| ቆንጆዎቹና ፖለቲከኞቹ |
|
| Wednesday, 01 October 2008 | |
|
ታክሲ ከሾፈሩ አይቀር ላዳ ነው፡፡ በተለይ ለኛ ለተቀጣሪ ሾፌሮች ላዳ ትመቸናለች፡፡ "ጥራት" ያለው አነስተኛ ሰው ይዞ መክነፍ፣ "ጥራት" ያለው የፖለቲካ ትንታኔ ለመስማት ያስችላል፡፡ ጥራት ያላቸው ቆንጆዎች ይዞ መብረር፣ ጥራት ያለው የሽቶ ዓይነት በመዓዛው ብቻ ለመምረጥ ያስችላል፡፡ ላዳ ውስጥ የጤፍና የዳቦ መወደድን እያወራ የሚያስጨንቅ አታዩም፡፡
ላዳ ውስጥ ስለምሽቱ ጥሩነት የሚያወሩ እንጂ ስለ መሳፈሪያ የሚያስብ ሰው አይሳፈርም፡፡ ስለኩራባይዜርና ስለ ብሉ ሌብል ውስኪ እንጂ ስለውሃና ድራፍት መወደድ የሚያወሩ ላዳን አይወዱም፡፡ እኛም ይኸው ስለሚሻለን ክፍያውን እላይ እንሰቅለዋለን፡፡ የቻለ ብቻ ደንበኞችን ይሆናል፡፡ "የቻለ ያንሳሽ" የሚል ቅፅል ስም እናውጣላት ይሆን? ላዳ ታክሲን መኪና ያለው ሳይቀር ይወደዋል፡፡ በላዳ ታክሲ ማንም ሳያውቅ ሹልክ ብሎ ጉዳይን ከውኖ መመለስ ይቻላል፡፡ መታወቅ የማይፈልግ ፖለቲከኛ፣ መታወቅ የማትፈልግ ቆንጆ ላዳን ይመርጣሉ፡፡ በዚህ ምክንያትም እኛም የፖለቲካ እውቀትና የቆንጆዎች ዓላማና እንቅስቃሴን ዕውቀት አጥለቅልቆናል፡፡ ሾፌር፣ የኮስሞቲክስ የሽያጭ ክፍል ኃላፊ መሆን ዕጣ ክፍሉ ሊሆን ይችላል ወይም". "የፖለቲካ ተንታኝ" ለመሆን ይቻለዋል፡፡ ክፋቱ እንደዚህ ዓይነት ተቋም አለመኖሩና አሉ ቢባሉም በችሎታ ተወዳድሮ የሚገቡባቸው አለመሆናቸው ነው፡፡ ማንም እንዳፈተተው ፖለቲካውን ሊፈተፍተው ይፈልጋል፡፡ አንደኛ ከፖለቲካ ሊቃውንት ጋር ለሚውለው ዕድል አይሰጥም፡፡ በታክሲዬ ውስጥ በየጊዜው ሲተነተንና ሲነገር የምሰማው ረቂቅ ፖለቲካ፣ በአላዋቂዎች ከሚፈተፍተው የተለየ መሆኑን አወቃለሁ፡፡ ግን ምን ያደርጋል? ባለታክሲን ነገሬ ብሎ ስለፖለቲካ የሚጠይቀው የለም፡፡ የላዳ ሾፌርነት ጥሩ ነው፡፡ ዘና ያደርጋል፡፡ በየ70 ሳንቲም መንገድ መጯጯህና መንቀዥቀዥ የለም፡፡ ዘና ብሎ እወንበር ላይ መለጠጥ ነው፡፡ መቻኮል አያስፈልግም፡፡ "የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል"፤ የሚባለው ተረት ለባለላዳ ሹፌር ፀባይ የተነገረ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እወንበራችሁ ላይ እንደተለጠጣችሁ፣ አንዳች የሚያህል ታኮ ጫማ አድርጋ የተራቆተ ጭኗን፣ ደረቷን እያሳየች እየተውረገረገች ትመጣና ዋጋ ሳትከራከር ከኋላ በር ጥልቅ ትላለች፡፡ ወዲያው ታክሲዬ በሽቶ መዓዛ ትናወጣለች፡፡ የሕይወት ሃድራ ይገባል፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹ ሲገቡ ዋጋ መከራከር ቀርቶ መጠየቅ የለም፡፡ በኔ ላዳ የሚሳፈሩበትን ዓላማ ዋጋ፣ ቀድመው ስለሚያስቡት ስለታክሲ ክፍያ አይጨነቁም፡፡ ብዙ ንግግር አይፈልጉም የሚሄዱበትን በአንድ ቃል ብቻ ይነግሩኛል፡፡ ሞተሬን አንስቼ ላፍ ነው፡፡ በፊት መስተዋት ከንፈሯን ቀለም ስትቀባ አያለሁ፡፡ ባሞጠሞጠች ቁጥር የምትሳም ትመስላለች፡፡ ያን ጊዜ ላዳ ትረገጣለች፡፡ በአየር ላይ እንደመክነፍ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ችግሩ የአዲስ አበባ መንገዶች በመኪና የተጨናነቁ መሆናቸው ነው፤ እናደዳለሁ፡፡ እንደዚያ ሲሆን ደንበኛዎቼ ይናደዳሉ፡፡ የዚች ዓይነት ልጆቿ ደግሞ መጨናነቅ አይፈልጉም፡፡ ያን ጊዜ እኔም መጨነቅ እጀምራለሁ፡፡ እነዚህ ዓይነቶቹ አብዛኛዎች ባህርያቸው አንድ ነው፤ አለባበሳቸው ያው ነው፤ አሁን አሁን ሱሪያቸው ከመቀመጫቸው ዝቅ እያደረጉ ሳይ እያስደነገጠኝ ተቸገርሁ እንጂ ቀሚሶቻቸውን እወድላቸዋለሁ፡፡ አጭርና ስስ፡፡ "እምብርቴን እዩልኝ" ልብሳቸውም አያስጠላም፡፡ እነዚህ ዓይነቶቹን ገና ሳያቸው ስንት እንደሚከፍሉኝ በደንብ አውቃለሁ፡፡ የት እንደሚሄዱም አውቃለሁ፡፡ ማወቄንም እነሱም ያውቃሉ፡፡ የጫማዋን ዓይነት፣ የቀሚሷን የሽቶዋን ደረጃ አመዛዝኜ፣ ደረጃዋን የጠበቀ ክፍያ እንደምትሰጠኝ በዓይኔ እነግራታለሁ፡፡ ባለሃብት፣ ባለሥልጣን፣ ታዋቂ ፖለቲከኛ ወይም አርቲስት፣ እያሰበች ስለምትሄድ ለኔ ክፍያ አትጨነቅም፡፡ ከታክሲዬ ሲወርዱ "ሃርድ" አይፈልጉም፡፡ በዚህ ሰዓት እዚህ ቦታ እንድትመጣ ብለው ያዙኛል በፈገግታ እሽታዬን እገልፃለሁ፡፡ ሲያዙም ደስ ይላሉ፡፡ ኧረ ቢረግጡም ደስ ሳይሉ አይቀርም፡፡ ጡታቸው ላይ አንገቴን እንደተከልሁ "ጉደኛ" የሚባለውን ብር ይወረውሩልኛል፡፡ በዓይኔ ሸኝቻቸው ወደ ቦታዬ እፈተለካለሁ፡፡ ተመልሼ በሰዓቱ ገጭ፡፡ ባለላዳ ቀጠሮ አክባሪ መሆኑ የተመሰከረለት ነው፤ ደንበኝነታችን ሳይናወፅ ይቀጥላል፡፡ የቆንጆዎቹ የተቀቡት ሽቶ፣ ከአፍንጫዬ ሳይወጣ ውበታቸው ከዓይኔ ሳይጠፋ ጠና ያሉ ፂማቸውን የሚያሻሹ "ባለካራባቶች" ጎልማሶች ያጋጥሙኛል፡፡ እነዚህኞቹ ሽክ ማለት ያበዛሉ፡፡ በገሚስ እንግሊዘኛ ስለሚናገሩ፣ አንዳንዱን ፍሬ ሃሳቡን አልይዘውም፡፡ ከእነዚህ ዓይነት ሰዎች ጋር ስሄድ አልጣደፍም፡፡ እነሱም መጣደፍ አይፈልጉም፡፡ የሃገራችንን ፖለቲካ አንጠርጥረው ያበጥሩታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲተቹ አይፈሩም፤ ሚኒስትሮቹን ከነሚስቶቻቸው እያነሱ ይተቻሉ፡፡ ባለሃብቶቹን፣ ተቃዋሚዎቹን በትችት "ራቁታቸውን ያስቀሩዋቸዋል"፡፡ "ምነው እንደነዚህ ዓይነቱ አገር ቢመራ" እስክል ድረስ ክሱንም ፍርዱንም ሁሉንም ያብራሩታል፡፡ "ምነው እንደነሱ ሁሉንም ባለሥልጣኖች ባወቅሁዋቸው" እስክል ድረስ የማይጠሩት ባለሥልጣን የለም፡፡ አይሰጉም፡፡ በተለይ የታላላቅ ባለሃብቶችን ስም እየጠሩ ያላቸውን ቅርበት እያነሱ ሲያወሩ እቀናለሁ፡፡ ላዳዬን ለመለወጥ ያምረኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በስማቸው እየጠሩ ሲያነሱ የባለታክሲዎች መብት እንዲከበር የእህል ዋጋ እንዲቀንስ የቤት መስሪያ ቦታ እንዲያሰጡን ቢያሳዝዙልኝ ብዬ እመኛለሁ፡፡ የሚዘልፏቸውን ያሳፈርኩ ዕለት ደግሞ አቤት ጭንቀቴ፡፡ የበለጠ ግን ሁሉንም ፖለቲካ ስላስተማሩኝ እወዳቸዋለሁ፡፡ የላዳ ሹፌር ፖለቲካን እንደተሳፋሪው ዓይን ያውቀዋል፡፡ ማ ተቃዋሚ ማ ደጋፊ እንደሆነ በእንቅስቃሴው እናውቀዋለን፡፡ ገንዘብ ላይ ግን ቁጥቦች ናቸው፡፡ ክርክር ያበዛሉ መኪና ቢኖራቸውም ላዳን ይፈልጋሉ፡፡ ለማንኛው ፣ሰወር፣ ብሎ ለመሄድ ላዳ የተሻለች ናት፡፡ እነዚህን ዓይነት ሰዎች የረቀቀ ፖለቲካ ሲሰማ ለሚውልና ለሚያድር ሹፌር ከየመንገድ ፖለቲከኛ ጋር ሊግባባ አይችልም፡፡ እኔም ከቤተሰቤም ከጓደኞቹም ልስማማ አልቻልሁም፡፡ ብነግራቸውም አይገባቸውም፡፡ ማወቅ አራርቆናል፡፡ ባለፈው ሳምንት የሆነውን ልንገራችሁ፡፡ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በወጣት ይተኩ የሚባል ነገር ሲወራ ሰነበተ፡፡ እኔም "እውነት ነው" ስል ሰነበትሁ፡፡ መሳሳቴን ያወቅሁት ግን አንድ ቀን ፖለቲከኛ ተሳፋሪዎቼ በትንታኔ አስደግፈው የሚባለው ትክክል አለመሆኑን ሲናገሩ ሰምቼ ነው፡፡ የላዳ ሹፌር ባልሆን ያንን ስህተቴን እንዴት አርመው ነበር? ሃገሪቱ በአሁኑ ሁኔታ መገኘቷም በራሱ ታላቅ ውጤት መሆኑ፣ ልምድ ያላቸው መሪዎች ባይኖሩ ኖሮ ሃገሪቱ የመዓት ውርጅብኝ እንደሚወርድባት ሲናገሩ ሰማኋቸው፡፡ ከዚህ የባሰ ከሚመጣስ የማውቀው ሰይጣን ይብላኝ፤ እስክል ድረስ ነገር ሁሉ ገባኝ፡፡ ለነገሩማ ሰውስ የት ይገኛል? እንደ ጥራ ጥሬ አይዘራ ነገር፡፡ ኧረ ባለሥልጣኖቻችን ዕድሜያቸውን ያርዝምልን". ግን ይኸንን መንገድ ዳር ለሚቆም ፓለቲከኛ ብናገር ማን ያምነኛል? ሰሞኑን ደግሞ ጋዜጦች የታላቁን ባለሃብት ሥራ እየወቀሱ ማውጣት ጀምረዋል፡፡ እኔም እውነት መስሎኝ "እንዴት እንዲህ ይደረጋል፡፡ በገንዘብ ክብራችን ተደፍሩዋል ስል ሰነበትሁ፡፡ አንድ ቀን ግን ያሳፈርኩዋቸው መልካቸውም ልብሳቸው ያማሩት ፖለቲከኞች የተናገሩትን ሰምቼ ራሴን ወቀስሁ፡፡ ንስሐ ገባሁ ብል ይሻላል፡፡ ፖለቲከኞቹ እንደሚሉት ታላቁ ባለሃብት ብዙ ነገር ሰጥተዋል፡፡ ለኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ስንት ስንት ገንዘብ አውጥተዋል፡፡ ዓይናችን ከሚያየው በላይ ብዙ ሥራ እንደሰሩ ሲናገሩ ሰማኋቸው፡፡ ለታላቁ አርቲስት ለጥላሁን ገሠሠ 500 ሺህ ዶላር ቤት ያውም አሜሪካ ገዝተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ታጠረ የሚባለው መሬት የታጠረበት ዕቃ ከመሬቱ ዋጋ በላይ እንደሚያወጣ ሲናገሩ ሰማኋቸው፡፡ ኧረ ስንት ስንት ነገር አድርገዋል፡፡ ግን አሁን ይሄን ብናገር ማን ያምነኛል፡፡ እኔ በላዳዬ ምክንያት ይኸን አወቅሁ፡፡ ይኸን እድል ያላገኘው ወገኔ ግን ብዙ ነገር ሳያውቅ እንዳወቀ ሆኖ መናገሩ አሳፈረኝ፡፡ ላዳዬ እውቀት ናት፤ ሃብትም ናት፤ ፖለቲካም ናት ሽቶም ቀሚስም እምብርትና ዳሌም ናት፡፡ ውበት ናት፡፡ ሽው በቸርችል ጎዳና፡፡ ሽው በቦሌ መንገድ፤ ሽው ወደ ቆንጆዎቹና ፖለቲከኞቹ፡፡ በሁሉም ቦታ እንገኛለን፤ ሁሉንም ነገር እናውቃለን የሚል ማስታወቂያ ማስለጠፍ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |