Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ኢሕአዴግ እና ሲ.ሲ.ፒ
ኢሕአዴግ እና ሲ.ሲ.ፒ E-mail
Wednesday, 01 October 2008
ImageImageበጌታቸው ንጋቱ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በሐዋሳ 7ኛ ድርጅታዊ ጉባዔውን ሲያካሂድ የተለያዩ አገራት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጋብዟል፡፡ በሐዋሳው ጉባኤ ላይ የሱዳን ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ፣ የሱዳን ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ፣ የየመን ጄኔራል ኮንግረስ ፓርቲ፣ የሕንድ ናሽናል ኮንግረስ፣ የኡጋንዳ ናሽናል ሬሲስታንስ ንቅናቄ፣ የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር፣ የኤርትራ ዴሞክራሲያዊ ጥምረትና የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ተገኝተዋል፡፡ ከሁሉም ተጋባዥ ፓርቲዎች ግን የብዙዎቹ ቀልብ የገዛውና አስተያየት የተሰነዘረበት የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ (ሲ.ሲ.ፒ) ነው፡፡

የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ (ሲሲፒ) ከኢሕአዴግ ጋር በምን ዓይነት የፖለቲካ አስተሣሰብ ቢገናኝ ነው የፓርቲዎችን ግንኙነት በማጠናከርና ከአንዱ ሌላው ይማራል በሚል የተጠራው በሚል አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፡፡ ሲሲፒ የቻይና ብቸኛ ገዢ ፓርቲ ነው፡፡ በቻይና ምርጫ አይካሄድም፡፡ ለቻይና ሕዝብ የማውቀልህ እኔ ብቻ ነኝ ይላል ሲሲፒ፡፡ የሚያራምደው ርዕዩተ ዓለምም በሶሻሊዝም መሥመር የተቃኘ ነው፡፡ ሲሲፒ ቻይናዊያን ቢቢሲ እና ሲ.ኤን.ኤን እንዲመለከቱ አይፈቅድም፡፡ ፓርቲው የቻይና ብቸኛ  ፓርቲ በመሆን ለዓመታት አገሪቱን እየመራ ይገኛል፡፡ ከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈፅም አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይገልፃሉ፡፡ የቤጅንግ ኦሎምፒክ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ሳቢያ ከምዕራባዊያን አገራት ከባድ ፈተና ገጥሞት ነበር፡፡ ቻይና ነፃ ሚዲያ አትፈቅድም፤ ሲሲፒ ላይ ትችት የሰነዘረ ሁሉ ወደ እስር ቤት ይወረወራል፤ ይገደላል፡፡ ሲሲፒ ፈርጠም ያለ ጡንቻ ያለው በመሆኑም ለማዕቀብና ለምዕራባዊያን ትችት አይንበረከክም፡፡

ኢሕአዴግ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ እንደሚመራ ይገልፃል፡፡ መድብለ ፓርቲ ስርዓት ስለሚፈቅድም በአገሪቱ ይብዛም ይነሥ፤ ጠንካራም ይሆኑ ደካማ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ኢሕአዴግ ነፃ ፕሬስ እንዲኖር ይፈቅዳል፤ የፕሬስ ነፃነቱ ምን ያህል ነው የሚለው የሚያግባባ ባይሆንም፡፡ ኢሕአዴግ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ይቀበላል፤ እንደማያከብራቸው በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቢወቀስም የሰብዓዊ መብት አያያዙን ለማሻሻል እንደሚጥርና ችግሮች እንዳሉ እንደሚያምን ይገልፃል፡፡

ኢሕአዴግና ሲሲፒ ሁለቱም ፓርቲዎች በተለያየ ደረጃም ቢሆን የሶሻሊዝምን ፅንሰ ሃሳብ ያራምዳሉ፡፡ ኢሕአዴግ ከምዕራብያዊያን ዴሞክራሲና የነፃ ገበያን በተወሰነ መልኩ ይወስዳል፤ አብዮታዊ በመሆኑም ወደ ሶሾሊዝም የሚያደላበት ሁኔታ ይታያል፡፡

የተቃውሞ ፖለቲካም በሲሲፒ ዘንድ ቦታ የለውም፡፡ ሲሲፒ በጠቅላላ የፓርቲ ፕሮግራሙ ላይ እንደሚያመለክተው "ፓርቲው የቻይና የሰራተኛ ክፍል፣ የቻይና ሕዝብንና ቻይናን የሚጠብቅ ነው፡፡ ሶሻሊዝም ቻይናዊ መልክ ይዞ እንዲመራም ማዕከላዊ አመራር ይሰጣል፡፡ ኮሙኒዝምን ማስፈንም የፓርቲው ከፍተኛው ሕልምና ታላቁ ግብ ነው" ይላል፡፡ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ማርክሲዝም ሌኒንዝምን ይቀበላል፤ የማኦ ዜዶንግ አስተሳሰብ የፓርቲው ነፍስ ነው፣ የዴንግ ዥያኦፒንግ ፍልስፍናም የፓርቲው መሰረት ነው፡፡ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲም የሚገለፀው በነዚህ ሶስት ፍልስፍናዎች ነው፡፡

ማርክሲዝም ሌኒንዝም የሰው ልጅና የማኅበረሰብን የዕድገት ታሪክ ስለሚያስተምርና የቻይና ኮሙኒዝም ሊረጋገጥ የሚችለው ሶሻሊስታዊ ማኅበረሰብ ሲመሰረት ብቻ በመሆኑ በሲሲፒ የሕልውና መሰረት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሲሲፒ የማርክሲዝም ሌኒዝምን መሰረተ ሃሳብ በመውሰድ ከቻይና ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር አጣጥሞ እንደሚቀበል ያስረዳል፡፡

የቻይና ኮሙኒስቶች ሁሉ መሪ የነበሩት ማኦ ዜዶንግ ማርክሲዝም ሌኒንዝምን ከቻይና አብዮት ጋር በማዛመድ የማኦ ዜዶንግ ፍልስፍናን ፈጥረዋል፤ ይህም የሲሲፒ መመሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሲሲፒ እንደሚያምነው ማኦ የቻይናን አብዮትና ግንባታ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ አስቀመጠዋል፤ ፓርቲውም በዚያው በመመራት አገሪቱን ወደ ልማት እንደመራት ያስረዳል፡፡ ሲሲፒ በማኦ መመሪያ መሰረት "ኢምፔሪያሊዝም፣ ፊውዳሊዝም፣ ቢሮክራት ካፒታሊዝምን በመዋጋት ሶሻል ዴሞክራሲን እናሰፍናለን" ይላል፡፡

ሶሻል ዴሞክራሲ ማለት ማርክስ በጀርመን ውስጥ እንዲፈፀም አስቦት የነበረ ከሶሻሊዝምና ከሊብራሊዝም (ዴሞክራሲ) ቆንጥሮ በመውሰድ ተቀምሞ የተሰራ ነው፡፡ ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ (Revolutionary Democracy) የሚለውን ከሲሲፒ ሶሻል ዴሞክራሲ (Social Democracy) ጋር የሚያነፃፅሩም አሉ፡፡

ሲሲፒ ሶሻል ዴሞክራሲ ያስፈልጋል ሲል ሕዝቦች ሲሲፒ ከሚያስበው ውጭ እንዲያስቡ አይፈልግም፡፡ ሌላ ፓርቲና የፖለቲካ አመለካከት ሁሉ የቻይና ሕዝብ መጥፊያ ናቸው ይላል፡፡ ለኢሕአዴግ ግን ሌሎች ፓርቲዎች እንዲኖሩ ታግለውት እንዲያሸንፉት በሕግ ይፈቅዳል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን "ኢሕአዴግ የምዕራባውያንን ግፊት ስለማይችለው እንጂ በውስጡ ለተቃውሞ ፖለቲካ ቦታ የለውም፡፡ እንደ ሲሲፒ ሁሉ ተቃዋሚዎች እንዲኖሩ አይፈልግም፤ ይሁን እንጂ ይህንን በግልፅ ሳይናገር እየገነባ ያለው የአንድ ፓርቲ ስርዓት ነው፡፡ እንደ ልባችን መንቀሳቀስ አንችልም፤ ሕዝቡን በሙሉ የአንድ ፓርቲ አባል ሊያደርገው ነው፡፡ ተቃዋሚነታችን ለይስሙላ እንጂ አሁን ባለው አያያዝ መቼም ቢሆን ኢሕአዴግ ስልጣን ከጁ እንዲወጣ አያደርግም፡፡ ይህ ደግሞ የአንድ ፓርቲ ሥርዓት መገለጫ ነው" ይላሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ግን የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ኃይሎች የሚያስተናግድበት የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መመሥረቱን ይገልጻል፡፡ ይሁን እንጅ ፓርቲው የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ከሌሎች ራሳቸውን ሊበራል ነን ከሚሉት እንደሚለይ ይገልፃል፡፡

በአንድ አገር ውስጥ የተለያዩ ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ ፓርቲዎች ሊኖሩ ይኖራሉ፡፡ በአብዛኞቹ ዴሞክራሲያዊ አገራት ሶሻሊዝምን የሚከተሉ ፓርቲዎች ይኖራሉ፡፡ በአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቲዎች ያሉ ሲሆን በአገሪቱ ለሥልጣን መቼም እንደማይበቁ ይታወቃል፤ ግን መንቀሳቀስ ይችላሉ፡፡ በሶሾሊዝም አራማጅ አገሮች ሲጀመር የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋምና የተለያዩ የፖለቲካ አቋም መያዝ አይፈቀድም፡፡ በኩባና በቻይናም ይህ እስካሁን ድረስ ተግባራዊ ሆኗል፡፡

ኢሕአዴግ ሲሲፒን በ7ኛ መደበኛ ጉባዔው ላይ ሲጋብዝ የፓርቲው ተወካይም በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ቃል ገብተዋል፡፡ አንደኛው በሌላኛው ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገቡና በወንድማማችነት ሁለቱ ፓርቲዎች ልምድ ሊቀሳሰሙና ሊማማሩ እንደሚችሉ ተወካዩ በጉባኤው ላይ ባሰሙት ንግግር ገልፀዋል፡፡

ኢሕአዴግ ከሲሲፒ ምን ሊማር ይችላል? የሚለውን ስናይ ሲሲፒ መድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ስለማይቀበል የመጀመሪያው ትምህርት የሚሆነው የአንድ ፓርቲ የበላይነት መማር ሊሆን ነው፡፡ ሲሲፒ የሊበራሊዝም አመለካከት የሆነው ግለሰባዊ ነፃነትና የሰብዓዊ መብት መከበርን ሳይሆን የሕዝብ አንድነትና ዕድገት ይደግፋል፤ የሕዝብን አንድነት ሊያፈልሱ የሚችሉ ሚዲያዎች በተለይም የምዕራባዊያን ሚዲያዎች ዓይነት አይፈቅድም፡፡ የቻይና መንግሥት የሚዲያዎችንና ኢንተርኔትን በማገት በዓለም የሚስተካከለው የለም፡፡ ሂዩማን ራይትስ ወች በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ማገት ሥራ መጀመሩዋን ይገልፅና ይኸም የቻይና የቴሌኮሙኒኬሽን ኩባንያዎች ወደ አገሪቱ ከገቡ በኋላ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ሲሲፒ ሕዝቡ መስማትና ማየት ያለበትን ይመርጣል፡፡ የሲሲፒው ተወካይ በኢሕአዴግ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ልምድ ለመለዋወጥ እንደሚፈልጉ መግለፃቸውና ለኢሕአዴግ ያላቸውን አጋርነት መናገራቸው ለአቅመ ቢሶች የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች የልብ ትርታ ይጨምርባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያና ቻይና እንዲሁም ቻይና እና አፍሪካ እስካሁን ድረስ ያላቸው ግንኙነት የኢኮኖሚያዊ ትስስር ቢመስልም በሌሎች አገራት የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ የማትገባው ቻይና በፓርቲ ደረጃ ከኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ ጋር በትብብር ለመስራት ማቀዷ የመጀመሪያው ፖለቲካዊ እርምጃ ሊሆን ይችላል፡፡

ኢሕአዴግ እንደ ሲሲፒ በአንድ ፓርቲ ስርዓት አያምንም፤ መድብለ ፓርቲ ስርዓት ይስፈን ይላል፤ ተቃዋሚዎች ግን ኢሕአዴግ ከስም ተቃዋሚነት እንድናልፍ አይፈልግም፤ ለታይታ ነው ይላሉ፡፡ ገዢው ፓርቲ በበኩሉ ተቃዋሚዎች በፓርላማ ቁጥራቸው መብዛቱ፣ አልተጠቀሙበትም እንጂ በ97 ምርጫ የአዲስ አበባ አስተዳደርን ሙሉ በሙሉ ተቃዋሚዎች ማሸነፋቸውን ፓርቲው ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ የቆመ መሆኑን እንደሚያሳይ ይገልፃል፡፡ ተቃዋሚዎች ግን በኢትዮጵያ ያለው መድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታው ቀርቶ ግብዓተ መሬቱ እየተፈፀመ መሆኑንና ኢሕአዴግም በተለይ ከምርጫ 97 ወዲህ ወደ ፍፁም የአንድ ፓርቲ ሥርዓት መቀየሩን ይገልፃሉ፡፡

የሲሲፒ ፕሮግራም እንደሚያሳየው የቻይና ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችን በአንድ ላይ በማጣመርና በራሳቸው እንዲተማመኑ በማድረግ በባህሏ የበለፀገች፣ ዘመናዊ ሶሻሊስት ቻይናን መፍጠር የፓርቲው መሰረታዊ መነሻ ነው፡፡ ለዚህም አራት ዋና መርሆዎች በማንሣት ነው እነዚህ መርሆዎችም የሶሻሊዝም ሥርዓትን መከተል፣ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ አምባገነን እንዲሰፍን ማድረግ፣ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ አመራርን ማጠናከርና የማርክሲዝም ሊኒንዝምና የማኦ ዜዶንግ አስተሳሰቦችን ማክበርና ማስፈፀም ናቸው፡፡

ኢሕአዴግ የስልጣኑ መነሻዎችና መርሆዎች ያደረጋቸውና አወቃቀሩንም ያስቀመጠው በብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት ላይ ነው፡፡ የአገሪቱን ልማት ማረጋገጥ የፓርቲው መሪ አጀንዳ ነው፡፡ ሲሲፒ የኢኮኖሚ ልማት የመጀመሪያ ሥራ ሆኖ ሌሎች የሚሰሩ ሥራዎችና የሚወሰዱ እርምጃዎች የኢኮኖሚ ልማቱን የሚደግፉ መሆን አለባቸው ይላል፡፡ ኢሕአዴግም የአገሪቱ ልማት የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርና በኢንዱስትሪ እያገዙ መሄድ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫው እንደሆነ ይገልፃል፡፡

ሲሲፒ ከምንም በላይ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ትኩረት እንደሚሰጥና ይህም የቻይናን ኢኮኖሚ በጥሩ ሁኔታ፣ በከፍተኛ ፍጥነትና ጥራት እንደሚያሳድግ ይገልፃል፡፡ ኢሕአዴግም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገሪቱ ተማሪዎች ከ70 በመቶ ያህሉ መሰልጠን ያለባቸው በሳይንስና ቴክኖሎጂ መስኮች መሆን እንዳለበትና አገሪቱም ለልማት የሚያስፈልጋትን የሰው ሀይል ከዚህ ማግኘት እንደምትችል ይገልጻል፡፡

ሲሲፒ ሕዝቡን በመምራት ሶሻሊዝምን እንደሚሰብክና ሶሻል ዴሞክራሲ በአገሪቱ እንዲሰፍን እንደሚያደርግ ይገልጻል፡፡ ቻይና ሶሻል ዴሞክራሲም ለምዕራባውያን ካፒታሊዝምና ሊበራሊዝም የማይንበረከክ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ኢሕአዴግ ሙሉ በሙሉ ሊበራሊዝምን አይቀበልም፤ በደምሳሳውም አይቃወምም፡፡ የሊበራል ፅንሠ ሃሳብ የሆኑትን ሰብዓዊ መብት፣ ነፃ ፕሬስ፣ ነፃ ገበያ፣ ምርጫ እና ሌሎችንም ኢሕአዴግ ይቀበላል፡፡ ሲሲፒ ግን በውስጡ ከሚያደርገው የፓርቲ አመራር ምርጫ በስተቀር ሕዝቡን በምርጫ አሳትፎ አያውቅም፡፡

ኢኮኖሚን በተመለከተ ሲሲፒ ገበያውን መክፈት እንደሚያስፈልግ ሲገልጽ ያለውንም የገበያ ስርዓት ሶሻሊስት ነፃ ገበያ (Socialist free market) በማለት ይጠራዋል፡፡ ኢሕአዴግ የግል ባለሃብቱ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ያለውን ረዳትነት ሲቀበል፣ መንግሥት በተወሰነ ደረጃ ከገበያው መውጣትና አቅርቦትና ፍላጎት ኢኮኖሚውን የሚመሩበት ዕድል እንዲሰጣቸው ያደርጋል፡፡ መንግሥትም ቁልፍ በሆኑ የንግድ ሥራዎች ላይ እጁን እንዲያስገባ ኢሕአዴግ ይፈልጋል፡፡ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መርህ የምዕራባዊያን የፋይናንስ ተቋማት የኢትዮጵያ መንግሥት ከቴሌኮሙኒኬሽንና ከመሣሠሉት ሥራዎች እንዲወጣ ቢጠይቁም መንግሥት ግን ሙሉ በሙሉ ነፃ ገበያን መከተል እንደማይቻል ያምናል፡፡ ይህንንም ከቻይናው ሶሻሊስት ነፃ ገበያ ጋር ማነፃፀር ይቻላል፡፡

ኢሕአዴግና ሲሲፒ የሚመሣሉባቸውና የሚለያዩባቸው የተለያዩ መርሆዎችና አስተሳሰቦች ቢኖሩም ፓርቲዎቹ አብረው ለመስራትና ለመማማር አስበዋል፡፡ ማን ከማን ምን ይማራል? የሚለው ግን ቀስ ተብሎ የሚታይ ይሆናል፡፡

የሲሲፒ አባላትና አመራሮች ራሳቸውን "ጓድ" በመባባል ይጠራራሉ፡፡ ኢሕአዴግም የሶሻሊስትን ፅንሰ ሃሳብና አመለካከት የሚመለከተውን ይህንኑ "ጓድ" መባባል በ7ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ በይፋ ተጠቅሞበታል፡፡ ኢሕአዴግ በሶሻሊዝምና በዴሞክራሲ አስተሳሰቦች መካከል ሆኖ "ጓድ" መባባሉን በገሃድ መጠቀም መጀመሩም የተለያዩ አስተያየቶቹን አሰንዝሯል፡፡
Last Updated ( Thursday, 02 October 2008 )
 
< Prev   Next >