| "በዱባይና በኢምሬትስ የምንገነባቸው... |
|
| Wednesday, 01 October 2008 | |
![]() ![]() ![]() "በዱባይና በኢምሬትስ የምንገነባቸው ህንፃዎች አዲስ አበባም ይገነባሉ"ሚ/ር ሳላምዚ ናጂ ቡላህ፣ የኮንትራክት ዘ ፊውቸር ስካን ኃ.የተ.የግ.ማ. የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮንስትራክት ዘ ፊዩቸር ስካን ኃ.የተ.የግ.ማ. በብዙ አገሮች በርካታ ኩባንያዎችን በሥሩ የሚያንቀሳቅስ አለም አቀፍ ድርጅት ነው፡፡ መቀመጫውን በዱባይ ያደረገው ስካን ኮንስትራክሽን በአፍሪካ ለሚያካሂደው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ሥራዎች ኢትዮጵያን ዋና ጽህፈት ቤቱ አድርጎ መርጧታል፡፡ በአፍሪካ ለሚያካሂደው የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኢትዮጵያ የተመረጠችው ባላት የረጅም ጊዜ ታሪክና በቅርቡም እያሳየች ያለው እድገት ሲሆን፣ በሌላ በኩልም የአፍሪካ መዲናና መቀመጫ ማዕከል መሆንዋም ነው፡፡ በርካታ የአህጉሪቱና አለም አቀፍ ድርጅቶች ጽህፈት ቤታቸውን የመሰረቱባት ኢትዮጵያ ታላላቅ ሆቴሎችና የአገልግሎት ተቋማት፣ የመንገድና የሌሎችም መሠረተ ልማት አውታሮች ሊስፋፉላት ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸው ሚ/ር ሳላምዚ ናጂሉላህ ይገልፃሉ፡፡ ኮንስትራክት ዘ ፊዩቸር ኃ.የተ.የግል.ማ. ከ200 እስከ 300 ሚሊዮን ብር በሚደርስ ዝቅተኛ የመነሻ ካፒታል በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት የሚያካሂድ ሲሆን፣ የካፒታል መጠኑ እንደየ ፕሮጀክቶቹ ብዛት የሚለያይ መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡ ኩባንያው በኢትዮጵያ ስለሚያከናውነው የኮንስትራክሽን ሥራዎች በተመለከተ ብርሃኑ ፈቃደ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ገበያው አለ? ሚ/ር ሳሊምዚ፡- በዱባይ በኢምሬትስና በሌሎችም አገሮች ያሉ ኩባንያዎችና ኢንቨስተሮች አይናቸውን በኢትዮጵያ ላይ እንደሚጥሉ አምናለሁ፡፡ አገሪቱ ትልቅ ተስፋ አላት፡፡ በቅርቡም የአፍሪካ ማዕከል በመሆን ትልልቅ የኢንቨስትመንትና የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባት እንደምትሆን ይታመናል፡፡ ሪፖርተር፡- ቀደም ብለው እንደገለፁልኝ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማዕከል ትሆናለች ብለውኛል፡፡ ኢትዮጵያ ቀድሞም የአፍሪካ አገሮች መቀመጫ ነች፡፡ ሚ/ር ሳሊምዚ፡- እያልኩ ያለሁት በኢንቨስትመንትና በንግድ ረገድ ነው፡፡ የአፍሪካ ማዕከልነቷን ያህል ዘመናዊ ሆቴሎች፣ የቱሪስት መስህብ የሆኑ መዝናኛዎች፣ የገበያ ማዕከሎች የስብሰባ አዳራሾችና ዘመናዊ መንገዶች ያስፈልጓታል፡፡ ኩባንያችን እነዚህን ሁሉ በጥራት መሥራት የሚችል ነው፡፡ በበርካታ አገሮች ውስጥ የኮንስትራክሽን ሥራ በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡ በአፍሪካ አህጉር ለምናካሂደው አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን እንደ ዋና የመሥሪያ ቤታችን መቀመጫ ማዕከልነት መርጠናል፡፡ አዲስ አበባን ዘመናዊ ከተማ ማድረግ አንዱ አላማችን ነው፡፡ ስለዚህ በአፍሪካ አገሮች በጅቡቲ፣ በኬንያ፣ በኡጋንዳ፣ በደቡብ አፍሪካና በሌሎችም ለሚሰራው ሥራ አዲስ አበባ በሚገኘው ቢሮአችን ግንኙነቱ ይመሰረታል፡፡ ለዚህ ነው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማዕከል ትሆናለች ያልኩህ፡፡ ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ኮንስተራክሽን ኢንዱስትሪን አጥንታችኋል? ሚ/ር ሳሊምዚ፡- እርግጥ የጠለቀ ጥናት አላደረግንም፡፡ ለሦስት ወራት ያህል እየተመላለስኩ በአዲስ አበባ ያለውን ገጽታ ተመልክቻለሁ፡፡ ብዙ መሠራት አለበት፡፡ አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ብዙም አላየሁም፡፡ እንደ ሸራተን አዲስ ያሉ ሆቴሎችና ማዕከሎች በብዛት ያስፈልጋሉ፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ ማዕከል መሆን ካለባት በጥራት የሚሰሩ በርካታ ማዕከሎችና መገልገያ ሥፍራዎች ሊኖሯት ይገባል፡፡ ሪፖርተር፡- ጥራትን ካነሳን የስካን ኮንስትራክሽን ልምድ እንዴት ይገለፃል? ሚ/ር ሳሊምዚ፡- በአለም ተወዳዳሪ ሆነን የዘለቅነው ለጥራት ካለን ዲስፕሊንና አቋም በመነሳት ነው፡፡ ያለ ገንዘብ እንደማንሰራው ሁሉ ያለ ጥራትም አንሰራም፡ አሰሪ ድርጅቶች እንኳ እንደነገሩ ለበስ ለበስ አድርገን እንድንሰራ ካስገደዱን የሥራ ውላችን እናቋርጣለን፡፡ መቶ ፐርሰንት ለጥራት ቅድሚያ እንሰጣለን፡፡ ስካን የሰራው ሕንፃ ተሰነጠቀ፣ ፈረሰ ሲባል መሥማት የሥራችን ውድቀት ሆነ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያም በጥራት የምንሰራቸው የኮንስትራክሽን ሥራዎች መጪው ትውልድ የሚያደንቃቸውና ለእኛም ኩራትና ክብር የሚያላብሱን መሆን አለባቸው፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ የሚመጡት ልጆች በኩራት "አባቴ የስካን ኩባንያ ኢንጂነር ነው"፣ "እናቴ የስካን ኩባንያ ሠራተኛ ናት" እንዲሉ እንፈልጋለን፡፡ ከምንም በላይ በጥራት ሰርተን ስማችንን ሁሌም የምናስጠራበት ታሪክ መጻፍ እንፈልጋለን፡፡ ሪፖርተር፡- መነሻ ካፒታላችሁ አልተገለፀም? ሚ/ር ሳላምዚ፡- እርግጥ ለመነሻ የተመዘገበው ካፒታል ከ200 እስከ 300 ሚሊዮን ብር ገደማ ነው፡፡ አሁንም መታወቅ ያለበት አንዱ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የሚያስፈልገው ካፒታል ከሌላው የተለየ በመሆኑ ጠቅላላ ካፒታላችን ይሄ ነው ብሎ ማስቀመጥ ይከብዳል፡፡ ሪፖርተር፡- የግብዓት አጠቃቀማችሁ ከአገር ውስጥ ነው ወይስ ታስመጣላችሁ? ሚ/ር ሳላምዚ፡- ከአገር ውስጥ ማግኘት የቻልነውን ያህል እንጠቀማለን፡፡ እዚህ ማግኘት ያልቻለውን ብቻ እናስመጣለን፡፡ በቅርቡም አስፈላጊ የሆኑ ማሽነሪዎችን ከባድ መኪኖችን፣ ሎደሮች፣ የኮንክሪት መሳሪያዎችን፣ ግሬደሮችና ሌሎችንም የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች እናመጣለን፡፡ ሪፖርተር፡- ሌሎች ጥሬ ዕቃዎችን እዚህ አላገኛችሁም? የዋጋውን ጉዳይ እንዴት ያዩታል? ሚ/ር ሳሊምዚ፡- አግኝተናል፡፡ ኢትዮጵያ ጥራት ያለውና ጠንካራ እምነበረድ ታመርታለች፡፡ ይህ ለእኛ በጣም ጠቃሚያችን ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ እንድንገለገልበት ያስችለናል፡፡ እንዳልኩህ እዚህ አገር ማግኘት እስከቻልን ድረስ 90 በመቶውን እንጠቀማለን፡፡ በዋጋ በኩል የራሳችን የሆኑ አምራች ኩባንያዎች ስላሉን ስጋት የለብንም፡፡ ሪፖርተር፡- ወደ ኩባንያዎ እድሜ ልመልስልዎትና ለምን ያህል ጊዜ ነው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ያቀዳችሁት? ሚ/ር ሳላምዚ፡- በኢትዮጵያ የኮንስትራሽን ዘርፍ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ እንዲኖረን እንፈልጋለን፡፡ የዘርፉ ምሰሶ የመሆን አላማ ይዘን መጥተናል፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ልምዱም እውቀቱም አለን፡፡ በአለም ላይ አሉ ከሚባሉ ኩባንያዎች ጋር በጋራ እንሰራለን፡፡ ኢትዮጵያም የዚህ ሥራችን አንዱ አካል ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ ሪፖርተር፡- የመጀመሪያ ሥራችሁ የምታደርጉት ምንድ ነው? ሚ/ር ሳሊምዚ፡- በማንኛውም ወቅት የትኛውንም ሥራ ለመስራት የሚያስችለን ዝግጅት አድርገናል፡፡ የሚያስፈልጉን ነገሮች በእጃችን ስላሉ የትኛውንም ሥራ ለመጀመር ችግር የለብንም፡፡ ሆኖም ምን ያህል እንደተዘጋጀንና አቅማችንም የቱን ያህል እንደሆነ ለማሳየት የሚረዱ ሶስት የሕንፃ ግንባታ ዲዛይኖችን ሰርተናል፡፡ ከሦስት ወራት በላይ በሆነ ጊዜ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ይሄን ስናደርግ ገና ውል አልተዋዋልንም፡፡ እውቅና አላገኘንም፡፡ ለሥራ መምጣታችንን ሁሉም እንዲገነዘቡልን እንፈልጋለን፡፡ ኢንቨስትመንቱን ቀድመን መጀመራችንም ለዚሁ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ዲዛይን ያወጣችሁላቸው ህንፃዎች ለምን ተግባር የሚውሉ ናቸው? ሚ/ር ሳላምዚ፡- ዲዛይን የወጣላቸው ሕንፃዎች ለገበያ ማዕበልነት፣ ለሪዞርት፣ ለሆቴልና ለሌሎችም ሰፋፊ ሥራዎች አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ሦስት ሕንፃዎች ናቸው፡፡ ሪፖርተር፡- ለእነዚህ ሕንፃዎች በሙያም ሆነ በሌላ መልኩ ድጋፍ ያደረገላችሁ አካል የለም? ሚ/ር ሳላምዚ፡- የራሳችን በቂ ካፒታል አለን፡፡ በዘርፉም ልምድና እወቀት እንዳለን ገልጫለሁ፡፡ የማንም እርዳታ ወይም ድጋፍ አላስፈለገንም፡፡ ቀድመን ወጪ አውጥተናል፡፡ የፈለግነው ሥራ መሥራት በመሆኑ ትክክል ነን፡፡ ሪፖርተር፡- የጥራት መጓደል ከሚያስከትሉ ችግሮች አንዱ የዋጋ መወደድ ነው፡፡ ብዙ ድርጅቶች ሕንፃም ሆነ ሌሎች ሥራዎችን ለማሰራት ወጪውን ስለማይችሉት ይመስለኛል ለጥራት ችግር የሚጋለጡት? ሚ/ር ሳላምዚ፡- ገበያው ውስጥ ባለው ተመጣጣኝ ዋጋ ነው የምንሰራው፡፡ በጥራት እንሰራለን ሰላልን ከገበያው በላይ የሆነ ዋጋ አንጠይቅም፡፡ በትክክል ከተሰራ የገበያው ዋጋ ለጥራት ችግር ነው ብለን አንገምትም፡፡ በእኛ በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ አለም አቀፍ ጥራቱን የጠበቀ ሥራ እንደምንሰራ ልናረጋግጥ እንፈልጋለን፡፡ በጥራት በኩል ከአለም አቀፍ አጋሮቻችን ጀርመኖች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለምንሰራቸው ሥራዎች ጥንካሬ እና የረጅም ጊዜ እድሜ ከእነርሱ ጋር እንሰራለን፡፡ ውበትን በተመለከተ በተለይ በሥነ ሕንፃ ረገድ የቱርክ አጋሮቻችን ሰፊ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ በሁለቱም አገሮች ያሉ ድርጅቶቻችን የካበተ ልምድና እውቀት ስላላቸው በጥራትም ሆነ በውበት ሥራዎችን እንደምንሰራ እምነት አለን፡፡ ሪፖርተር፡- እንደማስበው ብዙ የአገር ውስጥና የውጭ ተወዳዳሪዎች ይገጥማችኋል፡፡ ምን ያህል ስኬታማ ትሆናላችሁ? ሚ/ር ሳላምዚ፡- ያለ ውድድርና ያለ ተጽዕኖ የሚሰራ ሥራ የለም፡፡ በውድድር እናምናለን፡፡ ተወዳዳሪዎችም ነን፡፡ ከዚያ በላይ ችግሮች ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም የሚያስችለን ዝግጅት አድርገናል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ኢንቨስት ማድረግ እንዳለብኝ ያማከረኝ የቅርብ ወዳጄ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከስምንት ዓመት በላይ ቆይቷል፡፡ አሁንም እየሰራ ይገኛል፡፡ እርሱ የደረሰበትንና የሚገኝበትን ደረጃ እከታተል ስለነበር ትልቅ ለውጥ አይቻለሁ፡፡ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ መኖርም አለባቸው ተቋቁመናቸው ሥራችንን እንደምንወጣ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሪፖርተር፡- ኩባንያችሁ ለኢትዮጵያውያን የሚፈጥረው የሥራ እድል አለ? ሚ/ር ሳላምዚ፡- አዎ፡፡ በቋሚነት የሚቀጠሩ ከ500 እስከ 1000 ሠራተኞች ይኖሩናል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ በጊዜያዊነት የምንቀጥራቸው ደግሞ እንደ ፕሮጀክቶቻችን አይነት ከ2000 እስከ 10"000 ይደርሳሉ፡፡ በተለይ በጊዜያዊነት የሚቀጠሩት የፕሮጀክቶቻችን ስፋት በጨመረ ቁጥር በእቅድ ከያዝነው በላይ ሠራተኞችን እንፈልጋለን፡፡ ከማሰራት ባሻገር ተጨማሪ ሥልጠናዎችን እንሰጣለን፡፡ ለአብነት አንድ ኢንጂነር ከሰለጠነበት መስክ ባሻገር ሌሎችንም የምህንድስና ሥራዎች መሥራት የሚያስችለውን እውቀት እንሰጣለን፡፡ ትልቁ ነገር ጥራትን እንዲያውቁልን እንፈልጋለን፡፡ በኢትዮጵያ የአጭር ጊዜ ቆይታ ለማድረግ አልመጣንም ወደፊት እስካገኘን ድረስ ኢትዮጵያውያን ምሁራንን ብቻ መጠቀምና ማሰራት አላማችን ነው፡፡ እውቀቱ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በርካቶች እንደሆኑ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በአገራቸው ከእነርሱ የተሻለ ሰው ሊኖር ስለማይችል ቅድሚያው የእነርሱ ይሆናል፡፡ አሁን ዲዛይን ላዘጋጀንላቸው ፕሮጀክቶች ከ95 በመቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ለሥራ እንመድባለን፡፡ በተለይ ከአዲስ አበባ 10ሺህ ሰዎችን እንጠቀማለን ብለናል፡፡ ነገር ግን ጠንካራና ታታሪ ሠራተኞች መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ በአሁኑ ጊዜ በርካታ ኮንስትራክሽን እየተካሄደባት ይገኛል፡፡ የእናንተ ፋይዳ ምንድ ነው? ሚ/ር ሳላምዚ፡- ሕንፃ ከሕንፃ ይለያያል፡፡ እኛ ለምንሰራው ሥራ ዋስትናችን ጥራት ነው፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ነች፡፡ በሚቀጥሉት አሥርና አሥራ አምስት ዓመታት አሁን ካለችበት ፈጽሞ የተለየችና ውብ ከተማ እንደምትሆን በሥራችን ማሳየት እንችላለን፡፡ ቅድም እንዳልኩት የነገዎቹ ልጆቻችሁ በስካን ኩባንያ ውስጥ የሚሰራ የየትኛውም አይነት ሥራ ሠራተኛ ቤተሰብ በመሆናቸው ጥልቅ ስሜት እንዲሰማቸው ነው የምፈልገው፡፡ እንዳልከው በአዲስ አበባ በርካታ የኮንስትራክሽን ሥራዎችን አይቻለሁ፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ሁሉንም የጥራት መስፈርቶች አሟልቶ ያገኘሁት ሸራተን ሆቴል ነው፡፡ እንደሰማሁት ከተገነባ አሥር ዓመት አልፎታል፡፡ ዛሬም አዲስ እንደሆነ ይታያል፡፡ የምንሰራቸው ሆቴሎች፣ ሕንፃዎች፣ መንገዶችም ሆነ የገበያ ማዕከሎች የበለጠ ዕድሜ፣ ጥንካሬና ውበት የተላበሱ ስለመሆናቸው ከመናገር ባለፈ በሥራችን የምናሳየው ይሆናል፡፡ በዱባይና በኢምሬትስ የምንገነባቸው ሕንፃዎች አዲስ አበባም ይገነባሉ፡፡ ሪፖርተር፡- እናንተ ከውጭ መጥታችሁ ኩባንያ ስታቋቁሙ በአገር ውስጥ ልምድና አውቀቱ ያላቸው ብዙ አገር በቀል ኩባንያዎች አሉ፡፡ እነርሱንስ ከግምት አስገብታችኋል? ሚ/ር ሳላምዚ፡- ጥያቄው ዋጋን የተመለከተ ከሆነ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የሚጠይቁትን ዋጋ ነው የምናስከፍለው፡፡ የጥራት ጥያቄ አያስጨንቀንም፡፡ ኩባንያችን እንደ ዋና ፖሊሲው የሚተዳደርበት አቋም ነው፡፡ ለአብነት አንድ ቪላ በገበያ ዋጋ እንድንገነባ ተዋውለን ከሆነ የጥራቱ ጉዳይ የባለ ቪላው ሳይሆን የእኛ ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ ለእርሱ ጥሩ አድርገን የገነባንለት ከሆነ በርካታ ደንበኞችን ማፍራት እንችላለን፡፡ ስለዚህ በዋጋም በጥራትም ችግር የለብንም፡፡ ሪፖርተር፡- አልዘገያችሁም? ሚ/ር ሳላምዚ፡- የመጣንበት ወቅት ጥሩ ጊዜ ነው፡፡ አይኖች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ እያዩ ናቸው፡፡ ብዙ እንቅስቃሴዎችን እያየን ነው፡፡ በሌሎች አገሮች ገና ከኤርፖርት እንደወጣህ የምታየው የሚያማምሩ ሕንፃዎችን ነው፤ አይን የሚስቡና ጥራታቸው ከፍተኛ የሆኑ ሆቴሎችን ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ማስታወቂያ ነው፡፡ ኢንቨስተሮችን የመላክ አቅም ስላላቸው ሕንፃዎች፣ ሆቴሎችና ሌሎችም አገልግሎት መስጫ ተቋማት በስፋት ታያለህ፡፡ እኛም በዱባይ በኢምሬትስና በአውሮፓ አገሮች የምናደርገው ይሄንኑ ነው፡፡ አዲስ አበባም ኢንቨስተሮች በብዛት እንዲመጡ ለማድረግ ጥራትና ብቃት ያላቸው የአገልግሎት መስጫ ተቋማትና መንገዶች መገንባት አለባቸው፡፡ ወቅቱ ደግሞ አሁን ነው፡፡ ሪፖርተር፡- መቼ ነው ወደ ሥራ የምትገቡት? ሚ/ር ሳሊምዚ፡- ነገ መጀመር እንችላለን፡፡ ሁሉም ነገር ተዘጋጅቷል፡፡ ባለሙያዎች፣ ማሽኖች፣ ጥሬ እቃዎችና ሌሎችንም አጠናቀናል፡፡ የምንጠብቀው በመንግሥት በኩል ማሟላት የሚገባንን የሰነዶችና የርክክብ ሥራዎችን ማጠናቀቅ ነው፡፡ እነዚህ እንደተሟሉ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያዎቹን አምስት ፕሮጀክቶች መሥራት እንጀምራለን፡፡ ሪፖርተር፡- ኩባንያችሁ በተጓዳኝ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ዘርፎችን ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ? ሚ/ር ሳላምዚ፡- ዛሬ ላይ ሆነን መናገር ይከብዳል፡፡ በሁሉም የኮንስትራክሽን ዘርፎች ላይ ስለምንሰራ በተጓዳኝ ተጠቃሚ የሚሆኑትን ማወቅ የሚያስቸግር አይመስለኝም፡፡ ከመንገድ ሥራ አንስቶ እስከ ሆስፒታል ግንባታ፣ ከግድብ ሥራ እስከ ዘመናዊ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ድረስ እንገነባለን፡፡ ከዚህ አኳያ ተጠቃዎቹን ማየት ይቻላል፡፡ ሪፖርተር፡- ብዙ የውጭ ኩባንያዎች በተለያየ ጊዜ ይመጡና ታላቅ ሕልምና ሥራ ለመስራት እንደተዘጋጁ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም የረባ ስራ ሳይሰሩ፣ በየምክንያቱ የጀመሩትን እንኳ ሳይጨርሱ ይሄዳሉ፡፡ በዚህ በኩል ምንድ ነው የምትሉት? ሚ/ር ሳላምዚ፡- አንድና ሁለት ሕንፃ አቁመን ለመሄድ አልመጣንም፡፡ እንደ ሌሎችም የማይጨበጥ ሕልም አልያዝንም፡፡ ሌሎች አገሮች ውስጥ የምንሰራቸውን ነው እዚህ እንሰራለን የምንለው፡፡ አዲስ አበባ ጥሩ ተስፋ አላት፡፡ ኢትዮጵያ ገና ምንም ያልተነካ ብዙ ሃብት አላት፡፡ ሕዝቡና መንግሥት ለኢንቨስትመንት የሚመቹ ሆነው አግኝተናቸዋል፡፡ በጀርመን፣ በቱርክ፣ በግሪክና በዱባይ ያለንን ልምድና እውቀት እዚህም እንጠቀምበታለን፡፡ በአፍሪካ ለምናንቀሳቅሰው ሰፊ ሥራ በኢትዮጵያ ዋና ጽህፈት ቤታችን ይቋቋማል፡፡ ልክ ከዱባይ ሆነን በአውሮፓና በእስያ ገበያዎች ላይ እንደመንሰራው በአፍሪካም እንደዚያ እናደርጋለን፡፡ በኢትዮጵያ እንዳንሰራ የሚያደርገን ምክንያት የለንም፡፡ ገበያው አለ፤ አረጋጠናል፡፡ ዋጋው ተስማሚያችን ነው፡፡ ማንም የሚጠይቀውን ተመጣጣኝ ዋጋ እንጠይቃለን፡፡ ቋሚ ገበያ እንፈልጋለን፡፡ በኢትዮጵያ የሚታየው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተመራጭ ያደርገናል፡፡ ስለዚህ ሕልም ሳይሆን ሥራ ይዘን ነው የመጣነው፡፡ አንዳንዶች ጥለው መሄድ ብቻ ሳይሆን ከሌላ ያዩትን እየገለበጡ እንደሚሰሩም አይተናል፡፡ ለእኛ ይሄ ጥሩ አይደለም፡፡ የራሳችን አርክቴክቶች፣ መሀንዲሶች፣ ባለሙያዎችና እውቀቱ ያላቸው ብዙ ሠራተኞች አሉ፡፡ የዲዛይን ችግር የለብንም፡፡ ማንም ምንም ሳይከፍለንና ሳንዋዋል የራሳችንን ዲዛይኖች ሰርተናል፡፡ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል፣ ሪዞርት፣ የገበያ ማዕከል ያለው ትልቅ ሕንፃ በዲዛይን አዘጋጅተን ለመንግሥትና ለሌሎችም ባለ ድርሻ አካላት አሳይተናል፡፡ አንድ ፕሮጀክት ጀምረን አለመምጣታችንን ገና ሥራ ሳንጀምር መሥራት እንደጀመርን ለማስገንዘብ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በመጨረሻም ከስነ ሕንፃ ጋር በተያዘ አገሪቱ የረጅም ታሪክ ባለቤት ነች፡፡ ለመሆኑ በዲዛይኖቻችሁ ላይ የአገሪቱ ታሪኮች ይካተታሉ? (ይሄን ጥያቄ የሚመልሱት በስነ ሕንፃ ባለሙያ የሆኑትና የሚስተር ሳሊምዚ ባልደረባ ሚ/ር ሬይ ናቸው፡፡) ሚ/ር ሬይ፡- ስነ ሕንፃ ባህልና ታሪክ የሚካተቱበት ጥበብ ነው፡፡ ወደፊት በምንሰራቸው ሕንፃዎች የአገሪቱንና የሕዝቡን ታሪክና ባህል እናካትታለን፡፡ በዘመናዊው የስነ ሕንፃ ሥራና ዲዛይን አዲስ አበባ ሁለተኛዋ ዱባይ እንደምትሆን አረጋግጥልሃለሁ፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አለን፡፡ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ካፒታል እናንቀሳቅሳለን፡፡ የምንሠራቸው ሥራዎች ብዙዎችን እንደሚያማልሉ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስና በዱባይ የሰራናቸው የከተማ ማዕከሎች፣ የገበያ ሥፍራዎች፣ ጂምናዝየሞችና ሌሎችም በኢትዮጵያ ይደገማሉ፡፡ |
|
| Last Updated ( Thursday, 02 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |