Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow “ሥርዓተ ትምህርቱ የቴክኖሎጂ...
“ሥርዓተ ትምህርቱ የቴክኖሎጂ... E-mail
Sunday, 05 October 2008
Image“ሥርዓተ ትምህርቱ የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን ታሳቢ ማድረግ አለበት”

አቶ ዲሊሞ ኦቶሬ
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ

አቶ ዲሊሞ ኦቶሬ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ናቸው፡፡ የተወለዱት፣ የአደጉት፣ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ሆሳዕና ሲሆን ከሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን የማስተርስ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ናቸው፡፡ በትምህርት ሥርዓቱና ተጓዳኝ በሆኑ ሥራዎች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የትምህርትን ጥራት ከማረጋገጥ አኳያ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊንቀሳቀሱና የየበኩላቸውንም አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚያስችላቸው ስልት ወይም ጠቋሚ አቅጣጫ ምንድነው?

አቶ ዲሊሞ፡-
ትምህርት የልማት፣ የሥልጣኔና የቴክኖሎጂ መሠረት ነው፡፡ ለዚህም እውን መሆን የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ባለድርሻ አካላትና የዜጎችን ቅንጅታዊ እንቅስቀሴ ይጠይቃል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ጥራት ያለው ትምህርት የመሰጠቱ ተግባር ልዩ ትኩረት የሚሻ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማሳካት ደግሞ የተለያዩ ፓኬጆች ተዘጋጅተዋል፡፡ መንግሥት፣ ባለድርሻ አካላትና ዜጎችን ከሚያሳትፉት ከእነዚሁ ፓኬጆች መካከል አንደኛው የትምህርት ቤቶችን አካባቢ የማሻሻል (ስኩል ኢምፕሩቭመንት) ፕሮግራም ነው፡፡ ይህም ማለት ትምህርት ቤቶችን ከጫትና ሺሻ ቤቶች፣ እንዲሀም አዋኪ ከሆነ ነገሮች ማፅዳት፣ የትምህርት ሥርዓቱ ምቹ ሁኔታ ሳቢና ማራኪ እንዲሆን ማድረግን ይጠይቃል፡፡

ከዚህም ሌላ በትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ ነዋሪዎች የሚገኙ ከሆነ ከአስተዳደሩ አመራር ጋር በመቀናጀት ነዋሪዎቹን በሥርዓት ማስወጣትን ይጠይቃል፡፡ ከትምህርት ቤቶች ሕንፃ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመጠጥና የአልኮል ቤቶች፣ እንዲሁም የንግድ ሱቆችን ሥርዓት ባለው መንገድ መልክ ማስያዝ ወይም ወደ ሌላ አካባበ እንዲዛወሩ ማድረግ ይጠይቃል፡፡

ሁለተኛው ፓኬጅ ደግሞ የስነዜጋ ትምህርትን ማስፋፋት ነው፡፡ በሀገሪቱ የስነዜጋ ትምህርት ከተጀመረ አራት ዓመት ሆኖታል፡፡ ትምህርቱ በዓለም አቀፍ የሚታወቅ ቢሆንም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ሲታይ ግን ተፈጥሮ ወይም ማህበራዊ ሳይንስ ብለን እንከታተለዋለን እንጂ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ የዜግነት ኃላፊነታቸውን ተረድተውና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓታቸውን ጠብቀው ለሀገራቸው ሁለንተናዊ ዕድገት በቁርጠኝነት ሊነሳሱ እንደሚገባ በመጠቆም ረገድ ያተኮረ አልነበረም፡፡ አሁን በቅርቡ ተሻሽሎ የወጣው አዲሱ የስነዜጋ ትምህርት ግን በዚህች አገር ዴሞክራሰያዊ ሥርዓት እንዴት እውን ሊሆን እንደሚችል ከልጅነታቸው ጀምረው እንዲያውቁት ያደርጋል፡፡ አዲሱ የስነ ዜጋ ትምህርት በትምህርት ጥራት ላይ እንደ አንድ ፓኬጅ ሊካተት የቻለበት ምክንያት ዛሬ በትምህርት ላይ የሚገኙ ሕፃናት የነገ ሀገር ተረካቢዎች ስለሚሆኑ ነው፡፡ ሕፃናቱ ሀገርን የማስተዳደር ኃላፊነት ነገ ሊረከቡ ከሆነ በትምህርቱ ላይ ምን ዓይነት ሰዎችን ነው አሁን ያለው ሥርዓተ ትምህርቱ ማብቃት ያለበት የሚለውንም ይዳስሳል፡፡ ከዚህ አንጻር በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ የስነ ዜጋ ትምህርት ማካተቱ ልጆች ራሳቸው በኃላፊነት መንፈስ እንዲስተካከሉ የማድረግ ተልዕኮውን ይወጣል፡፡ ለዚህም እውን መሆን በክርክር መድረኮችና በስብሰባዎች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ የሥነ ዜጋ ትምህርት ከተጠናከረ ሺሻና ጫት ቤቶች እንዲሁም አልባሌ ቦታዎችን የሚያዘወትሩ ተማሪዎች ጥያቄ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ራሳቸውን ይጠብቃሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የሥነ ዜጋ ትምህርትን አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ለሥልጣን ማቆያው እንዲሆን ያመጣው ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው? ተሻሽሎ የወጣው አዲሱ የሥነ ዜጋ ትምህርት ከበፊቱ በምን ይለያል?

አቶ ዲሊሞ፡-
አይደለም፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ናቹራል ሳይንስ፣ ጂኦግራፊ፣ ፖለቲካል ሳይንስ በአንድ ወቅት ካልተጀመረ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እንዲጀመር የማድረግ መብት አለው፡፡ ሲጀመር ግን በርዕዮተ ዓለማዊ መልክ ሳይሆን ሀገራዊ ፋይዳ በሚያስገኝ መልኩ ነው መሆን ያለበት፡፡ ከዚህ አኳያ ዘንድሮ የሥነ ዜጋ ትምህርት በጣም ተሻሽሎና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ የተሻሻለውም ቀደም ሲል ያልነበሩትን አህጉራዊ፣ ዓለም አቀፋዊና አገር አቀፋዊ እሴቶችን በውስጡ በማካተቱ ነው፡፡ ወጣቶች ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮችን ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ሀገራችን ደግሞ ከእነዚህ ዓለምና አህጉራዊ ጉዳዮች ጋር ማጣጣም ይኖርባታል፡፡

ዓለም አቀፍ አማካሪዎችን ሀገራዊ ባለሙያዎች የተሳተፉበት፣ ተሻሽሎና ጥራት ባለው መልኩ የተዘጋጀው ይህው አዲሱ የሥነ ዜጋ ትምህርት በመታተም ላይ ነው ያለው፡፡ ሕትመቱ በሚቀጥለው ሳምንት ተጠናቅቆ ለተማሪዎች ይደርሳል፡፡ አዲሱ የሥነ ዜጋ ትምህርት የጥራት ፓኬጅ ማረጋገጥ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ በጫት፣ በሺሻ ቤቶችና አልባሌ ቦታዎች መዋል በትምህርት ላይ ምን ዓይነት አሉታዊ ተፅዕኖ ሊፈጥሩና በዜጎች አመለካከት ላይ ምን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ጉዳዮች በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካቷል፡፡  

ሪፖርተር፡- መምህራንን በተመለከተስ?

አቶ ዲሊሞ፡-
ሌላው የጥራት ፓኬጅ የመምህራን የልማት ፕሮግራም ነው፡፡ ይህም ት/ቤቶችን ከአዋኪ ነገሮች ከማጽዳት አኳያ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ መምህሩ እንደድሮው ክፍል ገብቶ አስተምሮ መውጣት ብቻ አይደለም፡፡ መምህሩ ሊያድግ፣ ሊበለጽግ፣ በገቢውና በትምህርት     (በእውቀቱ) ሊሻሻል ይገባዋል፡፡ መምህራን ባልጐለበቱበትና ባልበለጸጉበት ሥርዓተ ትምርቱን ማሳካት ጥያቄ ውስጥ ነው የሚገባው፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱ ሲሻሻል ግን የገበያና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች፣ እንዲሁም የመንግሥት ፖሊሲዎች ከግምት ውስጥ መግባት አለባቸው፡፡ የግሎባላይዜሽን ለውጦች ታሳቢ መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህን ሊያጣጥም የሚችል ሥርዓተ ትምህርት ሊኖር ይገባል፡፡ ይህንን መሸከምና ከዚህ ዳይናሚዝም ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል መምህርም ያስፈልጋል፡፡

ሌላው ፓኬጅ ደግሞ የትምህርት ቤት አመራርና አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻል ነው፡፡ ይህም ፓኬጅ ሊዘጋጅ ያስፈለገው የትምህርት ቤቶችን አካባቢ የማሻሻል፣ የሥነ ዜጋ ትምህርትንና የመምህራን ልማት ፕሮግራሞችን አስተሳስሮ የሚያንቀሳቅስ መሪ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ አመራሩ ይሄው ተሰምቶት መሥራት እንዳለበት ትምህርተ ቢሮው ያምናል፡፡ የህንን ሊያጠናክርና ሊሠራ የሚችል አዲስ ሀሳብ አፍላቂና ስትራቴጂ መሪ መፍጠር ያስፈለጋል፡፡ ስለዚህ በየትምህርት ቤቱ ያለው አመራር እንዴት ነው ተማሪዎችን እየመራ ያለው? ሕዝቡንስ እንዴት ነው እያደራጀና እያሳተፈ ያለው? እንዴት ነው የት/ቤቱን ፋይናንስ እየተጠቀመ ያለው? እንዴት ነው የት/ቤቱን ማህበረሰብና ባለድርሻ አካላትን በትምህርቱ ሥርዓት ውስጥ እንዲሳተፉ እያደረገ ያለው? የሚሉትንና ሌሎችንም ተመሳሳይ ጥያቄዎችን የትምህርት ቤት አመራርና አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ ፓኬጅ በተሟላና በአግባቡ ሊመልስ የሚችል ነው፡፡

አምስተኛው ፓኬጅ ደግሞ ኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይ.ሲ.ቲ) ነው፡፡ እስካሁን ሲሰጥ የቆየው የትምህርት ሥርዓት ዘመናዊነት የተላበሰ ሳይሆን ባህላዊ ነው፡፡ ዘመናዊነት የሚመጣው ደግሞ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥርዓተ ትምህርት ሲኖር ነው፡፡ ወጣቶች መዝናናት የሚችሉበት የወጣት ማዕከላት ሊኖር ይገባል፡፡ ማዕከላቱም በኮምፒውተር ሴንተር፣ በኢንተርኔትና ቴክኖሎጂ ባመጣቸው ጉዳዮች ላይ ሊደራጁ ይገባል፡፡ ይህ እውን ከሆነ ወጣቱ ትውልድ ከወቅቱ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር በቀላሉ ሊተዋወቅና ሊለማመድም ይችላል፡፡ በዚህ መለኩ እንቅስቃሴ ከተጀመረ አልባሌ ቦታዎች፣ በጫትና ሺሻ ቤቶች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ወጣቶች ቁጥር በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ በሂደትም ጭራሹን እርግፍ አድርገው ይተውታል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ በፕላዝማ ትምህርት እየተሰጠ ነው፡፡ ለሥርዓተ ትምህርቱ ያስገኘው ጠቀሜታ ምን ይመስላል? ከዚህም ሌላ በት/ቤቶች አካባቢ ያሉትን ጫትና ሺሻ ቤቶችን በሕግ ማስነሳት ወይም ማዘጋት ለምን አልተሞከረም?

አቶ ዲሊሞ፡-
በዚህች አገር ላይ ቀደም ሲል የነበረው የትምህርት ሥርዓት ፍትሃዊነት አልነበረውም፡፡ በመላ ሃገሪቱ የሚሰጠው ብሔራዊ ፈተና አንድ ዓይነት ቢሆንም በየክልሉ ያለው የመማር ማስተማሩ ሥራ ግን አንድ ዓይነት አልነበረም፡፡ በፕላዝማ መጠቀም ከተቻለ ወዲህ ግን ሥርዓተ ትምህርቱ አንድ ወጥ፣ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ከትምህርት ቤት ሕንፃዎች ጋር ተያይዘው የሚገኙትን የጫትና ሺሻ ቤቶች በአስተዳደር፣ በሕግ፣ በፖሊስና በፍርድ ቤት በማዘጋት የሚገኘው መፍትሄ ጊዜያዊ ነው የሚሆነው፡፡ ዘለቄታ የለውም፡፡ ዘላቂ ሊሆን የሚችለው ቀደም ሲል በተጠቀሱት ፓኬጆችና በሌሎችም ነጥቦች ላይ የትምህርት ሥርዓቱን የተጠናከረ እንዲሆን ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን እነዚህን አልባሌ ቦታዎች በሕግ ማስፈረስ፣ ሰዎችንም እንዲታሰሩ ማድረግ እንደትምህርት ባለሙያ ሲታይ መፍትሄ አይሆንም፡፡ ይልቁንም ት/ቤቶች ከአልባሌ ሥፍራዎች እንዲፀዱ ለማድረግ ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ መንቀሳቀስ ይገባል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የጫትና ሺሻ ቤቶች ከከተማው አይጠፉም፡፡ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ዋናው የአስተሳሰብ ለውጥ መፍጠሩ ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህን ፓኬጆች ተግባራዊ ለማድረግ በሚካሄደው እንቅስቃሰ ላይ እንደችግር ሆነው የሚታዩት ምንድናቸው?

አቶ ዲሊሞ፡-
ዋና ቁልፍ ችግር ሆኖ የተገኘው በልማት የተሟላ ምላሽ አለመስጠት ነው፡፡ ወጣቶቹ ራሳቸውን ማነጽ፣ እንዲሁም ትርፍ ጊዜያቸውን በልማትና በስፖርት እንቅስቀሴ ላይ ማሳለፍ የሚችሉበት ሁኔታ የመፍጠር ሥራም ገና አልተጀመረም፡፡ ለምሳሌ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመከላከል የሚችሉበትንና በዓለም አቀፍ ደረጃ መረጃ የሚያገኙበትን ሁኔታ የማመቻቸቱ ሥራ ገና ይቀረናል፡፡ በሚያረፍዱ ተማሪዎች ላይ የትምህርት ቤቱን በር በመዝጋት መፍትሄ ያስገኛል ወይ የሚለው ሁሉ መታየት ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም የት/ቤቱ በር የተዘጋበት አርፋጅ ተማሪ ወደ አልባሌ ቦታ እንደሚሄድ ጥርጥር የለውም፡፡ ስለሆነም ለአርፋጅ ተማሪዎች መፍትሄው በር መዝጋት ሳይሆን ሌላ ነገር መፍጠርን ይጠይቃል፡፡ ይህውም ክፍል ውስጥ ገብተው መማር እንኳን ባይችሉ ያረፈዱበትን ሰዓት በልማት ላይ ሊያውሉ የሚችሉበትን ሲስተም መቀየስ ወይም መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም አርፋጆች ተመልሰው ወደ ሌላ ቦታ እንዳይሄዱ የማድረግ ሥራ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት መከናወን ይገባል፡፡ ለዚህም እውን መሆን ጉዳዩ በሚገባ መጠናት ይኖርበታል፡፡ ጥናቱም ልጆቹ ለምን ያረፍዳሉ? ለዚህስ ዘላቂ መፍትሄው ምንድነው? በር መዝጋት ነው ወይ ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው? ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ያረፈደ ተማሪ እንኳ ቢኖር ያረፈደበትን ሰዓት በሌላ የልማት ሥራ ላይ እንዲያውለው ለማድረግ ምን መደረግ አለበት ለሚሉ ጥያቄዎች አስፈላጊውን መልስ መስጠት ይገባዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- የሥራና የትምህርት መግቢያ ሰዓት አንድ መሆን በትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ከዚህ አከያ በተለይ በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ የትምህርት ቤት መግቢያ ሰዓት ከሥራ መግቢያ ሰዓት ቢለይ ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

አቶ ዲሊሞ፡-
ጠዋት ላይ የመጨናነቅ ሁኔታ ይታያል፡፡ የትራንስፖርት እጥረትም አለ፡፡ ተማሪ ከሠራተኛ በኋላ ወይም በፊት ወደ ትምህርት ቤት ይወጣ ቢባል ሊያስከትል የሚችለውን ነገር ማየት ያስፈልጋል፡፡ ሠራተኛ ከገባ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት በኋላ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ይግቡ ቢባል በትምህርት ቤቱ ስምንት ሰዓት ወይም ዘጠኝ ሰዓት ድረስ መቆየት ግድ ይሆንባቸዋል፡፡ ስለሆነም ከቀትር በኋላ በአሥራ አንድ ሰዓት አካባቢ ወደየቤታቸው ሲመለሱ አሁንም የትራንስፖርት ችግርና ጭንቅንቅ መደገሙ አይቀርም፡፡ ይህን ችግር መፍታት የሚቻለው በሰዓት ማራዘም ሳይሆን በአዲስ አበባ ላይ ያለውን የትራንስፖርት ሥርዓቱን በማሻሻልና አቅሙንም በማሳደግ ነው፡፡ ከሕዝበና ከተማሪው ብዛትና አሰፋፈር፣ እንዲሁም ከትምህርቱ ሽፋን አንጻር ምላሽ ሊሰጥ የሚችል የትራንስፖርት ሥርዓትን መዘርጋት ነው፡፡ ችግሩም ሊቀረፍ የሚችለው በዚሁ ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የተማሪዎች ብዛት ይታወቃል?

አቶ ዲሊሞ፡-
በአዲስ አበባ ላይ የተማሪዎች ቁጥር በጣም ጨምሯል፡፡ ምዝገባው ስላላቀ ትክክለኛውን ቁጥር አሁን ለመናገር ያስቸግራል፡፡ ምናልባት ከዚህ ወር በኋላ ምዝገባው ሲጠናቀቅ ይታወቃል፡፡ የተማሪዎች ቁጥር የጨመረበትም ምክንያት እየተጠና ነው ያለው፡፡ እስካሁንም ከተካሄደው ጥናት ለመረዳት እንደተቻለው ኢትዮጵያ የሚሌኒየሙን የልማት ግብ በትምርት ዘርፍ ከማሳካት አንጻር ብዙ እንቅስቃሴ ማድረጓ፣ በ2015 ትምህርት ለሁሉም የሚለውን ግብ የማሳካቱ ጉዳይም አንድ ትልቅ ተግባር ሆኖ በመንግሥት በመሠራቱና ከዚህም አንፃር የተለያዩ ኮንፈረንሶችን በማዘጋጀት በሕዝቡ ውስጥ ትልቅ የማነሳሳት ሥራ መከናወኑ በሕዝቡ ውስጥ ተቀጥሬ ለመሥራት መማር አለብኝ፣ ከተማርኩ ሥራ መፍጠርና ተልዕኮ መሸከምም እችላለሁ የሚል ስሜት እንዲፈጠር ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ትምህርት ጥራት ችግር ሊንፀባረቅ ከሚችልባቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው በመጻህፍት ላይ ነው፡፡ ስለሆነም ለመማር ማስተማሩ ሥራ የሚያገለግሉ መጻህፍትን አሻሽሎና ማራኪ አድርጎ ለማውጣት ምን እየተደረገ ነው፡፡

አቶ ዲሊሞ፡-
የመማሪያ መጽሀፍቱን ለማሻሻል ትምህርት ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ ኮንስልታንቶቹ ጋር ተዋውሎ ነበር፡፡ በመማሪያ መጽሀፍት ላይ ማሻሻያ የተደረገው የውጭና የአገር ውስጥ ባለሙያዎች፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የየክልሉ ትምህርተ ቢሮዎችና መምህራን በተሳተፉበት ነው፡፡ ነገር ግን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር ስምመነት የፈጸሙ አካላት ባሉት ጊዜ ለሕትመት አላደረሱትም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት መጽሃፍቱ እንደዱሮው ዓይነት ሳይሆን ውሀ የማያበላሻቸው (ወተር ፕሩፍ) እና በተለያዩ ቀለማት ያጌጡ ወይም የተዋቡ (ከለርድ) ሆነው ስለሚታተሙ ነው፡፡ በዚህ መልኩ መታተማቸው ደግሞ ልጆቹ መጻህፉን እንዲያነቡ ይገፋፋቸዋል፡፡ ይህም ተማሪው ያለመምህር በራሱ ጊዜ የሚያነብበትን መንገድ ይፈጥራል፡፡

መጽሃፍቱ ታትመው ሲወጡ ቀድሞ የነበሩት መጽሀፍት በሙሉ በአዲሶቹ ይቀየራሉ፡፡ አዲሶቹ መጽሃፍት በአራት ክፍሎች (ኮምፖኖንቶች) የተደራጁ ሲሆን አንደኛ ው ክፍል ሥርዓተ ትምህርቱ የገበያን ፍላጎት ለያሟላ በሚችል መልኩ ማዘጋጀትን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አኳያ በዚህች አገር ላይ ተምሮ ሥራ ያጣ ሰው መኖር የለበትም፡፡ ሁለተኛው ክፍል ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ ሲሆን ይህም ሥርዓተ ትምህርቱ የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን ታሳቢ ማድረግ አለበት፡፡ ቴክኖሎጂው የደረሰበት የዕድገት ደረጃ ሌላ መጽሃፉ የሚያወራው ሌላ ከሆነ አይጣጣሙም፡፡ ስለሆነም ተማሪው፣ መምህሩ፣ መጽሀፉና ቴክኖሎጂው አብረው መሄድ አለባቸው፡፡ ሦስተኛው ክፍል ደግሞ የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት የመንግሥትን የልማት ፖሊሲን ጥያቄ መመለስ እንዳለበት ያስቀምጠል፡፡ ከዚህ አኳያ ሀገሪቱ የምትፈልገው የኢንዱስትሪው፣ የግብርናና የአገልግሎት ዘርፎችን አቀናጅቶ ማንቀሳቀስ የሚችል የተማረ የሰው ኃይል ነው፡፡ አራተኛውና የመጨረሻው ክፍል ደግሞ ዓለም አቀፋዊ ትስስርን (ግሎባላይዜሽን) የዳሰሰ ነው፡፡ ኢትየጵያ ለብቻዋ ደሴት አይደለችም፡፡ ዓለም በቴክኖሎጂ በግብይት፣ በፖለቲካ፣ በኢንዱስትሪና በቢዝነስ ወደ አንድ መንደር እየተቀየረ ያለበት ሁኔታ ሊያሳካ የሚችል ሥርዓተ ትምህርቱ ሊኖር ይገባል፡፡

በዚህም መሠረት እነዚህን አራት ክምፖናንቶችን ያካተተ መጽሃፍ ነው አሁን እየተዘጋጀ ያለው፡፡ በዚህ ዓመት ለሕትመት ያልደረሰውም እነዚህን ነጥቦች ታሳቢ አድርጎ በመዘጋጀቱ ነው እንጂ እንደ ትምህርት ሚኒስተርና እንደ ትምህርት ቢሮው የምናውቀው ነገር ቢኖር በ2001 ላይ ለመጀመር የሚያስችል እቅድ ነበር፡፡  

ሪፖርተር፡- በአዲስ መልክ ተሻሽሎ የተዘጋጀው የመማሪያ መጽሃፍ ለዘንድሮው የትምህርት ዘመን ካልደረሰ በምትኩ ምን ለማድረግ ነው የታሰበው?

አቶ ዲሊሞ፡-
የመማር ማስተማሩ ሥራ አሁን ባለው መጽሃፍ ይቀጥላል፡፡ መጽሃፍቱ በመስከረም ለተማሪዎች ይሰጥና በሰኔ ይመለሳል፡፡ በዚህ መልኩ መጻህፍቱ በተማሪዎች እጅ ሲዘዋወሩ መልካቸው ሊቀየሩ ወይም ሊላላጡ ይችላሉ፡፡ ይህንን ለማስተካከል የትምህርት ቢሮው አንድ የአሠራር ሥርዓት ዘርግቷል፡፡ በዚህም መሠረት ሕትመት ላይ ያለው መጽሃፍ ለ2001 እንደማይደርስ የሚያረጋግጥ መረጃ በ2000 ሐምሌ እንደደረሰን ወዲያውኑ የማስተካከያ እርምጃ ነው የተወሰደው፡፡ ትምህርቱ በነበረው የመማሪያ መጽሃፍ ይቀጥላል፡፡ በአገልግሎት ብዛት የተቀዳደዱ መጽሃፍትን ለማወቅ የሚያስችል በየሳብጄክቱ የኢንቬንተሪ ሥራ በየትምህርት ቤቱ ተካሂዷል፡፡ በዚህም ሥራ የትኛው መጽሃፍ ሪሳይክል ተደርጎ በ2001 ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፣ የትኛው መጽሃፍ ሪሳይክል ለማድረግ አይቻልም የሚለው ተለይቷል፡፡
በተካሄደው ኢንቬንተሪ ሪሳይክል ለማድረግ አይችሉም ተብለው የተለዩትን መጽሃፍት ሜጋና ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅቶች እያተሙ ናቸው፡፡ ይህም ሁኔታ በመንግሥትና በሕዝብ ትምህርት ቤቶች የሚታዩ የመማሪያ መጽሃፍት እጥረትን ለመቅረፍ የበኩሉን አስተዋጽአ ያበረክታል የሚል እምነት አሳድሯል፡፡   

ሪፖርተር፡- የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻ ድርጅት የተወሰነ ፐርሰንት አትሞ በትርፍ ለመሸጥ የሚያስችለውን ኮፑ ራይት ጠይቋችሁ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ለድርጅቱ ጥያቄ ምን መልስ ነው የሰጣችሁት?

አቶ ዲሊሞ፡-
የድርጅቱ ጥያቄ በገበያ ሥርዓት ከታየ መብት አለው፡፡ ማትረፍ ደግሞ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ መክሰርም የለበትም፡፡ ትርፉ ግን አንጻራዊ ነው መሆን ያለበት፡፡ ምክንያቱም በመጽሃፉ የሚገለገሉት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ናቸው፡፡ በአንድ ጊዜ ሁለትና ሦስት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ሰዎች መኖራቸወም መዘንጋት የለበትም፡፡ አንድ ሰው ለሦስትና አራት ልጆቹ መጻህፍት በውድ ዋጋ ቢገዛ በጣም ይጎዳል፡፡ ከዚህ አኩያ ለድርጅቱ የሰጠነው ምላሽ አይቻልም የሚል ነው፡፡ ያቀረብከው ፕሮፖዛል መፈተሽ ወይም መታየት አለበት፡፡ ለቢሮው ሶያሳወቅ ወይም ኮፑ ራይት ሳይኖረው አሳትሞ ቢገኝ እናሲዘዋለን፡፡ ማንም አታሚ ድርጅት መጽሃፉን አትሞ ገበያ ላይ መሸጥ የሚችለው መጀመሪያ የኛ ኮፒ ራይት ሲኖረው ነው፡፡ ይህ ሳይኖረው አትሞ ገበያ ላይ ካወጣ በወንጀል ይጠየቃል፣ በሕግም ይከሰሳል፡፡ ከዚህ አኳያ የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻ ድርጅት ያቀረበው ዋጋ ትንሽ ተጋንኗል፡፡ አሁን ከተፈጠረው የገበያ ሥርዓት አንጻር ግን መጨመር ላይ ልዩነት የለንም፡፡ ይህም ቢሆን የሕዝቡን የመግዛት አቅም ታሳቢ ማድረግ አለበት፡፡ በዚህ መልኩ እንዲቀርበን ጠይቀናል፡፡ እስካሁን ድረስ ግን አልመጣም፡፡ ትምህርቱ ከተጀመረና ካለፈ በኋላ አትማለሁ ቢል ግን በተማሪዎች፣ በገበያና በተወሰኑ ወላጆች ላይ ጫና ይፈጥራል፡፡ በመንግሥት የትምህርት ዘርፍ ላይ ምንም ዓይነት ችግር አያስከትልም፡፡ በግል የትምህርት ተቋማት ላይ ግን ችግር ያስከትላል፡፡ ምክንያቱም በግል ትምህርት ተቋማት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች መጽሃፍት ከገበያ ገዝተው ለልጆቻቸው መስጠት ይገባቸዋል፡፡    

ሪፖርተር፡- የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና የሚከታተሉ ተማሪዎች በመጨረሻ ዓመታቸው በተለያዩ ማምረቻና አገልግለት መስጩያ ድርጅቶች እየሄዱ የሥራ ልምምድ (አፕሬንትሺፕ) ያደርጎሉ፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ ድርጅቶች በሚገባ አያለማምዷቸውም፡፡ ለመመረቂያ ሲባል ብቻ በጥሩ ሁኔታ ተለማምዷል የሚል ማስረጃ ይሰጣሉ፡፡ የህም በጥራት ላይ ራሱን የቻለ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡

አቶ ዲሊሞ፡-
በኢትዮጵያ ያለው የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ዋና አቅጣጫ ውጤትን መሠረት ያደረገ የትምህርት ሥርዓት ነው፡፡ ይህም ማለት ገበያው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ነው ማቅረብ ያለብን፡፡ ለትምህርቱ ፍላጎት ሲባል ብቻ አናስተምርም፡፡ ሰዎች መማር ስላለባቸው ብቻ ማስተማር አይደለም፡፡ ይህንን በፕራይመሪ ላይ መሠረተ ትምህርት ስለሆነ እናስተምራለን፡፡ በዩነቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ላይ ግን መማር ስላለባቸው ሳይሆን የምናስተምረው ተምረው ሀገርን እንዲለውጡ ከማድረግ አኳያ ነው፡፡ ተምረው ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ለማድረግ ወይም ኢንዱስትሪና ተቋማት የሚፈልጉትን ነው እኛ እዚህ ቦታ ላይ የምናስተምራቸው፡፡ ከዚህ አኳያ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና (ቲ.ቪ.ኢቲ) ዙሪያ 70 ከመቶውን የሥራ ላይ ልምምድ (አፕረንትሺፕ) የቀረውን 30 ከመቶ በክፍል ውስጥ የንድፈ ሀሳብ ትምህርት ነወ የምንከተለው፡፡ ስለሆነም ተማሪዎቹ ለአፕረንትሽፕ ከወጡ ሥራ መፍጠር፣ በራሳቸው መመራትና ሥራ አክባሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መንግሥትን ጠባቂዎች አይሆኑም፡፡ በሀገር ልማት ውስጥ የራሳቸውን ጉልህ ድርሻ ሊያበረክቱ ይችላሉ፡፡ ከዚህ አኳያ የአፕረንትሺፕ ፕሮግራም በተቀናጀ መልኩ መመራት አለበት፡፡ ይህም ማለት ኢንዱስትሪዎች ወይም ፋብሪኻዎችና የቲ.ቪ.አ.ቲ ተቋማት በቅንጅት መሠራት ይኖርባቸዋል፡፡ ተማሪ ኢንዱስትሪና ፋብሪካ ራሱ ፈልጎና አፕረንትሺፕ አግኝቼያለሁ ብሎ መምጣት የለበትም፡፡ ከኢንዲስትሪ ጋር ቅንጅት መፍጠር ያለባቸው ተቋማቱ ናቸው፡፡ ቅንጅቱ ሲፈጠር ደግሞ ኢንዱስትሪ በየትኛው የሥልጠና መስክ ላይ ልምምድ ሊሰጥ እንደሚችል ተቋማት መስስማት አለባቸው፡፡ ተማሪዎቹም የሥራ ለይ ልምምድ ለማድረግ ወደ አንዱስትሪው የሚያመሩት ተቋማቱና ኢንዱስተሪው ባደረጉት ስምምነት መሠረት መሆን ይገባዋል፡፡ የኢንዱስትሪው ኃላፊዎችም አፐረንትሽፕ ላይ ያሉት ልምምዱን ጨርሰው ሲወጡ በውጤታቸው፣ በሥራ ብቃታቸውና ችሎታቸው ነው መመዘን ያለባቸው፡፡ ከተግባር አንጻር ሲፈተሹ ነው ውጤቶቻቸውን ወደ ተቋማቱ መላክ ያለባቸው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን መመረቅ አለበት በሚል ጽንሰ ሀሳብ ብቻ የሚሄዱ ከሆነ ኢንዱስትሪው ወይም ካምፓኒው ትውልድን እየገደሉ ነው ያሉት ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለዚህ ምን መያዣ ወይም መቆጣጠሪያና መከታተያ ስልት አላችሁ?

አቶ ዲሊሞ፡-
ለመመረቅ ሲባል ብቻ በተሰጣቸው ውጤት ቢያልፉም መያዥያ ቋት አለን፡፡ የልቀት ማዕከል (ሴንተር ኦፍ ኮምፒታንስ) ተቋቁሟል፡፡ አንድ ተማሪ በዲፕሎማ ቢመረቅ ለተመረቀበት ሙያ ብቃት አለው፡፡ ሰርቲፋይድ ነው፡፡ የሚለውን የመናረጋገጥበት መንገድ አለ፡፡ ስለሆነም አዲስ አበባ ውስጥ በየትኛውም የቲቪኢቲ ኮሌጆች ተመርቀው የሚወጡት በየሙያቸው ሰርቲፋይ እናደርጋቸዋለን፡፡ ይህንንም የሚገመግሙ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ሰርቲፋይ ለማድረግ ፈተና በንድፈ ሃሳብና በተግባር ደረጃ ይሰጣል፡፡ ፈተናውን አልፎ ሰርቲፊኬሽኑን ከያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር ይችላል፡፡ ከኮሌጅ ሲወጣ የሚይዘው ዲፕሎማ ትምህርቱን መከታተሉን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ እኛ የምንሰጠው ግን ለተመረቀበት ሙያ ብቁ ነው፡፡ የሚል ማረጋገጫ ነው፡፡ ይህንንም ተማሪዎቹና አፐረንትሽፕ የሚሰጡ ካምፓኒዎችም እያወቁት ነው፡፡ በዚህም መሠረት አምናም ዘንድሮም ብዙ ሺህ ተማሪዎችን ፈትነናል ሰርቲፋይ ለማድረግ፡፡ እንደ ድሮው በዲፕሎማ ብቻ አደለም ከቲቪኢቲ የሚመረቀው፡፡ ዲፕሎማ ሲደመር ሰርትፊኬሽን ነው፡፡ ከዚህ አኩያ አፐረንትሽፕ ለሚሰጠት ካምፓኒዎች በአሁኑ ጊዜ ሰርትፊኬሽን ስላለ ለምትሰጡት ሥራ ታማኝነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሊያድርባችሁ ይገባል እያልናቸው ነው፡፡

በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የሚዘጋጀውን ፈተና ክፍል ውስጥ ይሰጠዋል፡፡ የተግባር ፈተናውን ግን ወደ ኢንዱስትሪው ወስደን ነው የምንፈትነው፡፡ ተፈታኙ አንድ ነገር አምርቶ እንዲያሳየን ስዓቱን ወስነን እንሰጠዋለን፡፡ በተሰጠው የሰዓት ገደብ የተፈለገውን ወይም የተጠየቀውን አምርቶ ካቀረበ ሰርቲፋይድ ይሆናል፡፡ ማድረግ ካልቻለ ግን ተማሪው ሳይችል ነው ኢንዲስትሪው አፐረንትሺፑን ሰርቲፋይ ያድርገው ማለት ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- የልቀት ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት በምን ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው?

አቶ ዲሊሞ፡-
የአዲስ አበባ አስተዳደር አዲሱ ካቢኔ ሥራውን ከጀመረ በኋለ ከወሰናቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል አንዱ የልቀት ማዕከሉ በተቋም ደረጃ ተጠናክሮ ሥራውን እንዲጀምር የሚል ነው፡፡ በውሳኔውም መሠረት በተቋም ደረጃ እንዲጠናከር ለማድረግ የሚያስችል ውስጣዊ አደረጃጀት ሥራ እያከናወነ ነው ያለነው፡፡ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሕግ አንጻርም የሰው ኃይል መዋቅር እየተሠራ ነው ያለው፡፡ ማዕከሉ በአሁነ ጊዜ በትምህርተ ቢሮ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ከተወሰኑ ወራቶች በኋላ ራሱን ችሎ ከቢሮ ይወጣል፡፡ አሁነ ለጊዜው የተማረ የሰው ኃይል የለውም፡፡ ይህ እስኪሟላ ድረስ ሥራው መጀመር ስላለበተ በአካውንቲንግ፣ በማርኬቲንግ፣ በአሌክትሪክሲቲና በተለያዩ ዘርፎች ላይ ሰርቲፊኬሽን ጀምረናል፡፡ የዚህ ጽንሰ ሀሳቡ አዲስ ስለሆነ በዚህ ሥራ ለይ የሚሳተፉ ባለሙያዎችን ከገበያ ለማግገት አልተቻለም፡፡ የህም በመሆኑ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ከአየር መንገድ፣ ከግብይት ሥርዓት ተቋማት፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተወሰኑ ባለሙያዎችን አግኝተናል፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ናቸው ብቃትን የሚለኩት ወይም የሚፈትኑት፡፡
Last Updated ( Sunday, 05 October 2008 )
 
< Prev   Next >