| የተዋልዶ ጤና መብቶቻቸውን ማስከበር... |
|
| Sunday, 05 October 2008 | |
|
የተዋልዶ ጤና መብቶቻቸውን ማስከበር ላልቻሉ በአፋጣኝ መድረስ ያስፈልጋል ተባለ
ፈጣንና አስተማማኝ ዕድገት ለማረጋገጥ አሁንም በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተፅዕኖዎች ምክንያት የተዋልዶ ጤና መብቶቻቸውን ማስከበር ላልቻሉ ወገኖች በአፋጣኝ መድረስ ለአፍታም መዘንጋት የሌለበት አገራዊ ጉዳይ መሆኑን የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር አስታወቀ፡፡ "የተዋልዶ ጤና ለሁሉም" በሚል መሪ ቃል ከትናንት ጀምሮ ለሁለት ቀናት በመከበር ላይ ያለውን ልዩ ዝግጅት አስመልክቶ ማህበሩ መስከረም 22 ቀን 2001 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የጤና መብቶቻቸውን ማስከበር ላልቻሉ ወገኖች ፈጥኖ ለመድረስም ከመሰል ድርጅቶች ጋር የተቀናጀ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ለጥረቱም እውን መሆን በተለያዩ ክልሎች ባቋቋማቸው 18 ክሊኒኮች፣ 28 የወጣት ማዕከላትና ከ6ሺህ በላይ በሚሆኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አራማጆች በመታገዝ ላይ መሆኑን አስረድቷል፡፡ በተለይ ለወጣቶች ተዋልዶ ጤና አገልግሎት መስፋፋትና መጠናከር፣ ለጤናማ እናትነት መጎልበት፣ ለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት መገታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ማህበሩ አመልክቶ በተዋልዶ ጤናው የአገልግሎት ዘርፍ በየጊዜው የሚፈጠሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ አገር በማስገባት ለአገልግሎት ጥራት መሻሻል የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከቱን አስረድቷል፡፡ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እየተከበረ ባለው በዚህ ዝግጅት ላይ ማህበሩ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለሕዝቡ እየሰጠ ያለው አገልግሎት አዝናኝ በሆነ መልኩ የሚቀርብ ሲሆን ለማህበሩ ዓላማ መሳካት አይነተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉ የረዥም ጊዜ ያገለገሉ በጎ ፈቃደኞች ይሸለማሉ፡፡ በአገሪቱ የቤተሰብ ምጣኔ ፅንሰ ሀሳብ እንዲሰርጽና አገልግሎቱ እንዲስፋፋ በፋና ወጊነት ተጠቃሽ የሆነውና ለትርፍ ያልቆመው ይኸው የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር በጥቂት ሆኖም ትልቅ ራዕይ በሰነቁ በጎ ፈቃደኞች የተቋቋመው በ1958 ነው፡፡ በፕሮጀክት ማኔጅመንት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ሊሰጥ ነው ዚመን ዴቪሎፕመንት ኤንድ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በተለያዩ የልማት ዘርፎች በተሰማሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ለሚገኙ ባለሙያዎች በፕሮጀክት ማኔጅመንት ላይ ያተኮረ የአጭርና የረጅም ጊዜ ሥልጠና ከሚቀጥለው ሕዳር ጀምሮ እንዲሚሰጥ አስታወቀ፡፡ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማ የሚያስገኘው ይኸው ሥልጠና የሚያተኩረው በጤና፣ በትምህርትና በኮንስትራክሽን ዘርፎች በተሰማሩ መንግሥታዊ ድርጅቶችና ለትርፍ ባልቆሙ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ለሚገኙ ባለሙያዎች መሆኑን ኢንስቲትዩቱ አስረድቷል፡፡ በፕሮጄክት ማኔጅመንትና ልማት ላይ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና የመስጠት ተልዕኮ ያነገበው ይኸው ኢንስቲትዩት ሥልጠናውን የሚሰጠው ከካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር መሆኑንም አስታውቋል፡፡ |
|
| Last Updated ( Sunday, 05 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |