Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow በሒሳብ ሥራ ዝሆኖች ከሰው ይሻላሉ
በሒሳብ ሥራ ዝሆኖች ከሰው ይሻላሉ E-mail
Wednesday, 01 October 2008
Imageአንድ አዲስ ጥናት ዝሆኖች ከሰዎች በተሻለ በሒሳብ ሥራ ጎበዞች እንደሆኑ ማመልከቱ ዘ ሰን ዘግቧል፡፡

ሳይንቲስቶቹ በሁለት የተለያዩ እቃዎች ውስጥ ፍራፍሬዎችን በማስቀመጥ ዝሆኖችን የለቀቁ ሲሆን ዝሆኖቹ የተወረወሩትን ፍራፍሬዎች ብዛት በማስታወስ ብዙ ፍራፍሬዎች ወደያዘው ቅርጫት ማምራታቸው ለጥናቱ ድምዳሜ መሠረት ሆኗል፡፡

የጋዜጣው ዘገባ ዝሆኖቹ በፍጥነት አትክልቶቹን ሲወረውሩ እንኳን ለማስታወስ እንዳልተቸገሩ ጨምሮ አስታውቋል፡፡

ዝሆኖቹ 79 በመቶ በሚሆነው ጊዜ በትክክል እቃዎቹን የመረጡ ሲሆን፣ አሽያ የተባለው ዝሆን 87 በመቶ ትክክለኛ ምርጫ አድርጓል፡፡

የዝሆኖቹ ሂደት በፊልም ከተቀረፀ በኋላ በሰው ላይ ሲሞከር የሰው የስኬት ጣሪያ 67 በመቶ ብቻ ነበር፡፡

ጥናቱን ያስተባበረችው ዶ/ር ዲኦኮ ኢሪ በቶኪዮ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ሲሆኑ ዝሆኖቹን ያገኙት ከኡኖዙ ነው፡፡ "እኔ ራሴ ወደየትኛው ቅርጫት ምን ያህል ፍራፍሬ እንዳንጠባጠብኩ እረሳ ነበር" ብላለች፡፡

የግንባታ መሳሪያ ማርስ ላይ አለ

ለግንባታ ዋነኛ አቅርቦት የሆነው ብረት በማርስ ላይ በበቂ መጠን እንዳለ ሳይንቲስቶች ማመልከታቸውን ኒው ሳይንቲስት ዘግቧል፡፡

በብረት የተሞሉት ሜቲዮራይትስ በማርስ ላይ በግግር መልክ መገኘታቸውን የማርስ ፕላኔትን ለመውረር ላሳቡ ሁሉ ለግንባታ የሚሆን አቅርቦት ከወደ መሬት ማጓጓዝ እንደሌለባቸው ሳይንቲስቶቹ በማሾፍ መክረዋል፡፡

በክሊቭላንድ ኦሀዩ በሚገኘው የናሳ ግሌን የምርምር ጣቢያ የሚሰሩት ጅዮፍሬይ ላንዲስ የማርስ ብረቶች ከመሬት ብረቶች የሚለዩት በማርስ ደረቅ የአየር ሁኔታና የኦክስጅን እጥረት ስላለ ለዝገት እንደማይዳረጉ አብራርተዋል፡፡

በመሬት ማንኛውም ብረት ነክ ቁሳቁስ በኦክስጅን በተሞላው ከባቢ አየርና በእርጥበት ለዝገት ስለሚዳረጉ ለመከላከያ አይረን ኦክሳይድን በተለይም ሐይታይትን መጠቀም ግድ እንደሚል ተገልጿል፡፡ ነገር ግን አይረን ኦክሳይድ ከኦክስጅን እንዲፀዳ ለማድረግ ከፍተኛ የሃይል አቅርቦትን እንደሚጠይቅም ሳይንቲስቶቹ ግልጽ አድርገዋል፡፡

የቻይና የህዋ ልዑክ ወደ መሬት ተመለሰ

ሽያንዙ 7 የተሰኘው የቻይና የህዋ ልዑካን በተሳካ ሁኔታ የመሬት ዛቢያን ከዞሩ በኋላ ወደ መሬት መመለሳቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ወደ ህዋ በራሪው በሞንጎልያ በርሃ አካባቢ በሚገኘው የቤጂንግ የልዑክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ሲደርስ ሞቅ ባለስሜት የሚያጨበጭቡ ሰዎች ሞልተውት ነበር፡፡

ሦስቱ የልዑካኑ አባላት አስትሮናቶች ደህንነት የሚነበብባቸው ሲሆን፣ እቅፍ አበባዎችን ሲቀበሉና ለካሜራዎች እጃቸውን ሲያወለበልቡ ነበር፡፡

በህዋ ዛቢያ ላይ የልዑካን ቡድኑ አባላት ምርመራ ያካሄዱ ሲሆን፣ ይህም ለቻይና የህዋ ፕሮግራሞችና የሕዋ ላይ እርምጃ ፕሮግራሞች ጠቃሚ እንደሚሆን ታምኖበታል፡፡

የልዑካን ቡድኑ መሪ የ42 ዓመቱ ጂያ ሺጋንግ ከህዋ በራሪው መጀመሪያ የወጣ ሲሆን፣ "ታላቅ ግዳጅ ነበር፡፡ በአስቸጋሪ ፈተናዎች የተሞላ ቢሆንም ስኬታማ ፍፃሜ አግኝቷል" ብሏል፡፡

የቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂኢባው በቤጂንግ በመገኘት የልዑካን ቡድኑን የመሬት መድረስ የተመለከቱ ሲሆን፣ ሶስቱን የቻይና ዜጎች "ጀግኖች" ብለዋቸዋል፡፡

ጂያ ለህዋ ላይ እርምጃው የተጠቀመው ቻይና ሰራሽ አልባሳት ከ5 ሚሊዮን ፓውንድ እስከ 20 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ እንደወጣባቸው ተነግሯል፡፡

ሺያንዙ 8 እና 9 እ.ኤ.አ በ2010 ቻይና ልታቋቁም ላሰበችው የህዋ ላብራቶሪ ጠቃሚ እንደሚሆኑ የታመነባቸውና በቅርቡ ይፈፀማሉ ተብለው የሚጠበቁ ሲሆኑ፣ ከተፎካካሪዋ ጃፓንም እንድትለቅ ያደርጋሉ፡፡

ሳይንቲስቶች የአሜሪካ የኮንግረስ አባላትን አስጠነቀቁ

የአሜሪካ ሳይንቲስቶች በሞባይል ስልኮችና በጭንቅላት ካንሰር መካከል ያለው ግንኙነት ከሳምባና ሲጋራ ጋር ካለው ተመሳሳይ እንደሆነና በዚህም የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ሊጠናቀቁ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡

ሳይንቲስቶች ከተንቀሳቃሽ ስልክ የሚመነጨው የማግኔቲክ ፊልድ ተጽዕኖ በሰው ልጅ ላይ የሚያስከትለው አደጋ ዙሪያ የተከፋፈሉ ሲሆን በአልባኒ ዩኒቨርሲቲ የጤና እና አካባቢ ጥበቃ ተቋም ተጠሪ ዴቪድ ካርፔንተር "ኅብረተሰቡ በሲጋራና በሳንባ በሽታ መካከል ግንኙነት እንዳለ ለመገንዘብ 50 ዓመት ፈጅቶበታል፡፡ አሁን ያን ስህተት መድገም የለብንም" በማለት በአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ኮሚቴ ንዑስ ክፍልና በክትትልና ለውጥ ዙሪያ ለሚሰራው አካል ፊት ተናግረዋል፡፡

ሳይንቲስቶቹ አክለውም የጭንቅላት ካንሰር ለመዳበር በርካታ አመታት የሚፈጅ በመሆኑ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎቹ ጉዳቱን ወዲያውኑ ለማየት እንደሚገድባቸው አስጠንቅቀዋል፡፡

ለአሜሪካ ኮንግረሰ አባላት ገለፃ ያደረጉት ሳይንቲስቶች የተንቀሳቃሽ ስልክ አደጋ ከአዋቂዎች ይልቅ በህፃናቱ ላይ የከፋ አደጋ እንደሚያስከትል ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም ብዙዎቹ ሳይንቲስቶች የአሜሪካ የጤና፣ የደህንነት እና የአካባቢ ደህንነት ኤጀንሲዎች በራድቢ ፍሪኩዌንሲ እና ራድየሽን ስርጭት መጠን ላይ ገደብ እንዲያስቀምጡ ለኮንግረስ አባላቱ ጥሪ አድርገዋል፡፡

የጨው መጠንን መቀነስ የሚሊዮኖችን ህይወት ይታደጋል

የልብ ህመምና የልብ ምት በሽታ በዓለም ቁጥር አንድ ገዳይ በመሆኑ የአለም የልብ ፌዴሬሽን ሰዎችን የጨው መጠናቸውን እንዲቀንሱ ጥሪ እያደረገ መሆኑን ሲቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡

በጄኔቫ መቀመጫውን ያደረገው መንግስታዊ ያልሆነው ድርጅት ሰዎች በየቀኑ ከሚጠቀሙት የጨው መጠን ግማሽ የሻይ ማንኪያ ያህል ቢቀንሱ በጨው የተነሳ የሚሞቱ ሚሊዮኖችን መታደግ እንደሚቻል ገልጿል፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሽህርያር ሼይክ ከወደ ፓኪስታን በሰጡት ቃለ ምልልስ የጨው ተጠቃሚነት መጠንን በመቀነስ ከልብ ታማሚዎች 20 በመቶውን ከልብ ምት በሽታ ተጠቂዎች ደግሞ 15 በመቶውን መቀነስ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡

ሼኩ መጠነኛ የጨው መጠንን በመቀነስ በደም ግፊት ላይ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም አስምረውበታል፡፡

እንደ ፌዴሬሽኑ ገለፃ በየዓመቱ 17.5 ሚሊዮን ሰዎች በልብ ህመምና በልብ ምት በሽታ ይሞታሉ፡፡

ፌዴሬሽኑ ወደ 1 ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በደም ግፊት እንደተጠቁ አስታውቆ እ.ኤ.አ በ2025 ቁጥሩ ወደ 1.5 ቢሊዮን ከፍ እንደሚልም ግምቱን አስቀምጧል፡፡ ከጨው ተጠቃሚነት በተጨማሪ ውፍረት፣ የሰውነት አለመንቀሳቀስና ማጨስና መጠጣትም ለደም ግፊት ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ፌዴሬሽኑ ግልጽ አድርጓል፡፡

ከራስ መሳት ህመም ለማገገም መስታወት ይጠቅማል

አንድ የጃፓን ተመራማሪ ሰዎች በራስ መሳት ህመም ከተጠቁ በኋላ ለማገገም መስተዋት በመጠቀም ፓራላይዝድ ያደረገው አካላቸው እንደሚንቀሳቀስ ካሰቡ በፍጥነት ማገገም እንደሚችሉ መደምደሙን ሲቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡

በቶክዮ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የሚሰራው ካዙ አሚሞቶ "የአእምሮ ስነ ልቦና በማገገም ሂደት ውስጥ ትኩረት ከተሰጠው የሚጫወተው ሚና ቀደም ብሎ ከምናስበውና ከሚገባን በላይ ነው" ብሏል፡፡

ራስን መሳት ወደ አእምሮ በሚዘልቅ ኦክስጅን እና ግሉኮስ እጥረት የሚከሰት የአእምሮ ጉዳት ሲሆን፣ በብዛት የሰውነትን ግማሽ ክፍል እንዳይንቀሳቀስ ያደርጋል፡፡

መስተዋት ፊት የቀረቡ የበሽታው ተጠቂዎች የማይንቀሳቀስ አካላቸው የተንቀሳቀሰ ከመሰላቸው የማይንቀሳቀሰው አካል የተሻለ ምላሽ እንደሚሰጥ ጥናቱ ያረጋግጣል፡፡

በአሚሞቶ ጥናት 14 የበሽታው ተጠቂዎች ከመስተዋት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ሰውነታቸው እንደተንቀሳቀሰና እንደተጣጠፈ ተገልጿል፡፡

የበሽታው ምልክቶች በፊት፣ በእጅ፣ በእግር ላይ ያለመንቀሳቀስ፣ በመናገር፣ በመረዳትና በማዬት ላይ ማደናቀፍና በመራመድና በሰውነት ሚዛን ላይ ችግር የሚያስከትል ሲሆን፣ በንቃትና በራስ ምታት ላይም አስከፊ ችግሮችን ያስከትላል፡፡
 
< Prev   Next >