| ዋሸራ |
|
| Sunday, 05 October 2008 | |
|
ዋሸራ በኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥርዓት ትምህርት ውስጥ በቅኔ ቤት፣ በጥበባቱ ዘርፍ ታዋቂ የነበረና አሁንም ያለ ማዕከል ነው፡፡ በጎጃም ውስጥ ይገኛል፡፡ ዋሸራ የጥበብ ማዕከል በመሆኑ የሁሉንም ቀልብ መሳቡ ስላልቀረ ከመግቢያው ላይ ያለውን ግጥም አንዷ ተቀኝታለታለች፡፡ ስለ ዋሸራ ለማንሳት ሳይሆን በአዲስ አበባ በዋሸራ ስም ስለተቋቋመ አሳታሚ ድርጅት ለማንሳት ነው፡፡ ዋሸራ ባለፈው መስከረም 17 ቀን 2001 ዓ.ም በኢምፔሪያል ሆቴል የኪነ ጠቢቡን ተስፋዬ ገሠሠ የ50 ዓመት የሕይወት ዘመን ምርጥ የግጥም ሥራዎቹን መድበል ያስመረቀበትና ልዩ ልዩ ሥራዎቹን "የኢትዮጵያ መካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ወፎች"፣ "የእንስሳት መጻሕፍት"፣ "ወፎቻችን" በአማርኛና በእንግሊዝኛ፣ የከበደ ሚካኤል "የዕንቁላሉ ተረት" እና የጸጋዬ ገ/መድኅን "ሕይወት ቢራቢሮ" በሥዕልና በፎቶግራፍ ታጅቦ ያስተዋወቀበት ዕለት ነበር፡፡ በዚሁ ጉዳይ ዋና ሥራ አስኪያጁን ዶክተር ከበደ ታደሰን አነጋግረናል፡፡ ዋሸራ የሚለውን ስያሜ የመረጣችሁበት ምክንያት ምንድነው? ዋሸራ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቅኔ ት/ቤት ነው፡፡ የታወቀም ነው፡፡ ብዙዎች በዚያ አልፈዋል፡፡ አዲሱን ትውልድ በጥበብ ለማሻሻልና የንባብና የጽሑፍ ፍላጎቱን ለማነቃቃት፣ እውቀት የሚገበይበት እንደመሆኑ መጠን ከዚያ ተነሥተን ትውልዱን ለማነቃቃት ያደረግነው ነው፡፡ በመድረኩ እንደገለጻችሁት ዋነኛው ትኩረታችሁ በሕፃናት ሥነ ጽሑፍና በሥነ ፍጥረት ላይ ነው ለምን አተኮራችሁ? . እዚህ አለ የሚባለው ጉድለት በሕፃነት (ልጆች) መጻሕፍት አቅርቦት ላይ ነው፡፡ እኛ ልጆች የምንለው እስከ 15 ዓመት እስከ 18 ዕድሜ ሊሄድ ይችላል፡፡ በዚህ የዕድሜ ገደብ ሳሉ መጽሐፎች እንደልብ አይገኙም፡፡ መፍትሔ ለመፈለግ ነው፡፡ ሁለተኛው በሥነ ፍጥረት ላይ የምናተኩረው የአንዳንዶቻችን ዳራ በርሱ ስለሆነ ነው፡፡ በኪነ ጥበብም ሆነ በሥነ ጽሑፍ ጥሩ መልክ ያለ ቢሆንም ሥነ ፍጥረትን በተመለከተ ልጆችን በማስተዋወቅ፣ ስለሀገራችን አዕዋፍ፣ አዝርዕት ልዩ ልዩ ነገሮች ስለሌለ ያንን ለማገዝ የተሠራ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አብዛኞቹ በቀጥታ የተነሱ ፎቶግራፎች ያዘጋጀናቸው ነው፡፡ በፖስተሮቹም ሆኑ በመጻሕፍቱ እንዳየነው ስማቸው አዳዲስ የሚመስሉ አሉ እናንተ የሰየማችኋቸው ናቸው? እኛ ስንጀምር እውቀቱም የለንም፡፡ የወፎቹ ስም በአማርኛና ስለዛፎችም ሆነ አዝርዕት የለንም፡፡ ስንፈልግ፣ ስናስስ 80 በመቶ የአዕዋፋት ስም በአማርኛ አለ፡፡ ስለዚህ ከብዙ መጻሕፍት እያጣቀስን እንፈልጋቸዋለን፡፡ ዝርዝሮቹን ካልሆነ በቀር ዋና ዋናዎቹ ወፎች ስም አላቸው፡፡ ለምሳሌ ቢራቢሮዎችን ስንወስድ በአገራችን አስደናቂ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት በጣም ያምራሉ፡፡ ሁሉንም ቢራቢሮዎች ብለን ነው የምናልፈው፡፡ በውጭ ግን የሳይንስ ስም አላቸው፡፡ ወፎች ላይም ሆነ እዚህ ላይ የጎደሉትን ለመሙላት ሞክረናል፡፡ ጅምር ነውና ወደፊት ሊሻሻል የሚችል ነው፡፡ ቀደም ሲል የታተሙ ተያያዥ ጉዳዮችን ያነሱ መጻሕፍት ይኖራሉ ይኸኛው እትመት ለየት የሚያደርገው ምንድነው? ይኸኛው ለየት የሚያደርገው በእንደዚህ ዓይነት ዝርዝር የተገኘ የለም፡፡ ምስልን ከሥነ ጽሑፍ ጋር አዛምዶ የቀረበበት ሁኔታ የለም፡፡ ለምሳሌ የጸጋዬ ገብረ መድኅን "ሕይወት ቢራቢሮ" ግጥም በቢራቢሮዎች በማስደገፍ ያሳተምነው መጽሐፍ አለ፡፡ ባለቅኔው ለግጥሙ አስካክ፣ ለቃላቱ ውበት እና ስለ ሕይወት ጥልቅ የሆነ አስተሳሰባቸውን በቢራቢሮ ሥነ ሕይወት፣ ገጽታ፣ ውበትና የአኗኗር እውነታ ያላቸውን ትክክለኛ ግንዛቤ በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡ የግጥሙን ውበት ይበልጥ ለማድመቅና መልአክቱን ለማጎልበት፣ ብሎም የባለቅኔው ችሎታና የአስተሳሰብ አድማስ ለማመልከት ተስማሚ ከሆኑና የተገለጸውን ሁኔታ በተጨባጭ ከሚያሳዩ የቢራቢሮ ፎቶግራፎች ጋር አቀናብረን ለማቅረብ ሞክረናል፡፡ ግጥሙን ሊገልጹ የሚችሉ በርካታ ፎቶግራፎችን አሰባስበናል፡፡ በዚህ መልክ የቀረበ እኛ እስከምናውቀው የለም፡፡ በትምህርቱ ደግሞ የውጭ ዝግጅት አለ፡፡ አሳታሚዎችም ጸሐፊዎችም የምናቀርባቸው ፎቶግራፎች ሀገር በቀል እንዲሆኑ ፈልገን ነው፡፡ ሌላውን ለመዝጋት ሳይሆን የዓለምም የኛ ነው አብሮን እንዲኖር ብንፈልግም፤ በመጀመሪያ ሀገራቸው ውስጥ ያለውን በስማቸው በቅርቡ እንዲያውቋቸው ለማድረግ ነው፡፡ ስለዛፎች የምንጽፈው አለ፡፡ የዛፎቹ ስም በብዙዎቹ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አለ፡፡ አዲስ መፈልሰፍም የሚያስፈልገን አይደለም፡፡ የአማርኛውን የኦሮምኛውንና የእንግሊዝኛውን አዘጋጅተን አውጥተን በሳይንስ ደግሞ የሚያገናኘውን አብረን እንጽፍለታለን፡፡ በመጻሕፍት ብቻ ሳይሆን በፖስተር መልክም አዘጋጅተናል፡፡ የማሳተሚያው ዋጋ አልተገዳደራችሁም? አንዱ የምናደርገው የልጆች መጻሕፍት አሁን ባለው ማሳተሚያ ዋጋ ጥራት ያለው በባለቀለም ፎቶግራፎች ስናቀርብ ውድ ነው፡፡ ያንን ይዘን ገበያ ውስጥ ከገባንና ዋጋውን እንዲከፍል ካደረግን አይቻልም፡፡ ስለዚህ ለልጆች የሚፈለገውን በዝቀተኛ ዋጋ ለማቅረብ እንዲቻል ሌሎች ሥራዎች እንሠራለን፡፡ ለቱሪስቶች የሚሆኑ የጻፍናቸው ጽሑፎች ስላሉ ከነርሱ የምናገኘው ገንዘብ በተወሰነ ደረጃ እንደግፋለን፤ የሌሎቹን ዋጋ ቀላል እንዲሆንና አቅርቦቱ እንዲሰፋ እናደርጋለን፡፡ በታሪክ ነክ ሥራዎችስ ላይ ታተኩራላችሁ? ስለታሪክ እናስባለን፡፡ ግን የምናተኩረው ባልተነኩ አካባቢዎች ላይ ነው፡፡ ብዙ የታሪክ መጻሕፍት ተጽፈዋል፡፡ ነገር ግን ለየት ያለ አቅጣጫ ካለ እርሱን ይዘን እንመጣለን፡፡ እርስዎን የምናውቆት በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣንነት (የጤና ጥበቃ ሚኒስትር) ነበር፡፡ ከጥበቡ ማዕድ እንዴት ተከሰቱ? ሥነ ጽሑፍ፣ ቴአትር፣ ሙዚቃዎችን ከበፊት እወዳለሁ፡፡ አሁን የገባሁበት ብዙ ሕይወት አሳልፌያለሁ፡፡ ዋነኛው ሐኪም ነኝ፣ የሕክምናም መምህር ነኝ፡፡ ሳይንስ ነው የምሠራው፡፡ በሁለተኛው ወደ ፖለቲካ ገባሁኝ፣ በኔ ጊዜ ከነበሩ አብረን የመጣንበትና ያደግንበት ነው፡፡ ስለዚህ ስታገልበትም የቆየሁበትም ነው፡፡ በዚያው መሠረት ፖለቲካው ሲለወጥና ደግሞ ትግላችን ሰምሮ ሲመጣ መጥቼ ደግሞ በሌላ ዘርፍ ተሰማራሁ፡፡ አሁን ደግሞ ዕድሜ ገፋ እያለ ሲሄድ ደስ የሚሉኝን ልሥራ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥም ምን አስተዋጽዖ አደረጋለሁ ስል፣ ጡረታ በወጣሁበት ጊዜ ምን እንሥራ ብለን ተማከርን፡፡ አሳታሚ ብንሆን፣ ጥራት ባለው መልክ ጥሩ ነገሮችን ለማቅረብ ይረዳናል ብዬ ወደ ሦስተኛው ሕይወቴ ተሸጋግሬያለሁ፡፡ |
|
| Last Updated ( Sunday, 05 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |