Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ብቸኛው የሀገራችን ኳራንቲን ...
ብቸኛው የሀገራችን ኳራንቲን ... E-mail
Sunday, 05 October 2008

ብቸኛው የሀገራችን ኳራንቲን ያለሥራ ታጥሮ የተቀመጠ ቦታ አይደለም
(- ከሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች የሕዝብ ግንኙነት ክፍል የቀረበ)

የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች አካል የሆነው የኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃ.የተ.የግል ማህበር፣ በሀገራችን ኤኮኖሚያዊ ሕይወት ውስጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ከጀመረ ከ8 ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ድርጅቱ ለበርካታ ወገኖቻችን የሥራ እድል በማስገኘትና የሀገር ውስጥ ገበያን በማረጋጋት ለሀገራችንም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በሥጋ ኤክስፖርት አንደኛ በመሆን ጉልህ ድርሻውን በመወጣት ላይ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

 

ኤልፎራ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተሰማርቶ በእርሻ፣ በዶሮ እርባታና በሥጋ ምርቶች አስተዋጽኦ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡  ኩባንያው ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦም በተለያዩ ወቅቶች ከተለያዩ አካላት ሽልማቶችና የምሥክር ወረቀቶች አግኝቷል፡፡

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆኑት ኤልፎራ በፕራይቬታይዜሽን ፕሮግራም ካገኛቸው ቦታዎች አንዱ የሆነውን በሀዋሳ ከተማ መግቢያ በጥቁር ውሃ አካባቢ ያለውን የሻሎን የእንስሳት መጠበቂያ /ኳራንቲን/ በሚመለከት በተለያዩ የሪፖርተር ጋዜጣ እትሞች የተሰነዘሩት አስተያየቶችና በቀልድ ወይም "በአሽሙር" መልክ ለሕዝብ የተሰጡ መረጃዎች ናቸው፡፡  በተለይም የሪፖርተር ጋዜጣ አማርኛ እትም በረቡዕ መስከረም 14 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም. "የክቡር ሚኒስትር አምድ" እና በእሁዱ መስከረም 18 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም. በቀረበው የ"ተስፍሽና ገብርሽ" ካርቱን ጭውውት ላይ የተላለፉት መልዕክቶች የኤልፎራን ተግባር ትክክለኛ ገጽታ ለሕብረተሰቡ ያላቀረቡ ከመሆናቸውም በላይ የሪፖርተር ዜና ዘጋቢም ሆነ የአምዶቹ ጸሐፊዎች እግረ መንገዳቸውን ወደ ሀዋሳ ሲጓዙ ያቀረቡት ዘገባ የተሳሳተና መረጃ የለሽ መሆኑን መግለጽ እንወዳለን፡፡  ፀሐፊዎቹ ኤልፎራን በማነጋገር ዕውነታውን ለመፈተሽ ጥረት ቢያደርጉ ኖሮ እውነቱን ባገኙ ነበር፡፡ ግዴታችንን ለመወጣት የሚከተለውን እውነታ ለአንባብያን አቅርበናል፡፡

ኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ ከሚጠቀምባቸው ቦታዎች መካከል በሀዋሳ ከተማ መዳረሻ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኘው 3ሺህ 2ዐዐ ሔክታር መሬት በሻሎ ለእንስሳት መጠበቂያ የተከለለ ሥፍራ /ኳራንቲን/ ነው፡፡ በሻሎ የእንስሳት መጠበቂያ ወደ ተከለለው ሥፍራ የሚገቡትን እንስሳት ከውጭ ከብቶች ሳይደባለቁ ጤናቸውን በመንከባከብ ደረጃውን የጠበቀ የከብት ሥጋ ለኤክስፖርት ለማቅረብ ይቻል ዘንድ ኩባንያው የሚጠቀምበት ልዩና አስፈላጊ ኳራንቲን ነው፡፡  በዚህም መሠረት በጥናት በተደገፈ መልኩ በተራራ፣ በወንዝና በ13.5 ኪ.ሜ. ርዝመት ባለው አጥር እንዲከለል ተደርጐ በኳራንቲንነት ሥራ ላይ ውሏል፡፡

በዚህም መሠረት ወደግብጽና ሌሎች ሀገሮችም ኤልፎራ ላቀረባቸው የሥጋ የውጭ ሽያጮች አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ለዚህ ተግባርም በሺዎች የሚቆጠሩ ከብቶች በኳራንቲኑ እንዲጠቀሙ ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ኤልፎራ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ደንበኞቹ የሚያቀርበውን የሥጋ ምርት ለማግኘት በዚህ ተፈጥሮአዊ የማቆያ ቦታ ይገለገላል፡፡

በሥጋ የውጭ ገበያ ላይ በተጣለው የውጭ ሀገር መንግሥታት ማዕቀብ ኳራንቲኑን እንደተፈለገው መጠቀም አልተቻለም፡፡ ይህ በመሆኑም ኤልፎራ ከመሬቱ አንድ ሶስተኛ የሚሆነውን ለልዩ ልዩ ምርቶች በማረስ ለመጠቀም ባወጣው ዕቅድ መሠረት ይህንኑ ማድረግ ከጀመረ ጥቂት ዓመታት አልፈዋል፡፡ ለምሳሌ በዚህ ዓመት ብቻ 437 ሔክታር እርሻ በቆሎ የተዘራ ሲሆን 155 ሔክታር ቦሎቄ 5ዐ ሔክታር የበቆሎ ምርጥ ዘር እርሻ ለምቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ስለልማቱ ምንም ዕውቀት ለሌለው የውጭ ተመልካች የተፈጥሮ ግጦሽ ሣር የሚመስለውና በ137 ሔክታር የተዘራው የእንስሳት መኖ የሮደስ ሳር እርሻ ልማት ይገኝበታል፡፡ ገበሬ ላልሆነ የቢሮ ጸሐፊ ሮደስ ሳር ጥቅም የለሽ ሣር ቢመስለውና ጠፍ መሬት ሆኖ ቢታየው አይፈረድም፡፡ በአጠቃላይም 779 ሔክታር መሬት በእርሻ ልማት ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት የተደረገውን እንቅስቃሴ ለማስታወስ በ1999 ዓ.ም. በጠቅላላ 565 ሔክታር የለማ ሲሆን ለ2ዐዐዐ ዓ.ም. የምርት ዘመን ደግሞ 7ዐ8 ሔክታር ለምቶ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ እድገትን የሚያሳየው የልማት እንቅስቃሴ የዚህን ዓመት እርሻ ጠቅላላ ልማት ወደ 779 ሔክታር ከፍ አድርጐታል፡፡ በተከታዩ የ2ዐዐ1 ዓመት ይህ የልማት ሥራ ለማሳደግ ሰፊ እቅድ ተይዞ ሥራው ተጀምሯል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የኳራንቲኑ አጥር በጐርፍ ምክንያት በተፈጠረው የመሬት መሸሽ በመፍረሱ የ3.5 ኪ.ሜ. የእድሳት ሥራ በቅርቡ ተከናውኗል፡፡ ይህንንም ወሬን "ለማጣፈጥ" ሲባል ከሀዋሳው የኢህአዴግ ስብሰባ ጋር ማያያዝ ተገቢ አልነበረም፡፡ ሪፖርተሮቹ ሀዋሳ ለመሄድ ልዩ ምክንያት እንዳስፈለጋቸው ቢገባንም የሄዱበትን ዓላማ ትቶ ለ"አሽሙር" ማጣፈጫ ፍለጋ የኤልፎራን ወይም የባለሀብቱን ስም ያለአግባብ ማንሳት እንዲጐለብት ከምንፈልገው እውነት ላይ የተመሠረተ "ነፃ ጋዜጣ" ሥርዓትና ሂደት ጋር የሚጣጣም አይመስለንም፡፡

ወደ ሀዋሳ ሲኬድ በስተቀኝ ያለው የምርጥ ዘር እርሻ ያለ አጥር ያለመሆኑን ጋዜጠኛው የተመለከተው ይመስለናል፡፡ በአኳያው በስተግራ ያለው የኤልፎራ መሬት ታጥሯል፡፡  ይህ የሆነበት ምክንያት በኳራንቲን ውስጥ የገቡትን ከብቶች ከሌላ ጋር እንዳይደባለቁ ማድረግ አስፈላጊ ስለሆነ መሆኑን መገንዘብ አዳጋች አይሆንም፡፡ ይህ ባይሆንማ ማጠር ባላስፈለገም ነበር፡፡

ይህ ኳራንቲን ለወደፊት የውጭ ገበያ በሰፊው ከተገኘ በማለት ሰፋ ያለ መሬት በውስጡ እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ቀስ በቀስ የእርሻ ልማቱ እንዲያድግ ይደረጋል፡፡

በመጨረሻም የነፃ ፕሬስ መዳበርና ማደግ ራሱን የቻለ ውጣ ውረድ እንዳለበት የምናምን በመሆናችን ያልታሰቡ ድንገተኛ ስህተቶች አይፈጠሩ አንልም፡፡ ስለሆነም የድርጅቶቻችንን ጥቅም በሚጐዳ መልኩ ከእውነት የራቀ ሪፖርት ሪፖርተር ጋዜጣ  ሲያቀርብ፣ ጉዳዩ እርማት እንዲያገኝ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ፕሬስ እንዲያድግ በትክክለኛ አባባል "የፕሬስ ነፃነትን ከስቅላት ያድኑ" የሚለው ሪፖርተር፣ ትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ እውነትን ማቅረብ የፕሬሱን ዕድገት እንደሚያበረታታው በማመን ይህን ጽሑፍ ለተሰነዘሩት አስተያየቶች ማብራሪያ እንዲሆን ጋዜጣው በገፁ ላይ እንዲያሰፍረው አቅርበናል፡፡ 
 
< Prev   Next >