| እነ ሐይሌ በአሠላ ከ50 ሚሊዮን ብር... |
|
| Sunday, 05 October 2008 | |
![]() እነ ሐይሌ በአሠላ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ ግንባታዎችን አካሂደዋልበዳዊት ታዬ አትሌት ሃይሌ ገብረሥላሴን ጨምሮ አራት አትሌቶች ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ ግንባታዎች በአሠላ ከተማ ማካሄዳቸውንና ታዋቂ ያልሆኑ አትሌቶችም አሠላ ውስጥ በተለያዩ ኢንቨስትመንት መስኮች ውስጥ እየተሳተፉ መሆኑ ተገለፀ፡፡ የአሠላ ከተማ ከንቲባ አቶ ጀማል አሊ እንደገለፁት በአሁኑ ጊዜ በአሠላ ከተማ ውስጥ ኢንቨስት በማድረግ ላይ ካሉት ታዋቂ አትሌቶች መካከል አትሌት ሃይሌ ገብረሥላሴ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሣ በቀለና አይሻ ጊጊ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተለያዩ ግንባታዎችን አካሂደዋል፡፡ በአሠላ ከተማ ውስጥ ሃይሌ ገብረሥላሴ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ሁለት ህንፃዎች መገንባቱን ያስታወሱት ከንቲባው ቀነኒሣ በቀለ ከሦስት ቀናት በፊት አገልግሎት መስጠት የጀመረውን ለሆቴልና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ባለአራት ፎቅ ህንፃ ማስመረቅ ችሏል፡፡ ቀነኒሣ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፀው ይህ ህንፃ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ፈጅቶበታል፤ ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን አሠላ ላይ ለማካሄድ እቅድ እንዳለውም ገል”ል፡፡ በአሠላ ከተማ ውስጥ የቀድሞውን የከተማ አውቶብስ መናኸሪያ ቦታ የተረከበችው አትሌት ደራርቱ ቱሉም በስሟ የሰየመችውን ሆቴልና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጥ ህንፃ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ አስገንብታለች፡፡ ተጨማሪ ሥራዎችን ለመሥራት ሃሳብ አለኝ ያለችው ደራርቱ ከአሠላ ውጪ በተወለደችበት አካባቢ እሷን ጨምሮ ሌሎች አትሌቶች የተለያዩ ግንባታዎችን ለማከናወን እቅድ መያዝዋን ገልፃ በግሏ በቆጂ ውስጥ ክሊኒክ ለመገራባት በዝግጅት ላይ እንደሆነችም አስታውሳለች፡፡ በአሠላ አካባቢ ኢንቨስት ለማድረግ የጠየቁና እያካሄዱ ያሉት አትሌቶች ታዋቂዎቹ ብቻ አለመሆናቸውን የከተማው ከንቲባ ይገልፃሉ፡፡ እንደከንቲባው ገለፃ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ በኦሎምፒክና በአገር አቀፍ ደረጃ የማይታወቁ ነገር ግን በተለያዩ አገሮች ክለቦች ውስጥ የሚሮጡና ከአርሲ አካባቢ ብቻ የወጡ ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ አትሌቶች መኖራቸውን የተለያዩ መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን ከእነዚህ አትሌቶች ውስጥ አንዳንዶቹ በትውልድ አገራቸው አካባቢ ኢንቨስት ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህ አትሌቶች ውስጥም ለይላ የተባለች አትሌት ባለ አምስት ፎቅ ህንፃ እየገነባች ነው፡፡ ቃሲም ከድሮ የተባለ አትሌትም ባለአራት ፎቅ ህንፃ ግንባታ መጀመሩን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ሌሎች አትሌቶችም ለተመሳሳይ ግንባታ የቦታ ጥያቄ ማቅረባቸውን ከከንቲባው ገለፃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ባሳለፍነው ሐሙስ በአሠላ ከተማ ደማቅ አቀባበል ከተደረገላቸውና ሽልማት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል ጥሩነሽ ዲባባና ቀነኒሣ በቀለ በተለየ መልኩ በአሠላ ከተማ እያንዳንዳቸው 1 ሺህ 530 ካሬ ሜትር ቦታ ተሠጥቷቸዋል፡፡ ይህ ቦታ ለኢንቨስትመንት የተከለለ በመሆኑ የመረጡትን ግንባታ እንዲገነቡበት ታስቦ የተሰጠ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ለሁለቱ አትሌቶች የተበረከተው ቦታ በገንዘብ ቢተመን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ይህንን ቦታ ምን ሊያደርጉበት እንደሚችሉ ከንቲባውን ጠይቀናቸው “የሚያደርጉትን የሚያውቁት እነሱ ናቸው፡፡ እኛ የማበረታቻ ቦታ ሰጥተናል፤ የሰጠነው ቦታ የኢንቨስትመንት ቦታ ነው፡፡ ኢንቨስት ያደርጋሉ የሚል እምነት አለን” ብለዋል፡፡ ከአትሌቶቹ ሁለት ነገሮችን እንጠብቃለን ያሉት አቶ ጀማል በአትሌቲክስ ያስመዘገቡትን ድል በልማቱም እንዲደግሙ እንደሚፈልጉ ገልፀዋል፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ደራርቱ፣ ሃይሌ፣ ቀነኒሣና አይሻ ጊጊ የጀመሩትን ሥራ ሌሎች አትሌቶችም እንዲቀጥሉበት እንፈልጋለን ብለዋል፡፡ አትሌቶች አሠላ ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉና የአካባቢው ተወላጆችም አርሲና አሠላን ፕሮሞት ለማስተዋወቅ ታስቦ የተቋቋመው የአርሲ ተወላጆች ማህበር በሐሙሱ የአትሌቶች አቀባበል ተሳትፎ ያደረገ መሆኑን የማህበሩ ም/ሰብሳቢ አቶ መስፍን አወቀ ገልፀዋል፡፡ አሁን በአሠላ ቦታ የተረከቡ አትሌቶችም ጥሩ ሥራ ይሠራሉ፡፡ አሠላ ላይ ስለተሰጠው ቦታ ያነጋገርነው ቀነኒሣ በቀለ ቦታውን ሊገነባበት የሚፈልገውን ነገር ወደፊት እንደሚያስብበት ገል”ል፡፡ ጥሩነሽ ዲባባም ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፀችው በእርግጠኝነት በቦታው ላይ አንድ ነገር እሠራለሁ፤ የምሠራውን ሥራ ግን ላስብበት ይገባል የሚል መልስ ሰጥታለች፡፡ “እኛ አትሌቶች በአርሲና በአካባቢው በኢንቨስትመንቱ ረገድ ብዙም ያደረግነው ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡” ያለችው ደራርቱ ቱሉ ይህም የሆነበት ምክንያት ከዚህ ቀደም በነበረው የመንገድ ችግር ነው፡፡ “አሁን ያለው መንገድ ገና ከተጠናቀቀ አንድ ዓመት ገደማ በመሆኑ ብዙ ኢንቨስትመንት ሊስብ አልቻለም፡፡ አሠላ ብቻ ሳይሆን በቆጂም እንደልባችን ያልሠራንበት ምክንያት የመንገድ ችግር ነው፡፡ አሁን ግን ይህ መንገድ እየተሠራ ስለሆነ ሁላችንም ያሰብነውን በቆጂ ላይ እናደርጋለን፡፡ ቀደም ብሎ የነበረው የመንገድ ችግር እኛንም ሆነ ሌሎች ኢንቨስተሮች ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ እየተለወጠና ባለሃብቶች እየተሳቡ በመሆኑ ብዙ ለውጥ ሊመጣ ይችላል” ስትል እምነቷን ገልፃለች፡፡ “ከበቆጂ የወጣን አትሌቶች በቆጂ ላይ የየራሳችንን ሥራ ለመሥራት አስበናል፡፡ ለምሣሌ እኔ አነስተኛ ክሊኒክ እገነባለሁ፡፡” ያለችው አትሌት ደራርቱ ሌሎችም ማቀዳቸውንም አስረድታለች፡፡ ከበቆጂ አስተዳደር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ቀነኒሣ በቀለ በቆጂ ውስጥ 2.5 ሚሊዮን ብር የሚፈጅ ሆቴል ገንብቶ መጨረሱንና እስካሁን ድረስ ሥራ ባይጀምሩበትም በቆጂ ውስጥ ከአምስት በላይ የሚሆኑ አትሌቶች ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ቦታ ተረክበዋል፡፡ |
|
| Last Updated ( Sunday, 05 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |