Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ርካሽ ግን አሳሳቢ ምርቶች
ርካሽ ግን አሳሳቢ ምርቶች E-mail
Sunday, 05 October 2008
በናታን ዳዊት

ለተለያዩ አገልግሎቶች የምንጠቀማቸው ሸቀጣሸቀጦችና ሌሎች ምርቶች አብዛኛው ከውጭ የሚገቡ ናቸው፡፡ በቤት ውስጥ ከምንጠቀምባቸው ትናንሽ ቁሳቀሶች ጀምሮ እስከትላልቅ ማሽነሪዎች ድረስ ያሉ ምርቶች ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ የውጭ ስሪቶች ስለመሆናቸው ያለንበትን አካባቢ መቃኘት ብቻ ይበቃል፡፡
ሌላው ቀርቶ በየግል ከምንለብሳቸውና ከምንጫማው አልባሳትና ጫማዎች ውስጥ ብዙው እጅ ከውጭ የመጣ ወይም ከውጭ በመጣ ጥሬ እቃ የተሠራ ስለመሆኑ እያንዳንዳችን ምስክር ልንሆን እንችላለን፡፡

ባለንበት ቦታ ቆም ብለን አካባቢያችንን ስንቃኝ በኛ አገር የተመረተ እቃ፣ ቁሳቁስ ወይም ሌላ ምርት ለማግኘት አይናችን መድከሙ አልቀረም፡፡

ይህ እውነት የሚያመላክተን አገራችን ምን ያህል የውጭ እቃዎች ሸማች መሆንዋንና ለዚህም ሸመታ የምታወጣው ወጪ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ደግሞ ወደ ውጭ ከምንልከው ምርታችን የምናገኘው የውጭ ምንዛሪ ለነዳጅ ግዥ ብቻ የሚውል መሆኑንም መዘንጋት የለብንም፡፡

ስለዚህ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጅግ የተጣበበ መሆኑን ያሳየናል፡፡ የሚያሳዝነው ግን በገፍ የሚገቡት የውጪ እቃዎች ገበያውን ማጨናነቃቸው ብቻ ሳይሆን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስመ የውጭ እቃ ሸማቹ እየደረሰበት ያለው በደልም እየጐላ መምጣቱ ነው፡፡

ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰማው የሸማቾች ሮሮ የሚያመለክተው ጥራታቸውን ያልጠበቁ ምርቶች ገበያ ውስጥ በሰፊው መገኘታቸው አንዱ ሲሆን ሌላው ደግሞ ጥሩ ተብለው በሚታወቁ የንግድ ምልክቶች ስም ደረጃቸው የወረደ ምርቶች ሸማቹ እንዲገዛ መደረጉ ነው፡፡

ለዚህ አሳሳቢ ችግር መባባስ እንደምክንያት የሚቆጠሩት ደግሞ ኃላፊነት አንዳንድ ነጋዴዎች እንደሆነ ደግሞ መጠራጠር አይቻልም፡፡

እነዚህ ነጋዴዎች ውጭ ካሉ ኩባንያዎች ጋር በመመሳጠር በርካሽ ዋጋ እቃ በመግዛት የሚፈልጉትን የንግድ ምልክት በማስቀረፅ ለሸማቹ ያቀርባሉ፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ ሥራ ደግሞ ተመቻችተው የሚጠብቁ የውጭ ኩባንያዎች በጋራ መገኘታቸው ነጋዴዎቹን እንደ ልብ እንዲሠሩ አድርጓቸዋል፡፡

ከኤሌክትሮኒክስ ምርት ጀምሮ እንደ ሽቶ አልባሳትና የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦች ጭምር አስመስለው ከሚያመርቱ ኩባንያዎች ጋር በመደራደር በርካሽ ዋጋ የሚሰበስቡትና በሚቸረችሩት እቃ ሸማቹን እያሳሳቱትም ይገኛሉ፡፡

እነዚህ ምርቶች የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ በመሆኑ የአገልግሎት ዘመናቸው የዚያኑ ያህል ትንሽ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት የውጭ ምንዛሪ ተከፍሎባቸው መሆኑን ስናስብ ደግሞ ጉዳቱ ምን ያህል እጥፍ ድርብ እንደሆነ ያመለክተናል፡፡

በአሁኑ ወቅት የብዙ ምርቶች የጥራት ደረጃ ዝቅተኛ መሆን እና ጥቂት የማይባሉ ምርቶችም በተመሳሳይ መልኩ ገበያ ውስጥ መቅረብ ሸማቹ አማራጭ አጥቶ የግድ እነዚሁኑ ምርቶች እንዲሸምት እያስገደደ መምጣቱም ትልቅ ችግር እየሆነ ነው፡፡

በእርግጥ ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚፈልገውን ምርት ቢያገኝ የማይከፋ ቢሆንም በርካሽ ዋጋ ስለቀረበ ብቻ የሸማቹን ፍላጐት ማሟላት አይቻልም፡፡

እንዲህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች እየሰፉ በመጣ ቁጥር ደግሞ ጉዳቱ ሸማችን ብቻ ሳይሆን አገርንም የሚጐዳ እየሆነ መምጣቱ አይቀርምና ለሸማቹ የሚቀርቡ ማናቸውም ምርቶች የጥራትና ደረጃቸው በደንብ መፈተሽ ይኖርባቸዋል፡፡

መንግሥትም የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶች እንዳይገቡ በመከላከሉ ረገድ የሚኖረው ሚና ትልቅ መሆኑ ቢታመንም የራስን ከርስ ለመሙላት ሲባል ብቻ ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ ምርቶችን የሚያስገቡ አንዳንድ ነጋዴዎችም ወደ ህሊናቸው ተመልሰው አገርን ወገንን የሚጠቅም ሥራ መስራቱን ቢያስቀድሙ ትልቁን ሥጋት መቀነስ ይቻላል፡፡
 
< Prev   Next >