| በአሰላ የሕዝብ ፍቅር ለኦሊምፒክ ጀግኖች |
|
| Sunday, 05 October 2008 | |
![]() የቀነኒሳ አባት የንብ አውራ ለመያዝ አንድ ቀን ሙሉ ሮጠዋል - “ስጦታው ከጀግንነታቸው ጋር አይወዳደርም” አባዱላ ገመዳ - “ከስጦታው ሁሉ የበለጠብኝ የሕዝብ ፍቅር ነው” ኃይሌ ገ/ሥላሴ - መስማትና መራመድ ያቃታቸው ዋሚ ታወሱ (በኃይሌ ሙሉ) የአትሌት ቀነኒሳ አባት አቶ በቀለ በይቻ ፈረስ መጋለብ እንጂ ሩጫ አይወዱም፡፡ በህይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ረጅም ርቀት ሩጫ የሮጡት ከብዙ ዓመታት በፊት አንድ የንብ አውራ ከቀፎው ወጥቶ በጠፋበት ጊዜ ነበር፡፡ አቶ በቀለ አውራ ንቡን ለመያዝ አንድ ቀን ሙሉ ሮጠዋል፡፡ የሮጡት ሩጫ በእርዝመት ቢልካ 7 ጋሻ እንደሚሆንም ይናገራሉ፡፡ ከብዙ ድካም በኋላ አውራ ንቡን ይዘው ወደ ቤት ቢመለሱም በሰውነታቸው ላይ የደረሰው ድካም ግን ቀላል አልነበረም፡፡ ከዚያች ቀን አድካሚ ሩጫ በኋላ አቶ በቀለ ለአንድ ወር ያህል አልጋ ይዘው ነበር፡፡ ሩጫን በዚህ መልኩ የሚያውቁት የአትሌት ቀነኒሳ አባት ልጃቸው ሯጭ እንዳይሆን ቢመክሩት አይፈረድባቸውም፡፡ “ቀነኒሳ አስተማሪ እንዲሆን ነበር የምፈልገው” ይላሉ አባቱ በቤጂንግ ኦሎምፒክ የሁለት ወርቅ ባለድል የሆነው አትሌት ቀነኒሳ ግን እርሳቸው ከጠበቁት በተቃራኒ ሯጭ ሆኖ የቤተሰቡን ሕይወት ለውጧል፡፡ የቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ጀግና የዓለም ባለታሪክ ሆኗል፡፡ ሩጫውን አቁሞ ትምህርቱን ብቻ እንዲማር ሲወተወት የነበረው ልጃቸው አሁን በአሰላ ከተማ የጀግና አቀባበል ሲደረግለበት ሲያዩ “ይህ የእግዚአብሄር ተአምር ነው” ከማለት ውጪ ደስታቸውን የሚገልጹበት ቃላት አላገኙም፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በቤጂንግ ኦሎምፒክ ድል ላስመዘገቡ፣ በውድድሩ ለተሳተፉ አትሌቶች፣ ለቡድን መሪዎችና ለጋዜጠኞች በሱሉልታ ለመኖሪያ መንደር የሚሆን 30ሺ ካሬ ሜትር ቦታ እና የተለያዩ ሽልማቶች ሰጥቷቸዋል፡፡ ድል እና ሽልማትን ባህላቸው ላደረጉት ለነሀይሌ ገብረስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለና ለጥሩነሽ ዲባባ የአሁኑ የኦሮሚያ ክልል የመሬት ስጦታ በተጨማሪ ሁልጊዜም ማግኘት የሚፈልጉት የሕዝብ ፍቅር ነው፡፡ ይህን የሕዝብ ፍቅር ደግሞ የጀግና አቀባበል ካደረገላቸው የአርሲና የአካባቢው ሕዝብ አግኝተዋል፡፡ ቁጥሩን ለመገመት የሚያስቸግር በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ በአሰላ ስታዲየም ተገኝቶ በድላቸው የተሰማውን ኩራት ገልጾላቸዋል፡፡ በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አባዱላ ገመዳ የክልሉ መንግሥት አትሌቶቹ በተወለዱበትና ባደጉበት አካባቢ የጀግና አቀባበል እንዲደረገላቸውና የሽልማት ስጦታ እንዲበረከትላቸው የወሰነው ለባለድል አትሌቶች የሚሰጠው ክብርና ፍቅር ሌሎችንም ያበረታታል፣ ጥቂት አትሌቶችን ብቻ ሳይሆን ሺህዎችን ይፈጥራል በሚል እምነት መሆኑን ከገለፁ በኋላ “ለነዚህ ጀግኖች አትሌቶች የሚበረከተው ስጦታ ከጀግንነታቸው ጋር አይወዳደርም የሚመጥነው ነገር ቢኖር የህዝብ ፍቅርና አቀባበል ብቻ ነው” ብለዋል፡፡ እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ በቤጂንግ ኦሎምፒክ ለተሳተፉ አትሌቶች፣ የቡድን መሪዎችና ጋዜጠኞች ሱሉልታ ላይ “የቤጅንግ የአትሌቶች ሜዳ” በሚል መንደር ገንብተው የሚኖሩበት 30ሺ ካሬ ሜትር ቦታ የተሰጣቸው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ አትሌቶች ከአዲስ አበባ ወደ ሱሉልታ ለልምምድ ሲሄዱ የሚደርስባቸውን ድካም ለመቀነስና ሁለተኛው ደግሞ አሰልጣኞች፣ ሯጮች እና ቡድን መሪዎች እዚያው እየተመካከሩ ቢኖሩ ይሻላል ከሚል እሳቤ የተነሳ ነው፡፡ ለራጮች እና ለሩጫ ያላቸውን ክብር ለመግለጽ ይመስላል አቶ አባዱላ ገመዳ ንግግራቸውን ከጨረሱ በኋላ ዱብ ዱብ እያሉ ወደ መድረኩ ተመልሰዋል፡፡ ለአትሌቶች የመኖሪያ መንደር ይሆን ዘንድ የኦሮሚያ ክልል ስላበረከተው ቦታ ምን እንደተሰማው ያነጋገርነው ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ ከቦታው ስጦታ ይልቅ የአካባቢው ሕዝብ ለአትሌቶቹ ባሳየው ፍቅርና ክብር ስሜቱ እንደተነካ፣ ይህንን የሕዝብ ፍቅር ይዞም ለቀጣዮቹ አስር አመታት ለመሮጥ እራሱን እንዳሳመነ ገልጾልናል፡፡ “የመሬት እና የወርቅ ስጦታ በተለያየ ጊዜ አግኝቻለሁ፡፡ በሌላ ጊዜም አገኘዋለሁ፣ ከስጦታዎቹ ሁሉ የበለጠብኝ የሕዝብ ፍቅር ነው፡፡ ያን ያህል ሕዝብ በስታዲየሙ ተገኝቶ ላመጣነው ውጤት እውቅና መስጠቱና ለእኛ ያለውን ፍቅር መግለጹ አስደስቶኛል፡፡ በዚህም ለሚቀጥሉት አስር አመታት እሮጣለሁ ብዬ ነው የማስበው፡፡” የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በቅርቡ ድል ያስመዘገቡ አትሌቶችን ብቻ ሳይሆን እድሜያቸው የገፉ አዛውንት አትሌቶችንም ጭምር አስታውሶ የገንዘብ እና የመሬት ስጦታ ማበርከቱ ለአትሌቶች አቀባበል በአሰላ ስታዲየም የተገኘውን ሕዝብ አስደስቷል፡፡ ከተሸላሚዎች መካከል ደግሞ አንዱ የቀድሞው አትሌት ዋሚ ቢራቱ ናቸው፡፡ ከአምስትና ስድስት አስርት አመታት በፊት ሚዳቆ አባረው ይይዙ እንደነበር የሚናገሩትና በተለያዩ የአገር ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች በርካታ ሜዳሊያዎችን የሰበሰቡት የቀድሞው አትሌት ዋሚ በአሰላ ስታዲየም የሰተጣቸውን ሽልማት የተቀበሉት ራሳቸውን ችለው በመራመድ ሳይሆን በሁለት ሰዎች ተደግፈው ነበር፡፡ እነዚያ የሚወናጨፉ እግሮች አሁን ራሳቸውን ችለው መቆም አቅቷቸዋል፡፡ ክልሉ ለእኚህ ታሪካዊ አትሌት የ50ሺህ ብር ቼክ እና በሱሉልታ ከተዘጋጀው የአትሌቲክስ የመኖሪያ መንደር የቦታ ካርታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለገንዘብና ለቦታ ሽልማት እንግዳ የሆኑት የቀድሞው አትሌት ዋሚ ከነሀይሌ ገብረስላሴ በተቃራኒው የተሰጣቸው የቦታ ካርታና የገንዘብ ሽልማት ትኩረታቸውን ሳይስበው አልቀረም፡፡ የቦታ ካርታ ሽልማቱ ለአትሌቶች በተሰጠበት ጊዜ የካርታ መለዋወጥ ተከስቶ ነበር፡፡ በተሰጣቸው የቦታ ካርታ ላይ የሌላ ሰው ስም እንደተፃፈበት የተገነዘቡት አትሌት ዋሚ ከጎናቸው ለነበረ አንድ ሰው (የቅርብ ዘመዳቸው ይመስላል) በተደጋጋሚ ስለተፈጠረው ስህተት ሲያነሱለት ነበር፡፡ ዋሚ መጨረሻ ላይ የተረጋጉት የመድረክ አስተዋዋቂው ለአትሌቶቹ በተሰጠው የቦታ ካርታ የስም መለዋወጥ ስህተት መፈጸሙን ገልጾ ስህተቱ ከዝግጅቱ በኋላ እንደሚታረም ከተናገረ በኋላ ነበር፡፡ አትሌት ዋሚ ቢራቱን የኦሮሚያ ክልል በሰጣቸው የገንዘብና የቦታ ካርታ ሽልማት ዙሪያ ልናነጋግራቸው ሞክረን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጆሮአቸው የሚሰካውን የማዳመጫ መሳሪያ አዲስ አበባ ትተውት የመጡ መሆኑንና በስታዲየም ከተገኘው የሕዝብ ጩኸት ጋር መደማመጥ አስቸጋሪ መሆኑ ስለተገለጸልን የፈለግነውን ማግኘት አልቻልንም፡፡ ለጀግኖች አትሌቶቹ የተዘጋጀው የአቀባበል ስነ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እዚያው አሰላ ከተማ ውስጥ በአስር ሚሊዮን ብር ወጪ አስገንብቶ በእለቱ ወደ አስመረቀው ሆቴል ጎራ አልን፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ከሆቴሉ በር ቆመው ለጀግናው አትሌት ያላቸውን ፍቅር በሰፊው ሲገልፁ ተጋባዥ እንግዶች ደግሞ በሆቴሉ የቀረበላቸውን የነፃ ምግብና መጠጥ እየተቋደሱ ሲዝናኑ አገኘናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገነቡ በርካታ ሆቴሎች በሚመረቁበት እለት ለአገልግሎት የሚያስከፍሉት ዋጋ ከአዘቦት ቀን ዋጋ በእጥፍ የሚበልጥ ቢሆንም አትሌት ቀነኒሳ ግን በእለቱ ምግብና መጠጥን ጨምሮ ከክፍያ ነፃ የሆነ የመኝታ አገልግሎት ለእንግዶች እንዲሰጥ በማድረግ ልግስናውን አሳይቷል፡፡ ሆቴሉ ውስጥ ትንሽ አረፍ ካልን በኋላ የቀነኒሳ አባት አቶ በቀለ በይቻ ወደ ተቀመጡበት ወንበር ጠጋ በማለት በልጃቸው ድል ስለተሰማቸው ደስታ፣ ስለቀደምት ህይወታቸውና ቀነኒሳ ዝነኛና ሀብታም ከሆነ በኋላ ስላለው ኑሯቸው እንዲያጫውቱን ስንጠይቃቸው ፈቃደኝነታቸውን በፈገግታ ገለጹልን፡፡ የአራት ወንድ ልጅና የሁለት ሴት ልጆች አባት የሁኑት የ52ት አመቱ አዛውንት አቶ በቀለ በይቻ ተወልደው ያደጉት በሸዋ ክፍለ ሀገር ሜታ ሮቢ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው፡፡ ተወልደው ባደጉበት አካባቢ መሬት በከበርቴዎች ብቻ የተያዘ ስለነበር እድሜያቸው ለአቅመ አዳም ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ለተወሰነ ጊዜ ጭሰኛ በመሆን ነበር ኑሯአቸውን ሲገፉ የቆዩት፡፡ አርሰው፣ ዘርተው፣ አጭደውና ከምረው ያመረቱትን አብዛኛውን ምርት ለባለ መሬቱ ማቅረብ ግድ ይላቸው ነበር፡፡ ያመረቱትንም እህል በአህያ ጭነው ከሜታ ሮቢ ወደ አዲስ አበባ ወስደው ይሸጣሉ፡፡ ይህ የጭሰኝነት ህይወት ያልተመቻቸው አቶ በቀለ የትውልድ መንደራቸውን ትተው ወደ በቆጂ ሄዱ፡፡ እዚያ እንደደረሱ ከአካባቢው ከበርቴዎች ለእርሻ የሚሆን መሬት ተከራዩ፡፡ መሬቱን የተከራዩት በ160 ብር ሲሆን ክፍያው የሚጠናቀቀውም በስምነት አመት ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ “ስምንት አመት ረጅም ጊዜ ነው፡፡ ያን ያህል ጊዜ የሚጠብቅ አከራይ ከበርቴ እንዴት ሊኖር ቻለ?” ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ አቶ በቀለ ሲመልሱ “ኪራይ የሚከፈልበት ጊዜ ረጅም ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን የድሮ ሰው የዋህ ስለነበር መሬቱን ካከራየው ሰው ገንዘብ አይቀበልም ነበር” ሲሉ የበቆጂን ህይወት ይገልጻሉ፡፡ በኪራይም ቢሆን የራሳቸው መሬት ባለቤት የሆኑት አቶ በቀለ ቀንና ሌሊት በመስራት ከእርሻቸው ያገኙትን ምርት ለሁለት ክረምት ያህል ሸጠው ገንዘብ ካገኙ በኋላ ሌላ መሬት ገዙ፡፡ በዚህ መልኩ ከመሬት ላይ መሬት እየጨመሩ ጥሩ ህይወት መምራት ጀመሩ ልጆችም ወለዱ፡፡ በቆጂ መኖር ከጀመሩ በኋላ በቂ ንብረት ከብቶችና 22 የንብ ቀፎዎች አፍርተው እንደነበር የሚናገሩት አቶ በቀለ ልጃቸው ቀነኒሳ መምህር እንዲሆን ይፈልጉ እንደነበር አልሸሸጉም፡፡ ሩጫውን አቁሞ ትምህርቱን ብቻ እንዲከታተል ብዙ ጊዜ ቢመክሩትም ቀነኒሳ ግን “እግዚአብሄር የፈቀደውን ነው መሆን የምችለው” በማለት በሩጫው መቀጠሉን ያስታውሳሉ፡፡ አቶ በቀለ ሁኔታውን አሁን ቆም ብለው ሲያስቡት ይገርማቸዋል፡፡ ቀነኒሳ ያገኘው ድል እና ሀብትም በእግዚአብሄር ተዓምር የተገኘ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ የኦሮሚያ ክልል ለቀነኒሳና ለሌሎች ጀግኖች አትሌቶች ባበረከተው ሽልማትና በህዝቡ አቀባበልም ተደስተዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ለአትሌት ቀነኒሳ በቀለና ጥሩነሽ ዲባባ ካበረከተው የቦታ ካርታ እና የወርቅ ሽልማት በተጨማሪ ፈረስ ሸልሟቸዋል፡፡ በኦሮሞ ባህል ፈረስ የድል ምልክት ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡ “ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መኪና ሸለሙት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ደግሞ ፈረስ ሸለሙት” ሲሉ አቶ በቀለ ፈገግ አሉ፡፡ የቀነኒሳ አባት ፈረስ መጋለብ ይወዳሉ፡፡ የሚደነብር ፈረስ ግን ይፈራሉ፡፡ በቤታቸው ሁለት ፈረስ አለ፡፡ አንዱን ለግልቢያ አንዱን ደግሞ ለጭነት ይጠቀሙበታል፡፡ አቶ በቀለ ቀደም ሲል የነበራቸውን ህይወትና ቀነኒሳ ጥሩ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ የሚመሩትን ሕይወት አስመልክተው ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ፡፡ “ድሮ ለፍቼ ነበር የምኖረው፤ ጥሩ ኑሮ ብኖርም ሀሳብ ሳወጣና ሳወርድ ሌሊት አልተኛም ነበር፡፡ አሁን ግን እግዚአብሄር ይመስገን ዘና ብየ ነው የምኖረው” በልጃቸው አማካኝነት ሀብታም ከሆኑ በኋላ ጎረቤቶቻቸውና ዘመዶቻቸው ገንዘብ እንዲሰጧቸው የሚጠይቁአቸው መሆኑን አቶ በቀለ አልሸሸጉም፡፡ ገንዘብ ለሚጠይቋቸውም የለኝም የሚል ምለሽ አይሰጡም፡፡ “ሁለን ነገር የሰጠኝ እግዚአብሄር አይደል? እርሱ የሰጠኝን ለምን እከለክላለሁ?” የሚል አቋም አላቸው፡፡ ከአቶ በቀለ በኋላ ያነጋገርነው የአትሌት ቀነኒሳን ታላቅ ወንድም ታምራት በቀለን ነበር፡፡ የቀነኒሳ የሁለት አመት ታላቅ የሆነው ታምራት አባቱ በህመም ምክንያት ስራ መስራት ሲያቆሙ ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ግብርና ስራ ለመመለስ ተገዶ ነበር፡፡ “በወቅቱ እኔ ብማር ኖሮ ወንድሞቼ መማር አይችሉም ነበር” የሚለው ታምራት ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ግብርና መመለስ ከባድ ነገር ቢሆንም ለቤተሰብ ሲባል የተከፈለ መስዋዕትነት በመሆኑ ቅር እንዳላለው ይናገራል፡፡ ታምራት በ1985 ዓ.ም ትምህርቱን ሲያቋርጥ የ3ኛ ክፍል ተማሪ ነበር፡፡ ለአስራ ሁለት አመታት ያህል ቤተሰቦቹን ሲረዳ ከቆየ በኋላ በ1997 ዓ.ም ወደ ትምህርት ቤት ተመልሶ አሁን 8ኛ ክፍል ደርሷል፡፡ ከትምህርቱ ጎን ለጎን የወንድሙን ንብረት ያስተዳድራል፡፡ በአሰላ የተገነባውን አዲስ ሆቴል እንቅስቃሴም ይቆጣጠራል፡፡ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ሆነ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ከዚህ ቀደም አድርገውት በማያውቁት መልኩ የኦሮሞያ ክልላዊ መንግሥት የተረሱ አትሌቶችን አስታውሶ ሽልማት መስጠቱ የሚያስመሰግነው ነው፡፡ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በዚህ በኩል ከኦሮሚያው ክልል ተሞክሮ በመውሰድ የተረሱ አትሌቶች መድረክ የሚያገኙበትን ሁኔታ ሊያመቻች ይገባዋል፡፡ በተለያዩ አገሮች በሚደረጉ አለም አቀፍ ውድድሮች ከውድድር እራሳቸውን ያገለሉ የየሀገሩ የቀድሞ አትሌቶች ተጋባዥ እንግዳ በመሆን ሽልማት እንዲሰጡና ሪባን እንዲቆርጡ ይደረጋል፡፡ ይህን ሁኔታ የሚያመቻቹት የየሀገሮቹ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ናቸው፡፡ የእኛ አገር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ግን ከውድድር ራሳቸውን ያገለሉ ታላላቅ አትሌቶች ሳያጣ ይህንን ማድረግ አልቻለም፡፡ በአገር ቤት የተለያዩ የግብዣና የሽልማት ስነስርዓት ላይ አይጠራቸውም፡፡ሽልማት ባይሰጣቸው እንኳ ሽልማት እንዲሰጡ አያደርጋቸውም፡፡ አንዳንዴም የታዋቂ ስፖርተኞችን ሞት በእድር ጡሩምባ የሚበሰርበትም ጊዜ አለ፡፡ ሰሞኑን የኦሮሚያ ክልል ያደረገው ክልሉ አትሌት በማፍራት ብቻ ሳይሆን የተረሱ አትሌቶችንም በማስታወስ ግንባር ቀደም መሆኑን ነው፡፡ |
|
| Last Updated ( Sunday, 05 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |