| መንግሥት በሊዝ የሚሸጠው መሬት... |
|
| Sunday, 05 October 2008 | |
|
መንግሥት በሊዝ የሚሸጠው መሬት በዓመት እንኳ ከሦስት ሺህ ግለሰቦች አይበልጥም
አቶ እስራኤል ካሣ የአፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በቅርቡ አዲስ ከኦፕሬቲቭ ባንክ ለመመስረት ሥራ የጀመረው የአዲስ አበባ የህብረት ሥራ ማህበራት ዩኒየን ቦርድ ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስታስቲክስ የመጀመሪያ ዲግሪ ይዘው በአሜሪካ ኮምፒዩተር ሳይንስ ተምረዋል፡፡ በብሔራዊ ባንክ ውስጥ አገልግለዋል፡፡ በኢኮኖሚያዊ፣ በኮፕሬቲቭ ባንክና በፋይናንስ ጉዳዮች ዙሪያ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት በተለየ ምን መደረግ አለበት? አቶ እስራኤል፡- ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ማምጣት የሚያስችሉ አምስት የመፍትሔ አቅጣጫዎች እንዳለ አስባለሁ፡፡ የመጀሪመያው የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ነው፡፡ ይህም ቀና አመለካከት የያዘ፣ አገራዊና አህጉራዊ ራዕይ ያለው ሕብረተሰብ መፍጠር ሥራ መፍጠር የሚችል እና የጋራ አመለካከት የያዘ ዜጋን ማፍራት መቻል ነው፡፡ ሪፖርተር፡- እንደዚህ ያለው ባለ ራዕይ እንዴት ነው የሚፈጠረው? አቶ እስራኤል፡- በሁለት መንገድ መፍጠር ይቻላል፡፡ አንደኛው ሚዲያው ይህንን ራዕይ እንዲያስተጋባ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው የትምህርት ሥርዓቱን በዚህ አቅጣጫ መቅረፅ መቻል ነው፡፡ በዚህ መንገድ ችግር ፈቺ፣ ተሳታፊነት ያለውና አዲስ ሃሳብ ማመንጨት የሚችል ሕብረተሰብ መፍጠር ይቻላል፡፡ በተለይ የግልና የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሥርዓተ ትምህርት ቀረፃውን በማሻሻል ለጥትና ምርምር ምቹ መንገዶችን መፍጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- ሁለተኛ የመፍትሔ አቅጣጫ ሊሆን ይገባል የሚሉት ምንድነው? አቶ እስራኤል፡- ሁለተኛው አቅጣጫ የአደረጃጀት ችግርን መቅረፍ መቻል ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት በተጠናና የሌሎችን አገሮች ልምድ ለመውሰድ አደረጃጀታቸውን ማሻሻል ይኖርባቸዋል፡፡ አደረጃጀትን ማሻሻል ሲባል አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ተቋማዊም ሆነ ሥልጣን የያዘው ማዕከላዊነትን የጠበቀ አደረጃጀት መፍጠር መቻል ነው፡፡ ሆኖም የሃሳብ ግጭት፣ ክርክሮች እና ውይይቶች ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የኢኮኖሚ ድርጅቶችን በተመለከተ በተለይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከፍተኛ ታክስ ከፋዮች ናቸው በአክሲዮን የተደራጁ ቢሆኑም የአክሲዮን ባለድርሻ ያልሆነ ሰው የቦርድ አባል ሆኖ ይሠራል፡፡ መሆን የነበረበት ባለ ሙሉ ድርሻ ሆኖ ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሠራር መፍጠር ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ጥቅሙ ምንድን ነው? አቶ እስራኤል፡- የቦርድ አባል የሚሆነው ሰው የአክሲዮን ባለድርሻ ቢኖረው ለሥራ የበለጠ ይነሳሳል፡፡ ጥቅም ያገኝበታል፡፡ የሚመራው ድርጅት ትርፋማ እንዲሆን ከልቡ የሚሠራበት መንገድ ይፈጠራል፡፡ ሪፖርተር፡- የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ከግለሰቦች ይልቅ የአክሲዮን ማህበራት እንዲገዟቸው ቢደረግ ጥቅሙ ሰፊ ነው የሚሉ አሉ? አቶ እስራኤል፡- ትክክል ነው፡፡ በአገሪቱ የአክሲዮን ገበያ የለም፡፡ ይሄ አንዱ የአደረጃጀት ችግር ለመሆኑ መሻሻል ይገባዋል፡፡ በአክሰዮን ብዙ ድርጅቶችን ማቋቋም ይቻላል፡፡ ያሉትም እንዲያድጉ በር ይከፍታል፡፡ ሪፖርተር፡- ብዙ የልማት ድርጅቶች ለበርካታ ጊዜ ጨረታ ወጥቶባቸው ያልተሸጡ አሉ፡፡ ከግለሰብ ይልቅ በአክሱዮን እንዲሸጡ ማድረግ አይቻልም? አቶ እስራኤል፡- ይቻላል፡፡ ባንኮችና ሌሎች ድርጅቶች እንደሚያደርጉት የልማት ድርጅቶቹንም ለመነሻ የሚሆነውን የአክሲዮን ዋጋ ለሕዝቡ በማሳወቅ የራሱ የሕዝቡ ንብረቶች እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል፡፡ ተገቢም ነው፡፡ በማህበራዊው መስክም ቢሆን አደረጃጀትን በተመለከተ እድሮችና የሕብረት ሥራ በመሥራት ከፍተኛ ሚና ሊወጡ ይችላሉ፡፡ የከተማ አስተዳደርም ቢሆን አደረጃጀት ላይ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ከተሞች ልማትን ለማምጣት የሚያስችል፣ ሕዝቡ ተሳታፊ የሚሆንበትና ማዕከላዊ ቋንቋ (የፌዴራል የሥራ ቋንቋ) በሁሉም ከተሞች እንዲስፋፋ መደረግ አለበት፡፡ አብዛኞቹ ከተሞች ውስጥ ከ10 እስከ 20 በመቶው ቀድሞ የነበረ ኗሪ ሲኖራቸው 80 በመቶው ከሌሎች አካባቢና ከገጠር የሚመጣ ሕብረተሰብ ነው የሚኖርባቸው፡፡ በተጨማሪም ከየብሔረሰቡ የተውጣጣ ሕዝብ የሚኖርባቸው በመሆኑ የፌዴራልና የክልሉ ቋንቋዎችን እንደ አስፈላጊነቱ መጠቀም ይቻላል፡፡ ይህ በሁሉም ከተሞች ሊኖር የሚገባ ነው፡፡ ነገር ግን የሕዝቡን ፍላጐት መሠረት ማድረግ ግድ ይላሉ፡፡ ሦስተኛው የመፍትሔ አቅጣጫ የመሬት፣ የፋይናንስና የሕግ ተቋሞች ለሥራ ፈጣሪዎች በነፃ ገበያ መርህ መሠረት ምቹ አሠራሮች መዘርጋት አለባቸው፡፡ ለአብነት የሕግ ተቋማትን ብናይ አንድን ጉዳይ ከአምስት እስከ ስምንት ዓመት በሚደርስ ጊዜ ነው እልባት የሚያበጁለት፡፡ ይሄ በቀልጣፋና ጊዜ ቆጣቢ በሆነ አደረጃጀት ሊቀየር ይገባዋል፡፡ የመሬት አሠራር አሁንም በነፃ ገበያ ማዕቀፍ ውስጥ አይደለም፡፡ በገዥና ሻጭ መካከል ውድድር ሊኖር ይገባል፡፡ ዋጋ የሚወስነው በአቅርቦትና ፍላጐት ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ መሬትን በሚመለከት አቅራቢው መንግሥት ብቻ በመሆኑ የሞኖፖል አሠራር ነው ያለው፡፡ በዋናነት የመሬት ችግር በከተሞች አካባቢ የሚስተዋል ነው፡፡ ሕብረተሰቡ በቀላሉ መሬት አግኝቶ፣ ቤት ሠርቶ መኖር የሚችልበት አሠራር አይደለም ያለው፡፡ ግለሰቦችም መሬትን በመሸጥና በመለወጡ እንቅስቃሴ ላይ ቢሳተፉ የመንግሥት ገቢ ያድጋል፣ ገዢዎችም በዋጋ ረገድ ጫና አይደርስባቸውም፡፡ አሁን ባለው አሠራር መንግሥት በሊዝ የሚሸጠው መሬት ዓመት እንኳ ከሦስት ሺህ ግለሰቦች አይበልጥም፡፡ ሪፖርተር፡- በአሁን ወቅት የሚታየው የግል ባንኮች እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? አቶ እስራኤል፡- ባንኮች ንግድ ላይ የተመረኮዙ ናቸው፡፡ የተለየ ነገር የላቸውም፡፡ አሁን መምጣት ያለበት የተለየ አገልግሎትና ጠቀሜታ ያለው ባንክ ነው፡፡ በቅርቡ የሚቋቋመው የሕብረት ሥራ ባንክ ለየት ያለ ሐሳብ ይዞ ይመጣል የሚል ግምት አለኝ፡፡ አራተኛው የሕብረት ሥራ ማህበራት አንዳንዴም የሙያ ማህበራት ከመንግሥት ልዩ ድጋፍ የሚያገኙበት መንገድ ሊኖር ይገባል፡፡ ብዙ አገሮች ለውጥ ያመጡት ለሕብረት ሥራ ማህበራት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ስለዚህ ከመንግሥት የሕግ፣ የቦታ፣ የገንዘብና የሙያና የሌሎችም ድጋፍ ቢደረግላቸው ለውጥ ማምጣት ይችላሉ፡፡ እንደ ካናዳ፣ ጃፓን፣ ኔዘርላንድና እንግሊዝ በመሳሰሉ አገሮች ሕዝቡ ተደራጅቶ የራሱን ምርት በማምረት እየተጠቀመ ይገኛል፡፡ አሜሪካን አገር ገጠሩ ሁሉ በኤሌክትሪክ መብራት የተዳረሰው የኤሌክትሪክ ሕብረት ሥራ ማህበርት በመኖራቸው ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በአገራችን ስቶክ ማርኬት የለም ይህ ባለመኖሩ የፈጠረው ችግር አለ? አቶ እስራኤል፡- በፋይናንስ እንቅስቃሴውን ስቶክ ማርኬት መኖር አለበት፡፡ ስቶክ ማርኬት የሌለበት አገር እንዴት እንደሚያድግ እኔ አይገባኝም፡፡ አብዛኛዎቹ አገሮች ለእድገታቸው ዋነኛ መሠረት የሆናቸው ስቶክ ማርኬት ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለእስቶክ ማርኬት መመስረት በሩን ሊከፍት ይገባል አለበት፡፡ ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም ስቶክ ማርኬት ለመጀመር በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በኩል የተለያዩ ስራዎች እየተሠሩ ነበር፡፡ አሁን ምን ደረጃ ላይ ደርሷል? አቶ እስራኤል፡- በወቅቱ ተሞከረ ጥናት ተጠና ከዚያ በኋላ የደረሰበትን ደረጃ አላውቅም፡፡ ሪፖርተር፡- ስቶክ ማርኬትን ለማስጀመር ምን መደረግ አለበት? አቶ እስራኤል፡- መንግሥት ስቶክ ኤክስጀንጅን አዋጅ ማውጣት ነው፡፡ ከተፈለገ እንደ ህንድ ካሉ አገሮች ልምድ መውሰድ ይችላል፡፡ በአፍሪካም በስቶክ ኤክስጀንጅ ሥራ ብዙ የሠሩ አገሮች አሉ ከነሱም ልምድ ወስዶ አዋጁ የሚተገበርበትን እርምጃ መውሰድ ይችላል፡፡ ሪፖርተር፡- የዚህ የስቶክ ኤክስቼንጅ ዋነኛ ጥቅሙ ምንድነው? አቶ እስራኤል፡- ለካፒታል ሞብላይዜሽን ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፡፡ አንድ ሰው የ500 ብር የ3000 ብር አክሲዮን መግዛት ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው ጥሩ ሃሳብ ኖሮት አክሲዮን ላደራጅ ቢል በየቤቱ እየሄደ ከመለመን ይልቅ የተደራጀ ካፒታል ሊያገኝ ይችላል በቀላሉም ካፒታል ማግኘት ይችላል፡፡ ሪፖርተር፡- በእርሶ እምነት አሁን ያሉት የአገሪቱ የፋይናንስ ሴክቸሮች ወይም ባንኮች እንቅስቃሴን እንዴት ይመለከቱታል? አቶ እስራኤል፡- አሁን ያሉት ባንኮች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኮፒዎች ናቸው፡፡ ምንም አዲስ ነገር የለም፡፡ ለየት ያለ ባንክ መውጣት አለበት፡፡ ሪፖርተር፡- ለየት ያለ ሲባል? አቶ እስራኤል፡- ለየት ያለ ሃሳብ ይዞ የሚሄድ ስንል እንደ ኮፕሬቲቭ ዓይነት ባንኮች ማቋቋም አንዱ ነው፡፡ እኛም በቅርቡ የምናቋቁመው የኮፕሬኤቲቭ ባንክ ለየት ያለ ሃሳብ ይዞ ይመጣል የሚል ሃሳብ አለን፡፡ ለብዙ አገራት ለውጥ ምክንያት የሆኑት የህብረት ሥራ ማህበራት ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ የህብረት ሥራ ማህበራት ከመንግሥት ልዩ ድጋፍ ቢደረግላቸው ብዙ ለውጥ ሊመጡ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ የካናዳ ኔዘርላንድ፣ እንግሊዝ፣ ጃፓን ጥሩ ምሣሌዎች ናቸው፡፡ ለምሣሌ አንድ ኢንቨስተር ከብት ማደለብ ላይ ቢገባ ለራሱ ጥቅም ነው የሚያስበው፡፡ የአገር ውስጥ ገብያ ጥሩ ከሆነ ለአገር ውስጥ ይሰጣል፡፡ የውጭ ገበያ ከሆነ ለውጭ ይሸጣል፡፡ ግን የህብረት ሥራ ማህበራት ወደ ማምረቱ ከሄዱ ለውጭም አይልኩ መጀመሪያ ራሳቸውን ነው የሚመግቡት፡፡ ስለዚህ የህብረት ሥራ ማህበራት መኖር ብዙ ጥቅም አለው፡፡ ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ያለው የአገራችን የህብረት ሥራ ማህበራት የሥራ እንቅስቃሴ ደረጃ ምን ያህል ነው? አቶ እስራኤል፡- ጥሩ ነው፡፡ ግን ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ ለምሣሌ በንጉሡ ጊዜ ኬንያውያን ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው ነበር በህብረት ሥራ ማህበራት ዙሪያ ልምድ ይወስዱ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ ትላልቅ የህብረት ሥራ ማህበራት ነበሩ፡፡ አገር አቀፍ ፌዴሬሽን ጭምር ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የለም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ውክልና አለመኖሩ በዚህ ዘርፍ ብዙ መሠራት እንዳለበት ያሳያል፡፡ በአንፃሩ ግን ኬንያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የሚታወቁ ትላልቅ ባንኮች ትላልቅ ህንፃዎች የኮፕሬቲሶች ናቸው፡፡ ሪፖርተር፡- ምን የተለየ ነገር ታመጣላችሁ? አቶ እስራኤል፡- የኮፕሬቲቭ ባንክ የሚለየው ሁለት ዓይነት ዘርፍ አለ፡፡ አንደኛው አሁን እንዳሉት የንግድ ባንኮች የንግድ ባንክ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ኮንሲውመሩን መሠረት ያደረገ የብድር ስርዓት ይፈጥራል፡፡ ለምሣሌ ቤት ለመግዛት ለሚፈልጉ የ20ና የ30 ዓመት ብድር ይሰጣል፡፡ መኪና፣ የቤት እቃ”“ ወዘተ የብድር ስርዓት ይፈጥራል፡፡ ምክንያቱም መስሪያ ቤቱ አባል የሆኑ ሰዎች ከደሞዛቸው ይቆረጣል ማለት ነው፡፡ ሪፖርተር፡- የሌሎች አገሮች ኮኦፕሬቲቭ ባንኮች ልምድ ምን ያሳያል፡፡ አቶ እስራኤል፡- ለምሣሌ የኔዘርላንድን ልምድ ብንወስድ ራሱ ባንክ 5 ሚሊዮን አባል ያለው፡፡ የኮፕሬቲቭ ባንክ ነው፡፡ ስለዚህ 5 ሚሊዮኑም የዚህ ባንክ ባለአክሲዮን ናቸው፡፡ ግን 500 ተቋማት ናቸው በባንኩ የሚወከሉት፡፡ ስለዚህ ይህ ባንክ 500 ለሚሆኑ ኩባንያዎች ላይ ኢንቨስት ያደርጋል፡፡ ሪፖርተር፡- የግል የትምህርት ተቋማት በአገሪቱ ውስጥ ያላቸው አስተዋፅኦ ምን ድረስ ነው? አቶ እስራኤል፡- የግል ተቋማት ከፍተኛ የሆኑ አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው፡፡ ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በግል ተቋማት ውስጥ እየተማሩ ነው፡፡ እነዚህ የግል ተቋማት መንግሥትን እየደገፉ ነው፡፡ ታክስ እየከፈሉ ነው፡፡ ብዙ ወጣቶች ወደ ወንጀልና ወደ ሌላ እንዳይሄዱ ወደ ልማት እንዲሄዱ ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ እነዚህ የግል ተቋማት እንዲደራጁና እንዲጠናከሩ ማድረግ ይገባል፡፡ እንዲደራጁ ስል የተመቻቸ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ለማለት ነው፡፡ አንዳንድ አገሮች ቦታ ከመስጠት አንስቶ የሚፈልጉትን ዓይነት ህንፃ ገንብቶ እስከመስጠት የሚደርሱ አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት እገዛዎች፣ ብዙ ጥቅም አላቸው፡፡ ለምሣሌ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ በመንግሥት በጀት ነው የሚተዳደረው፡፡ 5 ሺህ ተማሪ ቢኖረው መቶ ሚሊዮን ብር ይመድባል፡፡ የግል ዩኒቨርሲቲ ግን በራሱ በጀት ነው የሚተዳደረው፡፡ ስለዚህ የግል ኮሌጆችን ዩኒቨርሲቲዎች መኖር የመንግሥትን በጀት በመቀነሱም ረገድ ትልቅ ጥቅም ይኖራቸዋል፡፡ የውድድር ስሜትም በመፍጠር የግል ተቋማት ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ በዚህ የውድድር መንፈስ ጥራት ያላቸው ይቀጥላሉ የሌላቸው ሊቆሙ ይችላሉ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |