| ኃይሌና በርሊን ተግባብተዋል |
|
| Wednesday, 01 October 2008 | |
የዓለም ማራቶን ክብረ ወሰንን ሰበረ በጀርመን መዲና በርሊን ባለፈው እሁድ በተካሄደው 35ኛው በርሊን ማራቶን ኃይሌ ገብረሥላሴ አዲስ የዓለም ክብረወሰን በማስመዝገብ አሸነፈ፡፡ በሴቶች ጀርመናዊቷ ኢርና ሚኬቲንኮ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች፡፡ የዓለም ማራቶን ክብረወሰን ባለቤት ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ በበርሊን ማራቶን አዲስ የዓለም ክብረወሰን ማስመዘገብ የቻለው፣ የዛሬ አመት በራሱ ተይዞ የነበረውን ሰዓት በ27 ሰከንድ አሻሽሎ ርቀቱን 2፡03፡59 በመግባት ነው፡፡ በ35ኛው የበርሊን ማራቶን ኃይሌና በሴቶች ያሸነፈችው ኢርና ሚኬቲንኮ አስደናቂና አስገራሚ ብቃት አሳይተው፣ አሸናፊ መሆናቸው የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማኅበር (አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ) ዘገባ አመልክቷል፡፡ አንድ ሚሊዮን ጀርመናውያን በተከታተሉት የበርሊን ማራቶን፣ ኃይሌ አዲስ የዓለም ክብረወሰን ያስመዘገበው በራሱ ተይዞ የነበረውን ሪከርድ 27 ሰከንድ አሻሽሎ የገባ የመጀመሪያው ሯጭ ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ በሴቶች ያሸነፈችው ጀርመናዊቷ ኢርና ሚኬቲንኮ በበርሊን ነዋሪ ታላቅ ድጋፍ በመታገዝ በርቀቱ 4ኛውን የዓለም ፈጣን ሰዓት አስመዝግባለች፡፡ ሚኪቴንኮ እስከ ዛሬ በሴቶች በአማካይ ተይዞ የቆየውን 2፡20 ሰዓት 2፡19፡19 በማጠናቀቋ የመጀመሪያዋ ጀርመናዊት አትሌት ለመሆን በቅታለች፡፡ በዓለም ካሉት ፈጣን የማራቶን ሯጮችም ሰባተኛዋ መሆን እንደቻለች ዘገባው አመልክቷል፡፡ ከሴቶች ማራቶን ፈጣን ሯጮች ውስጥ እንግሊዛዊቷ ባለ ሪከርድ ፓውላ ራዲክሊፍ፣ ኬንያውያኑ ካተሪን ንዴሪባ እና ሚዙኪ ኑጎቺ ይገኙበታል፡፡ "የርቀቱ ታላቅ ሰው" በሚል የዓለም መገናኛ ብዙሃን የዘገቡለት ኃይሌ 42.195 ኪሎ ሜትር የሸፈነውን በርሊን ማራቶን ሲሮጥ የቅርብ ተፎካካሪዎቹ የነበሩት ኬንያውያኑ ጀምስ ኬዋምባይ እና ቻርልስ ካማቲ ነበሩ፡፡ የውድድሩ መጠናቀቂያ ጊዜ እየቀረበ በሄደ ቁጥር ግን ካማቲ ኃይሌንና ኬዋምባይን መቋቋም ሳይችል ቀርቶ ወደ ኋላ ሊቀር መገደዱ ተገልጿል፡፡ በውድድሩ ሁለተኛ የወጣው ኬምባይ ግን ርቀቱ ሊጠናቀቅ 5 ኪሎ ሜትር ሲቀረው፣ ኃይሌን በቅርበት መከተል ሳይችል ቢቀርም ያስመዘገበው ሰዓት ከዓለም ፈጣን ሰዓት አንዱ ሆኖ ተመዝግቦለታል፡፡ ርቀቱን 2፡05፡34 ሰከንድ አጠናቋል፡፡ ቻርልስ ካማቲ በበኩሉ ውድድሩን ሶስተኛ ወጥቶ ያጠናቀቀው 2፡07፡48 ሰከንድ በሆነ ጊዜ ነው፡፡ በማራቶን ታሪክ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በፈጣን ሩጫ በተጠናቀቀው በርሊን ማራቶን፣ ኃይሌና አራት ፔስ ሜከሮች (አሯሯጮች) እንዲሁም ሁለቱ ኬንያውያን ሩጫውን የጨረሱት እጅግ ፈጣን በሆነ ጊዜ ሲሆን፣ ኃይሌ ፔስሜከሮቹን ቆራርጦ ማለፍ የጀመረው ከግማሽ በኋላ እንደነበረ ተገልጿል፡፡ ከውድድሩ በኋላ ኃይሌ ስለ አሯሯጮቹ ተጠይቆ "ትልቅ ስራ ሰርተዋል" ሲል በተለይ እስከ መጨረሻው አካባቢ የቆየውን አቤል የተሰኘ ኬንያዊ አሯሯጩን "ጠንካራ አትሌት" ሲል ገልጾታል፡፡ ኃይሌ እስከመጨረሻ የተፎካካሪውን ስለ ኬዋምባይ ተጠይቆ "ይህን ያህል ጠንካራ ሯጭ ይሆናል ብዬ አልገመትኩም ነበር" ብሏል፡፡ ውድድሩ ሊጠናቀቅ 5 ኪሎ ሜትር ሲቀረው ያልተጠበቀ ኃይል በመጨመር ኬዋምባይን ያመለጠው ኃይሌ በበርሊን ማራቶን፣ ለብሶ የሮጠውን 27 ቁጥር መለያ የዓለም ገዳም ቁጥር ሲሉ ጋዜጠኞች መዘገባቸውን መረጃው አመልክቷል፡፡ ኃይሌ እስከአሁን 19 ይፋዊ (ኦፊሻላዊ) ሪከርዶች ሲኖሩት፣ ሰባት ይፋዊ ያልሆኑ (አንኦፊሻላዊ) ሪከርዶች ባለቤት መሆኑም ተገልጿል፡ |
|
| Last Updated ( Thursday, 02 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |