Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ክቡር ሚኒስትር
ክቡር ሚኒስትር E-mail
Wednesday, 01 October 2008
("ለኢትዮጵያ ሕዳሴ ይተጋል" በሚል ርዕስ፣ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች መንግሥት እየሰበሰበ ያወያያል፡፡ ባለሃብቶችን ለማወያየት ትልቅ ስብሰባ ተጠርቷል፡፡ አይፈሩም፣ አልተነካኩም፣ በግልጽና በድፍረት ይናገራሉ፤ የተባሉት ክቡር ሚኒስትር፣ "እናንተም ሳትፈሩ ተናገሩ፤ እኔም ሳልፈራ እናገራለሁ" የሚል መግቢያ ሰጥተው በባለሃብቶችና ኢንቨስተሮች ዙሪያ ያለው ችግርና ትጋት ላይ የሚወያይ ስብሰባ ከፈቱ)

- እንግዲህ እንደገና ልድገመውና የኢትዮጵያ ሕዳሴ እውን ለማድረግ እንትጋ  ነው የምንለው፡፡ በናንተ በኩል የሚጠበቀው ትጋት ደግሞ በተቀላጠፈና ከሙስና በፀዳ መንገድ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ሕግ አክብራችሁ ኢንቨስት እንድታደርጉ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር፣ እኔ እዚህ ያለውን ባለሃብት ሁሉ አልወክልም፡፡ የራሴን ለመናገር ግን እኔ በትጋት ኢንቨስት እያደረኩ ነኝ፡፡ መንግሥት ግን መሬት በመስጠት እየተባበረን አይደለም፡፡
- የትኛውን መሬት ጠይቀህ ምን መሬት ተከለከልክ? ችግር ካለ እንዲፈታ ተብሎ ከክልልም፣ ከአዲስ አበባ ክፍለ ከተማም ተወካዮች እዚህ አዳራሽ ይገኛሉ፡፡ ምን መሬት ተከለከልክ? በግልፅና በድፍረት እንነጋገር፣ ተባብለናል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር፣ ማስፋፊያ ጠይቄ አልሰተጠኝም፡፡
- ይኸንን ክፍለ ከተማዎቹ ያስረዱ፡፡ ክፍለ ከተማና ቀበሌ፣ የጠየቁት መሬት ለምን አልተሰጣቸውም?
- (የክፍለ ከተማው) ክቡር ሚኒስትር የተሰጠውን መሬት አጥሮ አስቀምጦ ሌላ ማስፋፊያ ወይም ተጨማሪ የሚጠይቅ ሊሰጠው አይገባም፡፡ ሥራ ለጀመረ ነው ማስፋፊያ ወይም ተጨማሪ መሬት የሚሰጠው፡፡
- የተሰጠህን መሬት ሳታለማ ወይም ስራ ሳትጀምር ሌላ አይሰጥህም ነው የምትባለው ገባህ?
- ገባኝ፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ እኔኮ ግንባታ ጀምሬያለሁ፡፡ ኑ እና እዩት ብያቸው ግን ለማየት ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ እንዲያውም መሬቱን ለሌላ ባለሃብት ሊሰጡብኝ ወስነው ጉዳዩ ፍርድ ቤት ነው ያለው፡፡
- እንዴት ለሌላ ባለሃብት?
- ለሃይለኛ ባለሃብት፣ ለሚፈሩት ባለሃብት፣ ሁሉምኮ በእኩል አይታይም፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት በእኩል አይታይም?
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ አጥረው ያልገነቡ የሚቀሙ አሉ፤ አጥረው ባይገነቡም የማይቀሙ አሉ፡፡
- የምትለው ገብቶኛል፡፡ እኔም አንዳንዴ ይህ አገር ወዴት እያመራ ነው ብዬ እፈራለሁ፡፡ የአገራችን የልማት ሁኔታ በሚያጠናው ቡድን ውስጥ አባል ነኝ፡፡ አርባ ምንጭ ሄጄ የታጠረ አይቻለሁ፣ አዋሳ የታጠረ አይቻለሁ፣ ደብረ ዘይት የታጠረ አይቻለሁ፣ አዲስ አበባ የታጠረ አይቻለሁ፣ መቀሌ የታጠረ አይቻለሁ፣ ጎንደር የታጠረ አይቻሁ፣ ባህር ዳር የታጠረ አይቻለሁ፡፡ እንዴት ነው ነገሩ ብዬ በእጅጉ ገርሞኛል፡፡ ምናልባት ጉዳዩ የሚመለከታችሁ ሰዎች ወይም ወኪሎች እዚህ ካላችሁ ብታስረዱን ጥሩ ነው፡፡
- እ... እ...እ... ባለቤት ባልሆንም ወኪል ነኝ፡፡ አንዳንድ ገንዘብ አንሰጥም ያልናቸው ወይም የግል ቂም ያላቸው ጋዜጠኞች፣ የፃፉትን ፀረ ልማት ጽሁፍ አንበው ክቡር ሚኒስትሩ እንዳይሳሳቱ አደራ እላለሁ፡፡
- ጋዜጦች ስለጻፉ አይደለም፡፡ በአይኔ አይቸዋለሁ፡፡ ከኢሕአዴግ ስብሰባ ስመለስ ከመኪና ወርጄ ያየሁት የታጠረ መሬት አይቼ በእጅጉ አዝኛለሁ፡፡ ባነብም ሃጢአት የለውም፡፡ ግን ስላየሁ እንጂ ስላነበብኩ አይደለም፡፡ ለምን ታጥሮ ቀረ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር፣ አላነበቡት ይሆናል እንጂ በአንድ ጋዜጣ ላይ መግለጫ አውጥተን ነበር፡፡ ጋዜጣውን አላነበቡትም ይሆናል እንጂ እዛው እንኳን ሰፋፊ መሬት፣ መኖሪያ ቤት መስራትም ከባድ እንደሆነ ገልፀናል፡፡
- አንድን ጋዜጣ አታንብ ስትለኝ ቆየህና አሁን ደግሞ ሌላውን ጋዜጣ አላነበቡትም መሰለኝ እያልክ ትወቅሰኛለህ፡፡
- ከጋዜጣም ጋዜጣ አለ፡፡
- ጋዜጣውን እንተወውና አሁንስ ጥያቄው ከብዷችሁ ነው የማትሰሩት? ወይስ ረስታችሁትና ትታችሁት?
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር፣ ትተነው ወይም ረስተነው አይደለም፡፡
- የአርባ ምንጭን ተወው፣ የጥቁር ውሃን ተወው፣ የባህርዳርን ተወው፣ የመቀሌውን ተወው፣ የቦረናውን ተወው፣ የመቂውን ተወው፣ የጎንደሩን ተወው፣ የአዲስ አበባን ተወው፡፡ ይህን ሁሉ ጋሻ መሬት ተውት፣ ሁሉም ነገር አልቆ ከነመስሪያው ተሰጥቷችሁ ተጥሎ ለዝገት የተዳረገውን የዶሮ ርቢ ተወው፣ ሆራ ሆቴል ላይ ምን ሆንን ልትሉ ነው?" (አዳራሹ ሳቀ፣ አጨበጨበ)
- ክቡር ሚኒስትር፣ ሆራ ሆቴል ቀላል ነው ያለው ማነው? ሆቴልኮ ከባድ ሥራ ነው፡፡
- ይቅርታ መመላለስ ሆነ፡፡ ሊቀመንበር ሆነህ እንዴት ትከራከራለህ አትበለኝ፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዳሴ ይተጋል፣ ካልን በግልጽ መነጋገር አለብን፡፡ ቢሾፍቱ ውስጥ የአየር ሀይል የመኮንኖች ክበብ አለ፡፡ ሁለት ቦታ አንዱ በቅርቡ አሳድሶታል፣ አስፋፍቶታል፡፡ እጅግ ደስ የሚል ክበብ አድርገውታል፡፡ የመኮንኖች ክበብ አነስተኛ ባጀት ያለው ነው፡፡ የመኮንኖች ክበብ ተስፋፍቶና ጠንክሮ እየሄደ አጠገቡ ያለው ጠንካራ የነበረው እንዴት ለስምንት ዓመት ይዘጋል፡፡ የነበረው የተገነባው፣ ቀለም ቢቀባኮ በቀላል የሚሰራ ነው፡፡ ስንት ገቢ ያስገባ ነበር፡፡
- ክቡር ሚኒስትር "ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናገር" ተብሏል፡፡
- የናንተ ነገርኮ ሲያዩትም ሲይዙትም አላምር አለ፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ እንኳን ይህ ትንሽ ሆቴል ትልቅ ሆቴልስ እያስተዳደርን አይደለም፡፡ ትልቅ ሆቴልኮ ራሳችን ሰርተን በዓለም የታወቀ ሆቴል ሆኗል፡፡
- ትክክል፡፡ የምንኮራበት ሆቴል ሰርታችኋል፤ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ያን የመሰለ ሆቴል ሰርታችሁ "መከፈል የሚገባው ገንዘብ ስላልተከፈለ ስሙ ሊነጠቅ ነው፣ ሌላ ስም ሊወጣለት ነው" መባልን ስንሰማ እናዝናለን፤ እንደነግጣለን፡፡ ምክንያቱም ስሙ ሲነጠቅ ያገር ስምን ክብርም ይናጋልና የናንተ ብቻ አይደለም፡፡
- አይጨነቁ፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ እንኳን እሱን ገና ግዮን ሆቴልም እንገዛለን፡፡
- ስማ የኔ ጌታ የወሰዳችሁትን መሬት አጥራችሁ እያስቀመጣችሁና የደብረ ዘይት ሆቴል ከልጅነታችን ጀምሮ ስንዝናናበት የነበረ ሆቴል ቆልፋችሁ፣ ግዮን ሆቴል የሚሰጣችሁ ከሆነ የተሰጣችሁ ዕለት ሥራዬን በገዛ ፈቃዴ የምለቅበት ቀን ይሆናል፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ ሰውዬውኮ ለዚህ አገር በርካታ ነገር ሰርተዋል፤ አትርሱ እንጂ፡፡
- አልረሳንም፡፡ እናመሰግናለንም፡፡ ለተሰራው እናመሰግናለን፡፡ ስላልተሰራው ነው እያወራን ያለነው፡፡ ስለተሰራው አንድ ጋሻ ስናመሰግን ግን ስላልተሰራው መቶ ጋሻ አትውቀሱ፤ ልንባል አይገባም፡፡ የተሰጠው ጋሻ አልሙበት ተብሎ ነው፡፡
- አልሙበት መባሉን መቸ ረሳን፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ፈንጩበት የተባለ አስመሰላችሁት" የእሳቸውን ክርክር ባልሰማም የአንተ ግን ለዘላአለሙ ጠብቁን፤ የጠየቅነውን ሁሉ ስጡን የምትል ትመስላለህ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር፣ በኔና በእሳቸው መካከል ልዩነት የለም፡፡ አንዳንድ ጋዜጦች እንደሚሉት እርስዎም "አሽከር" ሊሉኝ ፈለጉ መሰለኝ፡፡
- ከጋዜጣም ጋዜጣ አለ እንዳልከው ከአሽከርም አሽከር አለ ብዬ ልመልስ ወይ? ባጭሩ እያልኩ ያለሁት የምትውጡትን ያህል አኝኩ ነው፡፡ ለልማት በምታደርጉት ሃቀኛ እንቅስቃሴ ሁሉ ሙሉ በሙሉ እንደግፋችኋለን፡፡ ለቀልድ፣ ለፌዝና ለጨዋታ በምታደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ተጠያቂ እናደርጋችኋለንም፡፡ መልዕክታችን ይሰራ ነው፡፡ አሁን ስብሰባው ስለ አንድ ድርጅት እንዳይመስል ለሌሎች ዕድል ልስጥ፡፡
- (ሌላ ባለሃብት እጅ አወጣ ዕድል ተሰጠው) ሕዳሴ እየተባለ ሲነገር እሰማ ነበር፡፡ አላመንኩም ነበር፡፡ ዛሬ ነው እኔ ሕዳሴ የሚለው ቃል በተግባር ያየሁት፡፡ ደፍሮ መናገር ይቻላል ስለተባለም ደፍሬ እንድናገር ይፈቀድልኝ፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ተናገር፡፡ እኔ ስለፈቀድኩልህ ሳይሆን መብትህ ስለሆነ፡፡
- ሕዳሴ እንዲህ በዓይኔ ባየሁትማ እውነትም "ይተጋል" እንጂ እኔም በታሰበው እንተጋለን፡፡ ሚኒስትር ደፍሮ እንዲህ ሲናገር እሰማለሁ ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፡፡ እውነትም ሕዳሴ ነው፡፡ እኛ እዚህ ያለን ባለሃብቶችም ሌሎችም የምናማው ብዙ ነገር አለ፡፡ ያወቁት ይሆናል፡፡
- አላውቀውም፡፡ ሃሜት መሆኑ ይቅርና በግልጽ እዚህ መድረክ ላይ ተናገረው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር፣ እኛ የምንሰማው፣ የምናየውም፣ የምናማውኮ ሚኒስትሮች ስትፈሩና ስትንቀጠቀጡ እንጂ እንደዚህ ሃቁን ስታወጡ አይደለም፡፡
- አልገባኝም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር፣.ፕሬዚዳንት የተባሉት ለስሙ እንጂ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና ፕሬዚዳንት ባለሃብቱ ናቸው ብለን ደምድመን ነበር፡፡
- ለምን?
- እኛን ትሉን እንደሆነ እንጂ እሳቸው የፈለጉትን ቢያደርጉኮ አትናገሩም? አትውቀስ፣ አትተንፍስ ዝምና ዝም ብቻ ነው፡፡ ዛሬ ስትተነፍሱ ሰማሁ፡፡ ሕዳሴ ነው አልሁ፡፡ ብቻ አደራ! ክቡር ሚኒስትር አደራ!
- የምን አደራ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር፣ እርስዎ ሃቁን ስለተናገሩ አንድ ነገር እንዳይያጋጥምዎ ከጎንዎ እንቆማለን፡፡ ቤቴ ከጎንዎ ነው፡፡ አደራ የምለው ግን እኔም ሃቁን ስለተናገርኩ አንድ ነገር እንዳያጋጥመኝ መንግሥት ከጎኔ ይቁም፡፡ አደራ እላለሁ፡፡

(ቤቱ ሳቀ፤ አጨበጨበ፣ እንደገና አጨበጨበ)

- እሳቸው መጥፎ ነገር ይሰራሉ ብላችሁ አታስቡ፤ አያደርጉም፤ አያስቡም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እሳቸው ሳይሆኑ "እሳቸው ነን" የሚሉትን ነው የምንፈራው፡፡

(ቤቱ ሳቀ፤ አጨበጨበ፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ ገረማቸው፡፡ ከእረፍት በኋላ ስብሰባው ይቀጥላል ብለው ወደ ሻይ ቡና ሄዱ)


- ግሩም ስብሰባ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንድ ነገር ግን ግራ ገብቶኛል፡፡ ይህ ሁሉ ባለሃብት እያጨበጨበና እየሳቀ ያለው እውነት ያን ያህል ቅሬታ ነበረው? አንተ ባለሥልጣን ነህ ይህን ችግር ታውቅ ነበር?
- አዎን አውቅ ነበር፡፡ እኛ ራሳችንም ችግር ውስጥ ነንኮ፡፡
- ምን የሚሉት ችግር?
- ክቡር ሚኒስትር፣ ወደ ቀጣይ ስብሰባ ከመግባታችን በፊት ከየክልሉና ከየክፍለ ከተማው የመጣው ባለሥልጣን ለአንድ አምስት ደቂቃ ቢያነጋግሩን፡፡
- እሺ እዚያ ትንሽ ክፍል ውስጥ ለአምስት ደቂቃ ውስጥ እንገናኝ፡፡ ሹማምንት ለተባሉት ሁሉ ንገርልኝ፡፡

(ክቡር ሚኒስትሩ የየክልል የኢንቨስትመንት ኃላፊዎችና የክፍለ ከተማ ሹማምንት ተሰብስበዋል)

- ይህ ነገር እያስተዋላችሁት ነው?
- (አንዱ) አዎን ክቡር ሚኒስትር፣ እንደዛሬ መድረክ ተከፍቶ አያውቅም የምለው ለዚህ ነው፡፡ እኛም እጅና እግራችንን ታስረናል፣ አንደበታችን ተዘግቷል፡፡
- ለምን?
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ ታጥሮ ታጥሮ የቀረ ስንት መሬት እያለ በሌላው ላይ መቆጣትና እርምጃ መውሰድ አልቻልንማ፡፡
- ለምን? በታጠረው ላይ እርምጃ አትወስዱም ነበር?
- ክቡር ሚኒስትር፣ በኋላስ?
- እንዴት በኋላስ?
- ጥቃት ቢደርስብንስ ማን ያድነናል?
- ማን ሊያጠቃችሁ? እሳቸው?
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ የእሳቸው ይቅር፡፡ ከአለቆቻችንስ ቢሆኑ፡፡ ጉዳትና ስህተት መሆኑን ቢያውቁም እንድንናገርና እርምጃ እንድንወስድ አይፈልጉምኮ፡፡
- ለምን አይፈልጉም?
- (ከክልል የመጣ ሌላ ሹም) በርካታ ሹሞኞቻችን በጥቅማ ጥቅም የተያዙ ናቸው፡፡ ዋነኛው ምክንያት ይኸው ነው፡፡
- (ሌላ ከአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ የመጣ) በጥቅማ ጥቅም የተያዙም አሉ፡፡ በዚህ ቢያዩትም እሳቸውን ከመንግሥት በላይ ስለሚያዩ የሚፈራ አለ፡፡
- እናንተ እዚህ ያላችሁትስ ትፈራላችሁ?
- አዎን እፈራለን! (በአንድ ድምፅ)
- አልገባኝም፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ ታጥሮ ለስምንት ዓመት የተዘጋ ለመሆኑ የማያውቅ ሚኒስትር አለ? ሁላችሁምኮ ታውቃላችሁ፡፡ አንዳችሁም ግን ለምን እንደዚህ ሆነ ብላችሁ ስትከራከሩ፣ ስታዝኑ፣ ስትቆጡ እርምጃ ስትወስዱ አትታዩም፡፡ አፋችሁ ተለጉሟል፡፡ አሁን ግን ደስ ያለን ነገር አለ፡፡
- ምን?
- አንዳንድ ባለሥልጣኖች እርምጃ ሲወሰዱ አይተናል፡፡ በዚህም ደስ ብሎናል፡ ግን ዋናው ነገር አልተወሰደም፡፡ እንኳን እርምጃ መውሰድ መናገርም የሚፈራ አለ፡፡
- ይኸውላችሁ እኔ አሁን ተናግሬ የለም ወይ? ሲሰሩ እናሞግሳቸዋለን፡፡ ሳይሰሩ ሲቀሩ እንወቅሳቸዋለን፡፡ በሚያለሙት ነገር እንደግፋቸው፣ የማያለሙትን እንቀማቸው፡፡
- አይ ክቡር ሚኒስትር ....
- ይኸን ስናገር አልሰማችሁም፡፡
- ሰምተናል (በአንድ ድምፅ)
- ታዲያ እኔ ሚኒስትር አይደለሁም?
- ከሚኒስትርም ሚኒስትር አለ! (በአንድ ድምፅ)
 
< Prev   Next >