Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ቡታጅራ
ቡታጅራ E-mail
Sunday, 05 October 2008
Imageበጌታቸው ንጋቱ

ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምዕራብ በ132 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ቡታጅራ ከተማ የመስቀል በዓልን ተንተርሣ ሰሞኑን ሞቅ ደመቅ ብላ ነው የሰነበተችው፡፡ ቡታጅራ የመስቀል በዓልን ለማክበር በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ተወላጆቿ ተሰባስበውባታል፡፡ የወረዳዋ ስያሜ በቅርቡ በመስቃንና ዶቢ በመባሉ የአካባቢው ነዋሪዎች መስማማት ባለማስገኘቱ ታስረው የነበሩት ብዛት ያላቸው ሰዎች ለበዓሉ መለቀቃቸው በዓሉን ደማቅ አድርጎታል፡፡ ቡታጅራ 37..163 ነዋሪዎች እንዳሏት የማዕከላዊ እስታስቲክስ መረጃ ያሳያል፡፡
ከአዲስ አበባ እስከ ቡታጅራ ያለው መንገድ በአገራችን የመንገድ ልማት መሠረት የተሠራ ደረጃውን የጠበቀ የአስፋልት መንገድ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ወደ ሆሳዕና የሚወስደው አውራ ጎዳና ቡታጅራን አቋርጦ ያልፋል፡፡ ወደ ቡታጅራ ሲሄዱ እግረ መንገድዎን የጢያ ትክል ድንጋይን የመጎብኘት እድልም ያገኛሉ፡፡

ከአዲስ አበባ ስንነሣ ቡታጅራን አይተናት ስለማናውቅ፣ እንደ ሌሎች የገጠር ከተሞች የደከመ እንቅስቃሴ ነበር የጠበቅነው፡፡ ወደ ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እየተቃረብን መምጣታችንን የአካባቢው ልምላሜና የእርከን ሥራዎች እየነገሩን ነው፡፡ ቡታጅራ ከተማ ስንገባም ይኸው ልምላሜ አልተለየንም፡፡

በዓል ቢሆንም ከተማዋ መንገድ ላይ ሰዎች በዛ ብለው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ዕለቱ መስከረም 17 የመስቀል ዕለት በመሆኑ ከተማዋ በዓል በዓል ትሸታለች፡፡ ስለቡታጅራ ከተማ ነዋሪዎች እና በአጠቃላይ ስለ ጉራጌ ሕዝብ መናገር የምንችለው ..ኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይ ናቸው.. የተባለው እንደዚህ ዓይነቶቹ ሕዝቦች ታይተው ነው በማለት ነው፡፡ ሁሉም ሰው ፊት ላይ ፈገግታ ይነበባል፡፡ በጉራጌ ባህል መሰረት ወደተጋበዝንበት መኖሪያ ቤት ስንገባ የማናውቃቸውም የምናውቃቸውም ፊቶች በእኩል ፈገግታና በእንኳን ደህና መጣችሁ ሞቅታ ተቀበሉን፡፡ አቀባበላቸው ከቤታችን እንዳለን አድርጎ ተሰምቶናል፡፡

በመስቀል የሚቀርበው ዋናው ምግብ ክትፎ በቆጮ ሲሆን ሰው በልቶ የሚጠግብ የማይመስላቸው ባለቤቶቹ ከአቅማችን በላይ እንድንመገብ በትህትናቸው አስገድደውናል፡፡ በቤት ውስጥ ያለው መስተንግዶ በተለያዩ ደረጃዎች እንደሚከፋፈል፣ ጎመንና አይብ የሚበላበት ሰዓት፣ ጥሬ ክትፎ የሚበላበት ጊዜ እንዲሁም የበሰለ ክትፎ የሚበላበት የተለየ ጊዜ እንዳለ አስጎብኛችን የሆኑት የአካባቢው ተወላጅ አቶ ማርቆስ ባኔር ገልፀውልናል፡፡ የአካበቢው ነዋሪዎች፣ ዘመድ አዝማድ፣ ጎረቤቶች አብረው ሆነው የጨዋታ፣ የሃሴትና የደስታ ጊዜ የሚያሳልፉበትና ልጆች ከወላጆቻቸው ምርቃት የሚቀበሉበት ልዩ ወቅት እንደሆነም አቶ ማርቆስ ይናገራሉ፡፡

ከቤት ውጭ ቡታጅራ ምን እንደምትመስል አስጎብኛችን አቶ ማርቆስ ሊያሳዩን ወጣን፡፡ በመጀመሪያ ያየነው የቡታጅራ ሆስፒታልን ይዞታ ነበር፡፡ በዓል በመሆኑ ኃላፊዎች በቦታው ባይኖሩም በሆስፒታሉ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ ማየት የምንፈልገውን እንዳናይ ምንም ዓይነት እንቅፋት አልፈጠሩብንም፡፡ ሆስፒታሉ ከሆስፒታልነት ይልቅ መናፈሻ ይመስላል፡፡ የግቢው ንጽህና፣ በግቢው ውስጥ ያሉ እጽዋት ለግቢው የሰጡት ግርማ ሞገስና ንጹህ አየር፣ በጥንቃቄ የተሰሩት የሆስፒታሉ ክፍሎችና መተላለፊያ ኮሪደሮች ምነው እንዲህ ታማሚን በመዓዛው ብቻ ሊፈውስ የሚችል ሆስፒታል ሁሉም ቦታ ቢኖር ያሰኛል፡፡ ስለ ሆስፒታሉ ጥራት፣ ስፋትና አቀማመጥ በመገረም ስንነጋገር አቶ ማርቆስ የቡታጅራ ሆስፒታል ሊያስደንቀን እንደማይገባ ከዚህ የበለጠ የምናየው ብዙ ነገር እንዳለ ነገሩን፡፡

ከቡታጅራ ሆስፒታል ወጥተን ጉዟችንን ወደ ግራር ቤት ተሃድሶ ሆስፒታል አደረግን፡፡ ከተማዋ ትንሽ ብትሆንም ይህ ሁለተኛው ሆስፒታል ከአገሪቱ ደረጃውን የጠበቀ የሚባል የአንገት በላይ ሕክምና የሚሰጥበት ተቋም መሆኑን ተረድተናል፡፡ ወደ ሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ስንገባ አፋችንን ከፍተን ተፈጥሮን ማድነቅ እንጂ ወደ አንድ የሕክምና ማዕከል የገባን አይመስልም ነበር፡፡ ሆስፒታል ስለመሆኑም ተጠራጥረን አስጎብኛችንን በጥያቄ እናጣድፈው ጀመርን፡፡ ግቢው ውስጥ እየተዘዋወርን ስንመለከት ሆስፒታል መሆኑን ረስተን ለመዝናናት ወደ ፓርክ የገባን መሰለን፡፡ በተለይም በዚሁ ቅጥር ግቢ ውስጥ የዱር እንስሳት ፓርክ መኖሩ ያስደንቃል፡፡ ታማሚዎች ራሳቸውን ዘና ለማድረግ ወደ ፓርኩ እንደሚመጡም ተገልጾልናል፡፡ የራሱ የተለየ ቅጥር ግቢ ባለውና በብረት በታጠረው ግቢ ውስጥ ጅብ፣ ገመሬ ዝንጀሮ፣ ሰጎንና ጃርት በተለያዩ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ አሁን ቁጥራቸው እየተመናመነ መምጣቱንና በፊት ግን ብዛት ያላቸው ሌሎች የዱር እንስሳት እንደነበሩም አቶ ማርቆስ ይናገራሉ፡፡

የመጀመሪያ ቀን ጉብኝታችንን አጠናቀቅን፡፡ ማንኛውም ሰው ከአዲስ አበባ ወደ ክፍለ ሃገር ሲመጣ መጀመሪያ የሚያሳስበው ነገር የመኝታ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እኛም ምን ዓይነት መኝታ እንደተዘጋጀልን ለመገመት የከተማዋን ገጠርነት በማሰብ ንፁህ ብቻ እንዲሆን ተመኝተናል፡፡ ግምታችንን ሁሉ መና ባስቀረ መልኩ ቡታጅራ ደረጃቸውን የጠበቁ መኝታ ክፍሎች ያሏቸው ሆቴሎችና እንግዳ ማረፊያዎች እንዳሏት ተረዳን፡፡ እጅግ ሰፊ ክፍል፣ ኪንግ ሳይዝ ሊባል የሚችል አልጋ፣ ቦይለር የተገጠመለት ሰፊና ንጹህ መታጠቢያ ክፍል፤ ከሁሉም በላይ ብዛት ያላቸው የዓለም አቀፍ ሚያያዎችን መከታተል የሚችሉበት ቴሌቪዥን መገኘቱ ከዚያች ትንሽ ከተማ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ሕዝብ ተሰብስቦ የሚያያቸውን የእንግሊዝና ስፔን እግር ኳስ ውድድሮች ካረፉበት ክፍል ሆነው መመልከት ይችላሉ፡፡ እንዲህ አይነት አገልግሎት ስም ያላቸው የአገራችን ክልል ከተሞች እንኳን የላቸውም፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ለሚለው ጥያቄ አቶ ማርቆስ ሲመልሱ፣ የአካባቢው ተወላጆች በተለያዩ ከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ በንግድ ሥራ ጥሩ ደረጃ ላይ በመድረሳቸው ለትውልድ አካባቢያቸው የተወሰኑ የልማት ሥራዎች ስለሚያበረክቱ ለውጦች እየታዩ መሆኑንና የከተማዋ የአንደኛ መንገድ ቦታዎችም ለተጨማሪ ልማቶች በሊዝ መሸጣቸውን ገለፁልን፡፡

በማግስቱ መስከረም 18 ቀን 2001 ዓ.ም በጠዋት ተነስተን ከቡታጅራ ከተማ ወጣ ብሎ ወደሚገኘው የተቦን ..ፕሮጀክት ሜርሲ.. በአስጎብኚዎቻችን ረዳትነት አመራን፡፡ ለተሽከርካሪ ብዙም ፈታኝ ባልሆነው ፒስታ መንገድ ሰባት ኪሎ ሜትር ያህል እንደተጓዝን ..ፕሮጀክት ሜርሲ.. ደረስን፡፡ የዚህ ፕሮጀክት መስራች ወ/ሮ ማርታ ገብረ ጻድቅ የአካባቢው ተወላጅ ሲሆኑ የአካባቢውን ሕብረተሰብ በጤና፣ በትምህርትና በእርሻ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ከፍተዋል፡፡ የመጀመሪያው የኦልሰን መታሰቢያ ሆስፒታል ነው፡፡ ሆስፒታሉ ሰፊ መሬት ላይ ተንጣሎ የተሰራ ነው፡፡ አልጋዎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ ከሆስፒታሉ ባገኘነው መረጃ መሰረት በአካባቢው ያለውን ኅብረተሰብ ጤና በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ግልጋሎት ሆስፒታሉ ይሰጣል፡፡ በአንዲት ትንሽ ከተማና በአካባቢዋ ታላላቅ ሶስት ሆስፒታሎችና ሌሎች ክሊኒኮች መኖራቸው የከተማዋንና የገጠር አካባቢዎቹን የተሻለ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ መገመት ቀላል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከቡታጅራ ራቅ ያሉ የጉራጌ ዞን አካባቢዎች ሆስፒታል እንደሌላቸው የአካባቢው ተወላጆች ያስረዳሉ፡፡

በፕሮጀክት ሜርሲ ስር መድኃኔ ዓለም የሚባል ትምህርት ቤት ይገኛል፡፡ ወደ ቅጥር ግቢው ስንገባ የትምህርት ቤቱ በጎ ፈቃደኛ ሰራተኛ የሆኑት አሜሪካዊው ዶ/ር ሮይ ኩልማን ትምህርት ቤቱን አስጎበኙን፡፡ ከ1500 በላይ ተማሪዎች ያሉት ይህ ትምህርት ቤት የተሻለ ጥራት ያለው ትምህርት እንደሚሰጥና ለልጆቻቸው የትምህርት ቤት ክፍያ መክፈል የማይችሉ አርሶአደሮች በጉልበታቸውና በበሬዎቻቸው ለትምህርት ቤቱ አገልግሎት ሰጥተው ልጆቻቸውን ማስተማር እንደሚችሉ ዶ/ር ሮይ ገልጸውልናል፡፡

በትምህርት ቤቱ ውስጥ ወላጅ አልባና ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ጋር የሚኖሩ የአካባቢው ሕጻናት የሚያድጉበት ክፍልም ይገኛል፡፡ ትምህርት ቤቱ የተለያዩ ዘመናዊ እርሻዎችን በማስፋፋት ለገበሬው ዘመናዊ እርሻን የሚያስተምር ሲሆን ከእርሻው የሚገኘውን ምርት ለተማሪዎች ቀለብ ያውላል፡፡ የከብት እርባታና የእንስሳት ማደለቢያም በዚሁ ድርጅት ውስጥ ይገኛል፡፡ የደለቡት ከብቶች ወደ አዲስ አበባ ተወስደው ይሸጣሉ እንጂ በአካባቢው አይሸጡም፤ ለምን ብለን ስንጠይቅ ዶ/ር ሮይ ሲመልሱ፣ ..እዚህ የምንሸጥ ከሆነ የገበሬውን ገበያ እንሻማለን፣ ይህ ደግሞ ያለንን ጥሩ ግንኙነት ያበላሽብናል.. ይላሉ፡፡ ዶ/ር ሮይ ስለ እያንዳንዷ እንቅስቃሴ ያደረጉልን ገለፃ ከአንድ ሰዓት በላይ የፈጀ ቢሆንም ከምናየው ድንቅ ተፈጥሮ እና መልካም ሥራ አንጻር ምንም ያህል የቆየን አልመሰለንም፡፡

በቡታጅራ በተለይ ለጤና ዘርፍ የተሰጠው ትኩረትና የአካባቢው ኅብረተሰብ ለለውጥና ለዕድገት ያለው ተነሳሽነት እጅግ የሚያስደንቅ ነው፡፡ በቡታጅራ በነበረን ቆይታ ተፈጥሮአዊውም ይሁን አካባቢያዊው ልማት መልካም የሚባል መሆኑን ተመልክተናል፡፡ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ አስተዳደራዊ ችግሮች እንዳሉ ግን ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ፡፡ በተለይም የወረዳው ስያሜ ባስነሳው ጠብ የተፈጠረው ችግር የሕዝቡን ሰላም እና የአካባቢውን ልማት የሚጎዳ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ነዋሪዎቹ ያስረዳሉ፡፡
Last Updated ( Sunday, 05 October 2008 )
 
< Prev   Next >