| ታሪክ - ተዝካር አውጭ |
|
| Wednesday, 01 October 2008 | |
|
በዘመናት፣ ውስጥ ታሪክና ሥራ የሌለው እጅም ልጅም፣ ወዳጅም፣ ተዝካር አውጭም ስም አስጠሪም የሌለው ነው፡፡ ተዝካር አውጭ ማለት ታሪክ ነው፡፡ ስም አስጠሪም ማለት ሥራ ነው፡፡ በሕይወቱ ሳለ የዋለባቸው ቀኖችና ያደረባቸው ሌሊቶች ሁሉ፤ የተመላለሰባቸው መንገዶች ከሕይወት በኋላ ምን ሠራህ? ምን ፈጠርህ? ምን አደረግህ? እስኪ አስረዳን? በማለት ሳይቆጣጠሩት እንደማይቀሩ ሕሊና ያመዛዝነዋል፡፡
"ዘመንየ ኩሎ ፈጸምኩ እንበለ ጸሎት ወጾም፡፡ መዓልት በመብልዕ፤ ወሌሊተ በንዋም፡፡" (ቀን ያለጸሎትና ያለ ጾም በመብል በመጠጥ በዋዛ በፈዛዛ፤ ሌሊት ያለ ቁም ነገርና ያለ ሥራ በዕንቅልፍና ያለ አሳብ ተዘርሮ በማደር፤ ዘመኔን ሁሉ ፈጸምሁ) ሲል ሕሊናውን በሕሊናው ወቃሽ የሆነው ባለ ቅኔ የተቀኘው ቅኔ፣ የዘመን በከንቱ ማለፍና፤ የጊዜ በክ (ብላሽ) ሁኖ መቅረት የሚያስከትለውን ጸጸት የሚያስረዳ ነው፡፡ እውነት ጣፈጠችም መረረችም፤ እንደ ተጠቃችና እንደ ተበደለች አትቀርም፡፡ እንደ ተከደነ ሳይከፈት፤ እንደተሰወረ ሳይገለጽ የሚቀር የለም የተባለው ስለዚህ ነው፡፡ ዘመን ቢያጠቃትና ቢበድላት ዘመን ይክሳታል፡፡ ዘመን ቢደብቁት ዘመን ይገልጣታል፡፡ ያዕቆብ ከአማቱ ከላባ ጋራ በተዋቀሰ ጊዜ "እውነቴ ይመሰክርልኛል" እንዳለው፤ የደግ ባለ ታሪክ ሰው ምስክሩ እውነት ነው፡፡ እውነትን ምርኩዝ ያላደረገ ሁሉ ኑሮው አንካሳ፤ ውጤቱ ወልካሳ፤ ታሪኩ ተልካሳ፤ እየሆነበት ሳይቸገር አይቀርም፡፡ (ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፣ ታሪክ አይሙት እንዲያጫውት፣ 1957) በሐረር ላይ ስለ ሆነው ነገር መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም የመስቀል ዕለት የሸዋ ሰው አዲስ አበባ ላይ አዲስ መንግሥት ሲያቋቁም፣ አቤቶ ኢያሱ ሐረር ላይ ሆነው ስለ መስቀል በዓል የወታደር ሰልፍ ይመለከቱ ነበር፡፡ እኩለ ቀን ሲሆን የስልከኞቹ አለቃ አቶ ተሰማ እሸቴ ከአዲስ አበባ በስልክ የሰማውን ወሬ ይዞ ከልጅ ኢያሱ ዘንድ ቀረበና እንዲህ አላቸው፣ "የሸዋ ሰው ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ስብሰባ አድርጎ አዲስ መንግሥት አቋቁሟል፣ ጌታዬንም እስላም ሆነዋል ብሎ ከመንግሥት ሽሮ ወይዘሮ ዘውዲቱን ንግሥት ብሎ አንግሠዋል፤ ደጃዝማች ተፈሪን አልጋ ወራሽ አድርጎ ሾሟል" ብሎ ነገራቸው፡፡ ልጅ ኢያሱም በነገሩ ስለ ደነገጡ፣ ሰልፉን አሰናበቱና ከሰልፉ ላይ ተነስተው ወደ ግቢያቸው ሄደው ያስቡበት ጀመር፡፡ በማግሥቱም ኀሙስ መኳንንቱ ሁሉ ከፊታቸው እንዲቀርቡ አዘዙ፡፡ ካህናትም መስቀልና ወንጌል ይዘው እንዲቀርቡ አደረጉና ሃይማኖት አለመለወጣቸውን ለማስረዳት በቃላቸው ይምሉ ይገዘቱ ጀመር፡፡ ቀጥሎም እንዲህ አሉ፡፡ "የሸዋ ሰው እኔን እስላም ሆነ ብሎ አመካኝቶ ይኸው አድማ አድርጎብኛል፡፡ እኔ እስላሞችን ማስጠጋቴና ወዳጅ ማድረጌ የኢትዮጵያን ወሰን ለማስከበር፣ ግዛታችንንም እስከ ባሕር ለማድረስ እንዲረዱኝ አስቤ ነው እንጂ ሃይማኖቴን ለውጬ እስላም አልሆንኩም፤" ካሉ በኋላ "በሉ እናንተም እንዳትከዱኝ ማሉልኝ" ብለው መኳንንቱን ጠየቁ፡፡ በዚህ ጊዜ ደጃዝማች ባልቻ ተነሱና "ጌታዬ ሃይማኖት ለወጡ የተባሉት እርስዎ ነዎትና አለመለወጥዎን እንድንረዳ መጀመሪያ እርስዎ ይማሉልን" አሏቸው፡፡ አቤቶ ኢያሱም ወደ ቀሳውስቱ ቀርበው በመስቀልና በወንጌል ማሉ፡፡ መኳንንቱም "የክርስቲያን ሃይማኖታቸውን የለወጡ መስሎን ነበር እንጂ ካልለወጡስ እኛም አንከዳቸውም" እያለ ተናገረ፡፡ ቀጥሎም እያንዳንዱ ሰው እየቀረበ "ጌታዬን አልከዳም፣ እንደ ወንጌሉ ይደምስሰኝ፤ እንደ መስቀሉ ይበሳሳኝ" እያለ እየማሉ አለፈ፡፡ ደጃዝማች ባልቻም በዚሁ ዓይነት ማሉ፡፡ (መርስዔ ኀዘን ወ/ቂ፣ የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፣ 1999) ወይ-በአራት መንገድ ሲፈታ የማማረጥ ቃል ምስጢሩ ማማረጥና ማሻሻል ነው፡፡ (ሐፄ ቴዎድሮስ ባሏን የሰቀሉባት) "ወይ አልተቀደሰ የባረኩት ሰው፤ ንጉሥ መስቀልዎን ቢተውት ምነው፡፡ ሁለተኛም የምኞትና የፍላጎት አንክሮ ቃል ይኾናል፡፡ (ግጥምና ሙሾ ስለጐንደር ጥፋት) ቴዎድሮስ መጣ ዓይኑን አፍጦ፤ ወይ መሸሸጊያ ታናሽ ቁጥቋጦ፡፡ ተከተለኝ ብዬ ዙሬ፣ ዙሬ ሳይ፣ ወይ ጥጋብ ወይ ኩራት ጎንደር ቀረ ወይ ሦስተኛም ያቤቱታ ቃል የጥሪ ተሰጦ ይሆናል፡፡ (ግጥም የበለው እኅት ተማርካ በመተማ ሳለች) ጐዣም አፋፉ ላይ የሚጣራው ማነው፤ ወንድሜ እንደሆነ ወይ በለው ወይ በለው፡፡ ምስጢሩ እንደ ላይኛው ነው፡፡ አራተኛም የጥያቄ ቃል ይኾናል፡፡ ኼደ ወይ መጣ ወይ፡፡ (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ 1948 ዓ.ም) ስለመስቀል በዓል ከእልፍኝ አስከልካይ የወጣ ፕሮግራም ስለ1963 ዓ.ም የደመራና የመስቀል በዓል አከባበር የግርማዊ ንጉስ ነገስት ዋና የእልፍኝ አስከልካይ ጽ/ቤት ትናንት ከዚህ የሚከተለውን የበዓል አከባበር ፕሮግራም አውጥቷል፡፡ 1ኛ. ቅዳሜ መስከረም 16 ቀን 1963 ዓ.ም ከቀትር በኋላ ከ9 ሰዓት ጀምሮ የግቢ ሚኒስቴር፣ የልዩ ልዩ ክፍል ባልደረቦችና በማዘጋጃ ቤቱ አማካይነት ከከተማው ሕዝብ የተመረጡ ከብሔራዊ ጦርና ከፖሊስ ሠራዊት፣ እንዲሁም ከፋይናንስ ክፍል ዘበኞቹ፣ ከምድር ጦር ሠራዊት፣ ከአየር ኃይልና ከክብር ዘበኛ የበዓሉ ተካፋዮች እንዲሆኑ የተመረጡ በወጣው ዝርዝር ፕሮግራም መሠረት በራስ ደስታ ዳምጠው መንገድ ስፍራቸውን ይይዛሉ፡፡ 2ኛ. በ11 ሰዓት ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት፣ ልዑል መርዕድ አዝማች አስፋው ወሰን ኃይለ ሥላሴን አስከትለው በፖሊስ ሞተር ብስክሌቶች ታጅበው በዳግማዊ ምኒልክ ዋና መንገድ፣ በልዑል መኰንን ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ድልድይ አልፈው የደመራ በዓል በሚከፈልበት መስቀል አደባባይ ይደርሳሉ፡፡ 3ኛ. ወዲያው ጸሎተ ወንጌል ይደረግና ካህናቱ ደመራውን ዞረው ከተመለሱ በኋላ፣ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ልዑል መርዕድ አዝማች አስፋው ወሰን ኃይለ ሥላሴን፣ ልዑላን መሳፍንቶችንና ክቡራን ሚኒስትሮችን፣ መኳንንቶችን፣ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን አስከትለው ደመራውን ሶሰት ጊዜ ከዞሩ በኋላ በሙሉ ቤት አዛዥ የተዘጋጀውን ችቦ ታድሎ ግርማዊነታቸው ደመራውን አቀጣጥለው ለመመልከቻ ወደተዘጋጀላቸው ልዑላዊ ቦታቸው ይመለሳሉ፡፡ 4ኛ. ግርማዊ ንጉሥ ነገሥቱን ተከትለው ደመራው የዞሩት ክቡራን ሚኒስትሮች፣ መኳንንቶች፣ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ አብረዋቸው የያዟቸውን ችቦ በደመራው ላይ ከጣሉ በኋላ ወደሥፍራቸው ይመለሳሉ፡፡ 5. ከዚህ በኋላ በንጉሠ ነገሥቱ ከዚህ ቀጥሎ በተመለከተው ቅደመ ተከተል የሰልፍ ተከታይ የሆኑት ምድቦች ችቦውን አብረው በዝግታና በስርዓት "እዮሐ አበባዬ መስከረም ጠባዬ" እያሉ ችቦዋቸውን እየያዙ ያልፋሉ፡፡ ሰልፈኛው በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ፊት አልፎ እንዳበቃ ግርማዊነታቸው በመጡበት አኳኋን ታጅበው በ12 ሰዓት ተኩል ወደ ኢዮ ቤልዩ ቤተ መንግሥት ይመለሳሉ፡፡ እሑድ መስከረም 17 ቀን 1963 ዓ.ም ከቀኑ በ6 ሰዓት ስለ መስቀል በዓል ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ለልዑላን መሳፍንት፣ ለብፁዐን ጳጳሳት፣ ለክቡራን ሚኒስትሮች፣ መኮንኖች፣ ለአየር ኃይልና ለባሕር ኃይል መኮንኖች፣ ለፖሊስ ሠራዊትና ለየክፍሉ መኮንኖች በታላቁ ቤተ መንግሥት የምሳ ግብዣ ያደርጋሉ፡፡ (አዲስ ዘመን፣ መስከረም 15 ቀን 1963 ዓ.ም) ኦ! እንዴት ያደምቃል ኦ" እንዴት ያደምቃል ውበት ላይ ውበትን በአንገት ላይ ሲያጠልቁት ሀቀኝነት/ጌጥን፡፡ ጥጌረዳ ውብ ናት በርቀት ሲያዋት ደሞም ታረካለች ቀርበው ሲያሸቷት፡፡ የዱር አበባውም እንደ ጥጌረዳ የጠደይ እስትንፋስ ቡጡ ሲፈነዳ ለጉድ ነው ሲፈካ" ግና፤ እንደ ጥጌረዳ መቼ ይመኙታል? እንደ ፍቅርኛ አንገት ሊያሸቱት ይሹታል? ከሩቅ እንደታየ፤ ከሩቅ ይጠገባል የመዓዛው ሽቱ በዓይናዋጅ ያከትማል፡፡ አንቺም ልጅ ውቢቱ፤ አንቺም ልጅ ጠጂቱ፤ መወድሴ ጨምቆ ካጣራሽ በኋላ ሐቅሽን ያሳያል እንደ ማር ወለላ፡፡ (ተስፋዬ ገሠሠ፣ ጎሕ ሲቀድ፣ 2000) ገራገር በኮንዶም ግዥ ምክንያት ፍቅረኛሞቹ ተጣሉ ባልና ሚስቶቹ ለቤት ወጭ ሽቦ በመስመር ግንኙነት (ኦን ላይን) ባዘዙት ግዥ ላይ ኮንዶም ጨምሮ በመላኩ የአራት ዓመት ግንኙነታቸውን የሻረውን ቲስከ ካምፓኒ ከሰሱ፡፡ የ40 ዓመቷ ሊኒን ኒውቤይ ፍቅረኛዋ የሚያዘወትረው የኮንዶም ዓይነት በሚገዙት ዕቃዎች ዝርዝር በመስፈሩ ከጀርባዋ ሌላ የፍቅር ግንኙነት እንዳለው ገምታ ግንኙነቷን አቋርጣለች፡፡ ኒውቤይ የ29 ዓመቱን ፍቅረኛዋን ኦንዲይ አሎያን ኮንዶሞቹን ማዘዙስ ከሌላ ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑን ስለሚጠቁም ከሳዋለች፡፡ "የቴስኮ ወዬን ስመለከት ያየሁትን ማመን አልቻልኩም ስለዚህ አንደይን ከሰስኩት" ትላለች ኒውቤይ፡፡ ሁለቱን ፍቅረኛሞች መለያየታቸውና መካሰሳቸውን የተረዳው ቴልኮ ጉዳዩን ሲመረምር የኮንዶሙ ግዥ የተጨመረው በአንድ አዲስ ሠራተኛው ስህተት መሆኑን ጠቅሶ በዋና ሥራ አስኪያጁ የተፃፈ የይቅርታ ደብዳቤ መላኩን ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡ ፍቅረኛሞቹ ይቅርታውን ተቀብለው ክሱን አንስተዋል፡፡ "ግን በእንዲህ ዓይነት ነገር ስንት ፍቅረኛሞች እንደተበጣበጡ ገምቱ" ብላለች ኒውቤይ፡፡ ወንጀለኛው ሥጋውን ለዓሳዎች ተናዘዘ የቴክሳሱ ነፍሰ ገዳይ ከሞተ በኋላ ሥጋው ተቆራርጦ ለዓሳዎች ምግብ እንዲሆን ተናዘዘ፡፡ ጌን ሄዞርን የተባለው የ47 ዓመቱ ጎልማሳ በፈፀመው ወንጀል የሞት ፍርድ ከተፈረደበት በኋላ የቀድሞ ኑዛዜውን ለውጦ ሥጋው ተቆራርጦ ለዓሳዎች እንዲሰጥ መናዘዙን ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡ ቀደም ሲል ወንጀለኛው አስከሬኑ ለአርቲስት ማክሮ ኢቫርስቲ ተሰጥቶ በአርት ኤግዚቢሽን እንዲታይ ፈቅዶ ነበር፡፡ አባቱን፣ እንጀራ እናቱንና እንጀራ ወንድሙን የገደለው ሄዘርን በሞት ቅጣት እንዲቀጣ ከተወሰነ በኋላ ለኤግዚቢሽን እንዲታይ ከፈቀደ በኋላ ኑዛዜውን መለወጡ አርቲስት ኢቫርስቲን ቅር አሰኝቶታል፡፡ ታሪኩ ብዙ የሚስበኝ አይደለም፡፡ ነገር ግን ለዚህ አርት አካል መሆን የፈለገው ለሕብረተሰቡ ሊጠቅም የሚችለው ይኸንን በማድረግ ብቻ መሆኑን ስላመነበት ነው፡፡ ይላል ኢቫርስቲ አርቲስቱ በቀድሞው ኑዛዜ መሠረት እንዲፈፀም ከፈለገ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ይኖርበታል፡፡ ሌባው የልጁን ቃላት በክንዱ እንዲያንጠለጥል ተፈረደበት ዳንኤል ክሊላንድ አሜሪካ ውስጥ በሚቺካን ካላማዞ ሲኖር በስርቆት ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ አሜሪካም ዳኛ ፓሜላ ላይትቬየት መረጃዎቹን አገናዝበው በስርቆት ወንጀል ጥፋተኛ ነህ ሲሉ በየኑበት፡፡ በቅጣቱ ላይ ግን የተለየ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ሌባው ክሌላንድ በፍርድ ቤት ሲጠየቅ ልጁ "አባቴ መስረቅህን አቁም" "Daddy stop steating" ብሎት እንደነበረ ተናገረ፡፡ ዳኛዋ የሱን ቃል ይዘው ወንጀሉ ሰባት ወራት ሊያሳስረው የሚችል ቢሆንም ቅጣቱ ተሻሽሎ ልጁ የመከረው ምክር ቃላት በክንዱ ላይ ተፅፎ ወይም ታትሞ ለሰባት ወራት ይዞ እንዲቆይ መፍረዳቸውን የካላማዞ ጋዜት ዘግቧል፡፡ ኢጣሊያዊው ሚስቱን ከቄሱ ጋር ተኝታ አገኛት ኢጣሊያዊው በጧት ገስግሶ ከሄደበት ወደቤት ሲመለስ የአካባቢው ቄስ ከሚስቱ ጋር አልጋ ውስጥ አገኛቸው፡፡ ንዴቱ የገነፈለበት ኢጣሊያዊ ባል ወደ ጳጳሱ ቢሮ በንዴት ገብቶ ስለድርጊቱ ማብራሪያ እንደሚፈልግ ይጠይቃቸዋል፡፡ ጳጳሱ ፖሊስ ጠርተው ከንዴት እንዲያበርደው ካደረጉ በኋላ ተጠርጣሪው ቄስ ወደሌላ ቦታ እንዲዛወሩ መደረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ የ53 ዓመቱ ቄስ በመፅሐፍ ቅዱስ እውቀቱ የተለየ ተብሎ የሚሞገስና ለባልና ሚስቱም ወዳጅ እንደነበር ድርጊቱን የዘገበው ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡ "ቄሱን ሁልጊዜም የማከብረው ነበር፡፡ አሁንም አከብረዋለሁ፡፡ መልካም ሰዎች አንድ ቀን በሰሩት ስህተት ሁሉንም ጥሩ ሥራዎቻቸውን ማጣጣል አይገባም"". ብለዋል ጳጳሱ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |