Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ሴት አሽከርካሪዎች
ሴት አሽከርካሪዎች E-mail
Sunday, 05 October 2008

በምሕረት አስቻለው

ከወንድ አሽከርካሪዎች ጋር ሲነፃፀሩ ሴት መኪና አሽከርካሪዎች በተለያየ መልኩ ጠንቃቆች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ እኛም በአዲስ አበባ ከተማ ስላሉ ሴት አሽከርካሪዎች አንዳንድ መረጃዎችን ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ትራፊክ መቆጣጠሪያና ምርመራ መምሪያ አመራን፡፡

 

"ከወንድ አሽከርካሪዎች ጋር ሲነፃፀሩ የሴት አሽከርካሪዎች ጥንቁቅነት በአገሪቱም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ይታያል፡፡ ሴት መኪና አሽከርካሪዎች የተሻለ የማሽከርከር ሥርዓት አላቸው፡፡ የትራፊክ ሕግና ሥርዓትንም ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡ ለጥንቁቅነታቸው የተለያዩ ምክንያቶች ይሰጣሉ፡፡ እናቶች ስለሆኑ አደጋን ይፈራሉ፣ ለውበታቸው ይጠነቃቃሉ፣ ሴቶች በባህሪያቸውም ረጋ ያሉ መሆናቸውና ባህላዊ ተፅእኖዎች በማሽከርከር ለሚያሳዩት ባህርይ አስተዋፅኦ እንዳላቸው በተደጋጋሚ ይነገራል" ያሉን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ትራፊክ መቆጣጠሪያና ምርመራ መምሪያ የሕዝብ ግንኙነት የሆኑት ዋና ሳጅን ዳንኤል ታደሰ ናቸው፡፡

ዋና ሳጅን ዳንኤል እንደገለፁት፣ በአገራችን ካሉት ሁለት ሚሊዮን የሁለተኛ ደረጃ መንጃ ፈቃዶች አብዛኞቹ የተያዙት በሴቶች ነው፡፡ ትልልቅ መኪኖችንና ታክሲዎችን የሚያሽከረክሩ ሴቶችም አሉ፡፡ በትራፊክ ሕግ ወይም ሥርዓት መጣስ በሚፈጠር አደጋ ያላቸው ድርሻ ግን እጅግ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ከደረሱ 8636 የትራፊክ አደጋዎች ሴት አሽከርካሪዎች የተሳተፉት በ214ቱ ላይ ብቻ ነው፡፡ 7452 የሚሆነውን አደጋ ያደረሱት ወንድ አሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ ከ214 አደጋዎች ውስጥ 12ቱ ከባድ፣ 29 ቀላል ጉዳትና 172 በንብረት ላይ የደረሰ አደጋ ነው፡፡ የሞት አደጋ ደግሞ አንድ ብቻ ሲሆን፤ ይህም አንዲት ሴት አሽከርካሪ በሌላ ወንድ አሽከርካሪ በተፈፀመባት ግጭት በመሞቷ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ምን አልባትም በሴት አሽከርካሪዎች ምንም ዓይነት የሞት አደጋ ላይደርስ ይችል ነበር፡፡

ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ለምሳሌ እንደ ኬንያ ካሉ አገሮች ሴት አሽከርካሪዎች ጋር ሲነፃፀሩ ኢትዮጵያዊያን ሴት አሽከርካሪዎች የተሻሉ እንደሆኑ ገለፁልን፡፡ እንዴት? በማለት ጠየቅናቸው፡፡ ምሽት ላይ መጠጥ ጠጥቶ፣ ቅሞ ወይም አደንዛዥ እፅ ተጠቅሞ የማሽከርከር ሁኔታ በሴት አሽከርካሪዎቻችን ላይ ታይቶ እንደማያውቅ፤ ይህም በሌሎች አገራት ካሉ ሴት አሽከርካሪዎች ጋር ሲነፃፀሩ የተሻሉ እንደሚያደርጋቸው አስረድተዋል፡፡ ሴት አሽከርካሪዎች ለሚያሳዩት መልካም የማሽከርከር ሥርዓት በ1999 ዓ.ም ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ ለሴት አሽከርካሪዎች የነዳጅና የነፃ መኪና እጥበት መስጠቱን፣ ሌሎች ድርጅቶችም በተመሳሳይ ሁኔታ ሽልማት የሰጡበትን አጋጣሚ አስታውሰዋል፡፡

ጠጥቶ፣ አንደንዛዥ እፅ ወስደው ወይም እየቃሙ አለማሽከርከር ሴት አሽከርካሪዎች በሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች ተካፋይ እንዳይሆኑ እንዳደረገ የሚናገሩት ዋና ሳጅን ዳንኤል በጣም አለመፍጠንና እርስ በርስ አለመሽቀዳደም የሴት አሽከርካሪዎች ጠንቃቃነት ሲነሳ የሚጠቀሱ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

"አብዛኛውን ጊዜ ሴት አሽከርካሪዎች ጥፋት የሚፈፅሙት ለልጆቻቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ለማድረግ በማሰብ፣ ዝርፊያን በመፍራት ወይም እቃ ለመግዛት የተከለከለ ቦታ ላይ በማቆም ነው፡፡ መጠጥ ጠጥታ በምሽት፣ እየቃመች የምታሽከረክር ወይም ገጭታ ለማምለጥ የምትሞክር ሴት አሽከርካሪ የለችም ለማለት የሚያስችል ሁኔታ ነው እየታየ ያለው፡፡ ሲያሽከረክሩ ቸልተኝነት አይታይባቸውም፡፡ ከተማ ውስጥ አስራ አምስት የሚሆኑ ሴት ታክሲ አሽከርካሪዎች አሉ፡፡ አብዛኞቹ ወንድ ታክሲ አሽከርካሪዎች ላይ የሚታየው እየቃሙ ማሽከርከር በእነሱ የለም፡፡ በእግረኛም ይሁን በትራፊክ ብዙ ክስ አይቀርብባቸውም፡፡ የአንበሳ ሴት አሽከርካሪዎች ላይም ሆነ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ሰርቪሶችን በሚያሽከረክሩ ሴቶች ላይም የሚታየው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡"

በከተማችን ላሉ ሴት አሽከርካሪዎች የትራፊክ ሥርዓት አክባሪነት ቤተሰብ የመምራት ሀላፊነት፣ በመጥፎ ተግባር ሰዎች እይታ ውስጥ መግባት አለመፈለግና ሌሎች ባህላዊ ተዕእኖዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ያምናሉ ዋና ሳጅን ዳንኤል፡፡ በክስ ከተያዙ መቶ መንጃ ፈቃዶች አንድ ወይም ሁለት ሴት አሽከርካሪዎች ሊገኙ እንደሚችሉ፤ በመቶዎች ሲሰላ በሚፈጠር አደጋ ተጎጂ በመሆን እንጂ በአደጋ አድራሽነት ያላቸው ድርሻ እጅግ በጣም አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሞባይል ስልክ እየተነጋገሩ በማሽከርከር በሚፈጠር አደጋ የሴት አሽከርካሪዎች ተሳትፎ ምን ይመስላል? በማለት ጠየቅናቸው፡፡ ሴቶች በሚያደርሱት ተደጋጋሚ አደጋ ሞባይል ስልክ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው "አንዲት ሴት አሽከርካሪ በሞባይል ስልክ እየተነጋገረች ስድስት አህዮችን ገጭታለች፡፡ ይህን ሁሉ አደጋ ስታደርስ በምታደርገው የሞባይል ስልክ ንግግር ተመስጣ ነበር፡፡ በመጨረሻም መኪናዋ ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ነው ሆኔታውን ያስተዋለችው፡፡ ከወንድ አሽከርካሪዎች በተለየ መልኩ በሞባይል ስልክ እየተነጋገሩ ከደሴትና ምሰሶ ጋር የሚጋጩት ሴት አሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ ወንድ አሽከርካሪዎችም በሞባይል ስልክ እየተነጋገሩ ያሽከረክራሉ፡፡ ነገር ግን እንደ ሴቶቹ በሀሳብ አይወሰዱም" በማለት መልሰዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በሴት አሽከርካሪዎች በንብረት ላይ በደረሰ መቶ ሰባ ሁለት አደጋ የሞባይል ስልክ ንግግር አስተዋፅኦ ቀላል እንዳልነበር ከንግግራቸው ተረድተናል፡፡ መኪና እያሽከረከሩ ሌላ ሥራ መስራት በትራፊክ ሥርዓት ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑ በደንብ የተቀመጠ ቢሆንም በእንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች የሚገኙ አሽከርካሪዎችን የመቅጣት ሥልጣን እንዳልተሰጣቸው ዋና ሳጅን ዳንኤል አመልክተዋል፡፡

ዋና ሳጅን ዳንኤል እንዳሉት፣ ሴት አሽከርካሪዎች የትራፊክ ሥርዓትን ከመጠበቅ ባሻገር በትራፊክ የሚቀርብባቸውን ክስ ባለመቀበል ክርክር ውስጥ አይገቡም፡፡ አብዛኞቹ ጥፋታቸውን በመካድ ከመከራከር ይልቅ በአግባቡ ይቅርታ ጠይቀው መሄድን ይመርጣሉ፡፡ በአንድ ወቅት ቦሌ መድኃኔ ዓለም አካባቢ አብዛኞቹ ወንድ አሽከርካሪዎች እንደሚያደርጉት አንዲት ሴት አሽከርካሪ ከትራፊክ ጋር ስትወዛገብ በመመልከታቸውን፤ ምን አልባትም ትራፊኩ ተሳስቶ ሊሆን ይችላል ብለው ለማሰብ ተገደዋል፡፡

በ1999 ዓ.ም በሴት አሽከርካሪዎች የደረሰው የትራፊክ አደጋ 196 የነበረ ሲሆን በ2000 ወደ 214 ከፍ ብሏል፡፡ የዚህ ምክንያት የሴት አሽከርካሪዎች ጠንቃቃነት መቀነስ ሳይሆን የሴት አሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪዎች መብዛትን ተከትሎ የታየ ለውጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
 
< Prev   Next >