| የአውሮፓ ሕብረት የወሊድ... |
|
| Sunday, 05 October 2008 | |
|
የአውሮፓ ሕብረት የወሊድ እረፍትን ለመጨመር አቅዷል
የአውሮፓ ህብረት የሴቶች የወሊድ እረፍት ቀን ከፍ የማድረግ እቅድ እንዳለው ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል፡፡ የህብረቱ ኮሚሽን የወሊድ ፍቃድን ከአሥራ አራት ወደ አሥራ ስምንት ሳምንታት ከፍ የማድረግ እቅድ ተግባራዊ መሆን ከቻለ አብዛኞቹን የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት ለእናቶች ከፍተኛ ድጋፍ እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል፡፡ ይህ ፕላን ሰራተኛ እናቶች እንዲሁም እናት ለመሆን በዝግጅት ላይ ያሉ ነፍሰ ጡር ሰራተኞችን መብት ከማስፋት ባሻገር በሴቶች ሙያዊ፣ ግላዊና ቤተሰባዊ ሕይወት ሚዛናዊነትን እንደሚያሰፍን የአውሮፓ ህብረት ማህበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽነር ቭላድሚር ስፒድላ ተናግረዋል፡፡ የተለያዩ ማህበራዊ መመሪያዎችን የሚከተሉት ሀያ ሰባቱ የአውሮፓ ህብረት አገራት ሙሉ ድምፅ ለፕላኑ ተፈፃሚነት ወሳኝ መሆኑን፤ ለተግባራዊነቱም የህብረቱ ፓርላማ ውሳኔ አስፈላጊነትን ዘገባው ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩል ይህ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕላን በህብረቱ አገራት በማሽቆልቆል ላይ የሚገኘውን የወሊድ ቁጥር ለማሻሻል የታለመ እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ናንሲ የተባለች የብራስልስ ኗሪ "የማልመው ነገር እውን ሆነ ማለት ነው ፕላኑ ተግባራዊ መሆን ከቻለ፡፡ መመሪያዎቹ የተለያዩ ሁኔታዎችን ያገናዘቡ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ሳምንታቱ ከፍ ስላሉ ከወሊድ በፊትም ሆነ በኋላ እረፍት መውሰድ ይቻላል፡፡ ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ከተጠበቀው ቀደም ብዬ ብወልድ ከፈቃዴ የተወሰነውን የእረፍት ቀናት አጣለሁ" በማለት ለቢቢሲ ተናግራለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ቢቢሲ ላይ ያለው የአውሮፓ ህብረት ህግ (እ.ኤ.አ በ1992 ተግባራዊ መሆን የጀመረው) ለወሊድ የሚፈቅደው አስራ አራት ሳምንታትን ነው፡፡ ከአሥራ አገራቱ ሳምንታት ውስጥ ሁለቱ ሳምንታት የግድ ከወሊድ በፊት መወሰድ እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡ የሴቶችን የወሊድ እረፍት በሚመለከት የቀረቡት አዲስ መመሪያዎች ሴቶች ቢያንስ ቢያንስ አሥራ ስምንት ሳምንታት የወሊድ እረፍት ማግኘት እንዳለባቸው ያመለክታል፡፡ ስድስቱ ሳምንታት የግድ ከወሊድ በኋላ መወሰድ እንደሚኖርባቸው፤ ቀሪዎቹን አንዲት እናት እንደ ፍላጎቷ ከወሊድ በፊት ወይም በኋላ መወሰድ እንደምትችል ያመለክታሉ፡፡ እንደ ቢቢሲ ዘገባ ሀያ ሰባቱ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት በቀረበው ፕላን መሰረት ሴቶቻቸውን ከወሊድ ፍቃድ በኋላ ወዲያው የሥራ ጫና እንደሚያበዙባቸው አመልክተዋል፡፡ የአውሮፓ አገራት ለወሊድ የሚሰጡት እረፍት የተለያየ ሲሆን ቤልጂየም አስራ አምስት፣ ፈረንሳይ አስራ ስድስት፣ እንግሊዝ ሀያ ስድስት ሳምንታትን ስትሰጥ በቡልጋሪያ እስከ አመት የወሊድ እረፍት የሚወሰድበት ሁኔታ አለ፡፡ አገራቱ የሚሰጡት የወሊድ እረፍት እንደሚለያይ፤ የደመወዝ ክፍያቸውም ሁኔታ ይለያያል፡፡ በአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት አነስተኛው የወሊድ እረፍት (አስራ አራት ሳምንታት) የምትሰጠው ጀርመን ስትሆን የእናቶቹን ሙሉ ደመወዝ ትከፍላለች፡፡ እንደ ቤልጂየምና ጀርመን ያሉ አገራት ረዥም የወሊድ ፈቃድ መሥጠት ሲጠበቅባቸው እንደ እንግሊዝ ቡልጋሪያ ያሉ አገራት ደግሞ ወላዶቹ ፍቃድ ላይ ሲሆኑ የተሻለ ክፍያ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አዲሱ የአውሮፓ ሕብረት ፕላን ያመለክታል፡፡ እንደ ቼክ ሪፐብሊክ ያሉ አገራት ህብረቱ በማህበራዊ አኗኗሮች ሁሉ ጣልቃ እንዳይገባ በተደጋጋሚ ድምፃቸውን ያሰሙ አገራት መኖራቸውን፤ አዲሱ ፕላን ቀጣሪዎች ሴቶችን ለመቅጠር እንዲያቅማሙ ሊያደርጋቸው ይችላል የሚል ፍራቻ ያላቸው መኖሩን የቢቢሲ ዘገባ አስታውቋል፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ የህብረቱ አባላት ከተቀበሉትና ፓርላማውም ከተስማማበት የሴቶች የወሊድ ፍቃድን የሚመለከተው አዲሱ መመሪያ እ.ኤ.አ በ2011 ተግባራዊ ሊሆን ይችላል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |