Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ሚዛናችሁን አትሳቱ
ሚዛናችሁን አትሳቱ E-mail
Sunday, 05 October 2008
ከሁለት ሣምንታት በፊት እሁድ ቀን በቤጂንግ ማራቶን አራተኛ የወጣውን አትሌት ድሪባ መርጊያ በሰጠው ቃለ ምልልስ የአቶ ጌታነህ ተሰማ ስም በማንሳት የአንድ ወገን አስተያየት ብቻ ተስተናግዷል፡፡
በቤጂንግ ማራቶን በወንዶች 3ኛና 4ኛ  የወጡትን አትሌቶች አሰልጥነው ለዚህ ያበቁት አቶ ጌታነህ መሆናቸውን ድሪባ መርጊያም አልሸሸገም፡፡ መጉላት የሚገባው የአቶ ጌታነህ የድሉ አስተዋፅኦ እንጂ የእሳቸውን ክብር ለሚያቃልለው፣ በህግም ሊያስጠይቅ በሚችለው የአትሌቱ ውንጀላ ቅድሚያ መሰጠት አልነበረበትም፡፡ ሪፖርተሮች እንዲህ ዓይነት ቃለምልልሶችን ስታደርጉ የሌላውን ወገን ድምፅ እኩል ማስተናገድ እንደሚገባችሁ ባትዘነጉት ጥሩ ነው፡፡

(ሰዋስሰው በዛብህ፣ ከጃንሜዳ)


በኮንዶሚኒየም አጠቃቀም ግለኝነት ቢወገድ

መንግሥት የህብረተሰቡን የመኖሪያ ችግር ለመቅረፍ በከፍተኛ ወጪ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በመገንባት ለተጠቃሚዎች እያስተላለፈ ይገኛል፡፡ ሆኖም ተጠቃሚዎች ቤቱን በመጠቀም ረገድ ችግር እየፈጠሩ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት የአንዳንድ ግለሰቦች ራስ ወዳድነት፣ የግለሰቦች ሕገወጥነት እና የስነ ምግባር ጉድለት (በፎቁ በረንዳ በሰው በር ፊት ፓንት፣ ካልሲ እና ጫማ ማስጣት፣ በመተላለፊያ መንገድ ላይ ምግብ ማብሰል ወዘተ... ይጠቀሳሉ፡፡ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጥቆማ ደርሷቸው በተለይም ህገወጥ ግንባታ የገነቡ የቤት ባለቤቶችም ወደነበረበት እንዲመልሱ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ከመፃፍ ውጪ ተከታትለው አስተማሪ እርምጃ አለመውሰዳቸውም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ፅሁፍ ያነሳሳኝ ዋና ምክንያት በቦሌ ገርጂ ኮንደሚኒየም ቁጥር አንድ አንዳንድ ነዋሪዎች የውስጥ ክፍሎችን በማፈራረስ እና የግል በረንዳቸውን በመቀላቀል በብሎኬት ግንባታ አካሂደዋል፡፡ በተለይ ምድር ቤት አካባቢ ያሉ ሰዎች የጋራ መተላለፊያው በረንዳ ላይ ተጨማሪ ክፍል በመስራታቸው የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንዲያውቁት ቢደረግም አስተማሪ እርምጃ ባለመውሰዳቸው ግንባታውን እንደትክክለኛነት ተወስዶ አንዳንድ ነዋሪዎች ህንፃው በሚለሰንበት ወቅት ተመሳሳይ ግንባታ ፈፅመው አጋጣሚውን በመጠቀም በመንግሥት ወጪ እንዲለሰን እና ቀለም እንዲቀባ አድርገዋል፡፡

በጣም የሚያሳዝነው በህገወጥ ግንባታው ቤታችን የተናጋ ግለሰቦች እና ከግንባታው ነፃ የሆኑ ጥቂት የህንፃው ኮሚቴ አባላት ለሚመለከተው የመንግሥት አካላት በቃልና በፅሁፍ በማሳወቃችን ቤታችንን ልታስፈርሱ ነበር አልሆነላችሁም በማለት ማንጓጠጣቸው ስሜታችንንና በህግ የመተማመናችን ሞራል የጎዳ ስለሆነ ህግ አክብረው የሚኖሩ ነዋሪዎች የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይዙ እንዲሁም በሌሎችም ኮንዶሚኒየም ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈፀም የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት በማነጋገር በጋዜጣችሁ እንድታስተናግዱ ከአደራ ጭምር እንጠይቃለን፡፡

(ከቦሌ ገርጂ ኮንዶሚኒየም ቁጥር 1 ነዋሪዎች)


አልአሙዲንን ለቀቅ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ቦታ በኢንቨስትመንት ስም ተረክበው ነገር ግን ግንባታ ያልጀመሩ ባለሀብቶች ጉዳይ በተከታታይ በመዘገብ ላይ መሆናችሁን ከጋዜጦቻችሁ ዘገባዎች መረዳት ችያለሁ፡፡ በብዙ ከተሞች ደግሞ ቦታ ተቀብለው አጥረው ካስቀመጡት ባለሀብቶች መካከል ሼህ መሐመድ ሁሴን አልአሙዲ ይገኙበታል፡፡ በርግጥ ባለሀብቶቹ በወሰዱት ቦታ ፈጥነው መገንባት እንደሚገባቸው ምንም አያከራክርም፡፡ ሼህ አልአሙዲን ግን ለሀገሪቱ ልማት እያደረጉት ካሉት ሰፊ ተሳትፎ አንፃር ሲታይ ቢዘገይም ማልማታቸው እንደማይቀር በመገንዘብ እሳቸውን ለቀቅ ሌሎቹን ጠበቅ አድርጉ እላለሁ፡፡

(ቤቲ፣ ከአዲስ አበባ)


ካምብሪጅ ለኢትዮጵያ አዲስ ዓመት እውቅና መስጠቷ ተገቢ ነው


ሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ መስከረም 21 ቀን 2001 እትም ኪንና ባህል ገጽ ላይ ..ካምብሪጅ ለኢትዮጵያ አዲስ ዓመት (እንቁጣጣሽ) የሕግ ዕውቅና ሰጠች፡፡.. በሚል ርዕስ የቀረበው ጽሁፍ ዓመቱን ሙሉ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ሲከበር የቆየው የሚሌኒየም በዓል የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለዓለም ሕብረተሰብ ለማስተዋወቅ ያበረከተው አስተዋጽኦ ውጤታማ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

የሚሌኒየሙ በዓል ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ፊደልና የዘመን አቆጣጠር ያላት መሆኑንም የዓለም ሕዝብ በድጋሚ እንዲረዳው በማድረግ በኩል ጉልህ ሚና መጫወቱን ከጽሁፉ መንፈስ ለመረዳት ያስችላል፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ የካምብሪጅ ከተማ ለኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ መስከረም 1 ቀን 2001 እውቅና መስጠቷም ሀገሪቱ የአፍሪካ ጥንታዊት፣ ነፃና ያልተቋረጠ ሕልውናውን ያረጋገጠች አገር መሆንም ያስመሰክራል፡፡

(ሚክሎል ብሥራት፣ ከአምስት ኪሎ)

ለአርቲስት ሚስቶች አስተማሪ ነው

በእሑድ ሪፖርተር ጋዜጣ ሴት አምድ ላይ የአርቲስት ታምራት ሞላን ባለቤት በማነጋገር ባቀረባችሁት ቃለምልልስ የአርቲስቶች የትዳርና የፍቅር ግንኙነት ምን እንደሚመስል ለማሳየት መሞከራችሁ ጥሩ ነው፡፡ የአርቲስቱ ባለቤት ወ/ሮ ጽጌ ነገሮችን የምትመለከትበት እይታና የባለቤቷን የሥራ ፀባይ የተረዳችበት ሁኔታ ለብዙ አርቲስቶች ሚስቶች፤ ለሌሎችም ቢሆን አስተማሪ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ በቀረበው ቃለምልልስ ላይ የአርቲስት ታምራት ሞላ ስለ ባለቤቱ የሰጠው አስተያየትም መካተቱ መልካም ነበር፡፡

(ዳግም፣ ከላፍቶ)

የሃሳብ ነፃነት ላይ ገደብ እስከመቼ?

ባለፈው እሑድ በሕግ አምላክ ላይ የወጣው ፅሁፍ ኢትዮጵያ አሁንም በታራሚዎች (እስረኞች) ላይ መረጃ የማግኘት መሠረታዊ መብታቸው ላይ በቅርብ ባወጣቻቸው ሕጎች ላይ ገደብ በማስቀመጥ እንደምታምን ማሳየቷን አይቻለሁ፡፡ በበርካታ ሀገሮች እስረኞች ከህብረተሰቡ ተገልለው ነፃነታቸውን ሲያጡ በማንበብና በመፃፍ ራሳቸውን እንዲያርሙ ጥረትና ማበረታቻ ይደረግላቸዋል፡፡ የእኛዎቹ ታሳሪዎች ግን በዚሁ መብታቸው ላይ በዓለም አቀፍ ህጎች ድጋፍ የሌለው ገደብ መደረጉ ያሳዝናል፡፡

(እስማኤል ኑርሁሴን፣ ከጎተራ)

የመልካም አስተዳደር መገለጫው


በህገ መንግሥቱ ውስጥ የተደነገጉ የሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ለማንኛውም ዓይነት የተፅዕኖ መዳፍ ሳይጋለጡ እንዲከበሩ ኃላፊነት የተሰጠውና በፌዴራል መንግሥቱ የህግ ሰውነት ያለው አንዱ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሲሆን በተጓዳኝም የአስተዳደር በደል የተፈፀመባቸው ዜጐች ተጐጅ ሆነው እንዳይቀሩ እና በደላቸውንም በቀላሉ አሰምተው መፍትሄ እንዲያገኙና መብታቸውን ለማስከበር ሲባል በህግ ሥልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ ዕንባ ጠባቂ ተቋም መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡

በመሠረቱ የኢፌዲሪ መንግሥት እነዚህን ድርጅቶች ህጋዊ ሰውነት ሰጥቶ በአዋጅ ያቋቋመበት ዋናው ዓላማ በህገ መንግሥቱ የተደነገጉ ድንጋጌዎች ሙሉ በሙሉ እንዲከበሩና በመልካም አስተዳደር እጦትም የተነሳ ዜጐች እስከመጨረሻው ተበድለው እንዳይቀሩ መብታቸውም መከበሩን ለማረጋገጥ በሚል ታሳቢነት ነው፡፡
የመንግሥት መሠረታዊ ዓላማው ይህ ሆኖ ሳለ እነዚህ ህጋዊ ስልጣንና ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚወስኑትንና የሚሰጧቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ለመተግበር የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋሞች ዳተኛ ሆነው ሲታዩ ይስተዋላል፡፡ ለህግ የበላይነት ተገዥ ያለመሆን አዝማሚያም ይታያል፡፡ በአብላጫው ደግሞ ከተጠያቂነት ለመዳን ሲባል ብቻ ስህተትን መቀበል እንደ ሽንፈት በመፈረጅ የእንቢተኝነት አባዜ ተጠናውቷቸው የሚታዩም አሉ፡፡
ወጣም ወረደ ግን በሚፈጠር የአስተዳደር ጥፋት ዞሮ ዞሮ ተጐጂው ያው የህብረተሰቡ አባላት በመሆናቸው መንግሥት ቢያስብበት መልካም ነው፡፡ ስህተትን ተቀብሎ በወቅቱ ማረም የመልካም አስተዳደር መስፈን አንዱ መገለጫው መሆኑን ሁሉም ወገን ሊገነዘብ ይገባል፡፡

(ከታዛቢዎች)

ከሶማሊያ መውጣት አለብን

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሊያ የእስልምና ም/ቤቶች በኩል የተቃጣበትን የወረራ ድግስ ለመመከት ከሁለት ዓመት በፊት በወሰደው እርምጃ እንደዜጋ በግሌ ቅሬታ አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን እያደር ኢትዮጵያ ብቻዋን በሚያባራ የእርስ በርስ ግጭቶች ተጋፋጭ መሆኗ፣ ዓለም አቀፉም ኅብረተሰብ ለሶማሊያ ትኩረት መንፈጉ ስመለከት ተገቢ ያልሆነ መስዋዕትነት እየተከፈለ መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ ስለሆነም መንግሥታችን ቦታውን ለሠላም አስከባሪ ኃይል ለቅቄ እወጣለሁ የሚለውን በጎ ምኞቱ አለመሳካቱን በመገንዘብ ሶማሊያን በፍጥነት ለቅቆ እንዲወጣ፣ በሶማሊያ ለሚገኝ ጦር የሚወጣ ገንዘብ ደግሞ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች መርጃ እንዲውል ቢደረግ ከታሪክ ተወቃሽነትም ያድናል እላለሁ፡፡

(ተመስገን ባህሩ፣ ከቃሊቲ)
 
< Prev   Next >