| ጤናችን በእጃችን? |
|
| Sunday, 05 October 2008 | |
|
ከሃሳብ አልተለየንም፡፡ ሰው ነንና እናስባለን፡፡ ለ2001 ዓ.ም ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ መስጠት ከጀመርን ቆይተናል፡፡ እንደ 2000 የሚሆን ከሆነ እንዲያልፈን ጠይቀናል፡፡ ይለፈን ብለናል፡፡ ምክንያቱም የተሻሻለ እንጂ የተወጠረ፣ የናረና የተናወጠ ኑሮ አቅለሽልሾን ነው፡፡
በ2001 ምን በዛ? ብትሉኝ በደላላው ዓይን የጤና ኮሌጆች ማስታወቂያ እላችኋለሁ፡፡ ይህ ሁሉ የጤና ኮሌጅ ከምኔው ተዋለዱ፣ በዙ ተባዙ ሳትሉ አትቀሩም፡፡ ወደፊት ምን እንደታያቸው አላውቅም፡፡ አምራች ሳይሆን ሕሙማን ይበዛሉ የሚል የጠንቋይ ወሬ ሰምተው ይሆናል፡፡ እኛ ደግሞ የምንለው መንግሥታችንን ተማምነን በሽተኛ ትውልድ ሳይሆን ጤናማ ዜጋ እናፈራለን ነው፡፡ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚለፋው፣ የሚሾመውና የሚሸልመው ዜጎች ጤናማ እንዲሆኑ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ጤና ጥበቃ በሽታን ሲያጠፋ፣ የጤና ኮሌጆች በሽታን ሲመኙ ይኖራሉ ማለት ነው? የማይሆን ንጽጽር ነው ብላችሁ ልታልፉትም ትችላላችሁ፡፡ እውነት፣ እውነት ስንነጋገር ግን የሆነች ነገር ብልጭ ትለናለች፡፡ ማን መክሰር ይፈልጋል? ሕሙማን በዝተው ኪሳቸውና ካዝናቸው እንዲወፍር የማይፈልጉ ስንት ይሆናሉ የሚል ቄንጠኛ ጥያቄ ብታነሱ አይገርምም፡፡ ነገርን ነገር እያነሳው መጨዋወት ያለ ነው፡፡ የፊት ለፊቱን እንጂ የጀርባውን ማን ያያል? የኮሌጆቹ ተመራቂዎች (ባለማስታወቂያዎቹ እንደሚሉን ከሆነ) ይፈለጋሉ፡፡ ገበያው አላቸው፡፡ ታማሚ ካለ አዎ ይቀጠራሉ፡፡ ባለቤቶቹም “ሥራ እንዴት ነው?” ሲባሉ “ግሩም ነው” ካሉ ዓላማቸው ትክክል ነው ማለት ነው፡፡ ደላላው ጋ ስትመጡም አካሄዱ አንድ ነው፡፡ ሁሉም ቤት ሠርቶ ከገባ ቤት ፈላጊ አይኖርም፡፡ ሁሉም ባለመኪና ከሆነ የመኪና ድለላ ደከም ይላል፡፡ ይህ ደግሞ በየትኛውም ዓለም ሊቆይ የሚችል አይደለም፡፡ ፍላጎት አለ፡፡ የጤና ኮሌጆቹ እንደዘበት ያነሳነው የማስታወቂያቸው መብዛት ተከትለን ነው፡፡ የዋጋ ንረቱ ሥጋት ሳይለቀን ደግሞ የበሽታ መዓት እንዳይመጣብን ፈርተን ነው፡፡ ለመከራ ያሰበው ቢነግድ አይተርፈው ዓይነት ሆነና ፍርሃት ለቆብናል፡፡ ውኃ ያስፈራናል፣ ገበያው ያስፈራናል፣ ኑሮው ያስፈራናል ወዘተ. ጀግና ነበሩ ከሚባሉ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ጀግንነት መውረስ አልቻልንም፡፡ በጦር፣ በጎራዴ ታንክ የማረኩ አባቶች ወልደውን፣ ኑሯችንን እንኳን በቁጥጥራችን ሥር ማዋል ተስኖናል፡፡ የጀግንነት ነገር እንደየሰው እምነት ነው፡፡ ጠንክሮ ሠርቶ ራሱን ብሎም አገሩን የቀየረም ጀግና ነው፡፡ ለአገሩ ተዋግቶ ጠላት ያንበረከከውም ጀግና ነው፡፡ የጀግንነቱ ደረጃ የኢትዮጵያ የጥራትና የደረጃዎች መዳቢ ባለሥልጣን ይድረስበት፡፡ እኛ የጀግንነቱን ዘርፍ መደርደር ብቻ ነው፡፡ የጤና ኮሌጆቹ የማስታወቂያ ውድድር፣ እኔ እበልጣለሁ ዓይነት ፉክክር ጥሩ ነው፡፡ የማስታወቂያው ፉክክር በተግባር ከዋለ ማድነቅ እንጀምራለን፡፡ “ልዩ መሣሪያ” አስመጥተናል ብለውን “አርተፊሻል” ወይም የተውሶ እንዳይሆን የጤና አምላክ ይርዳን፡፡ አስመርቀን እናወጣቸዋለን ያሏቸው “የሰለጠኑ ባለሙያዎችም” እንዳፋቸው ያድርግልን፡፡ ታፋ ላይ መውጋት ሲገባቸው ሆድ የሚወጉ እንዳይሆኑ እንመኛለን፡፡ በሥነ ምግባሩም ደረጃ የተጠበቁ እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡ የአሁኖቹን “የጤና ባለሙያዎች” ድርጊት በመኮረጅ አበሳችንን እንዳያስቆጥሩን ከመመኘት ሌላ የምናደርገው የለም፡፡ የእኛ አገር ኩረጃ ፈር የለቀቀ ነውና በዚህም እንሰጋለን፡፡ እግርና እጅ የማይለይ ሐኪም ባየንበት፣ ሐኪም ሲባል እንደነግጣለን፡፡ ምርመራ ሲባል እንጠረጥራለን፡፡ ይህንን ሥጋታችንን፣ ይህንን ጥርጣሬያችንን የሚያውቁ ኮሌጆች በማስታወቂያ “አይዞአችሁ” ይሉናል፡፡ እነርሱ ያሰለጠኗቸው የጤና ባለሙያዎች የተመደቡበትን በማሳየት የምስክሮች ቃል ያሰሙናል፡፡ አስመስካሪውና መስካሪው ግንኙነታቸው የሙያ ፍቅር ከሆነ ምንም አይደለም፡፡ የእከክልኝ ልከክልህ ከሆነ ግን ይኼም አስፈሪ ነው፡፡ የሚሆነውን ወደፊት እናያለን፡፡ ጥሩ ሊሠሩ ቃል ገብተው፣ ቃላቸውን ካፈረሱ መተዛዘባችን አይቀርም፡፡ ለነገሩ እስካሁን ድረስ ሲወቀሱ የነበሩትስ ባለሙያዎች እጃቸውን ሰቅለው ቃል ሲገቡ ያየናቸው አልነበሩም ወይ? ደላላው አምበርብር ምን ይታይሃል? ብትሉኝ “የተደበላለቀ ነገር” መልሴ፡፡ ቅቤ ጠባሽ ይበዛል፡፡ ያልሆነውንና የማይሆነውን ለመሆን ሲጣጣር ይታያል፡፡ ዞር ዞር ብላችሁ ስታዩ እንደ እኔው የሚደበላለቅባችሁ ይመስለኛል፡፡ በአንድ በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ ለወገኔ ሕክምና እሰጣለሁ፣ አስተምራለሁ እያለ፣ በሌላ በኩል ኪስን በኦፕራሲዮን ሞልቼ እገኛለሁ ያለ ጨካኝ ትታዘባላችሁ፡፡ አንዳንዶቹ የጤና ኮሌጆቻችን ከሰው ቀዶ ሕክምና የበለጠ ኪስን ቀዶ በማከም፣ ወይም ቀድዶ ከጥቅም ውጪ በማድረግ ይታማሉ፡፡ ማስታወቂያው ሌላ፣ ተግባር ሌላ ሲሆን ያናድዳል፡፡ መናደድ ሲበዛ ደግሞ ከቡሎኖች አንዱ ወይም ሁለቱ መታመማቸው አይቀርም፡፡ ጤናችንን ለመጠበቅ ኃላፊነት አለብን የሚሉ ወገኖች የበለጠ ጤናችንን፣ ኪሣችንን እንዳያወሳስቡብን የጤና አምላክ እንዲተባበረን እንጠይቃለን፡፡ እኛም የዋዞች አይደለንም፡፡ “ጠርጥር ካደረ ገንፎ አይጠፋም ስንጥር” እየተባለ ምሣሌ በሚነገርበት አገር ስለተወለድን እንጠረጥራለን፡፡ የጤና ኮሌጆች “እኔ እበልጣለሁ” የፉክክር ማስታወቂያ ስንሰማ እንጠረጥራለን፡፡ እንፈራለን፡፡ ለማንኛውም ደህና ማሰብ፣ ደህና መመኘት ይሻላል፡፡ እንደ አንድ ሰሞን በስሜት ተውጠን የጦር መሣሪያዎቻችን ወደ አካፋና ዶማ እንቀይራለን እንዳልነው አይሆንም፡፡ የጤና ኮሌጆች መብዛት የለባቸውም፣ መብዛታቸው አሉታዊ ነው አንልም፡፡ ሕዝቡ በመጽሐፉ ታዝዣለሁ ብሎ ያለ ቅጥ እየተባዛ ነው፡፡ የተባዛው ሁሉ ጤና ይሆናል አይባልም፡፡ እንደ ፍጥርጥሩ የሚታመም ይኖራል፡፡ ያለዚያማ ሞት አይኖርም ነበር፡፡ የታመመ ሁሉ እንዳይሞት የጤና ኮሌጆቻችን ድርሻቸውን መወጣት ይችላሉ፡፡ የታመመውን ለማዳን የሚጥሩ እንዳሉ ሁሉ፣ የታመመን ሞት የሚያፋጥኑም ሞልተዋል፡፡ ዓለም የተሠራችው በዚህ ሁኔታ ነውና ምን ይገርማል እንደምትሉ ይገባኛል፡፡ ጸሎታችን ሞትን የሚያፋጥኑ ሳይሆን ከሕመም የሚፈውሱትን እንዲያዝልን ነው፡፡ ጤና ኮሌጆቻችን ለጥራት ሲወዳደሩ እንደግፋለን፡፡ ለበጎ ተግባር ሲፎካከሩ እናደንቃለን፡፡ ለኪስ ኦፕራሲዮን ሲወዳደሩ ድምፅ ከመስጠት እንቆጠባለን፡፡ ለመታለል ሲሮጡ እንቃወማለን፡፡ እኛም ምዕመናን ጊዜውን አይተን የራሳችን እርምጃ መውሰድ ይጠበቅብናል፡፡ ለሌሎች ሲሳይ ከመሆን የጥንቱ የጠዋቱን “ኋላ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” የሚለው የጤና መርሕ ልናከብር የግድ ነው፡፡ ደህና ሁኑ፡፡ ሰላም! |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |