Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ፓርላማው ሲከፈት
ፓርላማው ሲከፈት E-mail
Sunday, 05 October 2008

        "ሰኞ ሥራ አለብን""

የዘንድሮ የ2001 ዓ.ም የ"መስከረም ወር፣ የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ" የሚውለው በ26 ነው፡፡ ላለፉት 13 አመታት እንዳየነው በሕገመንግስታዊ ድንጋጌ እንደተወሰነውም የመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ "የፌዴራሉ መንግስት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌዴራሉ መንግስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት" የሥራ ጊዜ መጀመሪያ ነው፡፡ ከዚህ ቀን ጀምሮ (በመካከል መንፈቀ ዓመቱ ላይ የሚኖረው የአንድ ወር እረፍት እንዳለ ሆኖ) እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ የሚዘልቀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን ዘንድሮ የሚጀምረው ሰኞ መስከረም 26 ቀን ነው፡፡

 

ስለዚህም የ3ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የሚጀመረው የሪፖብሊኩ ፕሬዚዳንት ለሁለቱ ምክር ቤቶች በሚያደርጉት የመክፈቻ ንግግር አማካኝነት ነው፡፡ በዚህም መሰረት የዛሬ ዓመት መስከረም 27 ቀን 2000 ዓ.ም እንደሆነው፣ ከዚያም በፊት በየዓመቱ መስከረም ወር የመጨረሻው ሳምንት ሰኞ ላይ እንደተለመደው የክቡር ፕሬዚዳንቱን ንግግር እናዳምጣለን፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትን የ2001 ዓ.ም ሌጂስሌቲቭ ፕሮግራም እንሰማለን፡፡

አገራችን ውስጥ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ገና ባልተነካው አመለካከትና ግምት መሰረት እንደነውር የሚቆጠረው ክብረነክ ተደርጎ የሚወሰድ ሆኖ ነው እንጂ የፓርላማዎች ሁሉ እናት ተደርጋ በምትቆጠረው በእንግሊዝ አሰራር እንደሚታወቀውና "ምስጢር" ሆኖ ሳይያዝ በግልጽ እንደሚነገረው በንግሥቲቱ (በንጉሡ) የሚቀርበው የፓርላማ የመክፈቻ ንግግር ራሱ እና በዚህ ንግግር አማካኝነት ይፋ የሚደረገው ዓመታዊ ፕሮግራም ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ያዘጋጀው ንግግርና የራሱ ፕሮግራም ናቸው፡፡ በዚህ እግረመንገዳዊ ጉዳይ ላይ አንድ ሁለት የግርጌ ማስታወሻዎችን አንስቼ ማለፍ እወዳለሁ፡፡

አንደኛው የንግግር ፀሐፊ (ስፒች ራይተር) ጉዳይና ሚና እንዲሁም ሙያ ነው፡፡ በሰለጠነው ዓለም የሁሉም ዓይነት ፕሬዚዳንቶች ንግግር የሚጻፈው በዚህ ዓይነት ባለሙያ ነው፤ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ለምሳሌ የእያንዳንዱን ስፒች ራይተር ስም ማንነት በግልጽና በነጻነት የሚናገሩት "ምስጢር" አዋቂ ውስጥ አዋቂ ሚዲያዎች ብቻ ሳይሆኑ ራሱ የእያንዳንዱ መሪ ወይም ፕሬዚዳንት አስተዳደር ነው፡፡ ምደባው ሥራው ሹመት ነው፡፡ ስለዚህም የፕሬዚዳንት ሬጋን፣ የፕሬዚዳንት ክሊንተን ወይም ቡሽ ንግግር ፀሐፊ ብሎ መናገር የትኛውንም ፕሬዚዳንት ክብር ማቃለል አያውቅም ማለት አለመሆኑ ማንም የሚያውቀው ነው፡፡

እኛ አገር ግን ጉዳዩ ዝብርቅርቅ ያለ የተደበላለቀ ነው፡፡ የኮሎኔል ወይም የሊቀመንበር ወይም የፕሬዚዳንት መንግሥቱ ንግግር ፀሐፊ ብለን የማንነጋገረው ወይም እንዲያ ተብሎ ሲነገር ያልሰማነው የማንሰማው ንግግሩን ሁሉ ሰውዬው ራሳቸው ስለሚጽፉት የሪፖርቱ አዘጋጅ ራሳቸው ስለነበሩ አይመስለኝም፡፡ በአንዱ ወይም በሌላ መልኩ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ንግግር ፀሐፊ እየተባለ ሲነገር እስከ አሁን ያልሰማነው ከንግግሩ ወይም ከሪፖርቱ ጀርባ ያሉ የነበሩ ሰዎችን ሙያዎችን ችሎታዎችን አሉኝ ብሎ መናገር ነውርና ክልክል የሚያደርግ ወግና ባህላችን አሁንም ስለቀጠለ ካላዘለቀ ብቻ አይመስለኝም፡፡ ይህ አሰራር አሁንም ገና ያልተዳረሰ መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ቢቻልም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግሮች ሪፖርቶች የሚያዘጋጅ ሰው የታደሉ አይመስለኝም፡፡ ንግግራቸውን ሪፖርታቸውን የሚጽፉ ሳይሆን ምናልባት የማስተርጎም አስፈላጊነት ቢኖር ይህንን እንኳ በቅጡ የሚወጣላቸው አለ ብሎ ለመናገር በእጅጉ ያዳግታል፣ ያስቸግራል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ምናልባትም በሚያስቸግር አሰራር የሪፐብሊኩን ፕሬዚዳንት የመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ንግግር የሚያዘጋጀው ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ የያዘው መንግሥት ማንኛውም ሰው ነው ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር ያዳግታል፡፡ ከአንዳንድ "የተፈቀደ" ማሻሻያዎች ጭማሪዎች በስተቀር የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ንግግርም የሚሸተው ያው የፈረደባቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ነው፡፡

የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት እንዲሁም የእንግሊዝ ርዕሰ ብሄር የሆኑት የንግሥቲቷ የፓርላማ ንግግር ሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ፕሮግራም፣ ሥልጣን ላይ ያለው አስተዳደር አዘጋጅቶ እንዲነበብ የሰጠው ንግግር ነው ብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ መናገር አሁንም ገና ነውር ነው፡፡ የአንዱን ክብር መንካት የሌላውን ሁሉንም እኔ ካልሰራሁት ብሎ መሟዘዝ ፍፁማዊ ስልጣንን ማወጅ ነው የሚመስለን፡፡ ትክክል ግን አይደለም፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት በየዓመቱ ሰኞ መስከረም ወር መጨረሻ ሳምንት ላይ የሚያቀርቡት የፓርላማ የሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ የመክፈቻ ንግግር የአስፈጻሚውን የመንግሥት ሥልጣን አካል ፕሮግራም የሚያቀርበው፣ ኢህአዴግ ራሱን የሚሸተው ፕሬዚዳንቱ ራሳቸው የተቀዱት ከዚያው ውሃ ስለሆነ አይደለም፤ መሆንም የለበትም፡፡ የተዘጋጀላቸውን ስለሚያነቡ ማንበብም ስላለባቸው ነው፡፡ ይህ ግን የአድማ ወይም የሴራ ምልክት አይደለም፡፡ የአዋቂና "የአላዋቂ" ግንኙነት መግለጫም በጭራሽ አይደለም፡፡ ደንብ ነው፡፡ ወግ ነው፡፡ ንግሥት ኤልሳቤጥ በየዓመቱ የሚያደርጉት ይህንኑ ነው፡፡ በእንግሊዝና በኢትዮጵያ መካከል ልዩነት ያለ መሆኑ ግን እውነት ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን በተለየ ምክንያት ጭምር በንግስቲቷና በፕሬዚዳንቱ መካከል እጅግ በጣም ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2001 ዓ.ም የምንሰማው የእኛም የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ንግግር የኢህአዴግ መንግሥት የዓመቱ ሊጂስሌቲቭ ፕሮግራም ነው፡፡

ለመሆኑ ሌጂስሌቲቭ ፕሮግራም ማለት ምንድ ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ መቼና እንዴት እንደምን ተጀመረ?

"በአገራችን የሎጂስቲቭ ፕሮግራም "ባህል" መሰረት የጣለው ወይም ጅምሩን ያስተዋወቀው በ2ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን አካባቢ ነው፡፡ ሁለተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ1992ቱ ምርጫ እንደተቋቋመ ሥራውንም የጀመረው መስከረም 1993 ዓ.ም እንደሆነ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ምክንያትና በዚያ መካከል በህወሓት አመራር ውስጥ የተፈጠረው ከፍተኛና አገር ጭምር ያናጋ ቀውስ ከሞላ ጎደል በ1993 ዓ.ም ሙሉውን የመንግሥት ሥራ ቀጥ ብሎ ቆሞ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አዲሱ ጅምር ውጥን የመጣው ከዚያ በኋላ ነው፡፡ በዚህም የ1994 ዓ.ምን የፌዴራል መንግሥት የሥራ እቅድ ሪፖርት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በዚህ የመስከረም 1994 ሪፖርታቸው "የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እቅዳችን"ን በተለይም በዚህ ርዕስ ስር "በየደረጃው የሚገኙትን የህዝብ ምክር ቤቶች ማጠናከር"ን አስመልክተው የተናገሩት (በጽሑፍ ያቀረቡት) ለዚህ ዓይነተኛ ምልክት ነው፡፡

"በየደረጃው ያሉ የመስተዳደር አካላት እቅዳቸውንና የፖሊሲ ሃሳባቸውን በየወቅቱና በተሟላ ሁኔታ ለመረጣቸው ምክር ቤት በዝርዝር እያቀረቡ በሰፋት እንዲመከርበት ያደርጋሉ፡፡ በየምክር ቤቱ ያሉ የኢህአዴግ አባላት በምክር ቤት አባልነታቸው በሚነሱት ጉዳዮች ላይ በሰፊው እንዲሳተፉ ለማበረታታት አስፈላጊ የሆኑ የአሰራር ለውጦች ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ የሌሎች ድርጅቶች አባላትም በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የላቀ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይበረታታሉ፡፡ በየምክር ቤቱ የሚመከርባቸው ጉዳዮች ለህዝቡ በሰፊው ቀርበው ህዝቡ እንዲወያይባቸው እንዲከራከርባቸውና የሚመስለውን ደግፎ የማይመስለውን ለመቃወም እንዲቻል ሁኔታዎች ይመቻቻሉ፡፡ ምክር ቤቶቹ ስራቸውን የግልጽነት መርህን በተከተለና ህዝቡ በሰፊው ሊሳተፍ በሚችልበት አኳኋን እንዲያካሂዱ ያደርጋል፡፡ ይህ ሪፖርት የዚህ አሰራር የመጀመሪያው ርምጃ ይሆናል ብለንም እናምናለን፡፡" ነበር ያሉት፡፡

የአቶ መለስ በ1994 ዓ.ም ከላይ በጠቀስኩት አንቀጽ ውስጥ በመጨረሻው አረፍተ ነገር "ይህ ሪፖርት የዚህ አሰራር የመጀመሪያው ርምጃ ይሆናል ብለንም እናምናለን" ለምን እንዳለ አሁን ከሰባት ዓመት በኋላ ሪፖርቱን ራሱን ማየትና ማንበብ ብቻ የሚገልጸው ነገር የለም፡፡ አቶ መለስ ይህን ያሉት እያነበቡት ያለው ይህ ሪፖርት የሚሰማበት የምክር ቤቱ ስብሰባ በቀጥታ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ስርጭት እየተሰማ ያለ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንደምናውቀው አቶ መለስ የሚገኙበት የምክር ቤቱ ስብሰባ በቀጥታ ሲሰራጭ እንሰማለን እናያለን፡፡

ከዚህ በተረፈ ከአቶ መለስ የ1994 ዓ.ም ሪፖርት በተጠቀስኩት አንቀጽ ውስጥ ያሉትን እያንዳንዱን አረፍተነገሮች ወደ ጥያቄ እየለወጡ እውነት? ውሸት? ብሎ ማንሳት ምላሹም ላይ "መገማገም" ይቻላል፡፡

እውን በየደረጃው ያሉ የመስተዳደር አካላት እቅዳቸውንና የፖሊሲ ሃሳባቸውን በየወቅቱና በተሟላ ሁኔታ ለመረጣቸው ምክር ቤት በዝርዝር ያቀርባሉ? በስፋት እንዲመከርበት ያደርጋሉ?  ከኢህአዴግ ውጭ ያሉ የሌሎች ድርጅቶች አባላት በፓሊሲ ጉዳዮች ላይ የላቀ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተበረታተዋል?  በምክር ቤት የሚመከርባቸው ጉዳዮች ለህዝብ በሰፊው ቀርበው ህዝቡ እንዲወያይባቸው እንዲከራከርባቸውና የመሰለውን ደግፎ የማይመስለውን ለመቃወም እንዲችል ሁኔታዎች ተመቻችተዋል?  ወይስ ተባብሰዋል? ተቀልብሰዋል?

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የ1994 ዓ.ም ሪፖርት "በየደረጃው ያሉ፣ የመስተዳደር አካላት እቅዳቸውንና የፖሊሲ ሃሳባቸውን በየወቅቱና በተሟላ ሁኔታ ለመረጣቸው ምክር ቤት በዝርዝር እያቀረቡ በሰፊው እንዲመከርበት ያደርጋሉ" ቢልም የዚህ ብቸኛ መገለጫ ከፌዴራሉ መንግሥት አኳያ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ከሚያቀርቡት የአስርተ"ኘ) ገጽ የመክፈቻ ንግግር ከሚገልጸው የህጎች ዝርዝር በላይ ከፍ አላለም፡፡ በዚህ ላይ የሚደረገውም ውይይት ሌላው ቀርቶ በ1999 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ የወጣው የምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት የስነምግባር ደንብ በአንቀጽ 12 በሰባት ንዑስ አንቀጾች "የሚዘረዝረውን" ያህል እንኳን ዝርዝርና ግልጽ አይደለም፡፡

የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት በየዓመቱ በመስከረም ወር የመጨረሻው ሳምንት ሰኞ የሚያሰሙን ንግግር የኢህአዴግ መንግሥት "እቅድና የፖሊሲ ሃሳብ" ወይም ሥልጣን የያዘው ፓርቲ መንግስት የሌጂስሌቲቭ ፕሮግራም የሚያደርገው ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ1994 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የፌዴራል መንግስት የሥራ እቅድ ሪፖርት ያስተዋወቀውና በዚያ መሰረትና ከዚያ ጀምሮ እየተለመደ በመጣው አሰራር ላይ ብቻ የተመሰረተ ግን አይደለም፡፡ እውን ይህ ነገር የመንግስት እቀድና የፖሊሲ ሀሳብ "በየወቅቱና በተሟላ ሁኔታ ረመንግሥትሪ ለመረጠው ምክር ቤት በዝርዝር እያቀረበ በሰፊው እንዲመከርበት" አድርጓል ወይ? ማለት ሌላ ጥያቄ ሆኖ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ1996 ዓ.ም በጥቅምት ወር ያወጣው የውስጥ ደንብም ይህንን የመንግሥት የሌጂስሌቲቭ ፕሮግራም "ህግ" ወይም "ደንብ" ማድረጉ አልቀረም፡፡

በዚህም መሰረት ይህ ለህትመት ያልበቃ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት ውጭ ብዙ ስርጭት የሌለው የምክር ቤቱ ውሳኔ ከሚወስናቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ምክር ቤቱ እንደምን አድርጎ ህግና ፖሊሲ እንደሚያመነጭ የሚደነግገው ነው፡፡ በዚህም ውስጥ መንግሥት ፖሊሲዎችንና ህጎችን በፕሬዚዳንቱ ንግግር አማካኝነት እንደሚያስተዋውቅ ይህም ኦፊሺያል እንደሚሆን ይወስናል፡፡ አዲስ ሕግ እንዲወጣላቸው የሚያስፈልጉ ጉዳዮች በፋይዳቸውና ቅድሚያ በሚሰጣቸው መጠን ልክ እና በቅደም ተከተላቸው፣ ህጎችም ረቂቁ የደረሰበት ደረጃ በሌጂስቲቭ ፕሮግራሙ ይገለጻል፡፡

ይህ ፕሮግራም የሚመለከተው ዓይነተኛ ህጎችን ማለትም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ህግ የሚያወጣባቸውን ጉዳዮች ብቻ እንጂ ሌሎችን (የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ፣ ሚኒስትሮች ምክር ቤት መመሪያ የሚያወጣባቸውን) ጉዳዮች አይመለከትም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አሁንም እንደገና እግረ መንገዳችንን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህንን የወሰነበትን የጭቃ ምች 1996 ዓ.ም ውሳኔ የህግ ቦታ በጥያቄ ብቻ አንስቶ ማለፍ እንዲህ ያለ ሌላው ቢቀር በአገር ሌጂስሌቲቭ ፕሮግራም ውስጥ የማይካተት ህግ ዓይነተኛና ይዘት ያለው መብትና ግዴታ የሚያቋቁም ሊሆን ይችላል ወይ ብሎ ጠይቆ በሌላ ርዕስ ሊስተናገድ የሚችል ውይይትና ሙግት መጋበዝ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

የመንግሥት ፖሊሲና የህግ ሀሳቦች ወይም የሌጂስቲቭ ፕሮግራም የሚቀርበውን፣ በየዓመቱ በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ የሚሰማው የፕሬዚዳንቱ ንግግር ከዚህ በተጨማሪ ቅደም ተከተላቸው የተሸጋሸገውን ወይም የኋላው ወደፊት የፊቱ ወደኋላ እንዲሆን የተደረገበትን ህግ እንዲወጣላቸው የተደረጉ ጉዳዮችን ማሳየት እንዳለበት የሚወስነውም ይኸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ1996 ዓ.ም ውሳኔ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይህ የሌጂስቲቭ ፕሮግራም እንዴት እንደሚዘጋጅ በዝርዝር የሚወሰነው ይህ የውስጥ ደንብ፣ እያንዳንዱ ሚኒስትር /ሚኒስትሩ ጉዳዩን የሚያቀርበው ለካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስቴር መሆኑንና ፕሮግራሙንም የሚያዘጋጀው ይኸው ሚኒስቴር መሆኑን ይወስናል፡፡

እዚህ ላይ አሁንም እንደ ሌላ ጉዳይ እግረ መንገዴን እንዳነሳ የሚያሰገድደኝ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስቴር የሚባለውን የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ወይም ፓርትፎሊዮ በተመለከተ ነው፡፡ መጋቢት 1997 ዓ.ም ታትሞ የወጣውን ሴንተር ፎር ኢንተርናሽናል ሌጋል ኮኦፕሬሽን የተባለው የሆላንድ አማካሪ ድርጅት ያጠናው የኢትዮጵያ (Comprehensive Justice Reform Program Baseline Study Report) ይህ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት የተቋቋመው በበርካቶች ለጋሽ ማህበረሰብና በኤክስፖርቶች የውሳኔ ሃሳብና ግፊት መሰረት መሆኑን ገልፆ እንደ ፈረንሳይ ባሉ አገሮች የመንግስት ዋና ፀሐፊ (ዋና ጽህፈት ቤት) የሚሰራውን ዓይነት ሥራ የሚሰራ እጅግ በጣም ተፈላጊና ጠቃሚ ምክር ቤት መሆኑን ሁሉንም በዚህ ረገድ የተባበሩትንና የተረባረቡትን ያመሰግናል፡፡

ለኢትዮጵያ የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ቀርቦ ነገር ግን ወሬውም ድምፁም የጠፋው ይህ በኢትዮጵያ የህግና የፍትህ ስርዓት ላይ በርካታ የሥራ ትችትና መሰረታዊ ለውጦች እንደ ውሳኔ ሃሳብ አድርጎ የሚያቀርበው ጥናት መቋቋሙን ደግፎ ስለተናገረለት የካቢኔ ጉዮዳች ሚኒስቴር (ሚኒስትር ለማቀርበው ምስጋና የመቋቋሙንም አስፈላጊነት አስመልክቶ የሚገልጸው ደስታ መኖር አለመኖሩን ራሴን ከመጠየቄ በፊት ለመሆኑ እንዲህ ያለ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት አለን ወይ?  ተቋቁሟል ወይ?)  የሚል ጥያቄ እንዳነሳ እገደዳለሁ፡፡ ጥናቱ የተካሄደው በጁን 2003 እና በማርች 2005 መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ ስለሆነ በዚህ ጊዜ ውስጥ የወጣ የአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የታወጀ ህግ ወይም ማሻሻያ እንዲህ ያለ መስሪያ ቤት ስለማቋቋሙ በጭራሽ አላውቅም፡፡ አሁን ሥራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው 1998 ዓ.ም አዋጅ በፀደቀበት የ3ኛው የምክር ቤቱ የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ውስጥ ስለሹመቱ የሰማነው የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር/ቴር እዚያ ህግ ውስጥ ስሙ የለም፡፡

ንግግሩ ውስጥ ወደሚካተተው በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጭቃ ምች 1996 ዓ.ም ውሳኔ በሚለው መሰረት ደግሞ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስቴር አደራጅቶ ፕሬዚዳንቱ የሚያቀርቡት ከሌጂስሌቲቭ ፕሮግራም አካል ወደሚሆነው የመንግስት እቅድ "የፖሊስና የህግ ሀሳብ" ዝርዝር ስንመለስ እንደምሳሌ እንደናሙና አድርገን የምንወስደው የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ባለፈው ዓመት መስከረም 27 ቀን 2000 ዓ.ም ያቀረቡትን የ3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ንግግር ነው፡፡ በዚህ ንግግር አማካኝነት ወይም እዚያ ውስጥ የቀረበው የመንግስት ሌጂስሌቲቭ ፕሮግራም ያካተታቸውና በኋላ ፀድቀው አዋጅ ሆነው ሲወጡ በሚጠሩበት አጭር ወይም ረጅም ርዕሳቸው፣ በስምና በስማቸው ብቻ የጠራቸው የኢኮኖሚውን ዘርፍ በዚያም ስር ግብርናውን፣ ንግድና ኢንቨስትመንቱን ፋይናንስና ታክስን የሚመለከቱት ናቸው፡፡ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር በሚል ሌላ ሰፊ ርዕስ ስርም የተካተቱ ሌሎች ረቂቅ ህጎች ነበሩ፡፡

ግብርናው ውስጥ የማዳበሪያ ማምረትና ንግድ፣ የእጽዋት ዘር፣ የደህንነት ህይወት፣ የእንስሳት በሽታ መከላከልና ቁጥጥር፣ የስጋ ምርመራ፣ የእንስሳት ኳራንቲና አጓጓዥ፣ የንብረት ሃብት ልማትና ጥበቃ የተባሉት ሲሆኑ እነዚህም ከሞላጎደል ሁሉም "የማሻሻያ" ረቂቆች ናቸው፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንት ንዑስ ዘርፍ ውስጥም ተካትተው በፕሬዚዳንቱ ንግግር ከተገለፁት መካከል የመጀሪያው ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1990ዎቹ አጋማሽ ድረስ እራሱን እናት ህጉን በሚመለከት ረገድ ብቻ ከሰባት ላላነሰ ጊዜ ሲሻሻል የቆየው አሁንም በ2000 ዓ.ም ማሻሻያ ይቀርብበታል ተብሎ ነገር ግን እንደ ፕሬዚዳንቱ ንግግር ቃል ማሻሻያው ሳይቀርብ የቀረው የኢንቨስትመንት አዋጅ ነው፡፡ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ማሻሻያም ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ ያንኑ ያህል ሲሻሻል የቆየ ነው፡፡ ሌሎችም እንደዚሁ በአመዛኙ ማሻሻያዎች ናቸው፡፡
በፋይናንስና ታክስ ንዑስ ዘርፍ ስር በ2000 ዓ.ም የመንግሥት የህግጋት መርሃ ግብር የተካተቱት በተለይም ግብርናን የሚመለከቱት ሁሉም ረቂቅ አዋጆች (የገቢ ግብርና የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ማሻሻያ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ማሻሻያ፣ የቴምብር ቀረጥ አዋጅ ማሻሻያ የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ ማሻሻያ) ሁሉም ማሻሻያዎች ናቸው፡፡ በዚያው የ2000 ዓ.ም የፓርላማ የሥራ ዘመንም አልቀረቡም፡፡

መንግሥት ፕሮግራሙን እንደ ኢትዮጵያ በሪፖብሊኩ ፕሬዚዳንት እንደ ታላቋ ብሪታንያ ደግሞ በንግሥቲቷ አማካኝነት ለፓርላማ ካቀረበ በዚህም ላይ ውይይት ተደረጎ እንደ ሁኔታው ከፀደቀ በኋላ መንግሥት የግድ በፕሮግራምህ በቃልህ ትገዛለህ ይህንንም ፕሮግራምህን ታሟላ ዘንድ ትገደዳለህ የግድ ባይባልም ለምሳሌ ከመልካም አስተዳደርና ከዴሞክራሲ ዘርፍ አኳያ (በፕሬዚዳንቱ የ2000 ዓ.ም ንግግር መሰረት) የሙስና ወንጀል ጠቋሚዎችና የወንጀል ምስክሮች የአካልና የስራ ጥበቃ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነሥርዓት አዋጅ፣ የማስረጃ ህግ ረቂቅ፣ የአስተዳደር ጉዳዮች ረቂቅ ማቅረብም የዘንድሮ ሥራ ነው፣ የዚያ የስራ ዘመኔ እቅድ እሱ ነው ካለ በኋላ ይህ ሳይሆን ሲቀር ጥያቄው የቃል ማጠፍ ወይም ቃልን ያለማክበር፣ ሲደጋገም ደግሞ ያንኑ ያህል በቃል አለመገኘት ብቻ አይደለም፡፡ ያለእነዚህ ሕጎች መቀጠል ይህንን የፖሊሲ ክፍተት ይዞ መጓዝ ማለት ነው፡፡

የዘንድሮው የመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ (ማለትም የመስከረም 26/2001 ዓ.ም) የመክፈቻ ንግግር የሚያስተዋውቀው ለፓርላማ ቀርቦ ውይይትና ሙግት የሚደረግበት የመንግስት የሌጂስሌቲቭ ፕሮግራም ምን የተለየ ነገር ይዞ ይመጣል? ብለን ለምንጠይቅ መንግስት በአገሪቷ ርዕሰ ብሄር አማካኝነት ለአገር የሚያቀርበው የራሱን ፖሊሲ ወደ ህግ የሚለውጥበት የሕግ ቅርጽና ይዘት የሚሰጥበት ጉዳይ ዝርዝር ተፈፃሚ ከሚሆን ገበያ የወጣ ሰው የሸመታ ማስታወሻ ሊስት በላይ እንዲሆን ስለምንፈልግ ነው፡፡ በገንዘብ አቅም ልክ መዘጋጀት፣ ልክ የሌለውን ፍላጎት ከአቅም ጋር አወዳድሮ መመጠንና መግታት፣ ቅደም ተከትል መወሰን፣ የባሰ የባሰውን፣ ይበልጥ የሚያንገበግበውን ቅድሚያ መስጠት የሚባል አይነት አሰራር ተራ ነገር ነው፡፡ የአገር የሌጅስሌቲቭ ፕሮግራም ግን በይዘትም በአይነትም ከዚህ የበለጠ የላቀና የተወሳሰበ ነው፡፡ እያንዳንዱ የውሃ ጠብታ በእያንዳንዱ ጣሪያ ላይ የሚፈሰውና የሚሰባሰበው ከእያንዳንዱ አሸንዳ የሚፈስሰው ውሃ እያንዳንዱ ጅረት ወንዝ ወደ አንድ ግብ መግባት መፍሰስ አለበት፡፡

ሌላው ቀርቶ የእያንዳንዱ የተሰበረ ረቂቅ ህግን የተጨመቀ አጭር ይዘት የሚያካትት ከፖሊሲ ወደ ህግ ሀሳብነትና ረቂቅ አዋጅነት ሂደት ውስጥ የሚደርስበትን የእድገትና የእርምጃ ደረጃ እንድናውቅ ሳይደረግ "በተሟላ ሁኔታ. . . በዝርዝር እየቀረበ በሰፊው እንዲመከርበት ይደረጋል" ስለሚባል እቅድ የፖሊሲ ሃሳብ ምን ብለን እናወራለን፡፡   
Last Updated ( Sunday, 05 October 2008 )
 
< Prev   Next >