| "ጎሕ ሲቀድ" |
|
| Sunday, 05 October 2008 | |
|
ከአርአያዎቻችን አንዱና ስመ ጥር የኪነ ጥበብ ሰው፣ ተዋናይ፣ ደራሲና ፕሮፌሰር የሆነው ተስፋዬ ገሠሠ የልደት ቀኑን የዘከረው እንደወትሮው ሁሉ ለአንባብያን የሚሆን መጽሐፍ አሳትሞ በማስመረቁ ነው፡፡ "ጎሕ ሲቀድ" ይሰኛል የመጽሐፉ ርእስ፡፡ የተመረጡ የ50 ዓመት ግጥሞችን በአንድ መድበል አዘጋጅቶ በዋሸራ አሳታሚዎች አማካይነት ለእይታ በቅቷል፡፡ መስከረም 17 ቀን 2001 ዓ.ም በኢምፔሪያል ሆቴል አመሻሽ ላይ በተዘጋጀው መሰናዶ የጥበብ ትውስታዎቹ ከግጥምና ከተውኔት ሥራው ጋር ተቀናብሮ ቀርቧል፡፡ የሙያ አቻዎቹ ምስክርነት የሰጡበትም ነበር፡፡ መጽሐፉ ሲገለጽ ለርእሱ መነሻ የሆነው ሩብ አያት ግጥም (ባለአራት መስመር ግጥም) ከዑመር ኻያም የተቀዳና ተስፋዬ ያዛመደው ግጥም ጎልቶ ይነበባል፡፡ "አሐዱ ጭቃ ሆይ" ተብሎ ሲቦካ የአዳም መጨረሻም ያን ጊዜ ተለካ፡፡ አዎ" ተፍጻሜተ ዓለምም የተበየነበት በኦሪት ዘፍጥረት ነው ጎሕ በቀደደበት" የግጥም መድበሉ ሁለት ክፍሎች አሉት፤ አንደኛው የደራሲው የራሱ ወጥ ግጥሞች (ከ1949 - 1999 ዓ.ም) ሲሆኑ፣ በሁለተኛው ክፍል ደግሞ አዛማጅ ትርጉሞች ቀርበውበታል፡፡ ደራሲው ስለ መድበሉ ይዘት ሰበብ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፡፡ "ከግእዝ ጀምሮ ወደ ልጁ ወደ አማርኛ የተላለፈልን ኢትዮጵያዊ ሥነ ጽሑፍና የሥነ ግጥም ቅርስ በመኖሩ ዕድለኞች ነን፡፡ የሕይወትን መልከ ብዙነት፣ ትርጉሙ ብዙነት የሚያሳይ መነፅር አለን፡፡ እጅግ የካበተ የገለፃ ዘዬና ቋንቋ ወርሰናል፡፡ ወጣቱ ትውልድም የራሱን እያከለበት አጎልብቶታል፡፡ በዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት የተነሳ ከሌሎች አገሮች ልምድና ቅርስ እንድንቋደስም ዕድል አግኝተናል፡፡ ስለዚህ ምንጫችን የአባቶቻችን ቅርስ ብቻ ሳይሆን በጣም ከበለጸጉ የባዕዳን ሥነ ጽሑፎችም ጭምር ሆኗል፡፡" ደራሲው ይህንኑ መርሕ በመከተል በመድበሉ ውስጥ የዊልያም ሼክስፒርን መወድሶችና የዑመር ኻያም ሩብ አያቶችን አካትቷል፡፡ "ለደራሲነትም ሆነ ለተርጓሚነት የመፎካከር ግፊት ነበረኝ፤ በወጣትነት ዘመኔ የከበደ ሚካኤል ሮሜዎና ዡልየት አዛማጅ ትርጉም፣ የጸጋዬ ገብረ መድኅን የሼክስፒር ተውኔቶች ትርጉም ያነሳሱኝ ነበር፡፡ እኔም እንደነሱ ብሞክርስ እል ነበር፡፡ ልብ ወለድም ስጽፍ የስብሐት ገብረ እግዚአብሔርን ዱካ በመከተል ነበር፡፡" የሚለው 72 ደመራ የለኮሰው ደራሲ በዝክረ ዕለቱ ታዋቂ ገጣሚያንና ተዋንያን ግጥሞቹን ከትዝታዎቻቸው ጋር አዛንቀው አቅርበውለታል፡፡ ተስፋዬ በግጥሙ ያኔም ሆነ አሁን የነበረውንና ያለውን ሕይወት የቃኘባቸው፣ የነፀረባቸው ግጥሞች አሉት፤ አንዱ ከ51 ዓመት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ታዋቂ በሆነው የ"አሰገደች አላምረው ቤት"ን የተመለከተበት ነው፡፡ ገጣሚው እንዳለው የአሁን የ70 ዓመቱ ሽማግሌ የጻፈው ሳይሆን በ20ዎቹ ውስጥ የነበረ ወጣት ነው የጻፈው፡፡ ሁለት ግጥሞች ለምፅላል ከጨለማ አድማስ ላይ ስትወጣ ጨረቃ አይተሃል? ወንዝ ላይ ተንሳፋፊ አበባ? አይቻለሁ እኔ፤ የሚበልጥ ቁንጅና ቆርቋሻ ወንበር ላይ ምፅላል ተቀምጣ፡፡ ---- " ----- ጥጌረዳ ቆርጦ ላንዳፍታ ማሽተት ከዛፍ ሥር ጥላ ውስጥ ከሣር ላይ መኛት ዶሮ ሲጮህ መብላት ፋሲካ ሌሊት ቡሄ ችቦ ማብራት ሙልሙል ዳቦ መግመጥ ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ሲጠባ ለመስቀል ደመራ ለጥምቀት ከተራ መኖር መደሰት ነው ከጤንነት ጋራ፡፡ ግን፤ ምፅላል፤ አንገቷን ስታጥፍ፤ ስታፍር ማየት ምፅላል ስታስካካ ስትቦርቅ መስማት ምፅላልዬን አቅፎ መደነስ ሩምባ ይሻለኛል ሞቼም ገነት ከምገባ፡፡ ስለ ኪነ ጠቢቡ ተስፋዬ የጥበብ ሰብእና ትውስታቸውን ካቀረቡት አንዱ የመድረኩ አጋፋሪ የነበረው ኪነ ጠቢብ ጌታቸው ደባልቄ ነበር፡፡ "ተስፋዬ ገሠሠን በአካል ሳይሆን በሙያ ያወቅሁት በ1952 ዓ.ም "ኢዮብ" የሚባለውን ቴአትር በተጫወተበት ጊዜ ነው፡፡ ግርማዊ ጃንሆይ ባሉበት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ኢዮብን ሲጫወት ራሱን ኢዮብን ያየሁት ዓይነት ቆጥሬ ነበር፡፡ የርሱን የወደፊት ጥበብ ጉዞ አእምሮዬ ውስጥ የተቀረፀው ያኔ ነው፡፡ አብረን ኖርን፣ አብረን ሠራን፤ ሁሉም ከርሱ ሙያውን እንዲቀስም ያደርግ ነበር፡፡ አሁንም ነው፡፡" ብሎለታል፡፡ "ኢዮብ" የተሰኘው ተውኔት የተስፋዬን የሕይወት ጉዞ የተለወጠበትን አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡ ተስፋዬ እንደሚለው ውጭ አገር ለመማር ያሰብኩትና ዝንባሌዬ ሕግ ነበር፡፡ ቤተሰቤም አንቱ የሚያስብል ሥራ ውስጥ እንድገባ ይፈልጉ ነበር፡፡ እንደ አጋጣሚ ግርማዊ ጃንሆይ ኢዮብን አይተው ነው ወደ ተውኔቱ እንድሄድ ያደረጉት፡፡ "እኛም ኦፔራችንን፣ኮ ከፍተናል፡፡ የተማሩ ያስፈልገናል" ብለው ወደ አሜሪካ እንድሄድ አደረጉኝ፡፡" ብሏል፡፡ በምረቃውና ዝክረ በዓል መድረኩ ከተነበቡት ግጥሞች ሌላ ድምፃዊው ፈለቀ ካሳ በክራር ግርፍ የጥበብ ሰዎችን የሚያዘክር ዜማውን ሲያቀርብ፣ በግጥም መድበሉ አንድ ሰበዝ መዝዞ አቶ ሔኖክ ያሬድ አቃቂር ሰጥቶ ነበር፡፡ "ያላለቀ ግጥም" በሚል ርእስ ገጣሚው የፀደይ ወቅትን ከአደይ አበባ ጋር አዛምዶ ያቀረበውን የዘመን ተፋልሶ አለበት በሚል ነበር ሐሳቡን ያቀረበው፡፡ "የፀደይ ፀሐይ ስታበራ ሰማያዊ ሆኖ ሰማዩ ሲጠራ ምድሪቷ አረንጓዴ በአረንጓዴ ሆና በአደይ አበባ ተከሽና ዕፀዋትና አዝርእት ሲፋፉ ሲፈኩ ምነው የሰው ልጆች ከሱ ጠወለጉ?"". ፀደይ በኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ ከመጋቢት 26 እስከ ሰኔ 25 ቀን ድረስ የሚውል የበልግ ወቅት በመሆኑ፣ መስከረም ላይ ከምትታየው አደይ አበባ ጋር ተዛምዶ እንደሌላት ያስታወሰው ሔኖክ፣ ብዙ ገጣሚያንና ሠዓልያን በሥራዎቻቸው ፀደይን ከአደይ አበባ ጋር በማገናኘት ዝበት መፍጠራቸውን ጠቁሟል፡፡ ለምሳሌም ባለቅኔው ጸጋዬ ገብረ መድኅን "በራ የመስቀል ደመራ" በሚለው ግጥሙ "በራ የመስቀል ደመራ፣ ፀደይ አረብቦ" ይለዋል፡፡ መስቀልም አደይም በፀደይ ሳይሆን በመፀው (የአበባ ወቅት) ነው የሚገኙት፡፡ አቶ ሐዲስ ዓለማየሁ "ፍቅር እስከ መቃብር" በሚሰኘው ልብ ወለድ ድርሰታቸው የመስከረምን የአበባ ወቅት ቢራቢሮዎቹና የሰብለ ወንጌል አገልጋዮች መስኩ ላይ ያሳዩት የነበረውን ትዕይንት ከፀደይ ጋር አመሳስለው ነው ያቀረቡት፡፡ አቃቂረኛው በአስተያየቱ እየተረሳ ያለውን መፀው የመስከረም ወቅት፣ ፀደይ ደግሞ የመጋቢት ፊታውራሪ መሆኑ ተገንዝበው ተጠባቢያን ለጥበባቸው ስምረት ሊጠቀሙበት ይገባል ብሏል፡፡ ኪነ ጠቢቡ ተስፋዬ ለቀረበው አቃቂርም "መፀውን አጥቼው ሳይሆን ፀደይ የሚለው ቃል ከፀዳ ጋር ስለሚሄድ ነው የተጠቀምኩት፡፡ ባለቅኔዎች ቃላትን ይፈጥራሉ ይቀይራሉ በዛ መብት ተጠቅሜ ነው የሠራሁት፤ ፀደይ ግን የበልግ ነው፤ እቀበላለሁ ለወደፊቱ ጠንቀቅ እላለሁ" ብሏል፡፡ |
|
| Last Updated ( Sunday, 05 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |