| ደቡብ አፍሪካ ለተፈናቃዮች... |
|
| Sunday, 05 October 2008 | |
|
ደቡብ አፍሪካ ለተፈናቃዮች እርዳታ መስጠት አቆመች
ድርጅቱ እንደገለፀው ፕሪቶሪያ አጠገብ በተሰራ ካምፕ የሚኖሩ 700 ያህል የውጭ አገር ዜጎች የደህንነት ጥበቃና የምግብ እርዳታ አያገኙም፡፡ ሜዲካል ቻሪቲ ሜዲሲን ሳን ፍሮንቴየር "ስደተኞቹ ደቡብ አፍሪካን ጥለው እንዲሄዱ ለማስገደድ የተደረገ ሙከራ በመሆኑ ድርጊቱ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የለውም" በማለት የደቡብ አፍሪካን መንግሥት ውሳኔ ተቃውሟል፡፡ የአገሪቱ ባለስልጣናት በግንቦቱ ወር ጥቃት ለተፈናቀሉ የውጭ አገር ዜጎች መጠለያ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ ካምፖች እንዲዘጉ ይፈልጋሉ፡፡ ባለፈው አመት ግንቦት ወር በተፈፀመው ጥቃት 80"000 (ሰማንያ ሺህ) የሚደርሱ የውጭ አገር ዜጎች ከቤታቸው መፈናቀላቸውንና 62 መገደላቸውን ተመድ አስታውቋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የስደተኞች ድርጅት ግን የተፈናቃዮቹን ቁጥር 100"000 ያደርሰዋል፡፡ በአካዥያ ካምፕ የሚገኙት አብዛኞቹ ስደተኞች የሱማሊያ፣ የኢትዮጵያ እና የብሩንዲ ዜጎች መሆናቸውንና ብዙዎቹም የመኖሪያ ፈቃድ የተሰጣቸው መሆኑን ኤም.ኤስ.ኤፍ ገልጿል፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት በግንቦቱ ወር ጥቃት ለተፈናቀሉ 1200 የውጭ አገር ዜጎች መጠለያነት ሲያገለግሉ የነበሩ ሶስት ካምፖች በደቡብ አፍሪካ መንግስት ትዕዛዝ እንዲዘጉ ተደርገዋል፡፡ ካምፖቹ እንዲዘጉ የተደረጉት በህገመንግስት ጉዳይ የሚነሱ ጥያቄዎችን የሚመለከተው የአገሪቱ ፍርድ ቤት ካምፖቹ ክፍት ሆነው እንዲቆዩ ያስተላለፈውን ውሳኔ በመጣስ ነው፡፡ ስደተኞቹ ተጠልለውበት የነበረው የጋውቲንግ አውራጃ መስተዳድር ግን አሁን ሰላም የሰፈነ በመሆኑ ተፈናቃዮቹ የውጭ አገር ዜጎች ወደ ቤታቸው መመለስ አለባቸው ብሎ ይከራከራል፡፡ ሩሴል ማስክሮጋር የተባሉ የአካባቢው የማህበረሰብ ልማት ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር የተዘጉት ካምፖች ተመልሰው የሚከፈቱበት ምንም አይነት ምክንያት እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ ከአፓርታይድ መውደቅ በኋላ እጅግ አስከፊ ደም መፋሰስ ያስከተለው ያለፈው ዓመት የግንቦት ወር ግጭት ከጁሀንስበርግ በስተሰሜን በምትገኝ አንዲት ከተማ ውስጥ ተጀምሮ ነው ግጭቱ ሌሎቹንም የአገሪቱን ክፍሎች ያጥለቀለቀው፡፡ በግጭቱ ጊዜ በፖሊስ ጣቢያ፣ በቤተክርስቲያን እና በመሰብሰቢያ አዳራሾች መጠጊያ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ ከነበሩት የውጭ አገር ዜጎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ዚምባብዌያን ሲሆኑ፣ አገራቸውን ጥለው የሄዱት ግጭትንና ድህነትን በመሸሽ ነበር፡፡ ሶስት ሚሊዮን የሚደርሱ ዚምባብዌያውያን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ ደቡብ አፍሪካ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ስደተኞች በአገሪቱ ለሚታየው ማህበራዊ ቀውስ፣ ስራ አጥነት እና ወንጀል መስፋፋትና የቤት እጥረት ምክንያት ተደርገው ይታያሉ፡፡ እውነታው ግን በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ በርካታ ጥገኝነት ጠያቂዎችና ስደተኛ ሴቶች በአገሪቱ ሥራ የማግኘት እድላቸው በጣም ጠባብ መሆኑ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ኑሮአቸውን የሚገፉት በጉልበት ሥራ ተሰማርተው ነው፡፡ ስደተኞቹ የጉልበት ሠራተኛ ሆነው የሚቀጠሩት ህጋዊ ባልሆነ እና የመንግሥት ቁጥጥር በማይደረግበት የሥራ ዘርፍ ውስጥ ነው፡፡ በዚህም በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ድርጀቶች ማለትም በጤና፣ በትምህርት እና በፍትህ የሥራ ዘርፎች የመቀጠር እድላቸው በጣም ጠባብ ሆኗል፡፡ የግንቦቱን ግጭት የቀሰቀሱት ደቡብ አፍሪካውያን በውጭ አገር ዜጎች ላይ ድብደባ ፈጽመዋል፡፡ ስደተኞችን በጩቤ ወግተዋል፡፡ በርካቶችን ገድለዋል፡፡ የፈሩትን ንብረታቸውን ዘርፈውባቸዋል፡፡ ቤታቸውን አቃጥለውባቸው ተቀምጠዋል፡፡ ጥቃቱ የበለጠ አስከፊ የሆነው ደግሞ የውጭ አገር ዜግነት ባላቸው ሴቶች ላይ ነው፡፡ የውጭ አገር ዜጋ የሆኑት ሴቶቹ በተፈጠረው ቀውስ በጣም የተጎዱት ድብደባና የአስገድዶ መደፈር ስለሚፈጸምባቸው ብቻ ሳይሆን የቤት ማቃጠልና ዝርፊያ በሚፈጽምበት ጊዜ ብዙውን ጊዜ በቤታቸው ውስጥ ስለሚገኙ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ በወንድ የበላይነት የሚያምኑ ህዝቦች የሚኖሩባት አገር መሆኗ የማያከራክር ጉዳይ መሆኑን በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ ወንዶችና በውጭ አገር ወንዶች መካከል ለተፈጠረው ግጭት የደቡብ አፍሪካ ሴቶች ምክንያት ተደርገው ተወስደዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካውያን ወንዶች የውጭ አገሮቹን ወንዶች ሚስቶቻችንን አባልገውብናል በማለት ይወነጅሉዋቸዋል፡፡ በውጭ አገር ዜጎች ጥላቻ በተነሳው ግጭት በሴቶች ላይ በርካታ የአስገድዶ መደፈር ወንጀሎች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች ቀርበዋል፡፡ ተጠንቶ የተፈጸመ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል አብዛኛውን ጊዜ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመፈጸም የሚያስችል መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ በግጭት ጊዜ በሴቶች ላይ የሚፈፀም አስገድዶ መድፈር ወንጀል በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ትስስር የማጥፋት አቅም እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በግጭት ጊዜ በተፈጠረ አስገድዶ መድፈር የተጠቁ ሴቶች የሚይዙት ቂምና ጥላቻ ብቻ አይደለም፡፡ ከእነሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ወንዶች በሙሉ ጥቃታቸውን ካልተበቀሉላቸው እነሱን ለመከላከል አቅም የሌላቸው እንደሆኑ አድርገው በነገር ጎሸም ያደርጓቸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ በግጭት ወይም በጦርነት ጊዜ የሚፈጸም አስገድዶ መድፈር የዘር ማጥፋት ወንጀል ማስፈጸሚያ ዘዴ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል በየቀኑ በሚፈጽምባት ደቡብ አፍሪካ ግን በውጭ አገር ሴቶች ላይ የተፈፀመው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል በውጭ አገር ዜጎች ላይ ከመነጨ ጥላቻ ጋር የተያያዘ መሆኑንና አለመሆኑን ለማወቅ እንደሚያስቸግር ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |