Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ደን ሲጠፋ ስደትና ዕልቂት ይከተላሉ
ደን ሲጠፋ ስደትና ዕልቂት ይከተላሉ E-mail
Sunday, 05 October 2008

በተስፋዬ ሁንዴ፣ ከደን ምርምር ማዕከል

ውኃ በምድራችን ላይ ሕይወት ያለው ፍጡር ሁሉ ከሚያስፈልገው መሠረታዊ ነገሮች አንዱና ዋነኛ ነው፡፡ ውኃ ለሕይወት አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን፣ ለሕይወትና ለልማት መጥፋትም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ይህም አሉታዊ ገጽታው የሚከሰተው ውኃ ከመጠን በላይ በሚበዛበትና ወይም እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት በሀገራችን በተደጋጋሚ በደረሰው ድርቅና የጎርፍ አደጋዎች የተቀጠፈውን የሰው ሕይወትና ያጠፉትን የልማት አውታሮችን ማስታወስ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ እንዲሁም በመዲናችን በየዓመቱ በክረምት ወራት ብቻ በልማት አውታሮች እና በሰው ሕይወት ላይ የሚደርሰውን ጥፋት ከምናየው እና ከምንሰማው ሁኔታ በጣም የሚያስደነግጥና የሚያስፈራ ነው፡፡

 

በቢልዮን ብር ወጪ የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ የአዲስ አበባ ዋና ዋና እና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በክረምት ወራት የሚሰጡት አገልግሎት ከመቀነሱም በላይ በየዓመቱ ለጥገና ተብሎ የሚወጣው ወጪ የከተማውን ዕድገት የሚፈታተኑት ዋነኛው ነው፡፡ በአጠቃላይ ሀገራችን በየዓመቱ በጎርፍ ምክንያት የምታጣው የሰው እና የቤት እንስሳት ሕይወት፣ ለም አፈር መጠን፣ የመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ የሚደርሰው ውድመት፣ ሌሎች የልማት ሥራዎችን ለማካሄድ ከምናወጣው ወጪ ጋር ተመጣጣኝ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

አብዛኞቹ የሀገራችን ከተሞች የተፋሰስ አያያዝ ፕላን ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ያላቸውም ቢሆኑ ሲተገብሩ አይታዩም፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ለሚሄደው የነዋሪዎችዋ ቁጥር በፍጥነት የከተማ ውኃ ተፋሰስ አያያዝ ፕላን ተግባራዊ ካልተደረገ ጥፋቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ የከተማው ቦታ በአብዛኛው በአስፋልትና በቤቶች በመያዙ ውኃ ወደ ከርሰ ምድር ውስጥ የመግባቱ መጠን በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ በዚህም ምክንያት በየዓመቱ በዝናብ ወራት የሚጨምረው የጎርፍ መጠን ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ሁኔታውን የከፋ የሚያደርገው አብዛኛው የከተማው ነዋሪዎች የሠፈሩት በወንዞች ዳርቻ በመሆኑ ለአደጋው ተጋላጨነታቸው የጎላ መሆኑ ነው፡፡

በከተማው ውስጥ በፍጥነት ቁጥሩ እየጨመረ ለሚሄደው ነዋሪ በቂ የውኃ አቅርቦት ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም በከተሞች ዙሪያ ያሉት ሰንሰለታማ ተራሮች የተፋሰስ ቁንጮዎች ቢሆኑም በተለያዩ ምክንያቶች ደን አልባ ሆነው እርቃናቸውን ቀርተዋል፡፡ ይህም በመሆኑ አፈሩ በየዓመቱ እየተሸረሸረ በመሄዱ አንዳንድ ቦታዎች ከአስፋልት የበለጠ ውኃ የሚያስገባ ንጣፍ አለት ላይ ደርሰዋል፡፡ በሌላ በኩል ከተራራው አናት ላይ እንደ ናዳ የሚወረወረው ጎርፍ በመሬት ገጽታ ላይ ያለውን ሁሉ ጠራርጎ ስለሚሄድ በመጠጥ ውኃ፣ በኃይል መስጪያ እና የመስኖ ግድቦችን በደለል በመሙላት ውኃ የመያዝ አቅማቸውን በየጊዜው እየቀነሰ እንዲሄድ ያደርጋል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ የመጠጥ ውኃ እጥረት ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ድቀትን ያስከትላል፡፡ የድሬ፣ የቆቃ፣ የገፈርሣ፣ የለገዳዲ ግድቦች እና ሌሎች የሀገሪቱ ሐይቆችም እንደ ሃረማያ ሐይቅ ደርቀው ወደ እርሻ መሬትነት የሚለወጡበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ ይህ ደግሞ ትንቢት መናገር ሳይሆን በየዓመቱ የእነዚህን የውኃ አካላት ጥልቀት በመለካት ምን ያህል እንደሚቀንሱ ማወቅ ይቻላል፡፡

ችግሩ በመሬት ገጽታ ላይ ያለውን የውኃ አካላትን ብቻ በማድረቅ የሚቀር ጉዳይ አይደለም፡፡ ከዓመት ዓመት የሚመነጩ ምንጮችና የሚፈሱ ወንዞች ሁሉ ከዚህ እጣ ፋንታ አያመልጡም፡፡ ምክንያቱም የሀገራችን ተራሮች በአብዛኛው በመራቆታቸው የዝናብ ውኃን ወደ ከርሰ ምድር ማስረግ አይችሉም፡፡

በደን መጥፋት የሚከሰቱ ችግሮች ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ለሰው ልጅ እና ለእንስሳት መኖሪያ ምቹና ተስማሚ ያልሆነ ሁኔታ ስለሚፈጥር ለስደት፣ ለዕልቂትና ለኋላ ቀርነት ይዳርጋል፡፡
 
< Prev   Next >