| ሚስትን መደብደብና ሴት ጓደኛን... |
|
|
| Monday, 21 January 2008 | |
|
ሚስትን መደብደብና ሴት ጓደኛን አለማክበር በኢትዮጵያ ሁሉም ክልሎች የሚፈፀም ድርጊት ነው - ድህነትና የኢኮኖሚ ጥገኝነት በሴቶች ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት አባብሷል ቤተሰብ ለማናቸውም ሰው የፍቅር፣ የደህንነት ምንጭና መጠለያ ይታሰባል፡፡ ነገር ግን ቤተሰብ፣ ሲታሰቡ የሚዘገንኑ ጥቃቶች ጭምር የሚፈፀሙበትም ነው፡፡ በተለይ ለሴቶች እና ለልጃገረዶች የቤተሰብ ትርጉም ሁልጊዜ ከቅድስና ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ከኦክስፋም እንግሊዝ ጋር በመተባበርና ከአውሮፓ ኮሚሽን የሲቪል ሶሳይቲ ፈንድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ያስጠናው ጥናት እንደሚለው፣ በቤት ውስጥ የሚፈጸም ጥቃት በአብዛኛው በወንዶች ጥቃት አድራሽነት የሚፈጸም ሲሆን ፈፃሚዎቹም ለሴቶችና ለልጃገረዶች በጣም ቅርብ የሆኑና የሚታመኑ የሚባሉ ናቸው፡፡ ባሎች፣ የወንድ ጓደኞች፣ አባቶች፣ የእንጀራ አባቶች፣ የወንድ አማቶች፣ ወንድሞች፣ አጎቶች፣ ልጆችና ሌሎች ወንድ ዘመዶች በቤት ውስጥ በሚገኙ ሴቶች ላይ ጥቃት ይፈፅማሉ፡፡ ሴቶችም ጥቃት አድራሾች ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ እንዳለ ቁጥሩ ግን አናሳ መሆኑ በጥናቱ ተቀምጧል፡፡ የቤት ውስጥ ጥቃት የሚገለጸው በአካላዊ፣ ፆታዊ፣ ሥነልቦናዊና የኢኮኖሚያዊ ጥቃቶች ሲሆን መጠኑ ግን የተለያየ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ ጥናቱ የተከናወነበት በአገር አቀፍ ደረጃ በፆታዊ ጥቃት ዙሪያ እየሠራ ያለው የማኅበሩ ፕሮጀክት አስተባባሪ ወ/ሮ የሺሃሳብ ወርቁ እንደሚሉት፣ ጥቃትን በተመለከተ አገር አቀፍ ጥናት/መረጃ ባለመኖሩ፣ በጉዳዩ ላይ የሚሠራ ሥራም ያልተቀናጀ በመሆኑ፣ በተለይም በዘርፉ የሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሕግ አውጪና አስፈፃሚ አካላትን አቅም መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ለሁለት ዓመት የሚቆየው ፕሮጀክት ተቀርፆ ላለፉት ስምንት ወራት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በዘርፉ የሚከናወኑ መነሻ መረጃ አስፈላጊ በመሆኑ የቤት ውስጥ ጥቃት ለምን፣ እንዴት ይፈፀማል? ስፋቱ ምን ያህል ነው? የሚለውን ማስጠናት የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ተደርጎ በመወሰዱ ጥናቱ ተካሂዷል፡፡ ቀጥለው የሚካሄዱ ተግባራት ጥናቱን መነሻ በማድረግ የሚከናወኑ ናቸው፡፡ እንደ ወ/ሮ የሺሃሳብ በየአካባቢው ባህልና የማኅበረሰብ ሁኔታ የተለያየ ቢሆንም የቤት ውስጥ ጥቃት በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ሴቶች ላይ የሚፈጸም ተግባር ነው፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የቤት ውስጥ ጥቃቶች መንስዔም በባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሕጋዊ እና ፖለቲካዊ አሠራሮችና ሂደቶች ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ በአገር አቀፍ ጥናቱ የቤት ውስጥ ጥቃትን መፈጸም ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል በጉዳዩ ላይ ስፋት፣ የፖሊሲ ቅኝቶች፣ የሕግ ማዕቀፍና ክፍተቶችን በተመለከተ የተጠኑ ጥናቶች ዳሰሳም ተከናውኗል፡፡ እንደ ወ/ሮ የሺሃሳብ ቀደም ሲል የቤት ውስጥ ጥቃትን በተመለከተ በተለያዩ አካላት የተጠኑ ጥናቶች በየራሳቸው በቂ ባይሆኑም በጥቅሉ ግን የቤት ውስጥ ጥቃት ተገቢው ትኩረት ያልተሰጠው ክስተት እደሆነ ያሳያሉ፡፡ ወ/ሮ የሺሃሳብ ጨምረው እንደተናገሩት ያለው ሕግ በዝርዝርና በአግባቡ የማይሸፍን በመሆኑ ዝርዝር ሕግ ለብቻው ሊወጣ አልያም ሊሻሻል የሚችልበት መንገድ እንዲመቻች ማድረግ ከጥናቱ ባሻገር ያለው የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ግብ ነው፡፡ ባለፈው ዓርብ ይፋ የሆነው የማኅበሩ ጥናት በአገሪቱ ስድስት የክልል ቦታዎች ናሙናነት የተከናወነ ነው፡፡ ይኸው አገር አቀፍ ጥናት የቤት ውስጥ ጥቃት በተለይም ሚስትን መደብደብ እና የሴት ጓደኛን ማዋረድ በሁሉም አካባቢዎች የሚታይ ክስተት ነው፡፡ በጥናቱ ውጤት መሠረት ለቤት ውስጥ ጥቃት ዋና መነሻ የሆነው ተጠቃሽ ነጥብ ድህነት ሲሆን የሴቶች የኢኮኖሚ ጥገኝነት ጥቃቱን ለማባባስ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም የአልኮል ሱሰኝነት ሌላው አባባሽ ነጥብ መሆኑ ተቀምጧል፡፡ ሴቶች የቤት ውስጥ ጥቃትን በተመለከተ ያላቸው አመለካከት በጥናቱ የታየ ሌላው ነጥብ ሲሆን ጥቃቱ በሴቶች ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ቢሆንም እንኳን ከተጠያቂዎቹ 69 በመቶ የሚሆኑት እንደሚሉት ሴቶች ስለተፈጸመባቸው መናገርን አሳፋሪ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ እነኚሁ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶችም ተጠቂዎቹ የቤተሰብን ገመና ለመጠበቅ በሚል ለሕግ አካላት ጉዳዩን ከማመልከት እንደሚቆጠቡ ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም የጥናቱ ውጤት እንደሚያመለክተው በማኅበረሰቡ ዘንድ ስለ ቤት ውስጥ ጥቃት ያለው ግንዛቤ አናሳ ቢሆንም እየተሻሻለ ነው፡፡ ጥናቱ በአስፈፃሚ አካላት የቤት ውስጥ ጥቃትን በተመለከተ ያለውን አነስተኛ የሕግ ሽፋን በማስፈጸም በኩል ቸልተኝነት ያሳያሉም ይላል፡፡ በፖሊስ በኩል ለምሳሌ የቤት ውስጥ ጥቃትን እንደ ከባድ ወንጀል ያለማየት ሁኔታ አለ፡፡ በመሆኑም በፖሊስ አመዘጋገብ የቤት ውስጥ ጥቃት ተለይቶ አይመዘገብም፡፡ ሌላው ቀርቶ እንደ ሌብነት ያሉ ወንጀሎች ከቤት ውስጥ ጥቃት ይልቅ ክብደት ይሰጣቸዋል፡፡ በመሆኑም ፖሊሶች ሴቶች እርቅ እንዲመሰርቱ ከማድረግ ባለፈ ጉዳዩ ላይ ምርመራ አያከናውኑም፡፡ ምንም እንኳን አጥቂዎች በቀላል ዋስ የሚለቀቁና ፖሊስም አፋጣኝ ምርመራ ለማድረግ ግድ የማይለው ቢሆንምየቤት ውስጥ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ሪፖርት ይደረጋሉ፡፡ ለሕግ አስፈፃሚዎች ከሚቀርቡ የቤት ውስጥ ጥቃት ዓይነቶች ተገዶ መደፈር፣ ድብደባና የአካል ጉዳት በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይም ቢሆን በቅርብ ሰዎች /በባሎችና ወንድ ጓደኞች/ የሚፈጸም ጥቃት ለብቻው አልተመዘገበም፡፡ በሴቶች ላይ በተደጋጋሚ ለሚደርሱ ጥቃቶች ደግሞ ሴቶቹን ለመጠበቅ እንዲቻል አጠገባቸው እንዳይደርሱ የሚያግድ ትዕዛዝ አይሰጥም፡፡ ጥናቱ በተጨማሪም በቤት ውስጥ ጥቃት ላይ ያተኮሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሥራዎችን በተመለከተ አስገራሚ ጥረቶች ቢታዩም የተቀናጁ ግን እንዳልነበሩ ጠቅሷል፡፡ በዚህ ረገድ የሴቶች ጉዳይ ጽ/ቤቶች እና የሴቶች ማኅበራት በተጠቂዎች የሚታመኑባቸው ተቋማት መሆናቸው በጥናቱ ውጤቶች ተጠቁሟል፡፡ ከሚፈጸሙ የቤት ውስጥ ጥቃት ድርጊቶች አብዛኞቹ ከእነኚህ ድርጅቶች ሪፖርት የሚደረጉ ሲሆን ድርጅቶቹም ጥቃቱን ለመዋጋት የተቻላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለጥናቱ መነሻ የሆነውና በጥናቱም የተረጋገጠው ዋና ነጥብ የቤት ውስጥ ጥቃት በብዙ ማኅበረሰቦች ዘንድ አሳሳቢ በሆነ መልኩ እንደ ተራና የተለመደ ጉዳይ እየተቆጠረ መጥቷል፡፡ ከቤት ውስጥ ጥቃት ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ደግሞ በሴቶችና በልጃገረዶች ላይ የሚፈፀም ነው፡፡ ሕፃናትና ሌሎች የቤተሰብ አባላትም የዚህ ጥቃት ሰለባ የሚሆኑበት ጊዜ አለ፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶችና ልጃገረዶችም ድብደባ፣ ትንኮሳ፣ ስድብና ማንቋሸሽ እንዲሁም ሌሎች የጥቃት ዓይነቶች በየቀኑ እየተፈፀሙባቸው ችለው ይኖራሉ፡፡ በጥናቱ ማጠቃለያ እንደተቀመጠው የቤት ውስጥ ጥቃት የገጠርና የከተማ ሳይባል ኢትዮጵያውያን ሴቶችን እየጎዳ ነው፡፡ በጥቃቱ የሚመጡ ጉዳቶች ደግሞ ሞት፣ አካል ጉዳት፣ ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ ፍቺ፣ የቤተሰብ መበተን፣ የንብረት መጥፋት፣ በራስ መተማመንን ማጣት፣ የደም ግፊት መጨመርና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ የቤት ውስጥ ጥቃትን ሴቶቹ ያላቸው አስተሳሰብ ደግሞ ለምሳሌ ባል በማንኛውም ምክንያት ሚስቱን መምታት ይችላል፣ አንዲት ሴት ባሏ/ጓደኛዋ ወሲብ በሚጠይቃ ጊዜ መቃወም አትችልም የሚል አመለካከት አላቸው፡፡ በጥናቱ የተካተቱት ሴቶች ያንጸባረቁት ደግሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን አመለካከት ነው፡፡ ጥናቱ የቤት ውስጥ ጥቃትን በማስቆም ረገድ በፖሊሲና በተግባር ደረጃ በጎ ጅማሬዎች እንዳሉ ቢጠቁምም ድርጊቱን ከማስቆም ደረጃ የሚመለከታቸው አካላት መቀናጀታቸው የግድ እንደሆነ ገል..ል፡፡ ጥናቱ የመፍትሄ ሃሳቦችን በተመለከተ መጠይቅ የተደረገላቸው ተካፋዮች ምን መደረግ አለበት? ለሚለው ያስቀመጡትን በመግለፅ ይጀምራል፡፡ ይኸውም በጤና ተቋማት በኩል በቤት ውስጥ ጥቃት ለተጠቁ አገልግሎት መስጫ ማዘጋጀት አለባቸው፣ ኅብረተሰቡንም ከቤት ውስጥ ጥቃት ጋር ተያይዞ የሚመጡ የጤና ችግሮችን በተመለከተ ማስተማርም ይገባል የሚሉ ናቸው፡፡ ፖሊስም ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት ለመከላከል ከማኅበረሰቡ ጋር ቢሠራ ስለ ቤት ውስጥ ጥቃት ለፖሊስ ሥልጠና ቢሰጥ፣ ብዙ ሴት ፖሊሶች ቢኖሩ፣ የድብደባና ሌሎች ወንጀሎች በአግባቡ ቢመዘገቡ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ አጠቃላይ የመፍትሄ ሃሳብ ደግሞ የማኅበረሰቡ የዕውቀት የቤት ውስጥ ጥቃት እንዲቀጥል አስተዋፅዖ እያደረገ በመሆኑ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ኅብረተሰቡን ማስተማር አለባቸው የሚለው የመጀመሪያው ነው፡፡ ሴቶች ስለ ጥቃቱ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግና የኢኮኖሚ አቅማቸውን ማዳበር፣ የሕግ ማዕቀፍ ያሉበትን ክፍተቶች መሙላት እና በየደረጃቸው ያሉ የማስፈጸም አቅም ማስወገድ በቅደም ተከተል የቀረቡ ናቸው፡፡ ተከታታይ ጥናት ማድረግ፣ በት/ቤት ደረጃ ማስተማር/ስለ ሰብዓዊ መብትና የጥቃት አስከፊነት ማስተማርና መንግሥት ከሌሎች አካላት ጋር ተባብሮ መሥራቱ ሌሎች ተጠቃሽ ነጥቦች ናቸው፡፡ ጥናቱ የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርና መንግሥትን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት ለሚያከናውኗቸው ተግባራት ግብዓት ይሆናል ተብሎ እንደሚታመን ወ/ሮ የሺሃሳብ አመልክተዋል፡፡ በቤተልሔም ነጋሽ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |