Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow "በሕግ ትምህርት ዩኒቨርሲቲዎች...
"በሕግ ትምህርት ዩኒቨርሲቲዎች... E-mail
Wednesday, 01 October 2008
Image"በሕግ ትምህርት ዩኒቨርሲቲዎች የተግባር ልምምድ ዕድል አይሰጡም"
አቶ ደጀኔ ግርማ

አቶ ደጀኔ ግርማ ጃንካ በጂማ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፋኩልቲ ዲን ናቸው፡፡ አቶ ደጀኔ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ (ኤልኤልቢ) በከፍተኛ ውጤት የተመረቁ ሲሆን ሁለተኛ የሕግ ዲግሪያቸውን (ኤልኤልኤም) ከደቡብ አፍሪካው ፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ በሰብዓዊ መብትና ዲሞክራታይዜሽን አግኝተዋል፡፡ ሰለሞን ጎሹ በዩኒቨርሲቲው የሕግ ፋኩልቲ ቤት ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የጂማ የኒቨርሲቲ የሕግ ፋኩልቲ ሥራ ከጀመረበት ጀምሮ ባለፉት ስድስት ዓመታት ምን አበይት ተግባሮችን ፈጸመ?

አቶ ደጀኔ፡-
ፋኩልቲው ራዕዩንና ዓላማውን ያሳኩ ተግባራትን በተሳካ ሁኔታ ፈጽሟል፡፡ አንደኛ በመደበኛው፣ በማታውና በክረምት መርሐ ግብር የሀገሪቱን የሕግ ባለሙያ ጥማት ለመቅረፍ የሚረዱ ከ1000 በላይ ብቃት ያላቸው የሕግ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ አስመርቋል፡፡ ሁለተኛ ፋኩልቲው ለኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት እድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያስችለውን የሕግ ምርምርና ጥናት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አከናውኗል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ፋኩልቲው የጂማ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መጽሄትን አቋቁሟል፡፡ መጽሔቱ በዓመት ሁለት ጊዜ ለሕትመት የሚበቃ ሲሆን ቀደም ብለን ሁለት ቅጾችን ለንባብ አብቅተናል፡፡ ለሦስተኛው ቅጽ የተሳትፎ ጽሁፎችን ለማግኘት ጥሪ አድርገናል፡፡ የፋኩልቲው አስተማሪዎች በሀገሪቱ ለማስተማሪያነት የሚጠቅሙ መጽሀፍትን እየጻፉና እያሳተሙ ይገኛሉ፡፡ ፋኩልቲው እነሱን ለመርዳትና ለማበረታታት ቁርጠኛ ነው፡፡ ሦስተኛ ፋኩልቲው በተማሪዎቹ አማካኝነት ለአካባቢው ማኅበረሰብ የነፃ የሕግ አገልግሎት መስጠት ችሏል፡፡ አራተኛ ፋኩልቲው ስድስት እና ሰባት ዓመት ብቻ የሆነው ቢሆንም በብሄራዊ የአምሳለ ፍርድ ቤት (Moot Court) ውድድሮች በተደጋጋሚ አሸናፊ ከመሆኑ ባሻገር በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ የአምሳለ ፍርድ ቤት ውድድር ሀገሪቱን መወከል ችሏል፡፡ በአምሳለ ፍርድ ቤት ውድድሮች ያገኘነው ድል ለፋኩልቲው መልካም ስም ገንብቷል፡፡ ለጂማ ዩኒቨርስቲም ትልቅ ስኬት ሆኖታል፡፡

ሪፖርተር፡- የእድሜው አጭር መሆን በፋኩልቲው እንቅስቃሴ ላይ ተፅእኖ አልፈጠረም?

አቶ ደጀኔ፡-
በጎላ ሁኔታ ተጽእኖ ፈጥሯል ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም በተቻለን አቅም ሁሉ እየሰራን ያለው ስራ ባሰብነው መልኩ እየሄደ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ተጨማሪ የሰውና የቁስ ኃይል ማግኘትና ያለንንም ማዳበር እንደሚያስፈልገን መካድ አይቻልም፡፡ ይህ ደግሞ በእንቅስቃሴዎቻችን ላይ መጠነኛ ተፅዕኖ ይኑረው እንጅ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ማሳካታችን አይቀርም፡፡

ሪፖርተር፡- ፋኩልቲው በወጣቶች ላይ ከመጠን በላይ ተመርኩዟል ተብሎ ይተቻል፡፡ ልምድ አልባ ነን ብለው ያስባሉ?

አቶ ደጀኔ፡-
በፍጹም አላስብም፡፡ አንደኛ አብዛኛዎቹ የሕግ መምህራን እዚህ ከመቀጠራቸው በፊት በሕግ ዙሪያ ተግባራዊ ልምድ ያካባቱ ናቸው፡፡ ጥቂቶቹ ጠበቃ ሆነው ሰርተዋል፡፡ ሌሎች ዳኛ የነበሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ገና ከመመረቃቸው በፊት የፍርድ ቤት ሬጂስትራር ሆነው የሰሩ ናቸው፡፡ የተቀሩት ለአቅም አልባዎች ነፃ የሕግ ማማከር አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ሲሆን ሌሎች ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ያደረጉ ናቸው፡፡ ስለዚህ እዚህ ሲቀጠሩ የተሰማቸው ስሜት አዲስ ሥራ የመጀመር ሳይሆን የቀደመ ስራቸውን የመቀጠል ነው፡፡ የበለጠ ደግሞ ወጣቶቻችን ስኬቶቻችን ናቸው፡፡ ወጣት አስተማሪዎች የፋኩልቲው ኃይል ናቸው፡፡ ፋኩልቲው ወደፊት እንዲራመድ ወጣቶቹ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እየሰሩ ነው፡፡ በሥራ መብዛት ቅሬታ አያቀርቡም፣ በዓላትን አያውቁም፣ በየጊዜው በሥራ ውጥረትና ጫና ሥር እንደወደቁ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሊተቹ ይገባልን?

ሪፖርተር፡- የጠቀሱት የወጣትነትን ጠንካራ ጎንን ነው፡፡ ከእነዚህ ጥቅሞች ጎን ለጎን ወጣትነት የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖዎች የሉትም?

አቶ ደጀኔ፡-
በእርግጥም ፍፁም ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ለምሳሌ ወጣቶች የሚገዳደራቸው ነገር ሲያጋጥማቸው በነገሮች ስሜታዊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚያ ላይ የጥቂቶቹ ልምድ በጣም ውስን ነው፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ወጣቶቹ ካላቸው ልምድ አንፃር ለስራው ብቁ እንደሆኑና ወጣት ስለሆኑ ብቻ መጠነ ሰፊ ትችት ሊያስተናግዱ አይገባም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የትምህርት ሚኒስቴር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የራሳችሁን የሰው ኃይል ቅጥር እንዳትፈፅሙ ከልክሏል፡፡ አሁን የሚመድበው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ነው፡፡ ነገር ግን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዋጅ የመቅጠር መብትን ለእናንተ ይሰጣል፡፡ ምን የሚሉት ነገር አለ?

አቶ ደጀኔ፡-
በአዋጁ አንቀጽ 7 መሰረት ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸውን የሰው ኃይል የመቅጠር ነፃነቱ አላቸው፡፡ ይህ ነፃነት አሁን ተወስዷል፡፡ ምክንያቱም በፋኩልቲው ደረጃ ለምሳሌ ረዳት ምሩቅ የሆነ መምህር ከመቅጠር ተከልክለናል፡፡ ሆኖም ከረዳት ምሩቅ በላይ የሆኑን መምህራን መቅጠር አሁንም የምንችል መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ሌላው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገደቡን የጣለው ከዓመታት በፊት ቢሆን ኖሮ እርምጃው ተቀባይነት ይኖረው ነበር፡፡ ምክንያቱም ያኔ በገበያው ላይ አጥጋቢ እጩዎችን ማግኘት አንችልም ነበር፡፡ አሁን ግን በገበያው ላይ ለረዳት ምሩቅነት የሚያመለክቱ ከበቂ በላይ ሰዎች ማግኘት የምንችል በመሆኑ ለፋኩልቲው ይመጥናሉ የምንላቸውን መምረጥ እንችላለን፡፡ ስለዚህ ገደቡ ለአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ይጠቅም ይሆናል እንጂ ለእኛ ፋኩልቲ ያለው አስፈላጊነት ያነሰ እንድያ ካለም ምንም ነው፡፡ በአገራችን ላይ ዘንድሮ ካስመረቅናቸው ውስጥ ሦስቱን ምርጦች መቅጠር ፈልገን የነበረ ቢሆንም በገደቡ የተነሳ አልቻልንም፡፡

ሪፖርተር፡- በሚሊዮን የሚቆጠሩ ለፋኩልቲአችሁ የተገዙ መጻህፍት በቤተመጻህፍት የቦታ እጥረት የተነሳ ከዘጠኝ ወራት በላይ በመጋዘን ለመቀመጥ መገደዳቸውን መረጃ ደርሶናል፡፡ የሚመጥናችሁን ቤተመፃህፍት ሳትገነቡ በፊት ይህን ያህል መጻህፍት መግዛቱ አስፈላጊ ነበ"?

አቶ ደጀኔ፡-
ይሄ የሚወስነው በተገኘው ገንዘብ ሁኔታ ነው፡፡ ገንዘቡን ለዚህ ጉዳይ በፍጥነት መጠቀም ካለብን የቤተመፃህፍት የቦታ እጥረት ችግር ቢኖርብን እንኳን መጻህፍቱን መግዛት ተፈላጊ ችግር ነው፡፡ ገንዘቡ ተገኝቶ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እስኪሞላ ድረስ መቆየት የሚችል ከሆነ የቦታ ጉዳይ በቅድሚያ መፈታት አለበት፡፡ እኛን ያጋጠመን ችግር የመጀመሪያው ነው፡፡ ፋኩልቲው መጻህፍቱን ለመጠቀም እንዳልከው ለረጅም ጊዜ ተቸግሮ የነበረ ቢሆንም በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ከእያንዳንዱ መጻህፍት ሁለት ሁለት ኮፒዎች ወደ ቤተመጻህፍታችን እንደተሻገሩ ከቤተ መጻህፍት ኃላፊው ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ይህን እንደመልካም እርምጃ አይተነዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ፋኩልቲው ከዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል?

አቶ ደጀኔ፡-
ከአስተዳደሩ የተለያዩ ክፍሎች ጋር በቅንጅትና በትብብር መልክ እንሰራለን፡፡ ከዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ እና ምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ቢሮ ጋር ያለን ግንኙነት ግን በብዛት ስራዎቻችን በበላይነት መምራት ነው፡፡ በእለት ከእለት ሥራዎቻችን ላይ ጣልቃ በመግባት ባይሳተፍም አጠቃላዩን የፋኩልቲውን እንቅስቃሴ ይቆጣጠራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- እየነገሩኝ ያለው መግባባት በመካከላችሁ ካለ ከላይ የገለጽነው ችግር ሳይቀረፍ ለምን ረዥም ጊዜ ወሰደ?

አቶ ደጀኔ፡-
የቤተ መጻህፍት ቦታ እጥረት የሕግ ፋኩልቲ የብቻው ችግር አይደለም፡፡ የሌሎች ፋኩልቲዎችም ችግር ነው፡፡ የእኛ ፋኩልቲ ከሌሎቹ ባነሰ መልኩ ታይቶ ከሆነ ያለን መግባባት ላይ ጥርጣሬ ሊያሳድር ይችላል፡፡ ነገር ግን የእኛ ፋኩልቲ የተፈጠረበት ልዩ ችግር ለእኔ አይታየኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም ሦስት ዙር ተማሪዎችን አስመርቃችኋል በሥራው አለም ስላላቸው ብቃት መረጃ አላችሁ?

አቶ ደጀኔ፡-
እስካሁን ከተመራቂዎቻችን የሥራ አለም የሰበሰብነው መረጃ አበረታች ነው፡፡ የተሳካ ሥራ በአግባቡ እየሰሩ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛ ፋኩልቲአችን ተማሪዎቻችን ከመመረቃቸው በፊት ለ2 ወራት ያህል በፍርድ ቤቶችና በሕግ ነክ ተቋማት ውስጥ ተግባራዊ ስልጠናና ተግባራዊ ልምምድ በማድረግ ከውጭው ዓለም ጋር እንዲተዋወቁ ያደርጋል፡፡ ሁለተኛ የዩኒቨርሲቲው ፍልስፍና በህብረተሰብ አቀፍ ትምህርት ላይ የተመረኮዘና ተማሪዎቻችንን ከህብረተሰቡ ማህበራዊና ሕጋዊ ጉዳዮች ጋር ገና በጧቱ የሚያስተዋውቃቸውና ለመመረቅ አንድ ዓመት እስኪቀራቸው ድረስ የተለያዩ መፍትሔዎችን እንዲሰጡ ስለሚያበረታታ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከህብረተሰብ አቀፍ ትምህርት የሚሰበሰቡት ዴታዎች፣ ግኝቶችና የመፍትሄ ሃሳቦች በዩኒቨርሰቲው ጥቅም ላይ አልዋሉም የሚል ቅሬታ ይቀርባል፡፡  

አቶ ደጀኔ፡-
ይሄ ጭፍን አስተያየት ነው፡፡ እውነትነቱንም እጠራጠራለሁ፡፡ ነገር ግን የሕግ ፋኩልቲአችን በተማሪዎቻችን የተሰበሰበውን ዳታ፣ ግኝትና የመፍትሔ ሀሳብ በአግባቡ ገና አልተጠቀመበትም፡፡ ይህም የሆነው የፋኩልቲው አባላት ገና በርዕሰ ጉዳዮቹ ላይ ጥናትና ምርምር ስላልጀመሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ይህ የፋኩልቲው ድክመት ተማሪዎቹን ከሕብረተሰብ አቀፍ ትምህርት ስርዓቱና ከህብረተሰቡ ተሞክሮ ትምህርት እንዳይቀስሙ በፍጹም አያደርጋቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- የሕግ ተማሪዎች በጠቅላላ ለሕጋዊ ችግሮች መፍትሔ ሰጭና ፈጣሪ ሆነው አይቀረፁም የሚል ትችት አለ፡፡ በሕግ ትምህርት ቤት የስርዓተ ትምህርት ለውጥ አስፈላጊነት ያምናሉ?

አቶ ደጀኔ፡-
በትክክል አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም እኔ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ያገኘሁበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤትን ጨምሮ ጥቂት የሕግ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቹ የእውነተኛውን አለም ልምድ የሚያገኙበትን እድል አይሰጡም፡፡ ነገር ግን የጂማ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ከላይ እንደገለጽኩት በህብረተሰቡ አቀፍ ትምህርትና በተግባራዊ ልምምዱ የተነሳ በዚህ ረገድ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በጣም ይሻላል፡፡

ሪፖርተር፤- ተማሪዎቹ ተግባራዊ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ በሕግ ንድፈ ሃሳቦች ላይ ማውራትን ያስቀድማሉ ተብለው እየተተቹ ከመሆናቸው አኳያ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ የሚሆኑት የሕብረተሰብ አቀፍ ትምህርትና ተግባራዊ ልምምዱ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ይቀርፋሉ ብለው ያምናሉ?

አቶ ደጀኔ፡
- ሙሉ በሙሉ አይቀርፉትም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ሁለቱ ፕሮግራሞች እንዳልከው የሚከናወኑት በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ሁለተኛ ፕሮግራሞቹ ሁሉንም አይነት የትምህርት አይነቶች አይሸፍኑም ሦስተኛ ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ችግሮች የፕሮግራሞቹ ውጤታማነት ላይ ተፅዕኖ ያሳርፋሉ፡፡ የሆነው ሆኖ የእኛ ተማሪዎች ተመሳሳይ ፕሮግራሞች ከሌላቸው የሕግ ትምህርት ቤቶች የተሻሉ መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ሪፖርተር፤- በሀገር አቀፍ ደረጃ በሕግ ሥርዓተ ትምህርት ለውጦች ላይ በሚሰራው ኮሚቴና በሕግ ምርምርና ጥናት ተቋም ውስጥ ያላችሁ ተሳትፎ ምን ይመስላል?

አቶ ደጀኔ፡
- ፋኩልቲው ብሄራዊ የሕግ ትምህርት ካሪኩለም ቀረፃ ላይ በኮሚቴው ውስጥ ተወካይ ነበረው፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የመማሪያ ማጻህፍት ዝግጅት ሲደረግ ተጋብዘናል፡፡ ከፋልቲው አባላት መካከል ተመርጠው ሥራውን የሰሩም አሉበት፡፡ እንዲሁም የእኛ ፋኩልቲ በመንግሥትና በግል የሕግ ትምህርት ቤቶች የትምህርት አሰጣጥና ግምገማ አሰራር ዙሪያ መመሪያ እንዲያዘጋጅ ኃላፊነት ተሰጥቶት ተወጥቷል፡፡ እነዚህ እንግዲህ ከኮሚቴው ጋር ያለን የሥራ ግንኙነት ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከሕግ ምርምርና ጥናት ተቋም ጋርም እንሰራለን፡፡ በዚህ ረገድ ተቋሙ በማስረጃ ሕግ ዙሪያ ረቂቅ ሰነድ እንድናዘጋጅ ኃላፊነት ሰጥቶን ነበር፡፡ ሥራውን አጠናቀን ከጥቂት ዓመታት በፊት ያስረከብን ሲሆን በቅርቡ ሕግ ሆኖ እንደሚወጣ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፤- የአዳዲስ የሕግ ትምህርት ቤቶችን መፈጠርና መጠናከርን እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ ደጀኔ፡-
የሕግ ትምህርት ቤቶች በብዛት እየተፈጠሩ መሆናቸው ጥሩ ቢሆንም ዘግይተዋል፡፡ ሀገሪቱ ሕግ የተማረ የሰው ኃይል ለረጅም ጊዜ ያህል እየፈለገች የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብቸኛው ት/ቤት ሆኖ መቆየቱ አግባብ አልነበረም፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ የሕግ ትምህርት ቤቶች ከተከፈቱ ወዲህ እድገታቸው በጣም ፈጣን ነው፡፡ በዚህ የመቀጠል ተስፋም አላቸው፡፡

ሪፖርተር፤- አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ቁጥር ሕግን ጨምሮ 30 በመቶ ብቻ እንዲሆንና የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ቁጥር ደግሞ 70 በመቶ እንዲደርስ የማድረግ አዝማሚያ ይታይበታል፡፡ ይህ ውሳኔ የሃገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተሰጠ ነው ብለው ያስባሉ?

አቶ ደጀኔ፡-
ይህ ቀመር ትክክል ነው ስህተት ለማለት በቅድሚያ የሃገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ማወቅ አለብን፡፡ በየትኛው የትምህርት መስክ ሃገሪቱ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት እንዳለባትና በየትኛው መስክ ደግሞ በአጣዳፊ ሁኔታ የሰው ኃይል እንደምትፈልግ በግሌ አላውቅም፡፡ ነገር ግን የተማረ የሰው ኃይል በሁሉም መስክ ማስፈለጉ አያከራክርም፡፡ መንግሥት የሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የሚያሳየው በተፈጥሮ ሳይንስ ተመራቂዎች እንደሚያንሱና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመራቂ በመስኩ ያስፈልጋል ካለ በቁጥሩ ላይ ስህተት አይታየኝም፡፡ ይልቅስ ስህተት የሚሆነው በዚህ ቀመር ላይ ትችት መሰንዘር ነው፡፡ በተጨማሪም መንግሥት እንዲህ አይነት ቀመርን ቅድሚያ ግምገማና ጥናት ሳያደርግ ቀመሩ ለሃገሪቱ እጅግ አስፈላጊ ነው በማለት አምኖበት እንደማያወጣው ነው የማስበው፡፡
 
< Prev   Next >