| “ብድር በምድር” ነበር አይደል?” |
|
| Sunday, 05 October 2008 | |
|
(በክርስቲና አያሌው፣ ከደሴ)
በምሥራቅ አማራ ትልቋ የንግድና የኢንቨስትመንት ከተማ ተብላ ከምትታወቀው ደሴ ከተማ፤ የውቦቹ ሀገር ተብላ ለዘመናት ከምትወደሰው ደሴ እነ ወይዘሮ አበበች ተስፋዬ፣ አቶ ጉልማ ለገሰ፣ አቶ ከበደ ሙሄ፣ አቶ ኤፍሬም ወልደሰማያት ሁሉ ይኖሩባታል፡፡ እነዚህና ሌሎች ከዘጠኝ መቶ የሚሆኑት ሰዎች የመሥራት አካላዊ አቅምና ሃብታቸውን በመጠቀም የዕለት ተዕለት ችግራቸውን ለማቃለል አንዱን ሲይዙት፣ ሌላውን ሲለቁት የኑሮው ጣዕሙ አልበጅ ብሏቸው ዛሬ ድረስ አሉ፡፡ በሕይወት ሽክርክሪት ውስጥ እንደሚሆን፣ መንገድ ዳር ብጣሽ ከረጢት ተዘርግታ ነፋስ ጠቅልሎ እንዳያነሳት በየማዕዘኗ በድንጋይ ተቆንጥጣ ጥልዝ ብሎ የጠወለገ ትንንሽዬ ጥቅል ጎመን፣ ጥርምትምት ያለ ቃሪያና ካሮት፣ የተጠራሞተ ቲማቲም ኮልኩለው እሸጣለሁ፤ ግዡ ውድ ነው፣ አልመርቅም ይቅር እንዳሉ ገበያው ሳይደራ፣ ወረቱም ሳይሰራ ድፍት ቅንት ሲሉ ውለው ይገባሉ፡፡ ይህ ሳይሆን ደግሞ የፕላስቲክ ሸራ ወጥረው ዳስ ቢጤ ቀለስ ተደርጎ ሁለት ብርጭቆዎች ይደረድሩና “ሻሂ አለ” ተብሎ በከሰል ዱቄት ካርቶን ላይ በተጻፈ ወልጋዳ የጽሑፍ ማስታወቂያ ታውጆ የሻይ ቡና ንግዱ ሊጧጧፍ ይሆናል፡፡ እናም ጧት የተጣደ የሻይ ማፍያ ዕቃ ቀኑን ሙሉ ብቻውን ሲዘፍን ውሎ ከሁለቱ ብርጭቆዎች አንዷ እንኳ ሳትቀዳለት ቀኑ መሽቶ ኪሳራውን ትርፍ ብሎ መቀበል ሳይወዱ ግዳቸው ሆኖ የሚኖሩ ናቸው፡፡ እንዲህም አሉ እንዲያ ካሏቸው ከሦስት እስከ ስድስት የሚደርሱ ቤተሰቦቻቸውና ነብስ ያላወቁ ቡቃቅላዎቻቸው ጋር የኮቾሮ ፍርፍርና የገብስ ቡና ለሁሉም አንጀት ትራስ ሆኖ ያድራል፤ ለነገም ቆንጅዬ ተስፋ ሆኖ ያልቃል፡፡ እነዚሁ ጎልማሶች፣ ወጣቶችና እናቶች ያን ከመሰለው የተንኳተተ አኗኗር ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለማላቀቅ ያስችላቸው ዘንድ ያዋጣናል፣ ይለውጠናል ባሉት የንግድና የሥራ መስክ ለመሰማራት ከያሉበት ተነሳሱ፡፡ እርግጥ ወኔና መሥራት መቻል ብቻውን ወረት ስላልሆናቸው መጠነኛ የገንዘብ ወረት ለማግኘት ተፈላለጉ፡፡ በአንድ ተቀናጁና ቡድን ቡድን ፈጠሩ፡፡ ለሥራቸው የሚፈልጉትን የሥራ መነሻ ብድር ገንዘብ ለማግኘት በማኅበር መደራጀት ግድና ግድ በመሆኑ፡፡ “መመሪያ ነው” አሉ፡፡ ይህች ብድር በዋዛ የማትገኝ፤ ግን ደግሞ የሁሉንም ተቧዳኝ ሰዎች የእንጀራ እጣ ፋንታ የምትወስን ናትና የተጠየቀውን መስፈርት አሟልቶ ለመገኘት ወደኋላ ያፈገፈገ የለም፡፡ በመሆኑም የንግድ ሥራ ፈቃድ በማውጣት፣ የመሥሪያ ቦታ በማፈላለግ፣ ቢዝነስ ፕላን በማዘጋጀት በኩል በግልም በቡድንም ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል፡፡ ሕጋዊ ሆነው የብድር ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችላቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አጠናቀቁ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ብድር እንዲያገኙ ፎርማሊቲዎችን እንዲያሟሉ ባለው መሰረት በመሆኑ ነው፡፡ አቶ ጉልማ ለገሠና አቶ ከበደ ሙሔ እንዳሉት፣. “ብድሩን ለማግኘት የሚያስችላችሁን መሥፈርቱን በሙሉ ብታሟሉ አሁን ለብድር የሚውል ገንዘብ ባለመኖሩ ልናስተናግዳችሁ አንችልም ተባልን፡፡ መንግሥት መሥራት ለቻለ ዜጋ “ሜዳውም ያው ፈረሱም ያውሉት” ያለውን ሰምተን እውነት መስሎንና ብዙ ብዙ ደጅ ጠናን፣ ባልጠበቅነው ሁኔታ ተንገላታን” ብለዋል፡፡ ባዘጋጁት የቢዝነስ ፕላን ብድር በማግኘት ዳቦ ቤት ለማቋቋም፣ የእህል ንግድ ለማካሄድ፣ የሸቀጣ ሸቀጥ ሽያጭ፣ የባልትና ሙያ ውጤቶች ሥራ መፍጠር እንዲችሉ ብሎም በዶሮና በግ እርባታ ለመሰማራት ሰርተው ከድህነት ጋር በልዩነት ለማደር አቅደው ነበር፡፡ ለዚህም አሁን ድረስ ጎልቶ ከሚታየው የመስራት ጉጉታቸውና ተነሳሽነታቸው ጋር የሚደመር ቢያንስ በነፍስ ወከፍ ከአምስት ሺህ እስከ ሰባት ሺህ ብር የሚያስፈልጋቸው የነበረ ቢሆንም ገንዘብ በብድር ማግኘት ዘበት ሆነ፡፡ የሥራ ማካሄጃውን ወጪ (ወረት) ከውጫዊ አካል ማግኘት እንደቅዥት አሰቡት፡፡ የተጠየቀውን መስፈርትም ለማሟላት ሲባል ባልበላ አንጀታቸው ከደሴ መግቢያ ጫፍ እስከ ደሴ መውጫ ጫፍ መንከራተታቸውን ምናልባት ጦሳ ተራራ ታዝቦ ይሆናል፡፡ እነሱ ግን አልታከቱም ነበር፡፡ ይሆናል ብለው ለማይሆን ከዚህም ከዚያም ከምንም ብለው ለጉዳዩ ያወጡት ወጪ “መርፌ ውጦ ማረሻ ተፋ” እንዲሉ ሆኖባቸዋል፡፡ “ተበድረን ተደግፈን ያገኘናትን ገንዘብ ለብክነት መዳረገችን፣ ባወጣነው የንግድ ሥራ ፈቃድ ግብር ዕዳ ማከማቸታችንና ለመሥሪያ የተከራየነው ቦታ ያለጥቅም መቀመጡ ለባሰ ችግርና ውጥረት ዳርጎናል” ያሉት በምሬትና በተሳቀቀ ሁኔታ ነበር፡፡ እነዚያ ከርታታዎች እንዳሉት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ተገቢውን ግልጋሎት ከመስጠት ይልቅ ያተረፈላቸው ልዩ ነገር መገላመጥ፣ መንከላፈት፣ መሰደብና መዋረድ ብቻ ነው፡፡ ተቋሙ ለብድር የሚውል በጀት የለም፡፡ ይበል እንጅ እስካሁን ለመሰል ብድር ፈላጊዎች ብድር እየሰጠ ስለመሆኑ ወደ ተቋሙ ሲሄዱ፣ ሲመለሱ ታዝበዋል፡፡ ታዲያ አሰራሩ በአድልኦ የተዝረከረከ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለው ነግረውኛል፡፡ የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ካሉት የዞን ቅርንጫፎች መካከል አንዱ የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ነው፡፡ ይህ ቅርንጫፍ በአሁኑ ወቅት በገጠርና በከተማ በሚገኙ ሃያ ስምንት ንዑስ ቅርንጫፎች ተደራጅቷል፡፡ ባለው ሥልጣንና ሃላፊነትም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ከቁጠባና ከለጋሽ ድርጅቶች፣ ከክልሉ መንግሥት በሚገኝ ድጋፍ እንዲሁ ህብረተሰቡ ከሚያስቀመጠው ከራሱ የቁጠባ ገንዘብ የብድር አገልግሎት ይሰጣል፡፡ “ከአምስት እስከ ሰባት የሚደርሱ ብድር ፈላጊዎች በማህበር ተደራጅተው ሲመጡ ማህበራቸውን ዋስትና በማድረግ እስከ ሶስት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር የሚደርስ ገንዘብ በብድር ማግኘት ይችላሉ” ይላል ያ የተፃፈው ነገር፡፡ (የተቋሙ የብድር አሰጣጥ መመሪያ) ይህ መመሪያ ሥራ ላይ እየዋለ ያለመሆን ግን ቅሬታዎች መከፋቶች የሚዥጎደጎዱበት መመሪያ፡፡ በአሁኑ ወቅት ተቋሙ የብድር አቅሙ 230 ሚሊዮን ብር መድረሱን የገለፁልኝን የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ አቶ መከተ ካሣ፣ የደሴዎቹ ችግረኞችየመቋቋሚያ ብድር ፈላጊዎቹ ከተሜዎች ብሶት ምንጩ ምንድነው? አልኳቸው፤ የሚባለው እንዲህ የሚሆነው ሌላ”. ብዬ ጠየቅኋቸው እንዲህም መለሱልኝ፡፡ “ተቋማችን ቀደም ሲል የገጠሩንና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕከል በማድረግ የብድር ሥርጭት ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ካለፈው ዓመት ወዲህ ግን በከተማ ለሚገኙ ድሆች ብድር እየተሰጠ ነው፡፡ ይሁንና ችግሩ ሊከሰት የቻለው የከተማው አነስተኛና ጥቃቅን ንግድ ሥራዎች ማስፋፊያ ጽህፈት ቤትና የቀበሌ አስተዳደሮች የከተማውን ብድር ፈላጊዎች የማደራጀትና ለመመሪያው ተገዥ የማድረግ ሥራ ዘግይተው መጀመራቸውና ረጅም ጊዜም በመፍጀታቸው ሲሆን፣ የተያዘው የብድር በጀትም ቅድመ ሁኔታዎችን ቀድመው ላጠናቀቁ፣ የአገልግሎቱ ፈላጊዎች እንጥፍጥፍ ተደርጎ ተሰጥቷል፡፡ ዘግይተው የመጡትን እንደመጡ ለማስተናገድ ገንዘቡ አለቀ” አሉ፡፡ በአንድ በኩል እስካሁንም ተቋሙ የማከፋፈሉን ሥራ እንደቀጠለ ነው፡፡ በሌላ በኩል ብድር ፈላጊዎች ገንዘብ ስለአለቀ አሁን ልታገኙ አትችሉም መባሉ ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የብድር ሥርጭት አሰራር እንደምትከተሉ ያመለክታልኮ? አልኳቸው ሥራ አስኪያጁን አቶ መከተን፤ እንዲህም መለሱ፤ “ተቋሙ ራሱ በራሱ መመሪያ አደራጅቶ የሚያበድራቸው መደበኛ ተበዳሪዎች አሉት፡፡ በተቋሙ በተከታታይ የሚበደሩ ደግሞ የሚመልሱ እንዲሁም የሚቆጥቡ እስካሁን ይስተናገዳሉ፡፡ በተጨማሪም በሌላ አካል ተደራጅተው ብድሩን እንድናበድር ብቻ ስለሆነ የመጣላቸው የብድር ገንዘብ ካለቀ እስኪመጣላቸው ድረስ ለጊዜው ሊቋረጥ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የአሰራር ልዩነት እንጂ የአድልኦ ማመልከቻ (ጠቋሚ) አይደለም፡፡ አሰራራችን እስካሁን አድልኦ የሌለበት መሆኑን በተለያዩ መንገድ አረጋግጠናል፡፡ ይህ መሰሉ አስተያየት የሚመነጨው ሰዎች የፈለጉትን ያጡ ጊዜ ነው፡፡” ተቋሙ ባለበት ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች ሳቢያ ተበዳሪዎቹ ለችግር መዳረጋቸውን ራሱ ተቋሙ ያምናል፡፡ የአገልግሎቱን ፈላጊዎች “በደንበኛ ንጉሥ ነው” ወግ መያዙ ቀርቶ የሰዎቹን ተደራራቢ ችግሮች ታሳቢና መሰረት ያደረገ መፍትሄስ ምን አለ?” ሲመልሱም፣ “የብድር መጠየቂያ መረጃቸው በተቋሙ የሚገኝ በመሆኑ የብድር ገንዘቡ እንደተለቀቀ (እንደመጣላቸው) በቅድሚያ የሚስተናግዱት እነዚሁ ሰዎች ይሆናሉ” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ እርግጡ ነገር ብድር ፈላጊዎቹ በእጅጉ ተጉላልተዋል፡፡ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በዙሪያቸው አሉ፡፡ ሆኖም ባዶ የሆነው የተቋሙ ካዝና በቅርብ ጊዜ ውስጥ መልካም ሁኔታ ይኖረዋል፡፡ የብድር ባጀቱ በቅርቡ (እስከ መስከረም መጨረሻ) ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህም ግንባር ቀደም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |