| ወጣት አብዮተኝነት በኬንያ |
|
| Wednesday, 01 October 2008 | |
|
በምሕረት አስቻለው
የኬንያ ወጣቶች ባለፈው ሳምንት ለሶስት ተከታታይ ቀናት "አገራችንን ዳግም መገንባት፣ በህብረተሰባችን መካከል እርቅን ማስፈን፣ የወጣት ኬንያውያን ችግሮችና ተስፋዎች" በሚል መሪ ቃል ባደረጉት ስብሰባ በአገራቸው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ጉልህ ተሳትፎ ለማድረግና የአመራር ሚና ለመጫወት ዝግጁ መሆናቸውን እንዳመለከቱ ዘኔሽን ዘግቧል፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ ኬንያውያን ወጣቶች በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ቢጋበዙም የተሳተፉት አንድ ሺህ ሦስት መቶ የሚሆኑ ወጣቶች ብቻ ናቸው፡፡ በስብሰባው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋና የፍትህ ሚኒስትሯ ማርታ ካሩዋ ለወጣቶቹ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ የተለያዩ የመንግስት መሥሪያ ቤቶችና መንግስታዊ ያልሆኑ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ተወካዮችም ተገኝተው ነበር፡፡ ከነዚህ አካላት በተጨማሪ በ2012 በኬንያ በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዋነኛ እጩ ተወዳዳሪዎች እንደሚሆኑ የተነገረላችው ሁለት ፖለቲከኞችም በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል፡፡ ይህም በወጣቶቹ ዘንድ የፖለቲካ መነቃቃትን እንደሚፈጥር የዘኔሽን ዘገባ ያመለክታል፡፡ ሚስተር ኦዲንጋም ሆኑ ፍትህ ሚኒስትሯ ሚስ ካሩዋ የወጣቶቹን ፖለቲካዊ ድጋፍ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን፣ ከወጣቶቹ መካከል ጥቂቶቹ ደግሞ ለቀጣይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተሳታፊ የሚሆኑ እጩዎች መገኘት ብዙም እንዳላስደሰታቸው ተጠቁሟል፡፡ የኬንያ ወጣቶች በማንኛውም የፖለቲካ መድረክ መሳተፍ የሚችሉበት ክፍተት ሊፈጠር እንደሚገባው ወጣቶቹ በስብሰባው ላይ ያስታወቁ ሲሆን፣ የመንግስት ተቋማቱ ደግሞ ስብሰባው ወጣቶቹና መሪዎቹ ማንኛውንም የፖለቲካ አጀንዳ ሊወያዩ የሚችሉበት መድረክ እንደሆነ ለወጣቶቹ ገልፀዋል፡፡ ይህ ስብሰባ እንዲካሄድ ከፍተኛ ጥረት ያደረገው የኬንያ ወጣቶች ተቋም (Youth Agenda) በተለያየ ጊዜ የተለዩ መድረኮች ላይ በርካታ የወጣት ቡድኖችን እንዲሳተፉ ጥሪ ያስተላልፋል፡፡ በዚህኛው ስብሰባ ላይም ከእምነት ተቋማትና ከሠራተኛ ማኅበራትም ወጣቶች እንዲገኙ ጥሪ አስተላልፎ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ከተለያዩ አካላት የተወከሉ ወጣቶች ቢሆኑም በስብሰባው ላይ የተሳተፉት ወጣቶችን ያማከለ አንድ አቋም ከማንፀባረቅ እንዳላገዳቸው ተገልጿል፡፡ ከተሳታፊዎቹ ወጣቶች በወቅቱ ያለውን የፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንዲቀጥል የሚፈልጉት ጥቂቶቹ መሆናቸውን አብዛኛዎቹ አገሪቷ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካ ዘርፍ ለውጥ እንደሚያስፈልግ አመልከተዋል፡፡ ይህንንም ወጣቶቹ ካደረጉት የተለያዩ ንግግሮች ለማወቅ እንደሚቻል፣ አቋማቸውም በተለያዩ መንገዶች መንፀባረቁን ዘገባው ጠቁሟል፡፡ የኬንያ ወጣቶች አብዮተኝነት በተንፀባረቀበት በዚህ ስብሰባ በአገሪቱ ላይ ጉልህ ለውጥ ለማምጣት ከታሰበ ዛሬ ነገ ሳይባል ወጣቶች በፖለቲካው ስልጣን ማግኘት እንደሚኖርባቸው የሚያመለክቱ ንግግሮችም በወጣቶቹ ቀርበዋል፡፡ ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ሥር ነቀል ለውጦችን ለማምጣት እርምጃ ከመውሰድ በፊት የአገሪቱን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችና ለውጦች ቅደም ተከተልና ታሪካዊ አመጣጥ ወጣቶቹ ሊያውቁና ሊረዱ እንደሚገባቸው በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡ እንደዚህ ያለውን የወጣቶች አብዮተኝነት መመልከት አስደናቂ እንደሆነ በመጠቆም የጥምር መንግስቱ የወጣቶቹን አጀንዳ የሚመለከት ምን ዓይነት ፖሊሲ ሊያወጣና ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚችል ጥያቄ የሚያነሱም አሉ፡፡ የወጣቶቹ ስብሰባ በመጨረሻ በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበረሰባዊና ባህላዊ ዘርፎች ሊደረጉ የሚገባ መሻሻሎችን በማስመልከት አሥራ አራት የመፍትሄ ሀሳቦችን አስቀምጧል፡፡ ወጣቱን ከጎኑ ማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም የፖለቲካ ኃይል የመፍትሄ ሀሳቦቹን ሊመለከት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ በወጣቶቹ እይታ አፋጣኝ፣ ነገ ዛሬ ሳይባል ፖሊሲ ሊቀረጽለትና በአስቸኳይ ተግባራዊ ሊደረግለት የሚገባው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኬንያውያን ወጣቶች ችግር ነው፡፡ እድሜያቸው ሀምሳ አምስት የሆነ በሲቪል ሰርቪስና በመንግስት ኮርፖሬሽኖች ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞች (ሴትም ወንድም) በአስቸኳይ ጡረታ እንዲወጡ ወጣቶቹ ጠይቀዋል፡፡ ይህ በአንዳንዶች እይታ ኬንያን ዴሞክራሲያዊና ፍትህ ወደሰፈነበት አገር የማሸጋገር ራዕይ የሰነቀ ተብሏል፡፡ በፖለቲካው ዘርፍ ወጣቶቹ ለውጥን ለማምጣት ከሚንቀሳቀሱ ተቋማትና የፖለቲካ መሪዎች ጋር አብሮ ለመስራት እንደሚፈልጉ ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የወጣቱን ችግር ለመፍታት ከሚንቀሳቀሱና ለአገሪቱ ልማት አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ አገራዊና አለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡ መንግስት በቀረቡት ጉዳዮች ላይ መሻሻሎችን እንደማያደርግ መንፀባረቁን ዘገባው አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ኬንያውያን የሚወያዩበት መድረክ እስካለ ድረስ የትኛው የፖለቲካ አካል መሠረታዊ ለሆኑት የአገሪቱ ጉዳዮች የመፍትሄ ሃሳብ ያመጣል የሚለውን መጠቆም ብዙም አስቸጋሪ እንደማይሆን የሚናገሩም አሉ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |