| የሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ... |
|
| Sunday, 05 October 2008 | |
የሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ ኢንቬስትመንት ሁኔታ፣ ችግርና መፍትሔ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ባለው የሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ ኢንቬስትመንት ላይ፣ በተለይም ለልማት ተወስደው ነገር ግን ሳይለሙ ታጥረውና ተጀምረው በሚቀሩ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥተን እየፃፍን ነው፡፡ ይህ ትኩረት ለምን አስፈለገ? እውነት አሳሳቢ ሆኖ ነወይ? የሼክ መሐመድ አላሙዲ ኢንቨስትመንት ተሳካ፣ አልተሳካ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ትርጉም ይህን ያህል የሚያሳስብና የሚያፅፍ ነው ወይ? አዎን አሳሳቢ ነው፡፡ ልዩ ትኩረትም ያስፈልገዋል፡፡ ኢንቬስትመንቱ በልዩ ትኩረትና ዓይን መታየት ያለበት ነው፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ካለው መንግሥታዊ ያልሆነ ኢንቨስትመንት ግንባር ቀደሙና ትልቁ ኢንቨስትመንት የሳቸው ነው፡፡ በእርሻ፣ በኢንዱስትሪ፣ በትራንስፖርት፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በማእድን፣ በፋይናንስና ንግድ በጤናና ትምህርት፣ በስፖርትና መዝናኛ፣ በማእድን ኢነርጂና ኮንስትራክሽን ወዘተ. ኢንቨስትመንት ተሳታፊ ናቸው፡፡ የገቡበት ዘርፍና ስፋት፣ የካፒታሉ ብዛትና የከፈተው የሥራ እድል እጅግ በጣም ከፍ ያለ ስለሆነ ልዩ ትኩረት ሊደረግበት ይችላል፡፡ ሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት አደርጋለሁ፣ ገንዘብም ከውጭ አመጣለሁ፤ ብለው መምጣታቸውና በርካታ የሥራ ዕድል መክፈታቸው በጠንካራ ጎን የሚጠቀስ፣ የሚያስመሰግናቸውም ነው፡፡ በአንድ በኩል እንደዚህ ዓይነት ትልቅ ጠንካራ ጎን እያለ፣ በተፃራሪው ደግሞ እጅግ አሳሳቢና ደካማ ጎንም ይታያል፡፡ በደካማ ጎንና በአሳሳቢው ጎን በዋነኛነት የሚጠቀሰው ኢንቨስትመንቱን ሊያራምድና ሊያሳካ የሚችል ማኔጅመንት የሌለ መሆኑ ነው፡፡ በአደረጃጀት አንጻር ሲታይ፣ ተገቢ የኢንቨስትመንት አደረጃጀት የለውም፡፡ ሚድሮክ ኢትዮጵያ ከየት ወዴት እንደሆነ፣ ከሚድሮክ ኢትዮጵያ ውጭ ያሉት ማኔጅመንታቸው ከየት በመለስና እንዴት እንደሚሰራ፣ በግልፅና በተገቢ ደረጃ የተዋቀረ አይደለም፡፡ ማኔጅመንቱን እንዲመሩ ከተቀመጡት ሰዎች አንዳንዶቹ፣ ሕጋዊ ኃላፊነትና አገራዊ ተቆርቋሪነት ይዘው እንደሚሰሩ ይታወቅላቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ግን በጎን፣ ባልታወቀ መንገድ፣ የታወቀ መዋቅርና አደረጃጀት ሳይኖራቸው “መሪዎች” ነን የሚሉና ሳይዘምቱም፣ ሳያዘምቱም “ቀኛዝማችና ግራዝማች” የሆኑ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያትም ብቃት ያለው አመራር፣ ብቃትና ሕጋዊነት በሌለው አመራር የሚታመስና የሚረበሽ መስሎ ይታያል፡፡ ቀስ በቀስም ሕጋዊ እውቅና ካገኙት ሥራ አስኪያጆች ይልቅ፣ ቢሮና መዋቅር ሳይኖራቸው የበላይነት በሚያሳዩ “ሞባይል ምስለኔዎች” የሚቆጣጠሩት ኢንቨስትመንት አይነት ሆኗል፡፡ ይህ ሁሉ ተጨምቆ አንድ ትልቅ ስጋት ያስነሳል፡፡ ስጋቱም ግልጽ ነው፡፡ ሼክ መሐመድ አንድ ችግር ቢገጥማቸው ራሱን ችሎ የሚሄድ ድርጅት ነው ወይ? አይመስልም፡፡ እና ምን ይሆናል? ይፈርሳል፡፡ ከፈረሰ መንግሥት ሊደጉመውና ሊያስተካክለው ይችላል ወይ? አይችልም፡፡ መሸከም የሚችል ሌላ ባለሀብት አለን ወይ? የለም፡፡ እንደ አሜሪካ ተያዥ የሚሆን (ቤይል አውት የሚያደርግ) አለ ወይ? የለም፡፡ አደጋው ከተከተለ፣ ሥራ የነበረው ሁሉ ስራ አጥ ይሆናል፡፡ ያበደረ ባንክ፣ ገንዘብ ያጣል፡፡ ማስተካከል የሚችል ማኔጅመንት ባለመኖሩ ንብረትና ገንዘብ ይባክናል፡፡ የነበረው እንዳልነበረ ይሆናል፡፡ ቀውስ ይሆናል፡፡ ይህ ሁኔታ ሊመጣ እንደሚችል ስለምንገምትና ስለምንገነዘብ ነው፤ ልዩ ትኩረት ያስፈለገዋል የምንለው፡፡ ከአሁኑ ካልታሰበበትና ድክመቱ ካልታረመ ጣጣ ይመጣል ብለን ስለምንሰጋ ነው፡፡ ችግሩን መፍታት ይቻላል ወይ? የሚፈታ ችግር ነው ወይ? ባለሃብቱ ችግሩን ለመፍታት ቆርጠው ከተነሱ ይፈታል ብቻ ሳይሆን በአጭር ጊዜ ሊሆን ይችላል፤ ብለን እናምናለን፡፡ ምኞታችንም ችግሩ ተፈቶ ባለሃብቱም አገራችንም ተጠቃሚዎች ሆነው ማየት ነው፡፡ ለመፍትሔውም የመንግሥት ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ ምን የሚሉት መፍትሔ? መፍትሔ አንድ፡- ብቁና ጠንካራ ማኔጅመንት መፍጠር፡፡ ያለውን ሁኔታ ገምግሞ፣ ጠንካራውን ማኔጅመንት ለይቶ ለችግር ፈጣሪው የመፍትሔ ሃሳብና አቅጣጫ አስቀምጦ ሙያዊና ከኢንቬስትመንቱ ጋር የሚመጣጠን ብቃት ያለው አመራር ማፈላለግ፡፡ በኢንቨስትመንቱ ዙሪያ ካሉት ብቁ ሰዎች፣ አስፈላጊ ከሆነም ከውጭ አማካሪዎችና ኤክስፐርቶች በማምጣት ብቁ ተቆርቋሪ ጠንካራ ማኔጅመንት በአስቸኳይ መፍጠር፡፡ መፍትሔ ሁለት፡- በግል ጥቅምና በስግብግብነት ከሕዝብ ጋር የሚያጋጩ፣ አቅምና ሕጋዊ ኃላፊነት የሌላቸው “ሻዶው ማናጀሮች” እና “ሞባይል ምስለኔዎች”ን ማስወገድ፡፡ የማኔጅመንት ችግር እንዳለና ዋነኛው ችግር እንደሆነ ለማንም ግልጽ ይመስለናል፡፡ በዙሪያቸው፣ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ጠፍተው ሳይሆን፣ የድርጅቱ ዋነኛ ታማኞች እኛ ነን፤ የሚሉና ለግል ጥቅማቸው ኢንቨስትመንቱን እያበላሹ የሚውሉ ስራቸውና ኃላፊነታቸው ይህ ነው፤ የማይባል፣ “ሞባይል” ሆነው፣ ሞባይል ይዘው በስልክ ነገሮችን እየፈተፈቱና እያገቱ የሚውሉ ስለበዙና የበላይነት ስለያዙ ነው፡፡ እነዚህ ዓይነቶቹ፣ ጓደኞችና ወዳጆች ከሆኑ፣ ከስራ ውጭ እገዛና ርዳታ ይደረግላቸው፡፡ ከኢንቨስትመንቱ ማኔጅመንትና ቁጥር ግን ሊወገዱ ይገባል፡፡ እባካችሁ እረፉ፣ ሊባሉ ይገባል፡፡ መፍትሔ ሶስት፡- “ሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ ፋውንዴሽን” ማቋቋም፡፡ ባለሃብቱ ገንዘቡን ለፈለገው ቢለግስ መብቱ መሆኑ አይካድም፡፡ ገንዘቡም ነው፡፡ ሆኖም ግን አግባብና ቀና ያለው ለህብረተሰቡና ለአገር በሚጠቅም ደረጃ ሲደረግ ዘለቄታዊና ሕዝባዊ ምስጋናን ያስገኛል፡፡ መንፈሳዊና ሕሊናዊ ኩራትና እርካታንም እውን ያደርጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለአንዱ ገልባጭ፣ ለሌላው ቡቲክ፣ እየበተኑና ለእገሊት ይህን ያህል ለእንቶኔ ይህን ያህል፣ እያሉ መሄድ ምስጋና ሳይሆን ሃሜትና አሽሙር ማስከተሉ መረሳት የለበትም፡፡ “ስጥ ስጥ ይለኛል” “ሸልም ሸልም ይለኛል” ይቅር፡፡ “ሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ ፋውንዴሽን፣” አቋቁሞ፣ በቦርድ እየተወሰነ ለስፖርት፣ ለስነ ጥበብ፣ ለሳይንስ፣ ለምርምር፣ እየተሰጠና የልማት መንገድ እየተፈጠረ መጓዝና አገር ወገንን መጥቀም ይሻላል፡፡ በአስቸኳይ ቢቋቋምና ሥራ ቢጀመርም ብዙ ነገር ይስተካከላል፣ ከሕዝብ ጋር እርቅ ይወርዳል፡፡ መፍትሔ አራት፡- አስተማማኝ ኢንቨስትመንት ላይ ማተኮርና ማጠናከር፣ የማይቻለውን መመለስና መዝጋት፣ መዋጥ የሚቻለውን ብቻ ማኘክ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየታየ ያለው የመሬት አወሳሰድና አጥሮ ማስቀመጥ፣ ድርጅትን ዘግቶ እንዳይሰራ ማድረግ፣ ሳይንስ ሳይሆን “ሁሉ ልጨብጠው” ስሜት የሚገፋፋው ይመስላል፡፡ በርካታ መሬት ተወስዶ ታጥሮ የሚቀረውም ለዚሁ ነው፡፡ መገምገም፣ መምረጥ (ፎክሰድ መሆን) አለአስፈላጊውን መተውና መመለስ የተሻለ ነው፡፡ መፍትሔ አምስት፡- ኩባንያዎች በአትራፊነታቸው፣ በሰው ሃይል አደረጃጀታቸው፣ በቴክኖሎጂ ትራንስፈርና በሕብረተሰባዊ ጠቀሜታቸው ይገምገሙ፣ ይለዩ፡፡ ኢንቨስትመንት አገርንና ሕዝብን የሚጠቀመው፣ አትራፊ ሆኖ ሃብት በመፍጠር፣ ከውጭ አገር ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስመጣትና በማስተዋወቅ፣ የሰው ሃይል እያሰለጠኑና እያስተማሩ በማዳበርና ብቁ ሙያዊ ሃይል በመፍጠር፣ ከዚህ ጋርም ለሕብረተሰቡ አስፈላጊ አገልግሎትና ጠቀሜታ በመስጠት ነው፡፡ ኩባንያዎች ከዚህ አኳያ በዚህ ሊገመገሙ ይገባል፡፡ መፍትሔ ስድስት፡- ከሌሎች ኢንቨስተሮች ጋር መወዳደርና መተጋገዝ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የመቃወም፣ የመጠራጠር፣ የማደናቀፍ ሁኔታ እንጂ አርአያ ሆኖ ባለሀብቶችንና ሌላ ኢንቨስተርን ማበረታታት አይታይም፡፡ ይህ በአስቸኳይ ተለውጦ አርአያ በመሆን ሌላውን መደገፍና ውድድሩን በአዎንታዊ መንፈስ ማራመድ ያስፈልጋል፡፡ የአመለካከት ለውጥ ይኑር፡፡ መፍትሔ ሰባት፡- መንግሥት አስፈላጊ እገዛና ድጋፍ ያድርግ፡፡ መንግሥት በሼክ አላሙዲ ያለውን ችግር ቀረብ ብሎ ሊያየውና ችግሩ እንዲፈታ ጠርቶና አነጋግሮ መፍታት ይጠበቅበታል፡፡ ኢንቨስትመንቱ ለአገር ጠቃሚ ነው፡፡ ጎጂውን አስወግዶ ጠቃሚውን ይዞ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ ሩቅ ሆኖ ተመልካች መሆን የለበትም፡፡ መንግሥት የማያለማውን በአስቸኳይ እንዲወገድ ያድርግ፡፡ የሚያለማውን ያግዝ፡፡ ሼክ አላሙዲንም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በድፍረት እየተገናኙ “ጋንግሪኑን መቁረጥ” ለሚድነው መድኃኒት ሊያዙ ይገባል፡፡ እነዚህ የተጠቀሱት መፍትሔዎች ጠቋሚዎች እንጂ ብቸኛ አይደሉም፡፡ ዋናው ከስሜታዊው አመራር ወደ የኢንቨስትመንትና የማኔጅመንት ሳይንስ በአስቸኳይ ማምጣት ነው፡፡ ከልብ ቆርጠው ከተነሱ ደግሞ የማኔጅመንትና የኢንቨስትመንት ሳይንስም “አንኳኩ ይከፈትላችኋል” ይላል፡፡ |
|
| Last Updated ( Sunday, 05 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |