| ነውጥ የለሽ ትግል እና ጋንዲ |
|
| Sunday, 05 October 2008 | |
በጌታቸውን ንጋቱ2ኛው ዓለም አቀፍ የነውጥ የለሽ ትግል ቀን (International non violence day) በአዲስ አበባ ሲከበር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አትዮጵያ የነውጥ አካሄድን እንደማትደግፍና የማኅተመ ጋንዲን አስተሳሰብ እንደምትደግፍ ገለፁ፡፡ የሕንድ መሪ የነበሩት ማኅተመ ጋንዲ 139ኛ ዓመት የልደት በዓል ላይ በተከበረው በዚህ የነውጥ የለሽ ቀን የመታሰቢያ ትምህርት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ናቸው፡፡ ባለፈው ሐሙስ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተዘጋጀው በዚህ 2ኛው ዓለም አቀፍ የኢ-ነውጥ ቀን ላይ በመገኘት ለእንግዶች የመታሰቢያ ትምህርት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀኑ ማኅተመ ጋንዲ በተወለዱበት ቀን መከበሩን ትክክለኛ እርምጃ እና ከዚህም የተሻለ ቀን እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ማኅተመ ጋንዲ ለሕንድ ነፃ መውጣትና ለሠላም ያደረጉት ትግልና ያስገኙት ውጤት የተለየ ሥፍራ እንዳለውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡ ማኅተመ ጋንዲ ነውጥ የለሽ ትግልን በመከተልና ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ሳያነሱ ባለመተባባርና እውነታን በመከተል ሕንድ ቀስፎ ይዞ የነበረውን ኮሎኒሊዝም ማስወገዳቸውን ሲገልፁ ድህነትን ማሸነፍ ይቻላል ብለው የተናገሩት አሁን እኛ ከድህነት ጋር ለምናደርገው ትግል በቀጥታ ይሰማናል” ብለዋል፡፡ ማኅተመ ጋንዲ ግጭቶችን በንግግርና በሠላም መፍታትና ያለ ሰላም ምንም ዓይነት ልማት አይመጣም በማለት የተናገሩትም ኢትዮጵያ ለምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ትክክለኛ መልዕክት ያስተላልፋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በአሁኑ ወቅት በአካባቢ፣ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉት ችግሮች፣ በጋንዲ ነውጥ የለሽ አስተሳሰብ መፍትሄ ሊያገኙ እንደሚችሉ እና ነውጠኝነት የሚኖረው ፋይዳ እንደማይኖር አስረድተዋል፡፡ “የጋንዲ የነውጥ የለሽ እና እውነት አመለካከቶች የአሁኑን ዓለም ሊቀይሩ የሚችሉ መሳሪያዎች ናቸው” በማለትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ሕንድና አፍሪካ አዲስ የትብብር መስመር ከፍተው እየሰሩ መሆናቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር “የደልሂ ስምምነትና የአፍሪካና የሕንድ ትብብር የጋንዲን አመለካከት ወደ አፍሪካ አስርፀዋል” ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት በጦርነትና በነውጥ ያለፈች አገር መሆኗን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ላለፉት ሁለት አስር ዓመታት የተሻለ አንፃራዊ ሰላም ማግኘቷንና ከኤርትራ ጋር ያለው የድንበር ችግር አለመፈታቱ በተወሰነ ደረጃ ሰላሙን እንደጎዳው ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ በጦርነት ችግራቸውን በድርድር ለመፍታት የተደረጉት ጥረቶች እስካሁን ውጤታማ አለመሆቸውን፤ ይሁን እንጂ ለሰላም እስከ መጨረሻው ድረስ ኢትዮጵያ ጥረቷን እንደምትገፋበት ተናግረዋል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ያለው ሠላም በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ የጋንዲን መርሆዎች መከተል አገራቱ ያለባቸውን ችግር ያለ ነውጥ በሰላም ለመፍታት እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አብዲላሂ ጃኔህ የነውጥ የለሽ ቀን በማኅተመ ጋንዲ የልደት ቀን እንዲከበር መወሰኑ ትክክለኛ ከመሆኑም በላይ ነውጥ የለሽ ትግል ምን እንደሆነ የሚሰብክ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሚስተር ጃኔህ አያይዘውም “የነውጥ የለሽ መልዕክት በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ ተፈላጊነት አለው፡፡ በሁሉም ሃይማኖቶችና አገራት ለዘላለም ትክክል ሆኖ የሚኖር አስተሳሰብ ነው” ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር የሆኑት ጉርጂት ሲንግ የማኅተመ ጋንዲ ጽሁፍ ከሆነው “ከእውነት ጋር ያለኝ ልምድ” “my experiments with truth” ውስጥ የተወሰኑ ንባቦች አሰምተዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በየዓመቱ መስከረም 22 ወይም ኦክቶበር 2 የዓለም አቀፍ የነውጥ የለሽ ቀን (International non-violence) ተብሎ እንዲከበር በወሰነው መሰረት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና በኢትዮጵያ የሕንድ ኤምባሲ ቀኑ በጋራ ለማክበር ችለዋል፡፡ ማኅተመ ጋንዲ ወይም ሞሃንዳስ ካራምቻንድ ጋንዲ የሕንዳዊያን የነፃነት አባት ተብለው የሚጠሩ ሲሆን ኦክቶበር 2/1869 እ.ኤ.አ ተወልደው በጃንዋሪ 30/1948 እ.ኤ.አ ሕይወታቸው በሰው እጅ አልፏል፡፡ ማኅተመ ጋንዲ የሕንድ ሕዝብ የፖለቲካና መንፈሳዊ መሪ በመሆን የሕንድን የነፃነት ትግል መርተዋል፡፡ ቅኝ ገዢዎችን ባለመተባበር፣ ባለመታዘዝ ያለ ጦር መሳሪያ ትግል ሕንድን ለቅቀው እንዲወጡ አድርገዋል፡፡ በዓለም ላይ ማኅተመ ጋንዲ ተብለው የሚጠሩት የእኚህ ግለሰብ ስም ትርጓሜ “ታላቂቱ ነፍስ” የሚል ሲሆን፣ በሕንድ ውስጥ ባፑ ወይም አባት ተብለው ይጠራሉ፡፡ በሕንድም የሕዝብ አባት የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ማኅተመ ጋንዲ እንደማንኛውም ሕንዳዊ መካከለኛ ኑሮ በመኖር፣ ባህላዊውን ዶቲ እና ሻውል ልብሶች በመልበስ ትግላቸውን ሚሊዮኖች እንዲቀላቀሉ በማድረግ ሕንድን መርተዋል፡፡ ጋንዲ ይመገቡ የነበረው አትክልትና ፍራፍሬ (Vegetarian) ሲሆን፣ ይህንንም ራስን ለማንፃትና ማኅበራዊ ተቃውሞዎችን ለመምራት ተጠቅመውበታል፡፡ የሂንዱይዝም እምነት ተከታይ የነበሩት ጋንዲ የሕንድ የነፃነት ንቅናቄ በተነሳ ቁጥር በቅድሚያ ለዘላለም የሚጠሩ ሆነው ይኖራሉ፡፡ በምዕራብ ሕንድ ጉጃራት ግዛት የተወለዱት ጋንዲ ከልጅነታቸው ጀምሮ በመልካም አስተዳደግ ያደጉ ሲሆን፣ ራስን ማንፃት፤ አትክልትና ፍራፍሬ ማዘውተር፣ ጾምና መቻቻልን ከእናታቸው ፑትሊባይ መማራቸው ይነገራል፡፡ በ13 ዓመታቸው ለ14 ዓመቷ ካስቱብራ ጋንዲ ተድረው ሃሪላል፣ ማኒላል፣ ራምዳስ፣ ዴቭዳስ የሚባሉ ልጆች ወልደዋል፡፡ ማኅተመ ጋንዲ በጃንዋሪ 30/1948 እ.ኤ.አ በጥይት ተመትተው ተገድለዋል፡፡ በኒው ደልሂ ሲዘዋወሩ ጋንዲን የገደለው ናትራም ጎድዚ አክራሪ የሂንዱ ተከታይ ሲሆን፣ ጋንዲ ከፓኪስታን ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመቃወም እንደገደላቸው ይነገራል፡፡ ጎድዚ እና ተባባሪው ናሪያን አፕቴ ኖቬምበር 15/1949 እ.ኤ.አ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በስቅላት ተገድለዋል፡፡ በኒው ዲልሂ የጋንዲ መታሰቢያ ሃውልት ላይ “ሂ ራም” የሚል ጽሁፍ ተጽፎበታል፡፡ ትርጉሙም “አምላክ ሆይ” የሚል ሲሆን፣ ጋንዲ በጥይት ከተመቱ በኋላ የተናገሩት የመጨረሻ ቃል እንደሆነ ይነገራል፡፡ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ሄዋሃሬል ኔሕሩ ለሕንድ ሕዝብ ሲናገሩም፣ ካጓደኞቼና ጓዶች ከሕይወታችን ውስጥ ብርሃናችን ጠፋ ሁሉም ቦታ ጨለማ ወርሶናል፡፡ ምን ብዬ እንደምነግራችሁ ግራ ገባኝ፡፡ እንዴት ብዬ መናገር እንዳለብኝ አላውቅም፡፡ ተወዳጄ መሪዎች እኛ እንደምንጠራው አባታችን፣ የሕዝባችን አባት ከአሁን በኋላ የለም፡፡ ምናልባት ያልኩት ተሳስቼ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ከአሁን በኋላ አናየውም፡፡ እነዚህን ሁሉ ዓመታት እንዳየነው ምክሩን ለማግኘት ወደሱ መሮጥ አንችልም፡፡ ይህ በምንም ሊካስ የማይችል ውድመት ነው፡፡ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለዚህ ሁሉ ሚሊዮን የሕንድ ሕዝብ ታላቅ ጥፋት ደረሰካ ብለዋል፡፡ |
|
| Last Updated ( Sunday, 05 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |