| "እኔን ትልቅ ዘፋኝ ያደረገኝ ሕዝብ ነው" |
|
| Sunday, 05 October 2008 | |
|
ሪፖርተር፡- ከ40 ዓመታት በላይ በሙዚቃው ዓለም ቆይተሃል የቀድሞ ዜማዎችህን ስትሰማ ምን ትላለህ? ለምሳሌ ሰበቡን፣ ስንዋደድ. . .? ታምራት፡- ብዙ ነገሮች አስታውሳለሁ፡፡ ለምሳሌ "ሰበቡን" አልዘፍንም፤ ብዬ ሦስት ጊዜ መቀጣቴን ያስታውሰኛል፡፡ ሪፖርተር፡- የታወቅህበትን ዘፈን ለምን አልዘፍንም አልክ? ታምራት፡- ቤት የማይመታ ግጥም ብዘፍን ያስተቸኛል ብዬ ነው፡፡ ያን ጊዜ ጋዜጦች በጣም ይፈራሉ፡፡ ጋዜጠኞች ተችተው ከሕዝቡ ይለያዩኛል፤ ብዬ እምቢ አልኩ፡፡ አለቃዬ ሻምበል ታደሰ 5 ብር ቀጡኝ፡፡ ግጥሙን ያቀረበው ሲራክ ታደሰ ነበር፡፡ ሪፖርተር፡- የሌላ ሰው ድርሰት ከነበረ አንተ ካልፈለግህ ለምን ዝፈን ተባልክ? ታምራት፡- በምድር ጦር ሙዚቃ አንድ ባህል ነበር፡፡ አንድ ዜማ ወይም ግጥም ሲመጣ ሁሉም እንዲያጠናው ይደረጋል፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሙያው ስለነበር ሁሉም ያጠናና የተሻለ ይዘፍነዋል የተባለው እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ በዚህ ምክንያት እኔ እንድዘፍን አለቃዬ ወሰነ፡፡ እኔ ደግሞ እምቢ አልኩ፡፡ ቅጣቱ ተጨመረብኝና በጠቅላላ 15 ብር ተቀጣሁ፡፡ ያን ጊዜ ደመወዜ 60 ብር ነው፡፡ 15 ብር መቀጣት ከፍተኛ ጉዳት ነው፡፡ በኋላ ጓደኞቼ ተቆጡኝ፡፡ በተለይ አባይ በለጠ፣ ጋዜጠኞች ቢተቹህ ተገድጄ ነው ትላለህ፤ ስላለኝ ዘፈንኩ፡፡ ውጤቱ የሚደንቀኝና ከጠበቅሁት በላይ ሆኖ የዓመቱ ኮከብ ዘፈን ተብሎ ተሰየመ፡፡ ጋዜጣው ሁሉ የእኔን ፎቶ ግራፍ ይዞ ወጣ፡፡ ሪፖርተር፡- አለቃህ ምን አሉህ? ታምራት፡- ሰበሰቡና ወቀሱን፡፡ መከሩንም፡፡ እናንተ ወጣቶች ስለሆናችሁ ግርግሩን ነው የምታዩት፡፡ እኛ ግን ከልምድም የምናውቀው ስላለ ነው የምንጫናችሁ፡፡ አልዘፍንም ያልከው ዜማ የዓመቱ ኮከብ ሲባል እምቢታህ ምን ያህል ስህተት እንደነበር መረዳት አለብህ፤ አሉኝ፡፡ ቅጣቱም ተሻረልኝ፡፡ እንዲያውም 50 ብር ደመወዝ ጭማሪ ተደረገልኝና 110 ብር ደመወዝተኛ ሆንኩ፡፡ ዘፈኖቼ እንዲህ እንዲህ ያለውን ነው የሚያስታውሱኝ፡፡ ሪፖርተር፡- በምድር ጦር ሙዚቀኛ ክፍል ለምን ብዙ ቆየህ? ታምራት፡- ያን ጊዜ ክፍሉ የተሟላ ነበር፡፡ ደራሲዎች ነበሩ፡፡ በእውነቱ የምድር ጦር ኦርኬስትራ ከኢትዮጵያ ቀርቶ በአፍሪካ የሚወዳደር ነበር፡፡ ሪፖርተር፡- ያን ጊዜ ክብር ዘበኛ፣ ፖሊስ ኦርኬስትራ፤ ባሉበት ምድር ጦር እንዴት ልዩ ይሆናል? ታምራት፡- አሉ፡፡ ሁሉም ግን የሚታወቁበት መለያ አላቸው፡፡ ክብር ዘበኛን ብትወስድ ድምፃዊ ያለበት ቤት ነው፡፡ ታላላቅ ድምፃውያን ነበሩ፡፡ ፖሊስን የወሰድህ እንደሆነ የታወቁ ተወዛዋዦች የነበሩበት ነው፡፡ ምድር ጦር ደግሞ በሙዚቃው፣ በባንዱ ልዩ ነበር፡፡ እንደዚያ ለማለት እንጂ ሁሉም ነበሩ፡፡ ስለዚህ ለሙዚቃው ስለተገዛሁ ከእዚያው መውጣት አልፈልግሁም፡፡ ኢሕአዴግ መጥቶ ክፍሉ ሲበተን ወጣሁ እንጂ እድሜ ልኬን ከዚያ እወጣለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ ሪፖርተር፡- ወታደራዊ ማዕርግ ተሰጥቶሃል? ታምራት፡- እኔ ሲቪል ነኝ፡፡ አንድ ጊዜ ግን በ1957 ዓ.ም ይመስለኛል ጓደኛዬ ተድሮ ወደ ወለጋ ሄጄ ባንዱ ወደ ኦጋዴን እንዲላክ ተወስኖ ኖሩዋል፤ በሬዲዮ አስጠሩኝና ስመጣ ኦርኬስትራው ሄዷል፡፡ ስለዚህ በባቡር እንዲጓዝ ስለተፈለገ የምክትል መቶ አለቅነት ማዕርግ አልብሰው ላኩኝ፡፡ ይህን ያደረጉት እኔን ለማክበር ወይም ለመሾም ብለው አይምሰልህ፡፡ የባቡር ዋጋ ለመኮንኖች በግማሽ ስለሚቀንስ ነበር፡፡ በየግንባርም ሙዚቃ ስናሳይ የምንለብሰው ወታደራዊ ልብስ ነበር፡፡ ከዚህ ውጭ ማዕርግ አልተሰጠኝም፡፡ ሪፖርተር፡- መሽቀርቀር ታበዛለህ፤ አበባ ማድረግ ትወዳለህ፡፡ ከቤተሰብ የወረስከው ባህርይ ነው ወይስ ተፈጥሮህ? ታምራት፡- ኧረ ከእኔ የተሻሉ የሚለብሱ ነበሩ፡፡ እነ ጥላሁን ገሠሠን የመሰሉ፣ እነ ዓለማየሁ እሸቴን የመሰሉ፣ እነ ምኒልክን የመሰሉ. . . ሌሎችም ግሩም ለባሾች ነበሩ፡፡ ሪፖርተር፡- ለትህትና ብለህ የምትናገር ይመስለኛል፡፡ የጠየቅሁህ በአንተ ላይ በተሰጠው አስተያየት ላይ ነው፡፡ ታምራት፡- መቼም የኢትዮጵያ አርቲስቶች ያን ጊዜ ድሆች ነን፡፡ ግን ምንም ይሁን ምን፣ አለባበስን መጠበቅ ይገባል፤ የሚል እምነት አለኝ፡፡ የምለብሰው ለራሴ ስሜት ብቻ ሳይሆን ለሙያውም ክብር ነው፡፡ ለሕዝቡም ክብር ነው፡፡ እኔን ትልቅ ዘፋኝ ያደረገኝ ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ያከበረኝን ሕዝብ ፊቱ ስቀርብ አክብሬ መቅረብ አለብኝ ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ያሁኖቹን ዘፋኞች ከአለባበስ አኳያ አይተሃቸዋል? ታምራት፡- አንዳንዶቹ መመከር አለባቸው፡፡ በሸራ ጫማ መድረክ ላይ ይወጣሉ፤ በጂንስ ሕዝብ ፊት ይቀርባሉ፡፡ እንዲህ አይነት አቀራረብ ሙያውን እንደማቅለል የሚያስቆጥር ነው፡፡ መድረክ ክቡር መሆኑን ይረሱታል፡፡ ሪፖርተር፡- የሃብታም ልጅ ነህ፡፡ ታምራት፡- ሃብታም ማለት. . . ሪፖርተር፡- የመሬት ባላባት፡፡ ታምራት፡- ነበሩ፡፡ ግን እኔን የሚያሳድጉኝ እንደማንኛውም የቤተሰብ ልጅ ነው፡፡ አባቴ ፊታውራሪና ወረዳ ገዥ ነበሩ፡፡ ግን አባቴ ትንሽ ሆኜ ስለሞቱ ወንድማቸው ደጃዝማች በዛብህ ናቸው ያሳደጉኝ፡፡ ሪፖርተር፡- የርሳቸውን ባህርይ በትንሹ ትነግረኛለህ? ታምራት፡- ደጃዝማች በዛብህ ኩሩ ነበሩ፡፡ (ሳቅ) ጎንደሬ ኩሩ ነው ይባላል፡፡ ያ እውነት ከሆነ እሳቸው የኩሩዎች ኩሩ ነበሩ፡፡ ሪፖርተር፡- እንዴት ነው የኩሩዎች ኩሩነት የሚገለፀው? ታምራት፡- ሌላውን ተወውና ሲሄዱ ጨርቃቸውን ጋሬጣ የያዘው እንደሆነ የተከተልናቸው እንድናስለቅቅ አይፈልጉም፡፡ ወደፊት መንጭቀውት ይሄዳሉ፡ መጠጥ ቤት የማይገቡ፣ የትም ቦታ የማያገኛቸው፣ ኃይለኛ . . . ሪፖርተር፡- አንተስ ኩሩ ነህ የሚባለው. . . ታምራት፡- በፍፁም አይደለሁም፡፡ አንዳንድ ሰው ሳያውቀኝ ብዙ ብዙ ይለኛል፡፡ የእኔን ግን ጓደኞቼ ይመስክሩ፡፡ ትዕቢተኛም ኩሩም አይደለሁም፡፡ አንድ ጊዜ እንዲህ ትባላለህ፤ ብለው የነገሩኝን አስታውሳለሁ፡፡ አንድ ሰው "ታምራት ከኩራቱ የተነሳ ታክሲ ሲጠብቅ አንድ ሰው ጥላ ይዞለት፣ ሌላው ደግሞ ታክሲ አስቁሞ ተነጋግሮለት ነው፤ የሚሳፈረው፤ አለ አሉ፡፡ ይህ በእውነቱ ስም ማጥፋት ነው፡፡ እኔ እራሴን አላሞግስም እንጂ ትሁት ነኝ ባይ ነኝ፡፡ ለምን የሚያውቁኝና ጓደኞቼን አይጠይቋቸውም? ሪፖርተር፡- ታዲያ የደጃዝማች ባህርይ ተጽዕኖ አድርጎብኛል የምትለው ምንድ ነው? ታምራት፡- በመጠጥ፡፡ ርሳቸው የሚጠጣ ሰው አይወዱም፡፡ ጅው አርጎ እንኳ የሚጠጣ አስወጣው፤ ሰካራም ብለው ነበር የሚሳደቡት፡፡ አሁን አለመጠጣቴ የእሳቸው ተጽዕኖ ያለው ይመስለኛል፡፡ ሪፖርተር፡- ጥሬ ስጋ በከፍተኛ ደረጃ እንደምትወድ ይታወቃል፡፡ ግን ብዙ ሰው ለምግብ መበተኛ ይረዳል የሚለውን መጠጥ ለምን አትጠጣም? ታምራት፡- ይህ መበተን የሚባለው ነገር ውሸት ነው፡፡ እኔ ውሃ ነው የምጠጣው፡፡ የእናቶቻችን አሰራር ተመልከት ስጋ አልቆረጥ ብሎ ሲያስቸግራቸው ውሃ ውስጥ ነው የሚከቱት፤ ሥጋ ውሃ ውስጥ ሲቀመጥ ይባዝታል፡፡ ይበሳሰካል፡፡ አልኮል ውስጥ ብታስቀምጠው ግን ያብጣል፡፡ ሪፖርተር፡- ቤተሰቦችህ ወደሙዚቃ ሙያ መግባትህን እንዳልወደዱት ብዙ ጊዜ ተናግረሃል፡፡ ያን ጊዜ ሳይሆን አሁን ስታስበው የሚቆጭህ ነገር የለም? ታምራት፡- ድምጻዊ በመሆን ብዙ ችግር ደርሶብኛል፡፡ የእኔ ድምጽን ሲሰሙ ረዳቶች ተባረዋል፡፡ የሚገድለኝ ሰው ተልኳል፡፡ ግን አዝማሪ የሚገኘው ጠጅ ቤት ነው ብሎ ፈልጎ ስላጣኝ ነው ፈጽሞ በዓይናቸው እንዳያዩኝ አስገልለውኛል፡፡ የአባቴን ስም እንድለውጥ ተነግሮኝ ነበር፡፡ ግን ያን ጊዜም ሆነ አሁን የሚቆጨኝ ነገር የለም፡፡ አሁንም በሙዚቃ በመገዛቴ ደስ ይለኛል፡፡ የሚጸጽተኝ ነገር የለም፡፡ ሪፖርተር፡- ይቅርታ ሳያደርጉልህ ሞቱ? ታምራት፡- ታመው ደከሙ ሲባል ባህር ዳር ሆስፒታል አይኔን ጨፍኜ ሄድሁ፡፡ ስለታመሙ ምን ያደርጉኛል ብዬ ነው፡፡ ሄጄ ጫማ ሳምሁ፡፡ እሳቸው አልሳሙኝም፡፡ ማታ በሌለሁበት "ያ እብድ አልመጣም ነበር?" ብለው ጠየቁ አሉኝ፡፡ ይኽን እንደ ይቅርታ ማድረግ፤ ቆጥሬዋለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- ይቅርታ እንዲያደርጉልህ አንድ ዜማ አውጥተህ አልተማፀንህም? ታምራት፡- አይ እንዲያውም የሚያስቆጣቸው ነው የዘፈንሁት፡፡ "አባቴ ሸማኔ፣ ወንድሞቼ ቀጥቃጭ፣ አዝማሪ ነኝ እኔ" የሚለውን ስዘፍን እንኳን ቤተሰቤ ጎንደሬ ነኝ የሚል ሁሉ ተነሳብኝ፡፡ የተማረው ወንድሜ ሳይቀር ያን ዘፈን እንዳልዘፍን ተጣልቶኛል፡፡ የበለጠ ነገሩ ሁሉ ከረረ፡፡ እኔ ግን ማ ተቆጣ ማ አልተቆጣ ግድ አልነበረኝም፡፡ ሪፖርተር፡- እናንተ የሽግግር ባለሙያዎች ናችሁ፡፡ እስኪ ሙዚቃ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ በደርግ፣ በኢሕአዴግ ጊዜ ምን እንደሚመስል አስተያየት ስጠኝ፡- ታምራት፡- በጃንሆይ ጊዜ ሥራህን እየወደዱ ግን አያከብሩህም፡፡ በመኪና ለሥራ የወሰደህ ሰው ሥራውን ስትጨርስ ዘወር ብሎ አያይህም፡፡ ለጋብቻ ትከለከላለህ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን በታላላቅ ቦታ አድርገው ሳይቀር ተመርጠህ የክብር ቦታ ይሰጡሃል፡፡ ያም ሆኖ ግን በ1950ዎቹና 60ዎቹ አጋማሽ ድረስ ሙዚቃ ያደገበት፣ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይበት ነበር፡፡ ደርግ ሁሉንም የኪነት ተሳታፊ አደረገውና ሙያው ዝቅ ተብሎ መታየቱ ቀረ፡፡ አብዮቱን በሁለት እግሩ ያቆመው ኪነት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የደርግ ኃላፊዎች የአርቲስቱን ተግባር ያውቁ ነበር፡፡ እንዲያውም አንድ ጊዜ ኮሎኔል መንግሥቱ፣ አንድ ካድሬ ስድስት ወር ከሚያስተምር አንድ ድምፃዊ አንድ ቀን ቢዘፍን የሚያስተምረው ይበልጣል፤ ብለዋል ይባላል፡፡ ግን የሙዚቃው ደረጃ እያዘቀዘቀ ሄደ፡፡ በሕዝቡ ውስጥ እንዲሰራጭ ቢደረግም የእድገቱ ደረጃ ግን ወረደ፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜ ሙዚቃ የባሰ አዘቀዘቀ፡፡ የውድድር ምንጭ የነበሩት የወታደር ኦርኬስትራዎች ተዘጉ፡፡ ስለዚህ እድገቱ ተዳከመ፡፡ አሁን ጥሩ ጥሩ ድምፃውያን አሉ፡፡ ግን ያልታረመና ያልታየ ሥራ ሁሉ የሚቀርቡበት ጊዜ ሆነ፡፡ ሙዚቃ ንግድ ሆነች፡፡ ንግድ በሆነ ቁጥር ደግሞ ትኩረት የሚሰጠው ጥራቱ ሳይሆን ከገንዘብ ሰብሳቢነት አኳያ ነው፡፡ አዲስ ነገር መስማት አልተቻለም፡፡ ሪፖርተር፡- ይህንን ለራሳቸው ትነግራቸዋለህ? ታምራት፡- አዎ" እኔ ቃለ መጠይቅ ስሰጥ ሁሉ የምናገረው ይህንኑ ነው፡፡ ሥራቸው በባለሙያ እየታረመ እንዲቀርብ እናገራለሁ፡፡ የሙዚቃ ማህበርና ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት እጃቸውን ካላስገቡ፣ ተስፋ ያለን አይመስለኝም፡፡ አሁንም በየቦታው ስትሄድ ጥላሁን ገሠሠ ከ50 ዓመት የዘፈነው ዘፈን ይወደዳል፡፡ ሰውም ይጠይቃል፡፡ የዛሬው ግን ቢበዛ ሦስትና ሁለት ዓመት በላይ አያልፍም፡፡ ይህ ለምን ይሆናል ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሪፖርተር፡- መሪዎች በሙያህ አነጋግረውህ ያውቃሉ? ታምራት፡- አላነጋገሩኝም፡፡ ግን ሸልመውኛል፡፡ በጃንሆይ ጊዜ ሁለት ጊዜ ተሸልሜያለሁ፡፡ አንደኛው የወርቅ ሰዓት ነው፡፡ አሁንም በእጄ ይገኛል፡፡ ሲሸልሙኝም ይህን ድምጽ እግዚአብሔር ነው የሰጣችሁና ጠብቃችሁ ያዙት፤ የሚል ማበረታቻ ቃል ነግረውኛል፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ በአጋጣሚ የሙዚቃ ቡድን አግኝተውኝ ስሜን ጠርተው ሰላምታ ሰጥተውኛል፡፡ ከአቶ መለስ ጋር ተገናኝቼ አላውቅም፡፡ ሪፖርተር፡- የምድር ጦር ኦርኬስትራን ለማሰባሰብ አልሞከራችሁም? ታምራት፡- ሞክሬ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ሲገባ ሁሉም ተበተነ፡፡ በኋላ ወደቤታችሁ ተመለሱ ሲባል ሲቪሎቹ ተገኘን፡፡ አቶ ታምራት ላይኔ ጋ ሄድሁና እናንተ መንግሥት ስለሆናችሁ መሪዎች ይመጣሉ፣ አቀባበል ይደረጋል፡፡ ባለፈው የሱዳንና የጅቡቲን መሪዎች በክራርና በመሰንቆ ነው የተቀበልነው፡፡ ለምን የመከላከያ የሙዚቃ ባንዶች አይሰበሰቡም? አልኩ፡፡ ወደ ጃማይካ (የማነ ኪዳኔ) ለሚባሉ ሰው መከላከያ ላኩኝ፡፡ እዚያም ሄድሁ፡፡ ሁለት ጊዜ ከቀጠሩኝ በኋላ ለማሰልጠን ብቻ የሚችሉ አራት ጥሩ ሙዚቀኞች ብቻ ነው የምፈልገው አሉኝ፡፡ የሙዚቃ ቡድን አቋም ስራ ተባልኩ፡፡ እኔም ይህን የሚሰሩትን መኮንኖቹን እንዲያዘጋጁ አድርገን ከ500 በላይ ባለሙያዎች እንዲሰበሰቡ መዋቅር ተሰራ፡፡ ግን ከ120 በላይ እንደማይቀበሉ ነገሩን፡፡ በግድ ተከራክረን 260 ያህል እንዲመለሱ ተደረገ፡፡ የእኔ ሃሳብ የደቡብም የምስራቅ ዕዝ፣ የፖሊስም የማዕከላዊ ዕዝም እንዲሰበሰቡ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ አገር ፍቅር ተዛወርኩ፡፡ በኋላ ግን ምክንያቱን አላውቅም ኦርኬስትራውን እንደገና በትነው አሁን የሰልፈኛ ሙዚቃ ብቻ ነው ያለው፡፡ ሪፖርተር፡- ሙዚቃ ትሰማለህ? ታምራት፡- እሰማለሁ፡፡ በተለይ የጥላሁን ገሠሠን አዳምጣለሁ፡፡ ጥላሁን መተኪያ የሌለው ነው፡፡ እስካሁንም አልተገኘለትም፡፡ ወደፊትም እንጃ፡፡ እድሜ ይሰጥ ቢሆን ለጥላሁን ከእድሜዬ ቀንሼ ብሰጥ እመርጣለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- ይህ አባባልህ የሌሎቹን ስሜት የሚነካ ነው፡፡ ታምራት፡- አይነካም፡፡ ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ የማንም ስሜት የሚነካ አይመስለኝም፡፡ ከተነካም ግድ የለኝም፡፡ ሙዚቃ የሚያውቅና የሚወድ ሰው ጥላሁንን የማያደንቅ አለ ብዬ አላስብም፡፡ |
|
| Last Updated ( Sunday, 05 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |