Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ካምብሪጅ ለኢትዮጵያ አዲስ ዓመት...
ካምብሪጅ ለኢትዮጵያ አዲስ ዓመት... E-mail
Thursday, 02 October 2008
Imageካምብሪጅ ለኢትዮጵያ አዲስ ዓመት (እንቁጣጣሽ) በሕግ እውቅና ሰጠች

በሔኖክ ያሬድ

የዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ከተማ ካምብሪጅ ለኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ መስከረም 1 ቀን 2001 ዓ.ም እውቅና መስጠቷና ድንጋጌ ማውጣቷ የከተማዋ ም/ቤት ገለጸ፡፡

ቅዳሜ መስከረም 3 ቀን 2001 ዓ.ም በካምብሪጅ ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት በደማቅ ሥነ ሥርዓት ባከበሩበት ጊዜ የከተማዋ ከንቲባ ዴኒስ ሲሞንስ የኢትዮጵያን አዲስ ዓመት ይፋ እውቅናን አውጀዋል፡፡

መስከረም 15 በወጣው የፕሬስ መግለጫና በአዋጁ እንደተመለከተው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት የኢትዮጵያን ሦስተኛው ሺሕ ዓመት (ሚሌኒየም) የሚቀበልበትና ከመስከረም 1 ቀን 2000 ዓ.ም እስከ መስከረም 1 ቀን 2001 ዓ.ም ዓመቱን ሙሉ ሲያከብረው የቆየ በመሆኑ፤ ለዓመቱ መባቻ እውቅና እንዲሰጠው አድርጓል፡፡

ሥነ በዓሉ የተከናወነው በሴንት ፖል (ቅዱስ ጳውሎስ) ቤተ ክርስቲያን ሲሆን አዘጋጁ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ነው፡፡

ለእንቁጣጣሽ እውቅና የሰጠውን ውሳኔ የካምብሪጅ ከተማ ምክር ቤት ያሳለፈው ሰኞ ጳጉሜን 3 ቀን 2000 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ነበር፡፡

የከተማው ምክር ቤት ውሳኔ ለኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ከሰጠው እውቅና ሌላ ለከተማዋ ኢትጵያውያን በፖለቲካዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚክ አንፃር ያበረከቱትን አስተዋኦ ይሁንታ ሰጥቶበታል፣ አወድሶታል፡፡

የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በጎርጎሪዮሳዊው ("ምዕራባዊ") ቀመር ሴፕቴምበር 11 ቀን የሚውል ሲሆን፣ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን የሚኖሩበት በመሆኑና የማኅበረሰቡም አካል በመሆናቸው ለክብረ በዓሉ እውቅና መስጠቱን ከተማው አመልክቷል፡፡

የከተማዋ ከንቲባ እንደተናገሩት "ኢትዮጵያ የአፍሪካ ጥንታዊት፣ ነፃና ያልተቋረጠ ኅልውናዋን ያረጋገጠች አገር ናት፡፡ ካምብሪጅ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የያዘች በመሆኑ ክብር ይሰማታል፡፡

እነርሱ የበለፀገ ብዝሃ ባህላቸውን ለከተማችን አበረክተዋል፡፡ ከአፍሪካ ወዳጆቻችንም ጋር አስተሳስረውናል፡፡ ውሳኔውን ያስተላለፍነው ድጋፋችንና ባልንጀራዊ መንፈስን በካምብሪጅ፣ በአፍሪካና በዓለም ዙርያ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወዳጆቻችን ለማሳየት ነው፡፡"

የኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ዩዝ ኢኒሼቲቭ መሥራች አቶ ሳሙኤል ገብሩ በካምብሪጅ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ በመርዳት በኩል የከተማዋ ከንቲባ ሲሞንስ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

"በእኔ ዕውቀት፣ ባለፉት ዘመናት በካምብሪጅ ለኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በአዋጅ እውቅና የሰጠ የለም፡፡ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብም ለከተማዋ ብዝሃ ባህል መለያም ያተረፈውን በረከት ያደነቀም ያወቀም የለም" ያሉት አቶ ሳሙኤል "ከንቲባዋ ሲሞንስ በካምብሪጅ ለኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ለሰጡት የማያቋርጥ ድጋፍ፣ እንዲሁም ድርጅታችን የኢትዮጵያ አሜሪካውያን ዩዝ ኢኒሼቴቭ ለዚህ ዐቢይ ቁም ነገር ላከናወነው ተግባር አዲስ ዓመታችን እንቁጣጣሽ በአዋጅ እንዲታወቅ ስላደረጉ በይፋ አመሰግናለሁ" ብለዋል፡፡

አዋጁ በኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ዩዝ ኢኒሼቲቭ፣ በከንቲባ ሲሞንስ እና በካምብሪጅ ከተማ የጋራ ጥረት የወጣ ነው፡፡ የዐዋጁ ይዘት የሚከተለውን ፍሬ ጉዳዮች ያካተተ ነው፡፡

. ኢትዮጵያ መስከረም 1 ቀን 2001 ዓ.ም አዲሱን ዓመት የምትጀምርበትና የምታከበርበት በመሆኑ፤ እና

. በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት የኢትዮጵያን ሦስተኛው ሺሕ ዓመት (ሚሌኒየም) የሚቀበልበትና ከመስከረም 1 ቀን 2000 ዓ.ም እስከ መስከረም 1 ቀን 2001 ዓ.ም ዓመቱን ሙሉ ሲያከብረው የቆየ በመሆኑ፤ እና

. ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማካይነት ባገኘችው ልዩ የቀን መቁጠሪያ (ባሕረ ሐሳብ) መሠረት ዓለም የተፈጠረው ከክርስቶስ ልደት 5"500 ዓመታት በፊት መሆኑ፣ በኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ (ካሌንደር) መሠረት አሁን 7501 ዓመተ ዓለም በመሆኑ፤ እና

. የኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ 30 ቀኖች ያላቸው 12 ወሮችና 5 ቀኖች፣ ወይም በሠግር ዓመት 6 ቀኖች ያሉት 13ኛ ወር ያካተተና አዲሱ ዓመት መባቻም መስከረም 1 ቀን በጎርጎሪዮሳዊው ቀመር ሴብተምበር 11 የሚውል በመሆኑ፤ እና

. ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጥንታዊና ነፃ፣ ያልተቋረጠ ኅልውናዋን ያረጋገጠች፣ ለአፍሪካ ኅብረት (አንድነት) ፋና ወጊና ችቦውን የያዘች፣ የራሷን ፊደላት፣ የአኀዝ (ቁጥር) ሥርዓትና ባሕረ ሐሳብ (ካሌንደር) የመሰረተች፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ባህላዊና ታሪካዊ መስተጋብር ሳይቋረጥ ጠብቃ ያኖረች በመሆኑ፤ እና

. የኢትዮጵያ ሺሕ ዓመት (ሚሌኒየም) የአፍሪካ ሺሕ ዓመት በተባበሩት መንግሥታትና በአፍሪካ ኅብረት አኅጉራዊና ሉላዊ ክብረ በዓል እንዲሆን በመደረጉና በዓሉም "ለኢትዮጵያ ሕዳሴ" መነሻ በመሆኑ፤ እና

. የካምብሪጅ ከተማ መሰረቱን በአሜሪካ ካደረገው የወጣቶች ድርጅት የኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ዩዝ ኢኒሼቲቭ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን አዲስ ዓመት 2001 ዓ.ም በማክበር ከኢትዮጵያውያን ወዳጆቻችንና ከካምብሪጅ ከተማ ጎረቤቶቻችን ጋር ያለንን አንድነት ለመግለጽ ዐዋጁ ታውጇል፡፡

የካምብሪጅ ከተማ ምክር ቤት በከተማዋ ላሉ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰቡ በመላዋ ከተማ ስም ኢትዮጵያውያን በካምብሪጅ ከተማ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚክና ፖለቲካዊ መስኮች ላበረከቱት አስተዋፅኦ አክብሮቱን ይገልጻል፡፡
Last Updated ( Thursday, 02 October 2008 )
 
< Prev   Next >