| አዳዲሶቹ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ምርት... |
|
| Wednesday, 01 October 2008 | |
|
አዳዲሶቹ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ምርት መጠን ከፍላጐት በላይ ሊሆን ይችላል
በዳዊት ታዬ በአሁኑ ወቅት በመገንባት ላይ የሚገኙትና ከ2009 በኋላ ሥራ ይጀምራሉ ተብለው የሚጠበቁት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የምርት መጠን በዚያን ወቅት ሊኖር ከሚችለው የገብያ ፍላጐት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችልና ለውጭ ገበያ ጭምር ሊውል እንደሚችል ተጠቆመ፡፡ ይህ የተገለፀው የአገሪቱን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በሚመለከት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ባጠናው የመጀመሪያ ዙር ጥናት ነው፡፡ በዚህ ገና ይፋ ባልሆነው የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት መሠረት ከ2002 ዓ.ም በኋላ ሲሚንቶ ማምረት የሚጀምሩትና አሁን በማምረት ላይ የሚገኙት ፋብሪካዎች ምርት ተደምሮ በዚያን ወቅት ይኖራል ተብሎ ከሚገመተው ፍላጐት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ያመለክታል፡፡ በዚህም ምክንያት በመገንባት ላይ የሚገኙት ፋብሪካዎች ከማምረት አቅማቸው በታች እንዲንቀሳቀሱ ወይም የውጭ ገበያን እንደአማራጭ እንዲጠቀሙ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ጥናቱ ጠቁሟል፡፡ የአገሪቱን ጠቅላላ የኮንስትራክሽን እንቅስቃሴ የዳሰሰው ይኸው ጥናት የኮንስትራክሽን ጥሬ ዕቃ አቅርቦትን በተመለከተ ባሰባሰበው መረጃ መሠረት የሲሚንቶ የአገር ውስጥ አቅርቦት እና ፍላጐት ክፍተትን ለመሙላት በርካታ ሲሚንቶ አምራች ባለሀብቶች የሲሚንቶ ኢንዱስትሪውን ተቀላቅለዋል፡፡ በዚህም እ.ኤ.አ 2006/07 ሦስት ብቻ የነበሩት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወደ 17 ከፍ ማለታቸውን ያሳያል፡፡ እነዚህም ፋብሪካዎች ሥራ ሲጀምሩ የአገር ውስጥ ምርትን ከፍ በማድረግ ከውጭ የሚገባው የሲሚንቶ መጠን ወደሚቀንስበት አቅጣጫ እንዲያመራ ያደርጉታል፡፡ እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም ከ14ቱ አዳዲስ ፋብሪካዎች ውስጥ 4ቱ ሥራ የሚጀምሩ ሲሆን ከበፊቶቹ 3 ፋብሪካዎች ጋር በመሆን የአጠቃላይ የአገር ውስጥ የሲሚንቶ ምርቱን በዓመት ወደ 1.4 ሚሊዮን ቶን ከፍ ያደርጉታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይኸው ጥናት ያመላክታል፡፡ እ.ኤ.አ 2009 ስድስት ተጨማሪ ፋብሪካዎች ሥራ ሲጀምሩ አጠቃላይ የአገሪቱ የሲሚንቶ ምርት ወደ 10.1 ሚሊዮን ቶን ያደርሱታል፡፡ ከዚህም ሌላ ጥናቱ እስኪጠናከር ድረስ በተሰበሰበው መረጃ መሠረት እ.ኤ.አ በ2010 ሁለት ተጨማሪ ፋብሪካዎች ሥራ ይጀምራሉ ተብሎ ስለሚጠበቅ ሥራ ሲጀመር አጠቃላይ የአገሪቱ የሲሚንቶ አቅርቦት 16.4 ሚሊዮን ቶን፣ በ2011 ደግሞ ተጨማሪ አንድ ፋብሪካ እንዲሁ የአገር ውስጥ አቅርቦቱን ወደ 17.6 ሚሊዮን ቶን ያደርሱታል፡፡ ሲሚንቶ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዋነኛ ግብዓት መሆኑን ያመላከተው ይኸው ጥናት በሲሚንቶ ላይ የሚፈጠረው ማንኛውም ነገር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን በማበረታታት ወይም በማዳከም በኩል ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቅሶ አሁን እየተገነቡ ያሉት ፋብሪካዎች በተያዘላቸው ጊዜ ከተጠናቀቁ የአገር ውስጥ ፍላጐትን ያሟላሉ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአገሪቱ ውስጥ ሶስት ሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች እንደነበሩ ያስታወሰው ይኸው ጥናት ሙገር ኢንተርፕራይዝ፣ መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ እና National Cement (ድሬዳዋ ሲሚንቶ) አ.ማ ናቸው፡፡ እነዚህ ኢንተርፕራይዞች ከምስረታቸው ጀምሮ ለአገር ውስጥ ገበያ ምርታቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም እየመራ ባለው የኮንብትራክሽን እንቅስቃሴ እና እየጨመረ በመጣው የሲሚንቶ ፍላጐት ሳቢያ ኢንተርፕራይዞቹ የአገር ውስጥ ገበያውን ፍላጐት ማሟላት እንደተሳናቸው ጥናቱ ያስታውሳል፡፡ በዚህም ሳቢያ እ.ኤ.አ 1999፣ 42 ብር በኩንታል የነበረው የሲሚንቶ ዋጋ በ2006 ዓ.ም 205 ብር በመድረስ በተጠቀሱት ጊዜያት ውስጥ የ388 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የዋጋ ጭማሪው እና እጥረቱ ተዳምረው ኢንዱስትሪው ላይ የጊዜና የገንዘብ ተፅዕኖ በማሳደር ፕሮጀክቶች በተፈለገው በጀት እና ጊዜ እንዳይጠናቀቁ አድርጓል፡፡ ይህም የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ለጊዜው ተጠናቀው ቢሆን ኖሮ ሊገኝ የሚችለውን ግልጋሎት እንዲቀንስ ማድረጉንም አመልክቷል፡፡ አሁን ያለው የሶስቱ ሲሚንቶ አምራቾች አቅም 1.75 ሚሊዮን ቶን በዓመት ሲሆን ሙገር 50.1 በመቶ፣ መሰቦ 48 በመቶ፣ እና National Cement 1.9 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ሙገር 876"000 ቶን በዓመት፣ መሰቦ 840"000 ቶን በዓመት እና National Cement 34"000 ቶን በዓመት በማምረት ላይ ይገኛሉ፡፡ በእ.ኤ.አ 1997/98፣ 782.7 ሺህ ቶን ገደማ የነበረው የሲሚንቶ ምርት በ2005/026 2"747.8 ሺህ ቶን የደረሰ ሲሆን በሂደት ምርቱ በአማካኝ በዓመት 22.6 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ጥናቱ የሚያሳይ ሲሆን በእ.ኤ.አ 2005/06 የነበረው የምርት ስፋት (መጠን) ከምርት አቅም በላይ የነበረ ሲሆን ይህም በፋብሪካዎች መስፋፋት ምክንያት የተከሰተ ነው፡፡ ሆኖም ከዓመት ወደ ዓመት ምርቱ በመውደቅ የሲሚንቶ ምርት በእ.ኤ.አ 2004/05 ከፍተኛ ማሽቆልቆል አሳይቷል፡፡ ከቀደምት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ይህ የፍላጐት መጨመሩ እንዳለ ነው፡፡ የሲሚንቶ ምርቱ ያሽቆለቆለበትም ምክንያት በአብዛኛው የማሽነሪዎች መበላሸት እንደነበርም ተጠቅሷል፡፡ እንደ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ጥናት እ.ኤ.አ በ2005/06 የሀገሪቱ የሲሚንቶ ፍላጐት 4.7 ሚሊዮን ቶን እንደነበር የሚገመት ሲሆን የሲሚንቶ ምርቱ ደግሞ 2.7 ሚሊዮን ቶን በመሆን የሁለት ሚሊዮን ቶን ክፍተት አሳይቷል፡፡ ይህም እንደሚያሳየው ክፍተቱ ከውጭ በሚገቡ የሲሚንቶ ምርቶች መሞላት እንዳለበት ሲሆን ካልሆነ ግን ሲሚንቶ ማግኘት ያልቻሉት የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ስራቸውን ለቀጣዩ ዓመት ማስተላለፍ ግድ ብሏቸው እንደነበርም ታውቋል፡፡ የሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ ጥናት እንደሚያሳየው ከ1992 እስከ 2000 ዓ.ም ታሪካዊ የእድገት ደረጃ ውስጥ የሲሚንቶ ፍላጐት በየዓመቱ 12 በመቶ ይጨምራል፡፡ አዲስ ፈቃድ የተሰጣቸው የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ (2008/09 ዓ.ም) ድረስ ስራ የማይጀምሩ በመሆኑ ምክንያት ክፍተቱ እንደሚሰፋ ይጠበቃል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |