Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ከኢትዮጵያ ሳተላይት ዕይታ ውጪ...
ከኢትዮጵያ ሳተላይት ዕይታ ውጪ... E-mail
Sunday, 05 October 2008
ከኢትዮጵያ ሳተላይት ዕይታ ውጪ የደቡብ ኮሪያን ሰርቨር በመጠቀም ቴሌን ዘርፈዋል የተባሉ ተከሰሱ

- በ10 ወራት አምስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል


በታምሩ ጽጌ

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ በ1997 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 33፣32 (1፣”ሀ”፣”2) እና (3) የተመለከተውን በመተላለፍ በኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን በተለያየ የሥራ ኃላፊነት ላይ ተሰማርተው ሲሰሩ ስልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም ከኢትዮጵያ ሳተላይት ዕይታ ውጪ የደቡብ ኮሪያን ሰርቨር በመጠቀም የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል ባላቸው ዘጠኝ ኢትዮጵያንና አንድ ደቡብ ኮሪያዊ ላይ መስከረም 22 ቀን 2001 ዓ.ም በከፍተኛው ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ክስ መሠረተ፡፡
የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ በክሱ እንዳመለከተው፣ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች አቶ አየለ እሸቱ (የብሮድባንድ ቡድን መሪ”፣ አቶ ዮናስ ኃ/ማርያም (የኮርፖሬሽን ሠራተኛ የነበረ”፣ ቴዎድሮስ አሰፋና ብሩክ አክሊሉ (የኮርፖሬሽኑ ሸያጭ ሠራተኞች) ሚ/ር ሚዩንግ ኪልዮን (ደቡብ ኮሪያዊ”፣ ትዕግሥት ተስፋዬ (ሃልኮም ኢንተርኔት አገልግሎት”፣ አልጋነሽ በርሄ (የናኦሚ ኢንተርኔት አገልግሎት ባለቤት”፣ ኤፍሬም ጌታቸው (የቪክ ቴክኖሎጂ ሰርቪስ ሥራ አስኪያጅ) ብርሃኑ ከፍ ያለውና ኢዮስያስ ይልማ ለተባሉ ግለሰቦች ህገወጥ ጥቅም ለማስገኘት ሲባል የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጐን በመተው ያለአግባብ ስልጣናቸውን በመጠቀም በመንግሥት ጥቅም ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን በክስ ቻርጁ ዘርዝሯል፡፡

ደቡብ ኮሪያዊው ሚ/ር ሚዮንግ ኪሊዮን በቱሪስት ቪዛ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን የሚገልፀው የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ፣ ለውጭ አገር ዜጐች ያልተፈቀደውን ኢንተርኔት ሰርቪስ ፕሮቫይደር (አይ.ሲ.ፒ) የተሰኘውን የብሮድ ባንድ አገልግሎት ማቋቋሙን በክስ ቻርጁ ላይ ዘርዝሯል፡፡

ሚዮንግ ኪሊዮን የብሮድ ባንድ አገልግሎቱን ያቋቋመው፣ የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ ምስክር ባደረጋቸው ሁለት ሰዎች ስም “ዩኒዲት ኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ኃ/የተ/የግል ማህበር” በተባለ የንግድ ማህበር ስም እንዲፈቀድለት ያቀረበውን ጥያቄ የኮርፖሬሽኑ የብሮድ ባንድ ቡድን መሪ አገልግሎቱን እንዲያገኝ ማድረጉን ዐቃቤ ሕግ በክስ ቻርጁ አመልክቷል፡፡

ደቡብ ኮሪያዊው በሕገ ወጥ መንገድ ያገኘውን የአይ.ሲ.ፒ የብሮድ ባንድ አገልግሎት ከኮርፖሬሽኑ ፈቃድ ውጭ ወደ አገር ውስጥ ባስገባቸው የቴሌኮሚዩኒኬሽን መሣሪያዎች አማካኝነት በአዲስ አበባ ሲ.ኤም.ሲ አካባቢ የራሱን መቆጣጠሪያ ጣቢያ በማዘጋጀት ደቡብ ኮሪያ ከሚገኘው “ቱዋይዝ ሎጂስቲክ ኃ/የተ/የግ ማህበር” የተሰኘውን ድርጅት ሰርቨር መጠቀሙን የክስ ቻርጁ ያመለክታል፡፡

ሚዮንግ ኪሊዮን ደቡብ ኮሪያ ከሚገኘው የግል ድርጅት ሰርቨር በመጠቀም ከኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ሳተላይት ቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ አገር ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት ከሚሰጡት ደንበኞች ሄልኮም ኢንተርኔት አገልግሎት፣ ናኦሚ ኢንተርኔት አገልግሎት፣ ቪክ ቴክኖሎጂ ሰርቪስ፣ ብርሃኑ ከፍ ያለውና ኤዩስያስ ይልማ (ሁሉም ተከሳሾች ናቸው) ጋር በመመሳጠር “ማኔጅ ዶት ቶክቱ አፍሪካ ኔት” በሚል አድራሻ ገብተው የኢንተርኔት አገልግሎት ለእያንዳንዳቸው መታወቂያ (አይ.ዲ”ና የይለፍ ቃል (ፓስ ወርድ) አዘጋጅቶ በመስጠት ወደ ውጭ አገር የተለያዩ ሰዎችን እንዲያስደውሉ ማድረጉን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ይዘረዝራል፡፡

ደቡብ ኮሪያዊው ከኢትዮጵያዊያኖቹ ጋር በመመሳጠር በፈፀመው የማጭበርበር ሥራ (ማስደወል) ከህዳር እስከ ነሐሴ ወር 2000 ዓ.ም ድረስ 4 ሚሊዮን 527 ሺ 845 ብር ከተከሳሾቹ ጋር በጋራ በመጠቀም በኮርፖሬሽኑ ጥቅም ላይ ጉዳት እንዲደርስና የአገሪቱን ደህንነት በሚያሰጋ መልኩ ድርጊቱን በመፈፀሙ መከሰሱን የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ የክስ ቻርጅ ያመለክታል፡፡

ዮናስ ኃይለማርያም የተባለው ተከሳሽ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኛ በነበረበት ወቅት ከደቡብ ኮሪያዊው አንድ ላፕ ቶፕ በስጦታ መልኩ በመቀበሉ፣ የብሮድ ባንድ ቡድን መሪው ኮርፖሬሽኑ የከለከለውን የአይ.ሲ.ፒ አገልግሎት እንዲፈቅድለት ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን በክስ ቻርጁ ተገል”ል፡፡

ቴዎድሮስ አሰፋና ብሩክ አክሊሉ የተባሉት የኮርፖሬሽኑ የጉርድ ሾላ ቅርንጫፍ የሽያጭ ሠራተኛ ሆነው ሲሰሩ ከነመለያ ቁጥራቸው 21 በተለያዩ ጊዜያት የተዘጉና አገልግሎት ላይ ያልዋሉ ሲም ካርዶችን መሐመድ ሬድዋን በተባለ ግለሰብ አማካኝነት ለሚ/ር ሚዮንግ ኪልዮን መሸጣቸውን ዐቃቤ ህግ አመልክቷል፡፡

በኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው ትዕግስት ተስፋዬ “ሄለን” በሚል መታወቂያና 47900 በሚል የይለፍ ቃል፣ አልጋነሽ በርሄ “ገነት” በሚል መታወቂያና 5797 በሚል የይለፍ ቃል፣ ኤፍሬም ጌታቸው “ኤፍሬም” በሚል መታወቂያና 961642 በሚል የይለፍ ቃል፣ ብርሃኑ ከፍ ያለው “ብርሃኑ” በሚል መታወቂያና “ብርሃኑ፣ ቱ” በሚል የይለፍ ቃልና ኢዮስያስ ይልማ “ኢዮስያ” በሚል መታወቂያና ለጊዜው ባልታወቀ የይለፍ ቃል በመጠቀም በእያንዳንዳቸው የኢንተርኔት አገልግሎት መስጫ ካፌዎች ከኮርፖሬሽኑ ፈቃድና ዕውቅና ውጭ ግለሰቦችን ከኢትዮጵያ ውጪ ስልክ በማስደወል የተጠቀሙና በኮርፖሬሽኑ ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን የክስ ቻርጁ በዝርዝር አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽንና አይ.ኤን.ኤስ.ኤ ለኮሚሽኑ ምርመራ መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ 11 የሰው፣ 10 የሰነድ፣ ከደቡብ ኮሪያዊው መኖሪያ ቤት በኤግዚቢትነት ሲያዝ የተቀረፀ ሲዲ 1 ኮፒና 21 የተሸጡ ሲም ካርዶችን በማስረጃነት አቅርቧል፡፡

ተከሳሾቹ መስከረም 22 ቀን 2001 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርበው የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ቢያመለክቱም ማመልከቻቸው ውድቅ ተደርጐ ለጥቅምት 4 ቀን 2001 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
 
< Prev   Next >