Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow የእምነቱን ክብረ በዓል ለምዕመኑ!
የእምነቱን ክብረ በዓል ለምዕመኑ! E-mail
Wednesday, 01 October 2008
ታምሩ በየነ

ባለፉት 34 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በመርህ ደረጃ እና የአገር መተዳደሪያ ሆኖ ከታወጀ ሕግ አኳያ መሰረታዊ ለውጥ ካየችባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ የሃይማኖት፣ የእምነት ነፃነት መሰረታዊ መደላደል፣ ንጣፍ ወይም የመሰረት ድንጋይ የሆነው የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የህሊናና የሃይማኖት ነፃነት ሊከበር የሚችልበት ዋነኛው ቅድመ ሁኔታ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ የሆኑበት አደረጃጀት መከተል አስፈላጊ መሆኑ የህግ እውቅና ያገኘው ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡
ይህም የኔ መንደርደሪያ ሀሳብ አከራካሪ መሆኑ ተቃውሞ ሊገጥመው መቻሉ እውነት ነው፡፡ መጀመሪያ እውቅና አግኝቷል የምትለው ነገር "ተረት ተረት" ነው የሚሉ እንዳሉ አልጠራጠርም፡፡ ቀጥሎም የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየት የህሊናና የሃይማኖት ነፃነት የመሰረተ ድንጋይ ነው የሚለው የማይስማሙ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ሃይማኖትና መንግሥት ተለያይተው ይኖራሉ በሚባሉበት አገር ነጻነቱ አለመኖሩን፣ መንግሥታዊ ሃይማኖት ተቋቁሞባቸው አገሮችን የተሻለ አንጻራዊ ነፃነት በአብነት እየተጠቀሱ የሚከራከሩ እንዳሉም ከወዲሁ መገመት አያዳግትም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት እኩልነትና የዚሁ መብት ነፃነት የተረጋገጠና የተከበረ ይሆን ዘንድ ቅድመ ሁኔታው መንግሥታዊ ሃይማኖት አለመኖሩ፣ ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ መሆናቸው ነው ባይ ነኝ፡፡ ይህም እውቅና አግኝቷል፡፡ እውቅና አግኝቷል ማለት ግን ተግባራዊ ሆኗል፤ የእኩልነት መብቱ የኅሊናና የሃይማኖት ነጻነቱ ተረጋግጧል ማለት የግድ እንዳይሆን ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ዛሬ፣ የመላ አገሪቷ መተዳደሪያ የበላይ ሕግ በሆነው ሰነድ መሰረት ሀ) መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው ለ) መንግሥታዊ ሃይማኖት አይኖርም ሐ) መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ በእነዚህ በሦስቱ እግሮች ጉልቻ ላይ የተቀመጠው የሃይማኖት መንግሥት ግንኙነት ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌ ከአምስቱ የሕገመንግሥቱ "መሠረታዊ መርሆዎች" መካከል አንዱ ነው፡፡ የሕገመንግሥቱ ምዕራፍ ሁለት ብቻውን የያዛቸው የእነዚህ አምስት መርሆዎች ድንጋጌዎች የመጀመሪያው የሕዝብ ሉዓላዊነት ሁለተኛው የህገመንግሥት የበላይነት ሦስተኛው የሰብዓዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶች አራተኛው የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት አምስተኛው የመንግሥት አሰራርና ተጠያቂነት መሆናቸው ሲታይ ለቦታው የተሰጠውን ፋይዳ መረዳት አያዳግትም፡፡

ሌሎች ሕገመንግሥታዊ የእምነት/የሃይማኖት መብትና ነፃነት ጥበቃ ድንጋጌዎችም አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የእኩልነት መብት አንዱ ነው፡፡ የሃይማኖት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የህግ ዋስትና አላቸው፡፡ በህግ ፊት እኩል ናቸው፡፡ ሌላው የሃይማኖት የእምነትና የአመለካከት ነፃነት ነው፡፡ ማናቸውም ሰው የህሊና እና የሃይማኖት ነፃነት ያለው መሆኑን ይህም መብት ማናቸውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክን የመከተል፣ የመተግበር የማስተማር፣ ወይም የመግለጽ መብትን እንደሚያካትት "ትምህርት በማናቸውም ረገድ ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካ አመለካከቶች እና ከባህላዊ ተጽዕኖዎች ነጻ በሆነ መንገድ መካሄድ" ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የሃይማኖት ተከታዮች ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋትና ለማደራጀት የሚያስችላቸው የሃይማኖት ትምህርትና የአስተዳደር ተቋማት ማቋቋም እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡ የጋብቻ የግልና የቤተሰብ መብቶች እንዲሁም የህጻናት መብት ድንጋጌዎችም በዚህ ከፍተኛ ማዕቀፍ ውስጥ በየራሳቸው ቦታ አላቸው፡፡ ይህ ከ1987 ዓ.ም ወዲህ ያለው ነው፡፡ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1987 ድረስ የነበረውም ከዚሁ የተለየ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያውያን የህሊናና የሃይማኖት ነፃነት የተረጋገጠ መሆኑን ከመደንገግ ጋር "መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው" የሚል ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክዓ ምድራዊ ገጽታ የረገጠው በ1980 ዓ.ም የኢሕዲሪ ሕገመንግሥት አማካኝነት ነው፡፡ በዚህ የሕገመንግሥቱ ድንጋጌ ውስጥ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው ከማለት ጋር "የሃይማኖት ድርጅቶች ሕጋዊ አቋም በሕግ ይወሰናል" ለምን እንደተባለም በኢትዮጵያ ልዩና ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ይመስለኛል፡፡

የ1980 ዓመቱን "የመንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆን መሰረት የተጣለው ግን ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ በተወሰዱ ልዩ ልዩ እርምጃዎች ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱና ትልቁ የ1948ቱ ሕገመንግሥት መታገድ/መሻር ነው፡፡ የገጠር መሬት መውረስ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች ወደመንግሥት መዛወር የሃይማኖት እኩልነትን፣ የህሊናና የእምነት ነፃነትን አረጋግጠዋል ወይም ከነጭራሹም ፖርላማቸው የነበር ማለት አይቻልም እንጂ የተቋቋመ መንግሥታዊ ሃይማኖት መሰረት አናግተዋል፡፡ በመንግሥትና በሃይማኖት መካከል ያለው ትስስር እየተለቀቀ ይህ ግን የእኩልነት መብት ወደሚያረጋግጥ የሃይማኖት ነፃነትን ወደሚጠብቅና ወደሚያከብር "ዓለማዊ" (ሴኩላር) መንግሥት አላመራም፡፡ ይህን በውጤትነት ያስከተሉ የተለያዩ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ መካከል ዋነኛው ወይም ከዋነኛዎቹ አንዱ ስልጣን የያዘው መንግሥት ባህርይ ነው፡፡ ፀረ መብት፣ ፀረ ነፃነት  በመሆኑ እየለየለት የሄደ አፋኝና ጨካኝ መንግሥት በመሆኑ ነው፡፡
የፖለቲካ ነፃነት፣ ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት፣ የመሰብሰብ ነፃነትና መብት በአጠቃላይ ሁሉም ዓይነት የሲቪልና የፖለቲካ መሰረታዊ ነጻነቶችና መብቶች በተረገጡበት ክፉኛ በታመሙበት ወቅትና ሁኔታ "የሃይማኖት መብትና ነፃነት ግን ደህና ነበር ጤነኛ ነበር" ማለት በጭራሽ አይቻልም፡፡ ከዚህም የተነሳ እንደ ሕዝባዊ በዓላት ያሉ ቢሻሻሉም የእንደዚህ ዓይነት እርምጃዎች ግብ የተለመደው ማስመሰያ ከመሆን በላይ ርቀው መሄድ አልቻሉም፡፡ ይልቁንም የተቋቋመ የመንግሥት ሃይማኖት የነበረውን የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥት የተካው ወታደራዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ሾሻሊዝም ማርክሲዝም ሌኒንዝም ሆኖ በመታወጁ መንግሥት ያረጋገጠው ነገር ቢኖር በ"እኩልነት" ሁሉንም ሃይማኖቶች መርገጥ ነው፡፡

ከዚህም የተነሳ ታላላቅ የሃይማኖት መሪዎች የሃይማቶቻቸው ህግና ደንብ ከሚፈቅደውና ከሚታገለው ከመንበራቸው በፖለቲካዊ ርምጃ ተወግደዋል፡፡ ያለፍርድና ያለህግ ተገድለዋል፡፡ በርካታ የእምነትና የሃይማኖት ተቋማት ተዘግተዋል ከአዋጅ ውጪ ተወርሰዋል ሰዎቹ ታስረዋል፤ ተባረዋል፡፡ የአሰራርና የተቋም "ነጻነታቸው" አልተነካም የተባሉ ሃይማኖቶች አስተዳደርና አመራር በወጣቱ፣ በሕዝባዊ ድርጅቶችና በሞያ ማህበራት ውስጥ እንዳለው በኢትዮያ ሠራተኞች ፓርቲ ደንብ ውስጥ በግልጽ እንደተመለከተው ያለ ግልጽ ቁጥጥር ስር አልዋለም ብሎ የማይዋሽበት፣ "በተዘዋዋሪ መንገድ" ቁጥጥር ስር የገባበት ሁኔታ የድርጊቱን ሰለባዎች (የሃይማኖት አባቶችም) ራሱን መንግሥትንም እኩል ማሳጣት፣ ያላዳገተው ጉዳይ ነበር፡፡

በሃይማኖት እኩልነት በእምነትና በኅሊና ነጻገት ላይ ያነጣጠረው አደጋ ለሁሉም እኩል በአሰራርና በተቋም ነፃነት ላይ ያነጣጠረ ብቻ አልነበረም፡፡ ኅሊናን ራሱን የተፈታተነ የማርክሲዝም ሌ"ንዝምን በዲያሌክቲካል ማቴርያሊዝምን (በነጻ ምርጫና በህሊና ነፃነት ላይ ተመስርቶ ብቻ ሊከተሉት ቢቻል የማያስነውረውን) የፍልስፍና መሰረታዊ ጥያቄና ተከታይ ምላሽ የሁሉም እና የእያንዳንዱ ሀይማኖት /እምነት/ አርቲክል ኦፍ ፌዝ/አንቀጽ እምነት/ ያደረገም ነበር፡፡ እግዚአብሔር/ፈጣሪ/ አምላክ የለም፤ ሰውን የፈጠረው አምላክ ነው ተረት ተረት ነው፣ በግልባጩ አምላክን የፈጠረው ሰው ነው "ገዢው ሀሳብ ሆነ"፡፡ "ዛሬ በዚህ ሰዓት ለአካለ መጠን ያልደረሱ ወይም የአስተዳደር ቢቀጥል (ወይም የብሄራዊ ውትድርና ሁለንተናዊ ግዳጅ ቢኖር) ለውትድርና አገልግሎት እድሜያቸው የበቃ ወይም የመምረጥ መብታቸው የበሰለ ወጣቶች አያውቁትም እንጂ "እንኳን አደረሳችሁ" ዓይነት ወቅታዊ የመልካም መግለጫና የሰላምታ አባባልም ይኸው በሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ ፖሊሲ ውጤት ነው፡፡

የኅሊናና የሃይማኖት ነፃነት፣ የእምነት መብት እኩልነት በመርህም በተግባርም በፈለጉት ሃይማኖት የማመን፣ የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል ሃይማኖቶቹን እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብት ጭምር አለው ማለት በአገራችን ሕገመንግሥት ውስጥ በዝርዝር ባይገለጽም የአለማመን መብትን ሃይማኖት የመለወጥ የ"መልቀቅ" መብትና ነፃነትን ጭምር ያጠቃልላል፡፡

ከዚህም የተነሳ ስለ "እንኳን አደረሳችሁ" (የዛሬዎቹ "ልጆች" እንደጠቅላላ እውቀት እንኳን ቢጠየቁ የማያውቁት) ነውርና ክፋት ሳወራና ስናገር ለዚህ ጉዳይ መነሻ በሆነው ፍልስፍና ህሊና እምነት የተፈጠሙ ሰዎች መብትና ነፃነት የላቸውም ማለቴ በጭራሽ አይደለም፡፡ በተቃራኒው የእነዚህ ሰዎች መብትና ነፃነት ሳይከበር የአለማመን የኢአማኒነት መብትና ነፃነት ሳይኖር የኅሊናና የሃይማኖት ነፃነት መብት ፈጽሞ ሊኖር አይችልም፡፡ አገራችን የተለያዩ ሃይማኖቶች የሚታመኑባት የሚመለኩባት አገር ነች፡፡ ያን ያህልም የእነዚህ ሃይማኖቶች ምርመራን በሰላም አብረው ተከባብረው የሚኖሩባት ናት፡፡ እንዲያውም ከዚህ አኳያ ቢያንስ ቢያንስ ወይም ከታላላቆቹ እምነቶችና ሃይማኖቶች አንጻር "በሰላም አብሮ የመኖር" ወግና ባህልን ሌላው የአገራችን የተከበረ "ሃይማኖት" ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ እምነትና ሃይማኖት ግን በታላላቆቹና በታወቁት ላይ ብቻ የተወሰነ መሆን የለበትም፡፡

እያንዳንዱ ሃይማኖትና እምነት የራሱ ዶክትሪን የራሱ የህይወት መመሪያ አለው፡፡ የራሱ እውነት የራሱ ሀቅ አለው፡፡ የመንግሥተ ሰማያት መንገድና ጐዳናም ይኸውና ይኸው ብቻ ነው፡፡ በግልጽ አንናገርውም ደፍረን ገልፀን አናወጣውም እንጂ የአንዱ የህይወት መንገድ ለሌላው የመንግሥተ ሰማያት ሳይሆን የገሀነመ እሳት ነው፡፡ ስለዚህም አንዱ ሌላውን "በውስጠ ታዋቂነት" ምስኪን የማይድን ሰው ይለዋል ማለት ነው፡፡ ማለት ነው ብቻ ሳይሆን ደግነቱ ሁሌም እናጋልጠው የምንለው አይደለም እንጂ ሀቁ ይኸው ነው፡፡ ኢአማንያንን ከሌላው የተለየ የሚያደርጋቸው ጉዳይ የመሰረታዊ ይዘት ይሁን የ"ብዛት" (በዛ የሚባል ነገር) በሰላም አብሮ ከመኖር ልማድና ወግ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ እሴትና ባህል አኳያ ታላቁ ጉዳይ፣ ታላቁ ሥልጣኔ በዋናው የሃይማኖት እና የእምነት ይዘት ላይ መግባባት የጋራ አቋም፤ የመያዝ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ሌላው በመሰረቱ በማያምንባት እምነት ሃይማኖት የማመን መብትና ነፃነት ያለው መሆኑ ነው፡፡ ሀሳብን፣ እምነትን በነጻ በመግለጽ መብትና ነፃነት የሚባለው መርህ ሆኖ የሚወሰደው በዚህም ላይ ጠንክሮ ተጠናክሮ ይሰራል፡፡ በሀሳብህ፣ በአመለካከትህ አልስማማም ይልቁንም ሀሳብህ ከሀሳቡ ይጣላል፡፡ ነገር ግን እሱን የመግለጽ ነፃነት የለህም ቢባል ከአንተ ጐን ቆሜ ለዚያ ነፃነት እስከመጨረሻው የምታገለው፣ የምዋደቀው እምነትህን ወድጀው ሳይሆን እምነትህን ሀሳብህን በነጻ የሚያዝና የመግለጽ መብትና ነፃነት ለኔም መብትና ነፃነት ብየ ነው፡፡ ማለት ለሃይማኖትም ይሰራል፡፡

2000 ዓ.ም በአገራችን የዘመን አቆጣጠር ላይ ተመስርቶ የኢትዮጵያ ሚሌንየም በዓል ሆኖ፣ ዓመቱን ሙሉ ሲከበር ከርሟል፡፡ የሚሌኒየሙን ዴቬሎፕመንት ጐል በፈረንጆች ዘመን አቆጣጠር ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት ሴፕቴምበር 2000 ላይ ጀምረን በዚያው በአውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር 2015 ላይ ድህነትን በግማሽ፣ የሕጻናት ሞትን በ3/4ኛ፣ የመጀመሪያ ትምህርትን እጦት በዚያን ያህል ለማስወገድ ከግማሽ መንገድ በላይ (ቢያንስ ቢያንስና በተረጋገጠ መልኩ ከጊዜ አኳያ) ሄደን ወጥተን ወርደን እያልን ጊዜያዊ መድረሻችንንም የሚሌኒየመ የልማት ግብ ብለን እየጠራን ወዘተ ወዘተ ስለሌለ ሚሌኒየም ለምን የሚባል ነገር አለ፡፡ በዚህ ውስጥም መታየቱ ማጋለጠ ያልቀረ የስሌት ስህተት አለ፡፡

የሆነው ሆኖ ግን ዓመቱ በሙሉ ሲከበር በተከበረው የኢትዮጵያ ሚሌኒየም ውስጥ የነበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት ሁሉ "ልዩ" ሆነው ልዩ ተብለው ተከብረዋል፡፡ በዓሎቹን ልዩ የሚያደርጋቸው በሚሌኒየሙ ውስጥ መዋላቸው እየተባለም የሚደነቅ ነገር ሰምተናል፡፡ ዓርብ የሌለበት ሳምንት፣ "አቦ" የማይነግስበት ወር፣ በየዓመቱ ዞሮ የማይመጣ የካቲት፤ ያለ ይመስል የሚሌኒየሙ በዓል አከባበር መድመቂያ ልዩ የሚያደርገው ሆኖ ከርሟል፡፡ የሚሌኒየሙ በዓል ሃይማኖታዊ በዓላትን ልዩ አደረገ አደመቀ ከማለት ይልቅ እውነቱን ለመናገር ሚሌኒየሙን እንዲያደምቁ የተገደዱት ከዚህም የተነሳ የሃይማኖት በዓላቱ እንደየሃይማኖታዊ ህጋቸው ቀኖናቸው ባህርይ መከበራቸውን ትተው እንዲተው ተደርገው መከራ ያዩት በዓላቱ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ሚሌኒየም ስሌትና አቆጣጠር ውስጥ እውነተኛው የሚሊኒየም መባቻ ካባተ እነሆ አንደኛው ወር እየተገባደደ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የመስቀልን እና የኢድ አልፈጥርን በዓላት አክብረናል፡፡ አንድ ዓመት ሙሉ የሚሌኒየሙ "አካል" ሆነው በሚሌኒየሙ ፕሮግራም ውስጥ ገብተው በዚያው ፖሊሲና አጀንዳ ውስጥ ተቃቅፈው የተከበሩትን የሃይማኖት በዓላት አከባበር ልዩ የሚያደርገው ምን ነገር አለ ቢባል በዓላቱ አሁንም በህገመንግሥታዊው ድንጋጌ የአንቀጽ አስራ አንድ መርህ ተፈፃሚነት ውስጥ የመከበር እድል አሁንም አለማግኘታቸው ነው፡፡ የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት የህገ መንግሥቱ የአንቀጽ 11 ድንጋጌ

1. መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው
2. መንግሥታዊ ሃይኖት አይኖርም
3. መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ይላል፡፡

የዚህ የሕገመንግሥቱ መሠረታዊ መርህ ትርጉም ሰፊና ውስብስብ ቢሆንም ከሌሎች መካከል የዚህ ጉዳይ ተግባራዊ አለመሆን ዋነኛው ትልቁ ጐልቶ የሚታይ መገለጫ መንግሥት በተለያዩ የስልጣን አካላቱ አማካኝነት ሃይማኖት ክብረ በዓል ውስጥ እገባለሁ፣ አልገባሁም ማለቱና መግባቱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሃይማኖቶቹ እራሳቸው በአመራራቸው አማካኝነት ሃይማኖቱን ማክበር ሃይማኖቱን መከተል በዓላቱንም ማክበር የእኛ ጉዳይ ነው፡፡ የአንተ ጉዳይና ድርሻ በነጻ ማክበራችንን ህጉ መከበሩን ማረጋገጥ ነው፡፡ በዓሉን ማክበር አይደለም፡፡ የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነጸነቶችን የማክበሩ ማረጋገጫ አንተ ከዚህ ውጭ ስትሆን እና ውስጥ ጣልቃ እገባለሁ ሳትል ስትቀር ነው፡፡ ብለው ይህንኑ ነፃነት እናስከብራለን፤ እንከላከላለን እያሉ ከዚህ አቅጣጫ ሲታገሉ ሲከላከሉ አናይም፡፡

የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ብሎ ነገር የአገራችን ምናልባትም ብቸኛ ልዩ መታወቂያ ሆኖ መቆየቱ፣ መዝለቁ የማይቀር ስለሆነ በዚህ ረገድ አንደኛው የመንግሥት "ማፈሪያ" የመገናኛ ብዙሃን ናቸው፡፡ በእነሱ እምነትና ኤዲተርያል "ሃይማኖት" መሰረት፣ አንዱ ሃይማኖት ከሌላው ሃይማኖት ተለየ ልዩነት ተደረገበት፡፡

አድልዖ ተፈፀመበት እንዳይባል ተብሎም መንግሥት እንዳይከሰስ እንዳይወቀስ ስለዚህም የሕገመንግሥቱ "የእኩልነት መብት" እንዳይናድ መፍትሄው ፍቱን መድሃኒቱ ሁሉምና እያንዳንዱን ሃይማኖት ውስጥ እኩል ጣልቃ መግባት ነው፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ምዕመናን የሚያከብሩትን በዓል ሲያስፈልግ ሽፋን መስጠት፣ መዘገብ ወጉና ባህሉ መሆኑ ቀርቶ የበዓሉ አከባበር ለሚዲያው ፕሮግራም፣ ለሚዲያው ሽፋን፣ ለሚዲያው አጀንዳ እንዲገዛ ያደርጋሉ፡፡ በዓሉ የሃይማኖቱ መሆኑ ቀርቶ የሚዲያው ይሆናል፡፡

ይህ መብትና ነፃነት ተግባራዊ መሆን እንዲጀምር የዚህን አቅጣጫ እንዲይዝ ሚዲያው ከዚህ ባህርይው መላቀቅ ከሃይማኖት በዓላት መከበር ፖለቲካዊ ነጥብ አስቆጥራለሁ ብሎ "መስገብገብ" ደግ አለመሆኑን መገንዘብ ይገባዋል፡፡ እምነቶች የበዓላትን አከባበር ለእኛ ተውልን የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ ይህን የመሰለ ተራና መሰረታዊም ጥያቄ ማንሳት የተገደዱት በዚህ ምክንያት ነው፡፡
 
< Prev   Next >