| የአክሲዮን ኩባንያ ዲሬክተሮች ቦርድ |
|
| Sunday, 05 October 2008 | |
|
በሰለሞን ጎሹ
ከላይ የተገለጸው የነቃ የሕግ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ ስሩን ሰዶ ነበር፡፡ የአሁኑ የሕግ ማህበረሰብ የሚያነሳ የሚጥለው የያኔዎቹን ሃሳብ ነው፡፡ ሕጎቹ ቀስ በቀስ እየተቀየሩ የሃገሪቱም ተጨባጭ ሁኔታ መልኩን እየለወጠ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የሕግ ማህበረሰቡ ንቃት ከምንጊዜውም በላይ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ በቅርብ ዓመታት የተቋቋሙት የሕግ ት/ቤቶች እና ማህበራት የራሳቸውን የሕግ መጽሄት በማቋቋም በወቅታዊ የሕግ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ መወያያ የሚሆኑ ጽሁፎችን እያስነበቡን በመሆኑ ምስጋና ልንቸራቸው ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰቪል ሰርቪስ ኮሌጅ፣ የኢትዮጵያ ጠበቆች ማኅበር፣ የቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ የጂማ ዩኒቨርሲቲ እና የአለማየሁ ኃይሌ መታሰቢያ ድርጅት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በማገዝ ረገድ ለተጫወቱት እና እየተጫወቱ ላሉት ሚና ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ የአለማየሁ ኃይሌ መታሰቢያ ድርጅት በሐምሌ 2000 ያወጣው የሕግ መጽሔት ሦስተኛው ቅጽ ነው፡፡ ድርጅቱ ከመጽሔቱ ባሻገር የሕግ ማህበረሰቡን እያወያዬ ውይይቱንም በመፅሐፍ መልክ እያሳተመ የሚገኝ በመሆኑ በዚሁ እንዲበረታ እንሻለን፡፡ ሌሎችም ይህንኑ መንገድ እንዲከተሉም እንመክራለን፡፡ ከፍ ብለን የጠቀስነው የአለማየሁ ኃይሌ መታሰቢያ ድርጅት የሕግ መጽሄት ከያዛቸው ሦስት የምርምር ጽሁፎች መካከል ለዛሬ ልናየው የወደድነው "የአክሲዮን ኩባንያ ዲይሬክተሮች ቦርድ" በሚል ርዕስ በአቶ በዛወርቅ ሺመላሽ የተጻፈውን ወቅታዊ ጽሁፍ ነው፡፡ አቶ በዛወርቅ ጽሁፉን ለመፃፍ ያነሳሳቸው ሦስት ምክንያቶችን ሲጠቅሱ አንደኛ በኢትዮጵያ ሕግ በአንድ አክሲዮን ማኅበርራ ውስጥ የመጨረሻው ባለሥልጣን የባለአክስዮን ጠቅላላ ጉባኤ ሆኖ ሳለ አንዳንድ አካላት (ኢንሸቲቭ አፍሪካ ተጠቅሷል) የመጨረሻው ባለሥልጣን ቦርድ እንደሆነ ማመናቸውን፣ ሁለተኛ ሕጉ ከሁለት ዲሬክተሮች በላይ ምርጫ የሚካሄድ ከሆነ ባንድነት ማካሄድ አይቻልም፣ ድምጽ የሚሰጠው ለያንዳንዳቸው በተለይ ነው ቢልም በልማድ እስከ 12 ዲሬክተሮች ባንድነት፣ ባንድ ጊዜ ምርጫ የሚካሄድበትን ሁኔታ መኖሩን፣ ሦስተኛ የንግድ ኩባንያ ሥራ አስኪያጆች ቦርዱን የሚከሰሱበት ሁኔታ ማጋጠምና አንድ የቦርድ ዲሬክተር ሊፈጽም የማይገባውን ፈጽሟል ተብሎ በጋዜጣ (ሪፖርተር ጋዜጣ ተጠቅሷል) ላይ መውጣቱን አንስተው ሁኔታዎቹ ብዥታ የሚፈጥሩ በመሆናቸው ሊወገዱ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በ1952 ዓ.ምቱ የንግድ ሕግ ስድስት አይነት የንግድ ማኅበሮች ተዘርዝረዋል፡፡ 1ኛ ተራ የሽርክና ማኅበር 2ኛ/ የአሽሙር ማኅበር 3ኛ/ የኅብረት ሽርክና ማኅበር 4ኛ/ ሁለት ዓይነት ኃላፊነት ያለበት የሽርክና ማኅበር 5ኛ/ የአክሲዮን ማኅበር 6ኛ/ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ናቸው፡፡ በተራ ቁጥር 5 እና በተራ ቁጥር 6 የተጠቀሱት ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ኩባንያዎች ደግሞ ሁለት ልዩ ባህሪያት አሏቸው፡፡ 1ኛ/ኩባንያዎቹን ካቋቋሟቸው ማኅበርተኞች ተለይተው ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ መቻላቸውና 2ኛ/ የማኅበርተኞቹ ኃላፊነት በኩባንያው ውስጥ ካስገቡት መዋጮ የማያልፍ መሆኑ ናቸው፡፡ ገና ከጅምሩ የአንድ አክሲዮን ኩባንያን መመስረቻ ጽሁፍና መተዳደሪያ ደንብ በማጽደቅ፣ ስራውን የሚመሩ ዲሬክተሮችን በመሾምና በመሻር፣ ሥራውን ከጀመረ በኋላም የሥራ አፈጻፀም ሪፖርትና የሂሳብ መግለጫ ሁሉ ቀርቦ የሚፀድቀው በባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ በመሆኑ የአንድ አክሲዮን ኩባንያ ከፍተኛ አካል የባአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ እንደሆነና ይህም ለብዙ ኩባንያዎች ተቀባይነት ያለው መሆኑን ፀሐፊው የተከራከሩ ሲሆነ ኢኒሼቲቭ አፍሪካ ባዘጋጀው አንድ ጽሁፍ ቦርድ የአንድ ድርጅት ወይም ማኅበር አስተዳደር የመጨረሻው ባለሥልጣንና ኃላፊ ነው መባሉንም ተችተዋል፡፡ የዲሬክተሮች ሥልጣንና ተግባር ወይም ግዴታ ምን እንደሆነ በንግድ ሕጉ አንቀጾች 347፣ 351፣ 362፣ 363፣ 364 እና 391 ተዘርዝሮ የተቀመጠ ሲሆን ዲሬክተሮቹ የሚመሩት ባንክ ከሆነ ስለባንክ ሥራ በወጣው አዋጅ ቁጥር 592/2000 ከአንቀጽ 14-17 የተደነገገውን መከተል አለባቸው፡፡ ሕጉ ከጣለባቸው ግዴታዎችና ሥልጣኖች በተጨማሪ በመመሥረቻ ጽሁፍና በመተዳደሪ ደንብ እንዲሁም በባአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔዎች የሚሰጧቸው እንደሚኖሩ የንግድ ሕጉ አንቀጾች 363 (1) እና 364"1) ደንግገዋል፡፡ አቶ በዛወርቅ የንግድ ሕጉ አንቀጽ 347"1) የማኅበሩ አስተዳደር ሥራ በማኅበርተኞች ብቻ መከናወን እንዳለበት ቢናገርም ለማለት የተፈለገው ማኅበርተኞች የሆኑ ዲሬክተሮች ናቸው የአስተዳደሩን ሥራ የሚረከቡት ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ የአስተዳደር ሥራም በንግድ ሕጉ ትርጓሜ ስላልተሰጠው በፍትሐ ብሄር ሕግ ቁጥር 2204 ላይ የአስተዳደር ሥራ የወካዩን ሀብት የማስቀመጥ፣ የመጠበቅ፣ ከሦስት ዓመት ለማያልፍ ዘመን የማከራየት፣ በብድር የተሰጠውን ሀብት የመሰብሰብ፣ ከሀብቱ የሚመጣውን ገቢ ተቀብሎ የማስቀመጥና ለተከፈሉ ዕዳዎች ደረሰኝ የመስጠት ሥራዎች እንዲሁም የሰብልን መሸጥ፣ ለሽያጭ የተመደቡ የንግድ ዕቃዎችን ወይም ይበላሻሉ ተብለው የሚታሰቡ ነገሮችን የመሸጥ ሥራ ተብሎ የተተረጎመውን መውሰድ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ ፀሐፊውን ንብረት የመሸጥ የመለወጥ ሥራ እንደማይንቀሰቀስ ንብረት መሸጥ፣ የማይንቀሳቀስ ንብረት አሲዞ መበደር፣ ካፒታል ኢንቬስት ማድረግ፣ የሚተላለፉ የገንዘብ ሰነዶች መፈረም፣ ለመታረቅ ውል መግባት፣ ለሽምግልና ጉባኤ እንዲታይ መስማማት፣ ስጦታ ማድረግ፣ እና ፍርድ ቤት መከራከር ሁሉ በፍትሐብሄር ሕግ አንቀጽ 2205 መሰረት ልዩ ውክልናን የሚጠይቅ በመሆኑ ከባለአክሲዮኖች የተሰጠ ልዩ ውክልና ከሌለ በስተቀር የዲሬክተሮች ስራ አይደለም ብለውታል፡፡ ነገር ግን የንግድ ሕግ አንቀጽ 35 የሚተላለፍ የገንዘብ ሰነድ መፈረምን በአስተዳደር ሥራ ውስጥ የሚያካትተው በመሆኑ ከፍትሐብሄር ሕጉ የተለዩ ሁኔታ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም ከላይ የተገለፁትንና ልዩ ውክልና የሚሹትን ሥራዎች ዲሬክተሮቹ እንዲያከናውኑ በማኅበሩ መመስረቻ ጽሁፍ ወይም በመተዳደሪ ደንብ የሚፈቀድላቸው ወይም በጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ የሚሰጥባቸው ሁኔታ እንዴ "ልዩ ውክልና" ሊታይ እንደሚችል አቶ በዛወርቅ ገልጸዋል፡፡ በንግድ ሕግ አንቀጽ 348 መሰረት የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር በባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ባልተመረጠ ጊዜ ዲሬክተሮቹ ከራሳቸው አንዱን ሊቀመንበር አድርገው መምረጥ ይችላሉ፣ መሻርም ይችላሉ፣ ዳሬክተሮችም የኩባንያውን ዋና ሥራ አስኪያጅ ይሾማሉ፡፡ ፀሐፊው ዋና ሥራ አስኪያጁ የአስተዳደር ሥራ ስለሚሰራና የማህበሩን የአስተዳደር ሥራ ደግሞ ማህበርተኞች ብቻ እንዲመሩት በንግድ ሕጉ አንቀጽ 347"1) የተደነገገ ስለሆነ ዋና ሥራ አስኪያጁም በግድ ባለአክሲዮን መሆን እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡ በተጨማሪም በሕግ ከተሰጠው የዳሬክተሮች ቦርድ ተግበርና ሥልጣን በተለዬ በመመሥረቻ ጽሁፍና በመተዳደሪያ ደንብ የሚሰጠው በዋና ሥራ አስኪያጁና በቦርዱ መካከል አለመግባባትን በመፍጠር መወነጃጀልን እንዳያስከትል ያስጠነቅቃሉ፡፡ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ በውሳኔ ሥልጣን የሚሰጠው ለዲሬክተሮች ቦርድ እንጅ ለዋና ሥራ አስኪያጁ እንዳልሆነ ያስታውሳሉ፡፡ አቶ በዛወርቅ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ዲሬክተሮችን ድክመት ካሳዩ ያስወግዳቸዋል እንጂ አመራር ወይም ትዕዛዝ ሊጣቸው አይገባም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በጥር 21/2000 ዓ.ም የሪፖርተር ጋዜጣ እትም የንግድ ኢንሹራንስ ጠቅላላ ጉባኤ በሥራ ላይ የነበረው የዲሬክተሮች ቦርድ ዋና ሥራ አስኪያጁን ያገደው በትክክል ነው ሲል መወሰኑን አንስተው ዋና ሥራ አስኪያጁን የመሾምና የመሻር ሥልጣን የዲሬክተሮች ቦርድ መሆኑ በግልጽ በህግ ቢቀመጥም ጠቅላላ ጉባኤው የቦርዱን እርምጃ ለመገምገም መሰባሰቡ ግን ሕጋዊ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡ ዲሬክተሮች ካሏቸው ሥልጣኖች ውስጥ የተወሰኑትን ለዋና ሥራ አስኪያጁ በውክልና የሚሰጡ ቢሆንም እንኳን ተጠያቂነታቸው እንዳለ ነው፡፡ ውክልናው ለሌላ ዲሬክተርም ሊሆን እንደሚችል ጸሐፊው ይገልጻሉ፡፡ እንዲሁም የኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዲሬክተር ሊሆንም፣ ላይሆንም እንደሚችል አቋም ይዘዋል፡፡ የብሄራዊ ባንክ መመሪያ ዳሬክተር የሆነውን ዋና ሥራ አስኪያጅ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አድርጎ መሾምን የሚከለክል ቢሆንም አቶ በዛወርቅ ይህን የንግድ ሕጉ ራሱ እንደሚከለክል ይከራከራሉ፡፡ ፀሐፊው የቦርድ ዲሬክተሮች ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሕግ ክፍተቶች መኖራቸው የገለፁ ሲሆን ከዚህ ጋር በተያያዘ በኩባንያ አመራር ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ሲያጋጥሙ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በራሱ አነሳሽነት ወይም በሌላ ሰው ጠቋሚነት ጉዳዩ እንዲመረመር የማስደረግ ሥልጣን በሕግ ተሰጥቶት እያለ አቅም የለኝም በሚል ሰበብ ከኃላፊነት መሸሹ ትክክል እንዳልሆነና ሕጉን ሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡ በንግድ ሕጉ አንቀጽ 350"3) መሰረት ዲሬክተሮች የሚመረጡበት የአገልግሎት ዘመን ከሦስት ዓመት አይበልጥም፡፡ አቶ በዛወርቅ አንድ ዲሬክተር ከስድስት ዓመት በላይ በተከታታይ መመረጥ አይችልም ብሎ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ያወጣው መመሪያ ሕገወጥ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ መመሪያው ዲሬክተሮችን ለአንድ ዓመት፣ ሌሎችን ደግሞ ለሁለት ዓመት በማለት እየለዩ መምረጥ መብት ላይም ገደብ እንደሚጥል ይተቻሉ፡፡ በተግባር እየተሰራበት ያለው የአመራረጥ ዘይቤ ድርብ መረጣ የሚባለውና ሦስትም አራትም ከዚያም በላይ የሆኑ ዳሬክተሮች በአንድ የምርጫ ወረቀት ባንድ ጊዜ የሚመረጡበት አሰራር እንደሆነ የሚያስረዱት ፀሐፊው የንግድ ሕጉ በአንቀጽ 350"5) ላይ ከ2 ዳሬክተሮች በላይ የሚመረጡ ከሆነ ምርጫው ለየብቻቸው እንጂ ባንድነት አንዳይካሄድ ስለሚደነግግ አሰራሩ ሕገ ወጥ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡ በመጨረሻም አቶ በዛወርቅ ለዲሬክተሮች የሚከፈለው ክፍያ በጠቅላላ ጉባኤ የሚወሰነው "የተወሰነ የሥራ ዋጋ" እና በተጣራው ትርፍ ላይ የሚከፈል "የትርፍ ድርሻ" በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ሰፍሮ የተፈቀደ ሊሆን እንደሚችል ገልፀው በመተዳደሪያ ደንቡ ውስጥ ሳይኖር ለዲሬክተሮች "የትርፍ ድርሻ" መክፈሉ ሕጉን የተከተለ ስላልሆነ መቅረት ይኖርበታል ሲሉ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡ ወንበር የአለማየሁ ኃይሌ መታሰቢያ ድርጅት ፔሮዲካል በዚሁ እትሙ በአቶ በዛወርቅ ሺመላሽ ፅሁፍ ላይ በአምሳሉ ባዬ የተሰጠ አስተያየትንም የያዘ ሲሆን ወደፊት የምንመለስበት ይሆናል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |