Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow "መንግሥት የእኛን ሐሳብ ይቀበል...
"መንግሥት የእኛን ሐሳብ ይቀበል... E-mail
Wednesday, 01 October 2008
"መንግሥት የእኛን ሐሳብ ይቀበል ሳይሆን ችግሩን አጣርቶ የሚወስነውን ለመቀበል ዝግጁ ነን"

አቶ አህመድ ያሲን

አቶ አሕመድ ያሲን ከስምንት ወራት በፊት ጀምሮ አዲስ በተመረጠውና ፊፋ (የዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር) እውቅና ያልሰጠው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴን በፕሬዚዳንትነት ይመሩታል፡፡ በወቅታዊው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሁኔታና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ ደረጀ ጠገናው አነጋግረናቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በእርስዎ የሚመራው የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ስለ እገዳው አስተያየቱ ምንድ ነው?

አቶ አህመድ፡-
በአሁኑ ሰዓት እየሰራን ያለው ፊፋ፣ በኢትዮጵያ ላይ ስለጣለው እገዳ ብቻ አይደለም፡፡ የፊፋ ጉዳይ ለእኛ አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ ሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ላለፉት አርባ አመታት ያለ ስርዓት፣ ያለ ራዕይ፣ ያለ እቅድና ያለ አቅጣጫ ይመራ የነበረው መስመር ሊይዝ ይገባል፡፡ ይህ ሥራ አስፈፃሚም፣ ላለፉት ስምንት ወር ሲንቀሳቀስ የቆየው ይህን ለማስተካከልና መስመር ለማስያዝ ነው፡፡ የፊፋን ጉዳይ ከተጠቀሱት እንደ አንዱ ነው የምንመለከተው፡፡

ሪፖርተር፡- እገዳው እስከዚህ ጉዳት አያመጣም እያሉ ነው?

አቶ አህመድ፡-
እንደዚያ ማለቴ አይደለም፡፡ የፊፋን ጉዳይ መፍታት እንዳለ ሆኖ ለማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የፊፋን ጉዳይ ብቻ ይዘን ብንቀጥል ኖሮ ሥራ አንሰራም ነበር፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ሥራ ስንጀምር በተለይ ከ2001 ጀምሮ ግብ ያለው ሥራ ለመስራት የመጀመሪያ ዓላማችን ፌዴሬሽኑ መስመር ይዞ እንዲቀጥልና ተቋሙ በሁለት እግሩ የሚቆም ተቋም እንዲሆን ነው ጥረት ስናደርግ የነበረው፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋማዊ ሥራ መስራት ሕግ ከማስከበርና ማክበር ጋር ምን ያገናኘዋል?

አቶ አህመድ፡-
ማንም ከሕግ በላይ ልሁን ያለ የለም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የፊፋ ጉዳይ ነው ተብሎ፣ ውዝግቡ ቢፈታ፣ የኢንተርናሽናል ተሳትፎዎችን የበለጠ ጠንካራ የሚሆነው የፌዴሬሽኑ የውስጥ አሰራር ስርዓትና መስመር ሲኖረው ነው፡፡ የውስጥ ስራው ካላማረ ኢንተርናሽናል ተሳትፎ ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ሊሰሩ የሚገባቸውን ሥራዎች የስትራቴጂ ፕላን አውጥተን ትግበራ ውስጥ ገብተናል፡፡ ይህም የፋይናንስ፣ የቅጥር፣ የአስተዳደርና የመረጃ አያያዝ የሚባሉት የውስጥ አሰራሮች በውጭ ሙያተኞች ተጠንቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡ ለዚህም የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ሰነድ ቀርቧል፡፡ የዓመቱ በቅርቡ በተካሄደው ጉባኤ ፀድቋል፡፡ ከፊፋ ጋር በተያያዘ በእናንተም ጋዜጣ ያየሁት ሁለት ቡድኖች መኖራቸውን ነው፡፡ በእርግጥ በጋዜጣው የሚሰፍሩት ጉልበት ያላቸውና ፖሊሲ አውጪ የሆኑ ነገሮች ቢሆኑም፣ አሁን ግን ገንቢ ሐሳብ አላየሁበትም፡፡ ይህን ስል ራሴን ለመከላከል አይደለም፡፡ ሁለት ቡድን የለም፡፡ ካለስ መገለጫው ምንድ ነው? የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማኅበር ነው፡፡ አባላቶቹ ናቸው ባለመብቶቹ፡፡ ከነዚህ አካላት ውጭ መሆን አይቻልም፡፡ ፊፋ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እውቅና መስጠት እንጂ ባለመብት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ፊፋም እኮ ማኅበር ነው፡-

አቶ አህመድ፡-
ነው፡፡ ይሁንና ለአንድ ብሔራዊ ፌዴሬሽን ባለቤቱ አባላቱ ሆነው እያሉ የእነሱን ውሳኔ ተቀብሎ እውቅና መስጠት ሲገባው፣ የለም ትክክል አይደለችም ሊላቸው አይገባም፡፡ እኛም ጥሪ ያደረግነው ለዚሁ አካል ነው፡፡ የቱ ጋር ነው ሁለት ቡድን አለ የሚባለው ጉባኤው ስልጣን የለውም ነው? እያንዳንዱ አሰራር በግልጽ የተከናወነ ነው፡፡ እገሌ ውጣ እገሌ ግባ አልተባለም፣ በጉባኤው የቀድሞዎቹ የሚልኳቸው ጭምር ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ይህ ጉባኤ በጋራ ተነጋግሮ በጋራ ወስኗል፡፡ ሁለት ቡድን የሚባል የለም፡፡  

ሪፖርተር፡- ክፍፍሉ፣ ይኸው ጠቅላላ ጉባኤ ያስቀመጠው ሕጋዊ አካል አለ፤ የለም የሚል ነው?

አቶ አህመድ፡-
ሕጋዊ አካል ነው፣ አይደለም፣ ወደሚለው ከመሄዳችን በፊት እኔ ላረጋግጥ የምፈልገው ራስን በመደበቅ በስልጣን ለመቆየት የምናደርገው አንዳችም ነገር አለመኖሩን ነው፡፡ እስካሁን ሁለት ጊዜ የጉባኤው አባላት ተሰብስበዋል፡፡ አንደኛው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ፣ ሁለተኛው መደበኛው ማለት ነው፡፡ ይኸው ጉባኤ በሙሉ ድምጽ ያፀደቀውን ነው እያስፈፀምን ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሕግ ተላልፋችኋል ተብላችኋል፡፡

አቶ አህመድ፡- መሠረታዊ ጥያቄ ይኸው ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ የሚታማው መንግስት ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ ሁለቴ በአንድ ጉዳይ ላይ መሳሳት አልፈለገም፡፡ መጀመሪያ አምቦ ላይ እርግጠኛ ባልሆንም ተሳስቷል ተብሏል፡፡ በወቅቱ የክለቦችም ትብብር ነበርና ሕግ ተጥሷል የሚለው አካል ጉዳዩን ወደ ፊፋ በመውሰዱ ያሁኑ ተመሳሳይ ውሳኔ ሊያስወስን ችለዋል፡፡ በዚህኛው ግን መንግሥት ዳግመኛ መሳሳት አልፈለገም፡፡ አባላቱም ጥንቃቄ በተመላበት አካሄድ ነው የወሰኑት፡፡

ሪፖርተር፡- ጉባኤው መጀመሪያ ኃላፊነቱን የሰጠው አካል ጉባኤውን እንዲጠራ ለምን አልተደረገም?

አቶ አህመድ፡-
ይህ ጉዳይ የጠቅላላ ጉባኤው እንጂ የሥራ አስፈፃሚው አይደለም፡፡ ጥያቄው መቅረብ ያለበትም ለጉባኤው ነው፡፡ የእኛ ኃላፊነት በችግሩ ዙሪያ ጉባኤው ውሳኔ እንዲሰጥ ጉዳዩን ማቅረብ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞ አመራር ጉባኤውን እንዲጠራ በእናንተ በኩል ሐሳብ ቀርቧል?

አቶ አህመድ፡-
ይህም ቢሆን የጉባኤው ስልጣን እንጂ የእኛ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የጉባኤው ፍላጎት ከሆነ ጉባኤውን የቀድሞ ይጥራ አይጥራ የሚለው የእርሱ ውሳኔ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞው ጉባኤውን ይጥራ የሚለው አግባብ አይደለም?

አቶ አህመድ፡-
ቢሆንም የሰጠሁህን ኃላፊነት በአግባቡ አልተወጣህም ካለ ማውረድም የሚችለው ይኸው አካል ነው፡፡ አሁን የተጠቀመውም ይህንኑ ስልጣኑን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ስልጣን ለማምጣት ደንብ እንዳለ ሁሉ፣ ለማውረድስ አያስፈልግም? የፊፋ ጥያቄም ይህ ነው፡-

አቶ አህመድ፡-
ፊፋ ይበል እንጂ ጉባኤው በደንቡና በሕጉ መሠረት ነው የቀድሞውን ያነሳነው፡፡ ያንን ሲያደርግ ፊፋን ናና ታዘብ ብሎ ነው፡፡ ይህንን ያለው እኔ ሳልሆን ጉባኤው ራሱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞ ጉባኤውን ጠርቶ ጉባኤው ደግሞ አልፈልግህም ብሎ ለማውረድ ችግር አለው?

አቶ አህመድ፡-
ይህም ቢሆን የጉባኤው ውሳኔ እንጂ የእኛ አይደለም፡፡ እኛ ሁሉንም አቅርበናል፡፡ እንዲያውም ጉባኤ ተብየው ተብለሃል፡፡ ምን ትላለህ፡፡ ያለህም ፊፋ ነው፣ ብለን አጀንዳውን አቅርበናል፡፡ ወስን ብለን ጠይቀናል፡፡ ጉባኤው ደግሞ የለም አልተሳሳትኩም የወሰንኩትም በትክክል ነው፡፡ መብቴም ስለሆነ ይከበርልኝ አለ፡፡ ሁለት ጊዜ ተገናኝቶ ተመሳሳይ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ ስለዚህ ጠቅላላ ጉባኤውን መጥራት ብቻ ሳይሆን፣ የጉባኤው ፍላጎት ከሆነ የቀድሞ አመራር ቢሮውን ይረከብና ይምራ ቢል እንኳ ደስተኞች ነን፡፡ ስለዚህ አጀንዳው እኛ ጋር ሳይሆን ጠቅላላ ጉባኤ ጋር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተገቢና ሕጋዊ አካሄድ ነው?

አቶ አህመድ፡-
ትክክል ነው ብሎ የጉዳዩ ባለቤት ካመነ፣ የለም ተሳስተሃል ልንለው የምንችልበት አግባብ ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ጉባኤው አልተሳሳትኩም፣ ያለመሳሳቴንም መጥቶ የፈተሸኝ ሰው የለም፣ እያለ ነው፡፡ ዝርዝር ውስጥ መግባት ባልፈልግም፣ መጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤውን የጠራው የቀድሞ አመራር ነው፡፡ አጀንዳ አላሲዝም በሚል ጉባኤውን በትኖ እስከወጣ ድረስ፡፡ ስለዚህ ፊፋ ከውሳኔ በፊት ችግሩ ምንድ ነው ብሎ ማጣራት ነበረበት እያለ ነው ጉባኤው፡፡

ሪፖርተር፡- ፊፋማ ከማላውቀው አካል ጋር አልነጋገርም ብሏል፡-

አቶ አህመድ፡-
ፊፋ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ እንዴት አላውቅም ይላል፡፡ ሊልም አይችልም፡፡ ጉባኤው የምመርጠውን አካል ማንሳትም፣ ማስቀመጥም ያለብኝ እኔ እንጂ ፊፋ አይደለህም፣ ያንተ ኃላፊነት እውቅና መስጠት ነው እያለ ነው፡፡  ስለዚህ ጉዳዩ ፊፋና ጠቅላላ ጉባኤው መካከል ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- በምክንያት እየኖርን አይመስልዎትም?

አቶ አህመድ፡-
በፍፁም፡፡ ነገሩን ከስሜታዊነት ነፃ ሆነን ከተመለከትነው፡፡ ምክንያት እዚህ ውስጥ ስፍራ የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ ታግዳለች?

አቶ አህመድ፡-
በእኛ እምነት በዚሁ ጋዜጣ ላይ ባለፈው ሳምንት በተገለፀው መሠረት መንግስት ዝም ብሎ ማየት የለበትም እንላለን፡፡ ጉዳቱ አገራዊ ሆኗል፤ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ አጀንዳ ተቀርፆላታል፡፡ መነጋገሪያ ሆናለች፡፡ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ውሳኔ ያስፈልገዋል፡፡ ምክንያቱም፣ በቀድሞ አመራር ውስጥ አስራ አንድ ሰዎች ነበሩ፡፡ የቀረው አንድ ሰው ነው፡፡ አስሩ እንዴት ለቀቁ የሚለው ራሱ አነጋጋሪ ነው፡፡ ከአስራ አንዱ አብዛኛው ችግሩን ተናግረው መልቀቃቸው ሊታይ ይገባዋል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የግል ድርጅት አይደለም፡፡ ማሕበር ነው፡፡ የክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎች አባል የሆኑበት፣ የክልል ፌዴሬሽኖችና ክለቦች አባል የሆኑበት ማኅበር ነው፡፡ ማሕበሩ ዓላማውን የማያስፈጽምለትን ሰው ሲፈልግ ያነሳል፡፡ ሲፈልግ ደግሞ ያስቀምጣል፡፡ እንደ ግል ኩባንያ የእኔነት ጉዳይ የሚነሳበት አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በዚህ ስርዓት ውስጥ አመራሩ በሥራ ለመቀጠል ቁጥር አለው፡፡ ከስድስት በታች ከሆኑ እንደማይቻል ነው ደንቡ የሚናገረው፡፡ ከስድስትም፣ ከሶስትም አልፎ አሁን ያለው አንድ ብቻ ነው፡፡ በጀርባ ያለውን እንተወውና አንድ ግለሰብ እንዴት ጠቅላላ አባላት ሊቃወም ይችላል? ለግል ክብር ሲባል የአገርን ክብር አሳልፎ መስጠት ይከብዳል፡፡ እዚህ ላይ መቅደም ያለበት አገር እንጂ ግለሰብ አይደለም፡፡
 
ሪፖርተር፡- የአገር ክብር በሁለቱም ወገን የለም፡፡ በአሁኑ ሰዓት እየተደረገ ያለው ቅድሚያ ለአገር ሳይሆን አልሸነፍ ባይነት ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡-

አቶ አህመድ፡-
እልህና አልሸነፍ ባይነት የሚያስፈልገው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ለእያንዳንዳችን መነሻ የሚሆነን በእግር ኳሱ የደረሰው አደጋ ነው፡፡ በነበረው አመራር በእግር ኳሱ ብቻ ሳይሆን፣ በፍትህ፣ በሐብት አጠቃቀም፡ በጊዜ ብክነት ጉዳት አልደረሰም የሚል ካለ ሌላ ነገር ነው፡፡ አሁን እያወራን ያለነው ስታዲየሞች ተመልካች አጥተው ባዶ የሆኑበት፣ ክለቦች ለሁለት ተከፍለው ውድድር የሞተበት ጊዜ ላይ መሆናችንን ነው፡፡ ይህ ለጉዳቱ በቂ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ እልህና አልሸነፍ ባይነት ውስጥ የሚገባው ስለጉዳዩ የሚቀርበው ምክንያት በቂ ሳይኖር ሲቀር ነው፡፡ ይመስላል እንጂ ይህ እልህ አይደለም፡፡ አንዳንዴ ፍትሕ ሊጎብጥ ይችላል፡፡ ጨርሶ ግን አይሰበርም፡፡ አሁን እየሄድን ያለው ጉባኤው በወሰነው በሁለት አካሄድ ነው፡፡ አንዱ በሕጉ አካሄድ እንዲቀጥል፣ ሌላው ደግሞ መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት እርምጃ ይውሰድ ሲሉ ጣልቃ ይግባ ነው፣ ካልሆነስ ምን ማለት ነው?

አቶ አህመድ፡-
በጣልቃ ገብነት ሳይሆን፣ ጉዳዩ ገደቡን ጥሷል፡፡ የመንግሥት የውስጥ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የፖለቲካ ውሳኔ የሚያስፈልገው ሆኗል፡፡ በሌለ ሐብትና ንብረት የተዘጋጀ ብሔራዊ ቡድን ከፍተኛ ገንዘብ ተከፍሎ ያደረገው ውድድር ውጤት ተሰርዟል፡፡ የወጣቱ ስሜት ተጎድቷል፡፡ ከፊፋ የሚደረጉ ድጎማዎች ቀርተዋል፡፡ ከእኛ በኋላ የፊፋ አባል የሆኑ አገሮች በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መስራች እንዳልሆንን አሁን በሴካፍ እንኳ ተወካይ አጥተናል፡፡ በሌላ በኩል ባለሀብቶች በሚገርም መልኩ ወደ እግር ኳሱ መጥተዋል፡፡ ባለሃብቱ ብሔራዊ ግዴታውን እንዲወጣ መሠረት እያሲያዙን ነው፡፡ አሁን ግን ባለሀብቱ እንዲርቅ እየተጎነተለ ነው፡፡ መንግስት ደግሞ እንደ አቅጣጫ ስፖርቱ ከመንግስት ጥገኝነት እንዲወጣ ይፈልጋል፡፡ ይህ ከበቂ በላይ በቂ የመንግስት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ የጣልቃ ገብነት ጉዳይ አይደለም፡፡ ብሔራዊ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ተመጣጣኝ የሆነ እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ እርምጃው የእኛን ስልጣን ተንከባከቡ አይደለም፡፡ ትክክል ያልሆነው አካል አይቶ በማውጣት፣  ፊፋ መጥቶ ጉዳዩን እንዲያጣራ የሚለውን ሥራ መንግስት መስራት አለበት ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ሁለቱን አካላት ያነጋግር ነው?

አቶ አህመድ፡-
ያነጋግር ነው ብቻ ሳይሆን፤ አገርን እዚህ ደረጃ የሚያስደርስ ችግር ምንድ ነው ብሎ ይጠይቅ፡፡

ሪፖርተር፡- በፊፋ "በሮድ ማፕ" መሠረት በቀድሞ አመራር ጠቅላላ ጉባኤው ይጠራ የሚል አቋም ቢኖረውስ?

አቶ አህመድ፡-
ሐሳቡ ከመንግስት ይምጣ እንጂ የፈለገው ይወሰን፡፡ ምክንያቱም ጉዳቱ የአገርና የሕዝብ ሆኗል፡፡ አገርንና ህዝብ የሚወክለው ደግሞ መንግስት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የሚመሩት አካል ጉዳዩ በዓለም አቀፍ እግር ኳስ ግልግል ፍርድ ቤት እንዲታይ ጠበቃ እስከመቅጠር ደረጃ መድረሱን ገልጿል፡፡ ሁኔታው የት ደርሷል?

አቶ አህመድ፡-
ለዚህ ጉዳይ የቀጠርናቸው ጠበቆች ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ ጠበቆቹ ለጊዜው የደረሱበት የሕግ ሂደት ዝርዝሩ ስላልደረሰን ብዙ ማለት አልችልም፡፡ ሙያተኞቹ ሁኔታውን ከተረዱ በኋላ ችግሩን ሊፈቱ እንደሚችሉ ማረጋገጫ መስጠት የቻሉ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ማረጋገጫው ምንድ ነው?

አቶ አህመድ፡-
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የተከተለው መንገድ እንደሚያዋጣ፡፡

ሪፖርተር፡- ከአገራችን አቅም አኳያ፣ የውጭ ጠበቃ ቀጥሮ ፊፋን መከራከሩ ጥቅም አለው?

አቶ አህመድ፡- ብዙ
ጊዜ የምንቀሳቀሰው አቅማችንን እያየንና እየመዘንን ነው፡፡ ዋናው የጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ በመሆኑ፣ በሕጉ መሠረት እንሄድበታለን፡፡ እዚህ ላይ ደረቅ ሕጉን ብቻም ሳይሆን በመሃል ነገሮች በሕግና ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ የሚለዝቡበትን አማራጭም የምንጠቀምበት አካሄድ ይኖራል፡፡ ሌላው ደግሞ በመንግስት በኩል መደረግ ያለበት ይደረግ የሚል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ነገሮች በሕግና ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ የሚለዝቡበት እድል ያበቃ አይመስልዎትም?

አቶ አህመድ፡-
አላበቃም፡፡ እንዲያውም ጊዜ አሁን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግስት ሚና ወሳኝ ነው፡፡ ምክንያቱም ጉዳቱ አገራዊ እየሆነ ስለመጣ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት በጉዳዩ የሚኖረው ሚና ወሳኝ ነው ሲሉ ከፊፋ ደንብ ጋር የሚኖረውን አካሄድ አጢነውታል?

አቶ አህመድ፡-
የመንግሥት ጣልቃ መግባት ማስፈራሪያ መሆን የለበትም፡፡ ጣልቃ ይግባ ስንል፣ ጠቅላላ ጉባኤ ይጥራ፣ ስብሰባ ይምራ፣ ሳይሆን የተደረገው ነገር የቱ ጋር ትክክል ነው፡፡ ስህተቱስ የሚለውን ዳኝነት ይስጥ ነው፡፡ የፊፋን ሕግ ይመልከት፣ እውነታዎችን ይመርምር፣ በተጨማሪ እየተደረገ ያለውንም ለምን ብሎ ይጠይቅ ነው፡፡  
ሪፖርተር፡- በአንድ ጉዳይ ላይ ሁለት አቋሞችን ይዞ መሄድ ይቻላል?

አቶ አህመድ፡- ይቻላል፡፡ ፍርድ ቤትም ቢሆን ጉዳዩ እልባት የሚያገኝበት መንገድ ካለ ይቀበላል፡፡

ሪፖርተር፡-
የፊፋ መተዳደሪያ ደንብ ይቀበለዋል?

አቶ አህመድ፡- አንድ የሕግ አካል የሚፈልገው ችግሩ መፈታቱን እስከሆነ ድረስ፣ ፊፋም የሚቃወም አይመስለኝም፡፡ እንዲያውም ወደ አንድ የሕግ አካል ሲኬድ፣ የፍርድ ቤቱ የመጀመሪያ ጥያቄ አደጋውን ለመቀነስ ሁለቱ ወገኖች ሙከራ ማድረግ አለማድረጋቸውን ነው፡

ሪፖርተር፡-
በቅርቡ በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ጉዳዩ በሚገባ ለውይይት አለመቅረቡ ይነገራል፡-
አቶ አህመድ፡- በተቻለ መጠን የነበረውን ሁሉ ለጠቅላላ ጉባኤ አቅርበናል፡፡ ያለ ልዩነት ነው፣ ሁሉም በአንድ ድምጽ ውሳኔውን የደገፉት፡፡ ጉባኤው ለማንም ክፍት ነበር፡፡ እንዲያውም የእኛ ፍላጎት የነበረው ሁሉም ክልሎች ያለ አንዳች ተጽዕኖ ሐሳባቸውን እንዲሰጡ ነው፡፡ የሚወስኑትን ለመቀበል ዝግጁ ነበርን፡፡ እንደሚባለው በፌዴሬሽኑ የመቆየት በአንዳችንም ፍላጎት የለም፡፡ እንደዚያ ለማድረግም ምክንያት የለንም፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ የሥራ መልቀቂያ አቅርበው ነበር፡፡ ውሳኔዎን ግን ከ30 ደቂቃ በላይ ሳይቆይ አንስተውታል፡፡ ችግርዎ ምን ነበር?

አቶ አህመድ፡-
ከመጀመሪያውም ቢሆን ወደዚህ ኃላፊነት የመጣሁት ባልገመትኩትና ባላሰብኩበት ሁኔታ ነው፡፡ ኃላፊነቱን ስቀበልም ለትንሽ ጊዜ በሚል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ኃላፊነቱን ሲቀበሉ ለትንሽ ጊዜ ተብሎ በወቅቱ አልተነገረም፡፡

አቶ አህመድ፡-
ለጊዜው በይፋ ባልናገርም፣ ለሥራ ባልደረቦቼ ግን መቆየት እንደማልችል እናገር ነበር፡፡ በእጩነት ካቀረቡ ወገኖችም ጋር ጥያቄውን አልቀበልም በሚል ለረጅም ጊዜ እየተከራከርን ሳለ ሌላ የምናቀርበው ሰው አላዘጋጀንም፤ ተብሎ ጫና መጣብኝ፡፡ ያንንም ለመቀበል ዝግጁ አልነበርኩም፡፡ ይሁንና ሕዝብ አገልግለን ካለ፣ መቀበል ይገባል የሚል ነገር መጣ፡፡ በተጨማሪም ለዚህ ዓመት ብቻ ነው ሲሉኝ ተቀብያለሁ፡፡ አስቀድሞ አለመገለፁ፣ ሥራ አስፈፃሚው ለጠቅላላ ጉባኤ እየተዘጋጀ እያለ፣ የለም እዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የሥራ መልቀቂያ አቀርባለሁ ብላቸው ከሞራል አኳያ ጥሩ ባለመሆኑና የራሴም ጉዳይ ስለሆነ ወቅቱ ሲደርስ ጥያቄውን ላቀርብ ችያለሁ፡፡ ነገሩ አስገራሚም የሆነው ለዚህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጥያቄውን ሲያቀርቡ "የምናገረው የማደርገውን ነው፡፡ የማላደርገውን ከመጀመሪያ አላነሳውም" ብለው ተናግረው ነበር፡-

አቶ አህመድ፡-
የዚያን ቀን ነበርክ?

ሪፖርተር፡- አለሁ፡-

አቶ አህመድ፡-
ከነበርክ ምን ተደረገ?

ሪፖርተር፡- ሐሳብዎትን እንዲያነሱ ጉባኤው ደጋግሞ ጠየቀ፡፡

አቶ አህመድ፡-
ትክክል ነው፡፡ ሐሳቤን እንደማላነሳ በምከራከርበት ወቅት፣ ጉባኤው እንዳለ ከተቀመጠበት  ተነስቶ ጠየቀ፡፡ ይህ በኢትዮጵያውያን ባሕል ደግሞ ከባድ ነው፡፡ ማክበርም ነበረብኝ፡፡ የተደረገውም ይኸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁንስ የአገልግሎት ጊዜዎን ያጠናቅቃሉ?

አቶ አህመድ፡-
ለትንሽ ጊዜ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ባለው ሁኔታ ደስተኛ ነዎት?

አቶ አህመድ፡-
ደስተኛ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ምኑ ነው ደስተኛ ያደረገዎት፣ አገር ታግዶ፣ ወጣቱ ከሚወደው ስፖርት ርቆ፣ የውጭ አምላኪ መሆኑ ነው?

አቶ አህመድ፡-
እንደዚያ ሳይሆን፣ ድሮ ውጭ ሆኜ እንዲህ ቢሆን ኖሮ ብዬ የምናገረውን፣ ነፃ በሆነ መልኩ ተግብሬ ዛሬ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስትራቴጂ ኖሮት፣ ዞሮ ዞሮ፣ ስትራቴጂ ዶግማ (የማይቀር ሃሳብ) አይደለም፡፡ በየጊዜው የሚሻሻል ነው፡፡ ቢያንስ ራዕይ ኖሮት፣ እቅድ ኖሮት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያለበት ተቋም እንዲኖረው ለማድረግና ግለሰቦች በፈለጉት ሁኔታ የፈለጉትን የማያደርጉበት ሲስተም መዘርጋት የሚለውን ለመተግበር ሐሳቡን ከሚያቀርብ አካል ጋር መስራቴ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ በእግር ኳሱ ከገጠማት እገዳ አኳያስ?

አቶ አህመድ፡-
ሁኔታዎችን አቅልዬ ስለምመለከት የሚያስጨንቀኝ ነገር አይደለም፡፡ የሚያስጨንቀኝ ማድረግ እየቻልኩ ሳላደርግ ስቀር ነው፡፡ መስራት ያለብኝን ሳልሰራ ስቀር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እገዳው በተለይ በአሁኑ ሰዓት በክለብ ደረጃ ለሚገኙ ተጨዋቾች የፕሮፌሽናልነት እድሉ ቢገኝ ያለው መልዕክት ምንድ ነው?

አቶ አህመድ፡-
ጊዜያዊ እንጂ ዘለቂ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ፣ የፊፋ "ሮድ ማፕ" ተቀባይነት እስካላገኘ ድረስ ጊዜያዊ ነው፣ ማለት ይቻላል?

አቶ አህመድ፡-
ሊታይ የሚገባው እግር ኳስ የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት መሆኑን ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች በተሟላና በተቀናጀ መልኩ ይዞ መጓዝ ይገባል፡፡ እግር ኳስን፣ እግር ኳስ የሚያሰኙት ከአቅም፣ ከሥራ፣ ከወጣት ስልጠና፣ ከልማትና ከማንኛውም ባለ ድርሻ አካላት አንፃር ተቀናጅቶ ሲሄድ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ፕሮፌሽናል የሚለው ከእነዚህ ነጥቦች አንዱ ነው፡፡ እስካሁን ወጣቶች ክለብ ገብተው ለመጫወት እድላቸው ጠባብ በመሆኑ፣ በወሬ ያለውን ፕሮጀክት ሳይሆን፣ እውነተኛውን ፕሮጀክት፣ በትንሽ ጊዜ ውስጥ አስፈላጊውን ድጋፍ አድርገን በርካታ ወጣቶችን የእድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ ነው፡፡ በየክልሉ አንድ አንድ ፕሮጀክቶች እንዲኖር ሐሳብ አለን፡፡ ደጋግመን መስራት ያሰብነውም እዚህ ላይ ነው፡፡ ከዚያን እግር ኳስ በራሱ መስፈርት የሚጠራቸውን ልጆች ይዘን እንሄዳለን፡፡ እስካሁን ግን ይህ እየተደረገ አይደለም፡፡ አሁን ያለው እግር ኳስ ተጨዋች ትምህርት ያልቀናው፣ አልያም በአጋጣሚ የተገኘ ነው፡፡ ያም ቢሆን፣ መስፈርቱ አይታወቅም፡፡ አሁን ግን ይህንን ለማስቀረት ነው ጥረት እያደረግን ያለነው፡፡ ፕሮፌሽናሊዝም ሊስፋፋ የሚችለውም በዚህ መልኩ መሄድ ስንችል ብቻ ነው፡፡
 
< Prev   Next >