ ተቃውሞታል፡፡ ባለፈው ሳምንት ፌይን ጎልድ በጆርጅታውን ዩኒቨርሲቲ፣ ዶናልድ ፔይን ደግሞ በዋሽንግተን ዲሲ ፕሬዚዳንታዊ የቅስቀሳ ዘመቻ ላይ ኢትዮጵያ ላይ ጣታቸውን መቀሰራቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት አልወደደውም፡፡ በሌላ አገር የውስጥ ፖለቲካ አሜሪካውያኑ እየገቡ እንደሆነ እንዲሁም አሁን ሴናተሮቹና የኮንግረስ አባላቱ የያዙት አካሄድ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካን ግንኙነት ሊያበላሸው እንደሚችል መንግሥት ይገልፃል፡፡

ዶናልድ ፔይን ባራክ ኦባማን ለኢትዮጵያ መንግስት ማስፈራሪያነትና ለድምጽ ማግኛነት ሰሞኑን መጠቀማቸውን የኢትዮጵያ መንግስት አውግዘዋል፡፡ በኦባማ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ ለመዘርዘር እና ለመተቸት ፔይን መሞከራቸው እንዳሳዘነው የኢትዮጵያ መንግሥት ገልጿል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ለባራክ ኦባማ ምርጫ ቅስቀሳ በዋሽንግተን ዲሲ ሲሰባሰቡ በዶናልድ ፔይን የተገባላቸው ቃል ኦባማ ሲመረጡ የኢትዮጵያ መንግስት ላይ የአሜሪካ አስተዳደር ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወሰድ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ለማስፈን እየተጣረ ነው፤ መድብለ ፓርቲ ሥርዓት እየተገነባ ነው፤ ነፃ ሚዲያ እያደገ ነው፤ ሠብዓዊ መብት ለመጠበቅ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የእምባ ጠባቂ ተቋምም ተገንብቷል፡፡ ለመሻሻልም ከፍተኛ ዕድል አለ" የሚለው የኢትዮጵያ መንግስት ዶናልድ ፔይን ይህንን ሁሉ አይኔን ግንባር ያድርገው ብለው መካዳቸውንና ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ሰብዓዊ መብት አያያዙ ተስፋ የሚያስቆርጥ መሆኑን መናገራቸውን ተቃውሟል፡፡ ዶናልድ ፔይንም አክራሪ ተቃዋሚዎችን በአሜሪካ ተቀምጠው የሚናገሯቸውን ብቻ ይዘው የኢትዮጵያን መንግሥት ሊተቹ እንደማይችሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ገልጿል፡፡

"ሚስተር ፔይን የእውነት ሰው ቢሆኑና ለሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ መስፈን የሚጨነቁ ቢሆኑ በኤርትራ ተገኝተው የሆነውን ካዩ በኋላ አስተያየት በሰጡ ነበር፡፡ ፔይን በቅርቡ ኤርትራን ጎብኝተዋል፡፡ ኤርትራ ሕገ መንግስት የላትም፡፡ ምርጫም አላካሂድም ብላለች፡፡ በኤርትራ ከአንድ ፓርቲ ሌላ ተቃዋሚ ፓርቲ መመስረት አይፈቀድም፡፡ ነጻ ሚዲያ አይፈቀድም፡፡ የሃይማኖት ነጻነት በኤርትራ የለም፡፡ በዚህም ምክንያት በሁሉም የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ኤርትራ ትወቀሳለች፡፡ የኤርትራ መንግስት 11 ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ባለስልጣናቱን እንዲሁም ጋዜጠኞችን አስሮ እስካሁን እነዚህ ሰዎች የት እንደገቡ አይታወቅም፡፡ ይህም ከሆነ ሰባት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዶናልድ ፓይኔ ግን በኤርትራ ያለውን የሰብዓዊ መብት ቀውስ ለመተቸት ምንም አይነት ፍላጎት የሌላቸው ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ ያሉትን መሻሻሎችና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማጣጣላቸው የሚያሳየው ሚስተር ፔይን ፀረ-ኢትዮጵያ አጀንዳ ይዘዋል" የሚለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የግለሰቡ አካሄድ ጤነኛ እንዳልሆነ ይገልፃል፡፡

ኦባማ ሲመረጡ ነገሮች እንደሚቀያየሩ ዶናልድ ፔይን የተናገሩትን አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰጠው ምላሽ "ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ ንቀት ነው፡፡ ሚስተር ፔይን ስለ ኦባማ ፖሊሲዎች ምን ያህል ጠንቅቀው ያውቃሉ ለሚለው መረጃ የለንም፡፡ ይሁን እንጂ ለሚስተር ኦባማ ድጋፍ ለማሰባሰብ በሚል ከአክራሪ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ያደረጉት ንግግር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ኦባማ ጠብ ይገጥማሉ ብሎ መናገራቸው የወዳጅነት መንፈስ ያለው አይደለም፡፡ የሚስተር ፔይንም ንግግር ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን የሚወዳደሩትን ኦባማን የሚመጥን አይደለም፡፡ ሚስተር ፔይን የኤች.አር 2003 አርክቴክት እንደሆኑ እናስታውሳለን፡፡ ያቀረቡት ረቂቅ የኢትዮጵያን ሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ ያሻሽላል ብለው ቢሆንም ከፍተኛ ትችት ገጥሟቸው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ ረቂቅ ሕጉ ለአሜሪካና ኢትዮጵያ መልካም ግንኙነት የማይበጅ በመሆኑም ተቀባይነት አጥቷል፡፡ ረቂቅ ሕጉ ለአሜሪካና አፍሪካ ግንኙነትም አደጋ ነበረው" ብሏል፡፡

በዴሞክራቶችና በሪፐብሊካን መካከል ያለው የፕሬዚዳንትነት ፍጥጫ የቀጠለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የሁሉም የአለም አገራት ጆሮዎች ወደ አሜሪካ አቅንተዋል፡፡ ኢኮኖሚዋ በቀውስ የሚናጥባት አሜሪካ የውስጥ ኢኮኖሚዋንና የውጭ ግንኙነቷን ለማስተካከል ቀጣዩን ፕሬዚዳንት ትጠብቃለች፡፡ ጆን ማኬይን ወይም ባራክ ኦባማ ከሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት ጀምሮ የአሜሪካ መሪ ይሆናሉ፡፡ ማንም ይመረጥ ማን ግን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የመጀመሪያ ሥራ የአገሩን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ነው፡፡ ይጠቅመኛል ካለው መንግሥት ጋር ይሰራል፤ አይጠቅመኝም ካለው ጋር አይሰራም፡፡ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲም "There is no permanent friend and enemy፤ only national interest is permanent"" ማለትም ቋሚ ወዳጅና ጠላት የለም፤ ቋሚ ብሔራዊ ጥቅም ነው የሚባል እውነታን መሠረት ያደረገ አስተሳሰብ በመኖሩ ኦባማም ተመረጡ፤ ማኬይን ለአገራቸው እንጂ ለሌላ አገር እንደማይሰሩ የሚሰጡ አስተያየቶች አሉ፡፡

አሜሪካ ከኢትዮጵያ የምታገኘው ጥቅም አላት፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ሃያል አገር ተደርጋ የምትቆጠረው ኢትዮጵያ አካባቢውን በኃያልነት ልትመራ የምትችል አገር ተብላ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ጠበብቶች ትጠራለች፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ለመግታትና ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ቀንድ አቻ የሌለው ኃይል ተደርጎ በመቆጠሩ በተለይ የቡሽ አስተዳደር የቅርብ ወዳጅ ሆኖ ሰርቷል፡፡ የቡሽ አስተዳደር ቢቀየርም የአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅምና አሜሪካ አይቀየሩም፡፡ መጪው አስተዳደር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ወደ ጠብ የሚገባው ብሔራዊ ጥቅሙ ከተነካ ብቻ ይሆናል፡፡ ብሔራዊ ጥቅሙ እየተከበረለት ለምን ሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ አላሰፈንክም ብሎ ከጥቅሙ አስበልጦ ለሌላ አገር ሕዝብ ልማትና ዕድገት የሚያስብ መንግሥት ይፈጠራል ማለት በኃይል ፖለቲካና በዓለም አቀፍ ሥርዓት (System and power politics) ቦታ እንደሌላቸው ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ መንግስትና በአሜሪካ መካከል የጥቅም ትስስር የሚላላ ወይም አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር የማይተባበሩት ሁኔታ ከተፈጠረ አለመግባባት አልፎ ተርፎም ወደ ተበላሸ የሁለትዮሽ ግንኙነት የማምራት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ባራክ ኦባማ ቢመረጡ የሚመረጡት ለአሜሪካ ሕዝብ ነው፤ የሚያገለግሉትም የአሜሪካን ሕዝብ፤ ተጠሪነታቸውም ለአሜሪካ ሕዝብ፤ ጥብቅና የሚቆሙትም ለአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የባራክ ኦባማ ፓርቲ የሆነው ዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላትና ባለስልጣኖች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚጣጣሙ አይደሉም፡፡ ዴሞክራቶች ሪፐብሊካኑን ለመቃወም በሚል ብቻ ሳይሆን ከዚያም ባለፈ ምክንያት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተቃቅረዋል፡፡

በምርጫ 97 በዴሞክራቶች የሚመራው የምርጫ ታዛቢ ቡድን ከሌሎች ሁለት ከአሜሪካ ድርጅቶች ጋር ከኢትዮጵያ እንዲወጣ የኢትዮጵያ መንግስት አዟል፡፡ ናሽናል ዴሞክራቲክ ኢንስቲትዩት (NDI) መባረሩንም ተከትሎ ዴሞክራቶች የኢትዮጵያን መንግስት መርዘው ይዘውታል፡፡ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር ለኢትዮጵያ መንግስት መልካም አመለካከት ያላቸው ሲሆኑ፣ የዴሞክራት ፓርቲ አባል ናቸው፡፡ በስልጣን ላይ የነበሩት ሪፐብሊካኖች በአብዛኛው የጆርጅ ቡሽ አስተዳደር በአፍሪካ ቀንድ የሚከተለውን ፖሊሲ የሚደግፉ ሲሆን፣ ዴሞክራቶችም ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ያደንቃሉ፡፡ ሚስተር ፔይን ግን "ማስመሰል ነው" ይላሉ፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆን ማለት የዓለም መሪ፤ የዓለም ቁጥር አንድ ሰው መሆን ማለት በመሆኑ፣ የአሜሪካ የፖለቲካ ለውጥ በየአንዳንዱ አገር የራሱ ለውጥ ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ለውጡ የአሜሪካን ጥቅም ለማስከበር እንጂ የሌላ አገር ሕዝብ እንዳይራብ፣ እንዳይታረዝ፣ መልካም አስተዳደር እንዳያጣ እንዳልሆነና ማንኛውም አገር የራሱን ጥቅም እንጂ የሌላውን አገር ጥቅም እንደማያስቀድም የተጨባጭ ፖለቲካ (realism politics) ተንታኞች ይገልፃሉ፡፡ የአሜሪካ አስተዳደር ለውጥ በኢትዮጵያና በአሜሪካ ግንኙነት ላይ የሚያመጣውም ለውጥ ከጥር ወር በኋላ የሚታይ ይሆናል፡፡
Last Updated ( Thursday, 06 November 2008 )
 
< Prev   Next >