Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ሲቪል ማኅበራትና ኤን.ጂ.ኦ አንድ ወይስ ሁለት?
ሲቪል ማኅበራትና ኤን.ጂ.ኦ አንድ ወይስ ሁለት? E-mail
Sunday, 05 October 2008
Imageበጌታቸው ንጋቱ

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን መጀመሩን ተከትሎ ዘንድሮ ሊፀድቁ ከሚችሉ ሕጐች መካከል የሲቪል ማኅበራት ረቂቅ ሕግ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል፡፡ ዓለም አቀፍ የሠብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ ረቂቅ ሕጉ የማያሠራ ነው በማለት ተደጋጋሚ ተቃውሞና ትችት እየሰነዘሩ የሚገኙ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ያሉት ድርጅቶች የሚሆነው ሕጉ ሲፀድቅ እናያለን በማለት በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡
ከሕጉ ባሻገር በቃላትና በትርጉም አለመግባባቶች በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መካከል ይታያል፡፡ መንግሥት ኤን.ጂ.ኦዎች (NGOs) የሲቪል ማኅበራት አይደሉም፤ የሚል ዕምነት እንዳለው ኢሕአዴግ አባላቱን ያወያየበት ሠነድ ያመለክታል፡፡ ኤን.ጂ.ኦዎች ደግሞ እኛም የሲቪል ማኅበራት ነን ይላሉ፡፡

እንደ ኢሕአዴግ ሠነድ ማብራሪያ ሲቪል ማኅበራት ማለት ዜጐች በተለያዩ መልኮች ለተለያየ ዓላማ የሚመሰርቱት ማኅበር ነው፡፡ የሃይማኖት፣ የልማት፣ የጤና ወይም ሌሎች ማኅበራት ቢሆኑም በዜጐች ፍላጎትና ለዜጐች ጥቅም ከተቋቋሙ የሲቪል ማኅበራት ይባላሉ የሚል ዕምነት እንዳለው ሠነዱ ያብራራል፡፡ ነገር ግን ከውጭ አገርና ከሌሎች ለጋሾች ገንዘብ እየሰበሰቡ የሕዝብን ፍላጐትና የልማት አጀንዳ ሳይዙ ፈንድ ለሰጣቸው ወገን ሪፖርት እያቀረቡ የሚኖሩ ድርጅቶች ኤን.ጂ.ኦ እንጂ ሲቪል ማኅበራት አይደሉም በማለት ሠነዱ ያብራራል፡፡

አሁን ያሉትን ኤን.ጂ.ኦዎችም “የኪራይ ሰብሳቢ መንግሥት ግልባጭ” እንደሆኑ ገዢው ፓርቲ ሲገልፅ በደሃ እና በልማት ስም የሚያገኙትን ገንዘብ ለአስተዳደራዊ ወጪ ማለትም ለመኪና ግዢ፣ ለነዳጅ፣ ለደመወዝና ለተለያዩ አላስፈላጊ ጉዳዮች እንደሚያውሉት ይገልፃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከ80 በመቶ በላይ የድርጅቶቹ ወጪ ለአስተዳደራዊ ጉዳዮች ቢውልም ለለጋሽ ድርጅቶችና ለመንግሥት የሚቀርበው ሪፖርት አብዛኛውን ለልማት ሥራ እንደዋለ የሚያሳይ ነው፡፡ ድርጅቶቹ ቁጥጥር ስለማይደረግባቸው በፋይናንስ ማጭበርበር ውስጥ እንደገቡም ይገልፃል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ለጥቅም የተቋቋሙ ከሚያበረክቱት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ይልቅ የሚያስከትሉት ቀውስ እንደሚኖርም ይጠቁማል፡፡ በመሆኑም ኤን.ጂ.ኦዎች በፍፁም ሲቪል ማኅበራት እንዳልሆኑ በተለይ ወደ አፍሪካ የሚመጡ ኤን.ጂ.ኦዎች ያሉበትን ደረጃ በመተቸት ይገልፃል፡፡

(Civil Societies) ዊክፒድያ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ በተቀመጠው ትርጉም መሠረት ከመንግሥት ውጭ ያሉ የማኅበረሰብ ቡድኖች በሙሉ ሲቪል ማኅበራት (Civil Societies) እንደሚባሉ ነው፡፡ እነዚህም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (ኤን.ጂ.ኦ”፣ የሠራተኛ ማኅበራት፣ የሕዝብ ማኅበራት፣ የበጐ አድራጐት ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ድርጅቶች፣ የሙያ ማኅበራት እና የመሳሰሉት የሲቪል ማኅበራት ይባላሉ፡፡ እነዚህ ማኅበራትም የአንድን ማኅበረሰብ ክፍል ፍላጐት ይገልፃሉ፣ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ የውይይት መድረክ ይፈጥራሉ፣ የመንግሥትን ፖሊሲና ስትራቴጂ ለማስቀየር የራሳቸውን ተፅዕኖ ይፈጥራሉ፡፡

መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGOs) ደግሞ የመንግሥት አካል ያልሆኑና በመንግሥት ያልተመሠረቱ ድርጅቶች ሲሆኑ ከመንግሥት ተፅዕኖም ነፃ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለትርፍ የማይንቀሳቀሱ፣ የንግድ ድርጅቶች ያልሆኑና የሚንቀሳቀሱበትን የፋይናንስ አቅም ከሌላ አካል አግኝተው ይሠራሉ፡፡ ኤን.ጂ.ኦዎች ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ በብዛት በዓለም ላይ የተፈጠሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ 2 ሚሊዮን፣ በሕንድ ከ1 ሚሊዮን በላይ ኤን.ጂ.ኦዎች እንደሚገኙ የተለያዩ መዛግብት ያመለክታሉ፡፡

በሲቪል ማኅበራት አንድ ዓይነት ፍላጐት ያላቸው ዜጐች ማኅበር ያቋቁማሉ፡፡ ማኅበሩም ለሁሉም አባላት እኩል ግልጋሎት ይሰጣል፡፡ የመምህራን ማኅበር በቅድሚያ ለመምህራኑ ጥቅም ሲቆም በመምህራን መካከልም ልዩነት አያደርግም፡፡ የሠራተኛ ማኅበር ወይም ሌሎች መሰል ማኅበራት ከማኅበረሰቡ ውስጥ ወጥተው ማኅበረሰቡን ያገለግላሉ፡፡ እንደ ኢሕአዴግ ሠነድ አገላለፅ ኤን.ጂ.ኦዎች ግን ለራሳቸው ሠራተኞችና ለራሳቸው ድሎት ቅድሚያ ሰጥተው እንሰራልሃለን የሚሉትን ሕዝብና የተጐዳ ክፍል በሁለተኛነት እንደሚያዩ፣ ገንዘብ እንደሚያባክኑና ተጠያቂነታቸው ገንዘብ ለሰጣቸው አካል እንጂ ለተጠቃሚው እንዳልሆነ ይገልፃል፡፡ መንግሥትም ሲቪል ማኅበራት እንዲጠናከሩ የሚፈልግ መሆኑን ሲገልፅ የጥገኛ መንግሥት ግልባጭ የሚላቸውን ኤን.ጂ.ኦዎች ጠቀሜታ አጣጥሎታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ያፀድቀዋል ተብሎ የሚጠበቀው ሕግ ይህንን ችግር መልክ ሊያስይዘው እንደሚችል ሲገልፅ እስካሁን ድረስ ሕግ ሳይወጣ በመቆየቱ ኤን.ጂ.ኦዎች ለአገሪቱ ልማት ሊያበረክቱ የሚችሉትን አስተዋፅዖ በበቂ ሁኔታ እንዳያበረክቱ እንዳደረጋቸው ይገልፃል፡፡ በአዲሱ ሕግ መሠረት ከውጭ አገር የሚመጡ ዓለም አቀፍ ኤን.ጂ.ኦዎች ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ እንዲሆን የተፈለገውም በእርሻና ግብርና ልማት፣ በትምህርትና በጤና ዘርፍ እንዲሁም በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ ነው፡፡

በአገር በቀል ድርጅቶች የፖለቲካ ሥራዎች፣ የሠብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ ሥራዎች እንዲሠሩ፣ እነዚህም አገር በቀል ድርጅቶች የሲቪል ማኅበራትን ሚና እንዲጫወቱና በኤን.ጂ.ኦዎች አሰራርና መንገድ እንዳይጓዙ 90 በመቶ የሚሆነው የገንዘብ ምንጮቻቸውን ከአገር ውስጥ እንዲሆን የውጭ ዕርዳታ ቢያስፈልጋቸውም ከ10 በመቶ በላይ ከውጭ አገር ዕርዳታ መቀበል እንደማይችሉ ያመለክታል፡፡ ይህ በመሆኑም ተጠያቂነታቸው ለሕዝቡ እንጂ ከውጭ ገንዘብ ለረዳው ሃይል ባለመሆኑ ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ይገለፃል፡፡

ዓለም አቀፍ ኤን.ጂ.ኦዎች ምንም ዓይነት የመልካም አስተዳደር፣ የሠብዓዊ መብት፣ የሴቶች መብት፣ በሕፃናትና በአካል ጉዳተኝነት እንዳይሠሩ አዲሱ ህግ እንደሚከለክላቸው ገልፀው፣ ይህ በአገሪቱ ያለውን የሠብዓዊ መብት አያያዝ ለመቀየር የሚያደርጉትን ጥረት የሚያሰናክልባቸው እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ዓለም አቀፍ ኤን.ጂ.ኦዎች በእነዚህ ተግባራት ላይ አይሳተፉም ለሚለው ዓለም አቀፍ የሠብዓዊ መብት ተሟጋቾች መንግሥት እያደረሰ ያለው የሠብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይጋለጥና አያያዙን ላለማሻሻል ነው ሲሉ፣ መንግሥት ግን ይህ የአገር ጉዳይ በመሆኑ የውጭ ጣልቃ ገብነት አያስፈልግም፤ ሥራውን ለመሥራት አገር በቀል ድርጅቶች በቂ ናቸው የሚል እምነቱን ይገልፃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ኤን.ጂ.ኦዎች የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ ቢሆንም መንግሥት ግን የፋይናንስ አያያዛቸው ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እንዳለው ያመለክታል፡፡

ኤን.ጂ.ኦዎች ሲቪል ማኅበራት እንደሆኑ ቢገልፁም፣ መንግሥት ግን ኤን.ጂ.ኦዎችንና ሲቪል ማኅበራትን ለያይቶ ማየት እንደሚገባ ይገልፃል፡፡ ከቃላት ትርጉም አንስቶ እስከ ተግባራት ድረስ ልዩነት እንዳለ መንግሥት ሲያምን፣ ኤን.ጂ.ኦዎች ግን ለሕዝብ ልማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ መንግሥት ግን የኤን.ጂ.ኦዎቹ ጠቀሜታ እምብዛም እንደሆነና የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ እንዳልሆነ ይገልፃል፡፡

አዲሱ ሕግ ያሠራል አያሠራም፤ በሚለው ላይም መንግሥትና ኤን.ጂ.ኦዎቹ የተለያዩ አመለካከቶች አሏቸው፡፡ መንግሥት “ሕጉ የሚያሰራ ነው፤ ምንም ዓይነት አፋኝ አንቀፅ የለውም፤ በፊት የለመዱት ያለ ሕግ መኖር ስለነበር ያ እንዴት ይቀራል ብለው ነው፤ በአገራችን የምንተዳደርበት ሕግ መንግሥት የማውጣት መብት አለው” ይላል፡፡ ኤን.ጂ.ኦዎች ደግሞ የመንግሥት አዲሱ ሕግ ሠብዓዊ መብት የሚያፍን፣ ጨርሶ የማያፈናፍንና የማያሠራ ነው የሚል ስጋታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡

አዲሱ ሕግ አገር በቀል ኤን.ጂ.ኦዎች 10 በመቶ ብቻ ከውጭ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያገኙ የሚለው አንቀፅ አገር በቀል ድርጅቶች እንዲዳከሙ የሚያደርግ መሆኑን የሠብዓዊ መብት ተሟጋቾች ያስረዳሉ፡፡ በሠብዓዊ መብት ሥራዎች ላይ የተሠማሩ አገር በቀል ድርጅቶች ከአገር ውስጥ 90 በመቶውን ፈንድ ያግኙ ከተባለ በአገር ውስጥ ምን ያህል ጠንካራ የፋይናንስ አቅም ያለው ድርጅት የእነዚህ ድርጅቶች ወጪ መሸፈን ይችላል? በኢትዮጵያስ ምን ያህል ለኤን.ጂ.ኦ ፈንድ ማድረግ የሚችል ተቋም አለ? የሚለው አጠያያቂ መሆኑን ዓለም አቀፍ ድርጅቶቹ ይጠይቃሉ፡፡ በመሆኑም የአዲሱ ሕግ ረቂቅ ከፀደቀ በኢትዮጵያ ውስጥ እየጠበበ የመጣውን የፖለቲካ መድረክ ይበልጥ የሚያጠብና የሚያጠፋ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ተደርጐበት አሁን የረቀቀው የሲቪል ማኅበራት ሕግ እንዳይፀድቅ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ቢሆንም፣ አዲሱ የፓርላማ ዘመን ግን ይህንን ሕግ እንደሚያፀድቀው ይጠበቃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሕጉ ዙሪያ ከሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን ሕጉም የሲቪል ማኅበራቱ የተሻለ የልማት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የሚረዳ መሆኑ በወቅቱ ገልፀዋል፡፡

የሲቪል ማኅበራቱ እና የኤን.ጂ.ኦዎች ኃላፊዎች በአገር ውስጥ ሕጉ ከመፅደቁ በፊት በራሳቸው ተነሳሽነት ያደረጉት ግፊት መጠነኛ ቢሆንም በዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኩል ግፊት ለማሳደር ተሞክሯል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሠብዓዊ መብት እንደሚጥስ፣ ይህንንም ከማሻሻል ይልቅ ወደባሰ ደረጃ እያደረሰው መሆኑን፤ አሁን ሊፀድቅ የተዘጋጀው ረቂቅ ከፍተኛ የፖለቲካና የሠብዓዊ መብት ቀውስ ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ አገራት ትብብር እንዲያደርጉ እየተጠየቀ ነው፡፡ የኤን.ጂ.ኦና የኢትዮጵያ መንግሥት ግንኙነት እየሻከረና ወደ አለመግባባት እየተቀየረ የመጣው ከምርጫ 97 በኋላ መሆኑንም ዓለም አቀፍ ድርጅቶቹ ይገልፃሉ፡፡

“የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ለሲቪል ማኅበራት ያላቸው ትዕግስት ከምርጫ 97 በኋላ እጅግ ቀጥኗል፡፡ በ2000 ዓ.ም በተካሄደው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ሲቪል ማኅበራት እንዳይታዘቡ ተደርገዋል፡፡ ገዢው ፓርቲም ከ99 በመቶ በላይ በምርጫው አሸንፏል፡፡ ይህ ምርጫ ምን ያህል ትክክለኛ ነው የሚለውን ለማወቅ ሲቪል ማኅበራት ቢሳተፉ የተሻለ ይሆን ነበር” የሚለው አምኒስቲ ኢንተርናሽናል አሁን የወጣው ሕግ ዓለም አቀፍ ተቋማት በዴሞክራሲና በሠብዓዊ መብት እንዳይሳተፉ፤ አገር በቀል ድርጅቶችን ደግሞ አቅማቸው የተገደበ በማድረጉ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ከፍተኛ ጋሬጣ እንደተደቀነበትና ይህ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጥሩ ተሞክሮ እንደማይሆን ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ዋነኛ አጋር የሚባሉትና ከፍተኛውን የውጭ እርዳታ ለኢትዮጵያ የሚሰጡት ዩናይትድ ስቴትስ እና እንግሊዝ ከዓለም አቀፍ የሲቪል ማኅበራት ኅብረት ከፍተኛ ትችት ተሰንዝሮባቸዋል፡፡ አሜሪካና እንግሊዝ የኢትዮጵያ መንግሥት የሠብዓዊ መብት ሪኮርድ የተበላሸ ቢሆንም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዳቸው እንዲሁም ሁለቱ አገራት ለኢትዮጵያ መንግሥት 600 ሚሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ መስጠታቸው እየተከሰተ ያለውን ችግር ሆን ብሎ አለማየት መሆኑን ድርጅቶቹ ያስረዳሉ፡፡

ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሲቪል ማኅበራትን ሕግ ለማሻሻልና የሚያሠራ ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች ሁሉ ባለመስመራቸውና ታላላቅ መንግሥታትም ዝምታ በመምረጣቸው የሲቪል ማኅበራት (ኤን.ጂ.ኦዎች) ሕልውና በኢትዮጵያ አጠያያቂ ደረጃ ላይ መድረሱን ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ይገልፃሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ለአገሪቱ እና ለሕዝቧ ዕድገት የሚበጁትንና ይሆናሉ የሚላቸውን ሕጐች የማውጣት ባለሙሉ መብት ነው፡፡ እስካሁን ባለው የኤን.ጂ.ኦዎች እንቅስቃሴ እንዳልረካ የሚገልፀው የኢትዮጵያ መንግሥት በሥራቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱም እንደሚገኙ ያስረዳል፡፡ ሲቪል ማኅበራቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ሊያጠፋቸው እንደተነሳ ቢገልፁም የኢትዮጵያ መንግሥት ሕጉ የሚያሠራ ነው፤ ሕግን መቀበል ያልፈለጉ አካላት ካልሆኑ በስተቀር ሕጉ የተሻለ ውጤታማ እንዲሆኑ መንገድ የሚከፍት ነው የሚል እምነት እንዳለው ይገልፃል፡፡

በስያሜ፣ በሚያበረክቱት አስተዋፅኦ እና ባላቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ መንግሥትና ኤን.ጂ.ኦዎች አይስማሙም፡፡ ኤን.ጂ.ኦዎች ታላቅ አስተዋፅኦ አበረከትን ሲሉ፤ መንግሥት አንዳንድ ኤን.ጂ.ኦዎች ራሳቸውን መንግሥት እንደሆኑና የማይተካ ሚና ያላቸው አድርገው ይቆጥራሉ ይላል፡፡ የተወሰኑ ማሻሻያዎች ተደርገውበታል የተባለው ረቂቅ ሕግ ሲፀድቅ በሕጉ መሠረት በኢትዮጵያ እንዳይሠሩ የሚታገዱ ኤን.ጂ.ኦዎች ይኖራሉ ብለው ኤን.ጂ.ኦዎቹ ፍራቻቸውን ይገልፃሉ፡፡ ፓርላማውም በዘንድሮው የሥራ ዘመኑ የመጀመሪያ ወራት ረቂቅ ሕጉን ያፀድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
Last Updated ( Sunday, 05 October 2008 )
 
< Prev   Next >