| አፍሪካን ለመርዳት በዓመት 720... |
|
| Sunday, 05 October 2008 | |
|
አፍሪካን ለመርዳት በዓመት 720 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል
በብርሃኑ ፈቃደ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰቱት የምግብና የነዳጅ ዋጋ ንረት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጦች የምግብ ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር የአፍሪካ አገሮችን እድገት ወደ ኋላ እየጐተቱ ያሉትን ችግሮች ለመድፈንና አፍሪካን ለመርዳት በዓመት 720 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ባንኪሙን ገለፁ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ሚ/ር ባንኪሙን እንዳሉት ለአፍሪካ በዓመት የተመደበው ገንዘብ በቅርቡ የአሜሪካውን ዎልስትሪት አክሲዮን ገበያን ለመደጐም ከተመደበው የ700 ቢሊዮን ብር በሶስት እጥፍ ያነሰ መሆኑን ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ዓመታዊው በተመድ የመሪዎች ስብሰባ ላይ አስታውቀዋል፡፡ በኒውዮርክ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሚ/ር ጄፍሪ ሴሽስ በበኩላቸው ለአፍሪካ የተጠየቀው ገንዘብ ከአፍሪካ ችግሮች አንፃር በቂ አይደለም፡፡ ሆኖም የአሜሪካ ኮንግሬስ ለዋልስትሪት ያፀደቀው 10 ትራሊዮን ገደማ የደረሰው ገንዘብ (በኢትዮጵያ ብር) ድንገተኛ አደጋ በሚያጋጥም ጊዜ ገንዘቡ መኖሩን ያሳያል ብለዋል፡፡ በመሪዎቹ ስብሰባ ወቅት አፍሪካውያን እንደተለመደው ቃል የተገቡላቸው የእርዳታ ስምምነቶች እንዲተገበሩላቸው አሳስበዋል፡፡ የታንዛንያው ፕሬዚዳንት ሚ/ር ጀካያ ኪክዌቴ እንዳሉት ባደጉ አገሮች የተፈጠረው የገንዘብ ቀውስ ቢያሳስባቸውም የበለፀጉ አገሮች አፍሪካን ለመርዳት የገቡትን ቃል ሊያከብሩ ይገባል፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት የሆኑት ሚ/ር ዶናልድ ካቤሩካ በበኩላቸው ዝግ እያለ ያለው የምዕራባውያን ኢኮኖሚ ለአፍሪካ ምርቶች ፍላጐት እንዲቀንስ ምክንያት ሊሆን ይችላል ባይ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ምዕራባውያንና ቻይና አፍሪካን በተመለከተ በተዘዋዋሪ የተፋጠጡበት ሁኔታ መፈጠሩን የሮይተርስ ዘገባ ያስረዳል፡፡ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ሚ/ር ሳርኰዚ አውሮፓና አፍሪካ የእርዳታውን ፍሰት ለማጠንከር መስማማታቸው አውስተው “ከሌላ አህጉር ለጋሾች ጋር መተባበር ለምን ያስፈልጋል?” የሚል ጥያቄ ቢያነሱም ቻይናን በይፋ አልጠቀሱም፡፡ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚ/ር ያንግ ጄይሺ አስረግጠው እንደተናገሩት የአፍሪካውያንን ሉዓላዊነት በማክበር ለመሠረታዊና የረጅም ጊዜ ፍላጐቶቻቸው መሳካት ያለሰለሰ ትብብር ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡ የረጅም ጊዜ ልማትን ለማረጋገጥ አፍሪካውያን በራሳቸው አቅም ላይ ሊመረኮዙ ይገባል ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቻይና በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤናና በንፁህ ኃይል አቅርቦት ዙሪያ ከአፍሪካ ጋር አጋር ሆና ትሠራለች፡፡ ሚ/ር ሳርኮዚ በኢኮኖሚ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ያሉ አገሮች (ቻይናን ሳይጠቅሱ) ለአፍሪካ የሚሰጡት ብድር በኋላ ለመመለስ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ለአፍሪካ የተመደበው ገንዘብ ከፍተኛ መሆኑን ቢገልፁም ዋና ፀሐፊው ባንኪሙን የበለፀጉ አገሮች ለግብርና ዘርፍ ብቻ 2.7 ትሪሊዮን ብር የሚገመት ድጐማ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል በቅርቡ የዓለም መገናኛ ብዙሃን እንደዋና የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ የሰነበተው የገንዘብ ቀውስ አገራችንን ይመለከት እንደሆነ ለማወቅ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን አነጋግረናል፡፡ ለጋዜጣችን ቅርበት ያላቸው ባለሙያ እንደገለፁት አገሪቱ በገንዘብ ረገድ ዓለም አቀፍ ትስስር የላትም ሊባል በሚችል መልኩ የሚገኝ በመሆኑ በባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ላይ የሚደርስ የገንዘብ ቀውስ ሊኖር አይችልም፡፡ የገንዘብ ቀውሱ በተለይ የአሜሪካ ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ከቻለ ግን በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያንም ሊነካካ እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |