| ያልተነቀለ የብሔራዊ ባንክ "ሰንኮፍ" |
|
|
| Monday, 21 January 2008 | |
|
አባዋሪ ጅብሪል
በመስከረም ወር 1996 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ሦስት አዳራሾች ውስጥ ተከፋፍለን ከተሰበሰብን በኋላ በመጨረሻው ቀን በተደረገው አጠቃላይ ስብሰባ በባንኩ ውስጥ እንዳሉ ከተጠቀሱ ችግሮች አንዱ የአስተዳደር መምሪያ ሀላፊዎች ቅንነት አለመኖር ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ የዚያን ጊዜው የአስተዳደር ተ/ም/ሥ/አስኪያጅ የአሁኑ የሠራተኛ ጉዳዮችና ሪከርድ ዋና ክፍል ሀላፊ እጃቸውን አውጥተው "...በመምሪያው የቅንነት አለመኖር የሚለው አባባል እኔ ያለሁበትን አካባቢ የሚመለከት ነውና ምን ማለት እንደሆነ ቢብራራ..." ይላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የባንኩ ገዥ "...መምሪያው ያለበት ችግር ከተባለው በላይ ነው፡፡ አሰራሩም የተጨማለቀና የሻገተ ነው..." ብለው ሲመልሱ በመምሪያው ውስጥ ባሉ የሥራ ሀላፊዎችና አንዳንድ ሠራተኞች አንጀቱ ያረረው ሠራተኛ በጭብጨባ ያደምቀዋል፡፡፡ በመጨረሻ የተዘጋጀልንን ስልጠና አጠናቃችኋል ተብለን ወደየቢሮአችን ተመለስን፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ምንም ለውጥ ላይመጣ ሁለት የዕረፍት ቀናችንን እና ሁለት የሥራ ቀናትን ጨምሮ ለዚህ ስልጠና ባንኩ ለአዳራሽ ኪራይና ለምግብ የዋቢ ሸበሌንና የግሎባል ሆቴልን ጨምሮ አራት መቶ ሺህ ያላነሰ ብር ወጪ ማውጣቱ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከግዮን መልስ በባንኩ ክበብ ውስጥ ለተዘጋጀው "ጌት ቱጌዘር" ፕሮግራም ለቢራ፣ ለድራፍትና ለመሳሰሉት ተጨማሪ ወጪ ተደርጓል፡፡ ባንኩ በጣም የቆዩና ሥር የሰደዱ ችግሮች ያሉበት ብቻ ሳይሆን አሁን አሁን በየቀኑና በየሣምንቱ አሳዛኝና አስደንጋጭ ነገር የሚሰማበት፣ እንደ ቻርሊና እንደ ሚስተር ቢን ፊልሞች አስቂኝ ድርጊቶች የሚፈጸሙበት፣ ውሳኔዎችንና የፕሮጀክት ሥራዎችን በማንዛዛትና በማጓተት ሪከርድ ሰብሮ በጊነስ መጽሀፍ ላይ ስማቸውን የተያያዙ በሚመስሉ የሥራ ኃላፊዎች የተሞላ ነው፡፡ ከብሔራዊ ባንክ ዋና ዋና ተግባራት አንዱ የአገሪቱን ብር ማሳተም፣ ማሰራጨት፣ መሰብሰብና ከዝውውር የሚወጡ የብር ኖቶችን ማቃጠል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህንኑ ሥራ ለረጅም አመታት አንጻራዊ በሆነ መልኩ በጥሩ ሁኔታ ሲያከናውን ቢቆይም ከቅርብ አመታት ወዲህ በተለይም ከአዲሱ የብር ለውጥ ጋር በተያያዘ ባንኩ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገብቶ ይገኛል፡፡ ያለውን ችግር በዚህ አምድ ላይ ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡ ችግሩን ዋና ዋናውን በዝርዝር የምንመጣበት ሲሆን ችግሩ የባንኩ ማኔጅመንት ወደ ብር ለውጥ ሲገባ በደንብ አስቦበትና አቅዶ ነው ወይ የገባበት የሚያስብል ነው፡፡ የእሳት ማጥፋት ስራ ዓይነት ሆኗል፡፡ በባለ 50 እና በባለ 100 ብር ኖቶች ላይ የሚሰራውን ፎርጅድ ለመከላከልና ለመቀነስ በሚል ምክንያት በኖቶቹ ላይ አንጸባራቂውን መስመርና ሌሎች ምስጢራዊ ለውጦችን አካቶ ያለምንም የቀለም ለውጥ ታትሞ የመጣው ብር ወደ ስርጭት ከገባና የቀድሞው ብር ወደ ባንኮች ሲመለስ፣ ተመልሶ ወደ ዝውውር እንዳይውል ቀነ ገደብ ተቀምጦለት ጎን ለጎን ሲሰራ ከቆየ በኋላ የብር እጥረት ሲያጋጥም የተሰበሰበው ብር ተመልሶ ወደ ዝውውር እንዲገባ ተደርጎ ቀነ ገደቡ ይራዘምና የተሰጠው ቀነ ገደብ ያበቃል፡፡ ባንኩ ህዝቡ በእጁ ያሉትን ገንዘቦች በጊዜ በአዲሶቹ ኖቶች እንዲተካ በተለያዩ ዘዴዎች በደንብ መቀስቀስና ማሳወቅ ሲገባው ተኝቶ ከርሞ የጊዜ ገደቡ ማብቂያ ሊዳረስ ሲል የይድረስ ይድረስ ስራ በመስራቱ ብዙ ህዝብና ድርጅቶች ለኪሳራ ተዳርገዋል፡፡ ለዚህም በህዝቡ በህዝቡ ሳይሰበሰብ የቀረው የቀድሞ የት በትንሹ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ እዚህ ላይ ከተሰሩት ስህተቶች አንድ ፎርጅድ ለመከላከል ታስቦ የብር ለውጥ ከተደረገ የኖቶቹ ቀለም ሙሉ ለሙሉ መለወጥ ነበረበት፡፡ ሁለተኛው ስህተት ከዝውውር ውጪ የሚሆኑት ኖቶች በሂደት እየተሰበሰቡና ተመልሰው ወደ ዝውውር እንዳይገቡ በማድረግ ማስወገድ ሲቻል ቀነ ገደብ ተቀምጦ ለመለወጥ በመሞከሩ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ብር ሳይሰበሰብ በመቅረቱና የኖቶቹ ቀለሞች መመሳሰል ተጨምሮበት ኖቶቹ ለፎርጅድ ስራ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ ሦስተኛው ስህተት የብሩ ጥራት ተጠብቆ እንዲታተም ባለመደረጉ በአዲሶቹ ኖቶች ላይ ያለው አንጸባራቂ መስመር በቶሎ ስለሚለቅ በዝውውር ውስጥ የበፊቱ ብር ነው፤ ወይም ፎርጅድ ነው፤ በሚል ጥርጣሬ ብሩን ለመቀበልና ላለመቀበል በተጠቃሚውና በሻጮች ዘንድ ጭቅጭቅ በማስከተል ላይ ይገኛል፡፡ የነቶሎ ቶሎ ቤት ትርፉ ይኸው ነው፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው የከረንሲ ማኔጅመንት ሥራ ብቃት ያለው የሥራ መሪና ሠራተኛን የሚፈልግ፣ የአገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ተከትሎ የብር ፍሰቱንና ዝውውርን አስቀድሞ በማጥናት ብር ማሳተምና ማሰራጨት፣ የባንኩንና የቅርንጫፍ ግምጃ ቤቶችን /ኢሹ ሆልዲንግ ብራንችስ/ የገንዘብ ማስቀመጫዎችን ማስፋት፣ ዘመናዊ የመቆጣጠሪያና ብቃት ያላቸው የማቃጠያ መሳሪያዎችን መትከልና በየጊዜው በሚደረግ ክትትል ከዝውውር የወጡ ኖቶችን ማቃጠል የሚጠይቅ ሰፊና ትልቅ ስራ ነው፡፡ ይህንን የማያከናውነው መምሪያ ተጠሪነቱ ለምክትል ገዥው ሲሆን ስራውንም በበላይነት የሚቆጣጠሩት እሳቸው በመሆናቸውና የበታቾቻቸውን እንደ አለቃ ስለማያዩዋቸው፣ ዋናው ገዥ ደግሞ ስራውን ሁሉ የምክትል ገዥው አድርገው በመውሰዳቸው ለብዙ አመታት የስራ እቅድና አፈጻጸም ሪፖርት ሲቀርብ አንዳንድ መመሪያዎችንና አስተያየቶችን ከመስጠት ውጪ ነገር ዓለሙን ትተውት ነበር፡፡ በመሆኑም ዛሬ የብዙ አመታት ችግሮች ተደማምረው የባንኩ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባንኮችና የአገሪቱ ችግሮች ሆነዋል፡፡ የብር መረጣና ቃጠሎ ስራ ባለው የአሰራር ደንብ መሰረት ጠቅለል ባለ መልኩ ሲቀርብ ከባንኮች የሚመጣው ብር ተቆጥሮ ከተመረጠ በኋላ ለዝውውር የሚውለውና የሚቃጠለው ተለይቶ በሚመለከተው ሰራተኛ ተፈርሞበትና ማኀተም ተደርጎበት የኢሹ ዋና ክፍል ተረክቦ የናሙና ቆጠራ እስኪደረግለት ድረስ በቮልት (ግምጃ ቤት) ውስጥ እንዲቀመጥ ያደርጋል፡፡ በኋላም ለዝውውር የሚውለው ሲሰራጭ መቃጠል ያለበት ኖትም ከኦዲት መምሪያ የሚመደቡ ሠራተኞችና ከራሱ ከመምሪያው የሚመለከታቸው ሠራተኞች ባሉበት ከውጪ የጄኔራል ኦዲተርና የፌዴራል ፖሊስ ተወካዮች ባሉበት እንደ ብሩ አይነት በመመሪያው ላይ በተቀመጠው ፐርሰንት መሰረት የናሙና ቆጠራ ተደርጎ ይረጋገጣል፡፡ በኋላ ወደሚቃጠልበት ቦታ ተወስዶ ከላይ የተጠቀሱት አካላት ባሉበት እንዲቃጠል ይደረጋል፡፡ ሆኖም ይህ አሰራር ሳይጠበቅ በ1996 ዓ.ም. የናሙና ቆጠራ ከተደረገና ከተጠናቀቀ በኋላ ከላይ የጠቀስናቸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አንድ ላይ ሆነው ፈርመውና ማህተም አድርገው በግምጃ ቤት ውስጥ 100 ብር ኖት እንዲቀመጥ ተደርጎ በሩ ይታሸጋል፡፡ እዚህ ጋር ብሩ እስኪቃጠል ድረስ ጥቂት ቀናት ያውም ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ካጋጠመ ታሽጎ እንዲቀመጥ መደረጉ አሳማኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም እንዲቃጠል የናሙና ቆጠራ የተረደረገለት ብር ለሳምንታንትና ለወራት በግምጃ ቤት ውስጥ እንዲቀመጥ መደረጉ ከመመሪያው ውጪ የሆነ አሰራር ጉዳዩ በዚህ አላበቃም፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ የባለ 100 ብር ኖት እጥረት በማጋጠሙ እንዲቃጠል የተቀመጠው ብር እንደገና ይቆጠርና የተሻሉት ኖቶች ወደ ዝውውር ይግቡ ተብሎ ቆጠራ ሲደረግ ከ38 ሺህ ብር በላይ ይጐድላል፡፡ ወንጀሉ በማን እንደተሰራ ለማጣራት ሲሞከር ሁሉም ራሱን ነጻ ሊያደርገው የሚችለውን ነጥብ እያስቀመጠ በመሄዱ እንቆቅልሽና ግራ የሚያጋባ እንደሆነ እስከ ዛሬ ድረስ አለ፡፡ ሁኔታውን የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል እያጣራው ነው፤ ከተባለ ከሦስት አመት በላይ የሆነው ቢሆንም እከሌ ነው ሳይባል ብሩን የበላውም ሆነ ያስበላው አካል ሳይታወቅና ሳይጠየቅ ጉዳዩ የውሀ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ሌላው የባንኩ ማኔጅመንት አስቀድሞ ሳይዘጋጅ ታትሞ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ያዘዘው ብር በጊዜው በተከታታይ በመግባት ላይ ነበር፡፡ ይሄ በራሱ ችግር አልነበረም፡፡ ነገር ግን መጀመሪያ ለሚመጣው ብር አዲስ ማስቀመጫ ባለመዘጋጀቱ አልያም አስቀድሞ ከየባንኮች የተሰበሰበው ብር ቦታውን እንዲለቅ ባለመደረጉ ግምጃ ቤቱ ውስጥ መሄጃ እስኪጠፋ ድረስ ስርአት በሌለው መልኩ ብሩ እየገባ እንዲቀመጥ መደረጉ የባንኩ ማኔጅመንት በተቀናጀ ሁኔታና በእቅድ የማይመራ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ይሄ ብቻ ሳይሆን አስቀድመን እንዳልነው ቀድሞ ያለው ክምችት ሳይቃለል ከዝውውር እንዲወጡ የተደረጉትና በአዲስ የተተኩት የባለ 50 እና ባለ 100 ብር ኖቶች ከየባንኩ ተሰብስበው ስለተጠራቀሙ ሌላ ፈጥረዋል፡፡ እነዚህን እንዲተኩ የተደረጉት የብር ኖቶች ለማቃጠል እንዲቻል ባለው መመሪያ መሰረት የናሙና ቆጠራ የሚደረገው እንደ ባለ አንድ፣ አምስትና አስር ብር ኖቶች የተወሰነ ፐርሰንት ሳይሆን 100 በመቶ ተቆጥረው ነው፡፡ ነገር ግን በማኔጅመንቱ ዳተኝነት የተፈጠረውን ክምችት ለማቃለልና ለማስወገድ ምክንያትና የባንኩ ማኔጅመንት ከሰባትና ስምንት አመታት በፊት ጀምሮ መስራት የነበረበትን የቤት ስራ ባለመስራቱና ለዚህም የጠየቀው አካል ስላልነበረ የተፈጠረው ችግር እንደ ተራራ ገዝፎ ሲመጣ መመሪያውን ጥሶ የባለ 50 እና 100 ብር ኖቶች 50 በመቶ የናሙና ቆጠራ ተደርጎላቸው እንዲቃጠሉ ይወስናል፡፡ ለዚህም ከአገር ውስጥ ባንኪንግና በተለያዩ መምሪያዎች ውስጥ ያሉና በቀድሞው መዋቅር የትሬዠሪ መምሪያ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ሰርተው የነበሩ ሰራተኞችን አሰባስቦ ቅዳሜና እሁድ የውሎ አበልና የትርፍ ሰአት ክፍያ እየተከፈላቸውና ብሩ ወደ ሚቃጠልበት ቦታ ተጓጓዘ፡፡ ሾፌሮችን ጨምሮ አብረው ለሚሄዱ የስራ ሀላፊዎችና ሰራተኞች ልዩ የውሎ አበል በመፍቀድ ስራው በዘመቻ መልክ እንዲሰራ ከታዘዘና ወደ ስራ ከተገባ በኋላ ሌላ አዲስ ነገር ተከስቷል፡፡ አሮጌ የብር ኖት ከተባለውና እስካሁን ከተቆጠረው ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ውስጥ፣ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ በዝውውር ላይ ያለው አዲሱ ብር ተገኝቷል፡፡ ለመሆኑ የ50 በመቶ የናሙና ቆጠራ ብቻ ተደርጎ ቀሪውም አብሮ ይቃጠል የሚል ውሳኔ ያስተላለፉት ሀላፊዎች በባንኩ ውስጥ የሚሰራውን ሥራ በደንብ ያውቁታል? ገና አሁንም ከዚሁ ከዝውውር የወጣ ነው ከተባለው የባለ 50 እና 100 ብር ኖት ውስጥ እስካሁን ተቆጠረ ከተባለው ብር ያልተናነሰ በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ብር ስላለ ከእርሱ ውስጥም በጊዜው ከተገኘው ያልተናነሰ በዝውውር ላይ ያለው አዲሱ የባለ 50 እና 100 ብር ኖት እንደሚገኝ በመታመኑ የ50 በመቶ የናሙና ቆጠራው ቀርቶ ወደ 100 በመቶ የናሙና ቆጠራ ወይም ወደ ትክክለኛው አሰራር እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ እዚህ ላይ የተሰራው ሌላው ስህተት የዚህ ብር መጠን ሪፖርት ሲደረግ ከህዝቡ የተሰበሰበው አሮጌ ኖት ነው ተብሎ ነው፡፡ አሁን በዝውውር ላይ ያለው ኖት ውስጡ በመገኘቱ በተገኘው ብር መጠን የተሰበሰበው መጠን ሲቀንስ በህዝብ እጅ ያለውና ያልተሰበሰበው በዚያው መጠን ይጨምራል ማለት ነው፡፡ በጣም የሚገርመው ይሄ ሁሉ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ልዩነት እንደ ትክክለኛ ቁጥር ተወስዶ አንዱ ለአንዱ ሪፖርት እያደረገ ተሰራ ተብሎ ለመንግስት ሪፖርት የተደረገው፡፡ ይኸ ጉዳይ በአንድ ጋዜጣ ከወጣ በኋላ በዋናው ገዥ የኢኮኖሚ አማካሪ የሚመራና የውጪ ባንኮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ በጊዜው የሰው ሀይል አመራር መምሪያ ሥራ አስኪያጅ የነበሩትን፣ የቀድሞውን የከረንሲ ማኔጅመንት መምሪያ ሥራ አስኪያጅና ሌሎችንም ሰዎች በአባልነት የያዘ ኮሚቴ አዋቅረው የተከማቸው ብር እንዴት ሊወገድ እንደሚችል ጥናት አስጠንተዋል፡፡ የተጠናው ጥናት ተግባራዊ ሳይደረግ በድጋሚ ወደ መሠረታዊ የሥራ ማሻሻያ ጥናት በመገባቱ ችግሩ እስካሁን አልተፈታም፡፡ ለመሆኑ ማኔጅመንቱ ብሩ በጊዜ ካልተቃጠለ ይሄ ችግር ሊከሰት እንደሚችል እንዴት ሳያስብ ቀረ? አውቆትና በወቅቱ ሪፖርት ተደርጎለት ከሆነ ለምን አፋጣኝ እርምጃ ሳይወስድ ቀረ? ለዚህ ጉዳይ ተጠያቂው ማን ነው? መልሱን የባንኩ ባለቤት ተገቢውን ማጣራት አድርጎ ይድረስበት፡፡ ሌላው ዓ.ም. ከተከሰተው በተጨማሪ በብሔራዊ ባንክ ታሪክ አጋጥሞ የማያውቅ የብር ስርቆትና በልዩ ሁኔታ ከህዳር ወይም ከታህሳስ 1998 ዓ.ም. ጀምሮ ተከስል፡፡ ይህ ጉዳይ የተለያዩና ራሳቸውን የቻሉ በቂ ምክንያቶችና በወንጀሉ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ያሉበት ነው፡፡ ቢሆንም የተከሰቱትን ዋና ዋና ነገሮች ሳንጠቅስ ማለፉ ትክክል አይመስለንም፡፡ በ1998 ዓ.ም. በህዳር ወይም በታህሳስ ወር ላይ በተለምዶ ሚንት ከሚባለው የገንዘብ መረጣና ማረጋገጫ ዋና ክፍል ግቢ ቮልት (ግምጃ ቤት) ውስጥ 10 ሺህ ብር ይጠፋል፡፡ ማነው የወሰደው? በሚል ማጣራት ሲደረግ ብር ለመጫን ከገቡት የቀን ሰራተኞች ውስጥ ነው የሚል ጥቆማ በመድረሱ ጉዳዩ ለፖሊስ ሪፖርት ተደርጎ የተጠረጠሩትን ሁለት ልጆች ተገቢውን ማጣራት ለማድረግ ረጅምና አሰልቺ ጊዜ ፈጀ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለልጆቹ ማንነቱ ያልታወቀ ክፍል አስቀድሞ መረጃ ይሰጣቸው ነበር የሚል ነው፡፡ ጉዳዩ ምን ላይ እንደደረሰ በአብዛኛው ሰው ዘንድ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በኋላ ላይ እንደታወቀው ከቁጥጥር ጉድለት የመጣ ችግር ነበር፡፡ ሁለተኛውም እንደዚሁ ከተወሰኑ ወራት በኋላ በዚያው ግቢ ውስጥ ብር ለመጫን ከገቡት የቀን ሰራተኞች ውስጥ አንዱ 10 ሺህ ብር ሰርቆ ሲወጣ እጅ ከፍንጅ በጥበቃ አባላት ይያዛል፡፡ ልጁም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰደ በኋላ ጥቂት ጊዜያት ታስሮ ተፈቷል፡፡ አሁንም ይሄ ጉዳይ ምን ላይ እንደደረሰ በአብዛኛው ሠራተኛ ዘንድ የማይታወቅ ሲሆን ችግሩም ሊከሰት የቻለው እንደ በፊቱ ሁሉ ብሩ ሲጫን ጥብቅ ቁጥጥር ካለማድረግ ነው ተብሏል፡፡ ሦስተኛው ስርቆትም እንደዚሁ ከውጪ አገር ታትሞ የመጣውን ብር የቀን ሰራተኞች ከመኪና ላይ እያወረዱ ሲያስገቡ ተፈፀመ፣ አንዱ የቀን ሰራተኛ ግምጃ ቤት ውስጥ ተደርድሮ ከተቀመጠው የባለ 100 ብር ኖት ውስጥ አንድ ብሪክ ወይም 100 ሺህ ብር ሰርቆ ይሰወራል፡፡ በጊዜው የነበሩት የስራ ሀላፊዎች ሁኔታውን እንዳወቁ በፍጥነት ለበላይ አካልና ለፖሊስ ሪፖርት ማድረጋቸውን አሁንም ጉዳዩ በፖሊስ እጅ እንዳለ ነው የሚታወቀው፡፡ እዚህ ላይ የሚነሱት ጥያቄዎች ልጁ ብሩን እንዴት በምን ይዞ በየት በኩል ወጣ? ባንኩ ስራውን ለመቆጣጠር በቂ የሰው ሀይል መድቦ ነበር? የቀን ሰራተኞች ለሁለት ጊዜያት የ20 ሺህ ብር ስርቆት ሲፈጽሙ የባንኩ ማኔጅመንት ስራው ቋሚና የማያቋርጥ መሆኑን እያወቀ አፋጣኝ የማስተካከያ ስራና የቁጥጥር ስልት ቢቀይስ ኖሮ 100 ሺህ ብር ከመንግስት ባንክ ያውም ከአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ውስጥ እንደዚህ በቀላሉ ይሰረቅ ነበር? የሚመለከተው አካል የሚያጣራው ጉዳይ ይሆናል፡፡ አራተኛውና ምናልባትም በጣም በረቀቀና ሁኔታ የተከሰተ በሚመስል መልኩ የተፈፀመው የገንዘብ ስርቆት በገንዘብ መረጣና ቆጠራ ዋና ክፍል ውስጥ ተከስቷል፡፡ አሁንም ስርቆቱ ይቁም ወይም ይቀጥል ተቆጥሯል ተብሎ የታሸገው ብር እንደገና ሲቆጠር የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ሰፊና ጠለቅ ያለ ከመሆኑም በላይ ገና ከጫፍ ያልደረሰ ነው፡፡ በሁሉም ዘንድ መነጋገሪያ የሆነው በ1996 ዓ.ም. ም ከተዘጋጀው ብር ውስጥ ከ38 ሺህ ብር በላይ ጎድሎ መገኘቱና ከዚያም በኋላ ስርቆት እየተፈጸመ በመምጣቱ ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ የተቃጠለው በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠረው ብር ወረቀት ላይ በሰፈረው ሪፖርት ሳይሆን በተጨባጭ ብሩ ሳይጎድል ነው ወይ የተቃጠለው ለሚለው ጥያቄ በቂና አስተማማኝ መልስ የሚሰጥ ሰው መገኘቱ አጠራጣሪ መሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ ስራው ይሄን ያህል ውስብስብና አስቸጋሪ አልነበረም፡፡ የባንኩ ማኔጅመንት በአዲሱ መዋቅር የዋና ክፍሉን የሰራተኞች ቁጥር አሳድጎ፣ የክፍሉን አሰራር ለውጦ፣ የስራው ብዛትና ሀላፊነት ጨምሮ እያለ ገና ድሮ ተመድበው ባሉ ሁለት የስራ ሀላፊዎች ስራውን ማሰራትና መቆጣጠር መፈለጉ ምን ያህል በትክክለኛ እቅድ እንደማይመራ የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህም ስራው ተበላሽቶ በተገቢው መንገድ የሚቆጣጠር አካል በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩና ዘመናዊ የቁጥጥር መሳሪያ ባለመኖሩ ምክንያት ብሩ እየተሰረቀ ሲበላ ከረመ፡፡ እስካሁንም ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ የጠፋው ትክክለኛ ገንዘብ ያልታወቀ ሲሆን በቅርብ የተከሰተውን የጉድለት መጠን ለማወቅ ባንኩ ከ100 በላይ የሆኑ የንግድ ባንክ ሰራተኞችን በትርፍ ሰአት ክፍያ ቅዳሜና እሁድ እያስገባ በማሰራት በኦዲት ሪፖርት ተረጋግጦ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ለማድረግ ከ200 ሚሊዮን ያላነሰ የባለ 10 ብር ኖትን አስቆጥሯል፡፡ ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩት ሦስት ሰራተኞች ከስራቸው ላይ ከታገዱና ታስረው ከተከሰሱ በኋላ በቀጠሮአቸው ቀን ከታሰሩበት ቦታ ፍ/ቤት ቢቀርቡም ወንጀሉን የሚመረምረውም አካል ሆነ አቃቤ ፍ/ቤት ባለመገኘታቸውና ጉዳዩን በተሰጣቸው ቀናት ውስጥ አጣርተው ባለመቅረባቸው ምክንያት ፍ/ቤቱ ሦስቱንም ሰራተኞች በዋስ ከእስር እንዲፈቱ ብይን ሰጥቷል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ክስ የመሰረቱት አካላት መረጃ ሳይኖራቸው ነው ወይ መረጃ ካላቸውስ በቀጠሮ ቀን እንዴት ፍ/ቤት ሳይቀርቡ ቀሩ? ከወንጀሉ ተጨማሪ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር፡፡ ስርቆቱን ያመጣው የክፍሉ አሰራር መለወጥ ነው፣ የቀን ሰራተኞቹ ቤተሰቦች የባንኩ ቋሚ ሰራተኞች ናቸው፡፡ እናም በስርቆት የተጠረጠሩት የቀን ሰራተኞች ሲባረሩ ከነዚህ ሰራተኞች ጋር ስለሚጋጩ ከዋናው ግቢ የተባረረ ወደ ሚንት ከሚንት የተባረረ ወደ ዋነው ግቢ ገብቶ እንዲሰራ ይደረጋል፣ ከቀን ሰራተኞች ውስጥ አንዳንዶቹ ክፍለ ሀገር አይሱዙ ገዝተው ያሰራሉ ይባላል፣ እንደዚህ የሚወሩትንና ሌሎች እስካሁን ድረስ በግልጽ ያልወጡና ያልታወቁ ነገሮች በተጨባጭ አጣርቶ እውነቱን ይዞ ይወጣል ተብሎ ሲጠበቅ የወደፊቱን ባናውቀውም እስካሁን ባለው ሁኔታ ጉዳዩ ሁሉ የሦስቱ ሠራተኞች ጉዳይ ብቻ ሆኖ በእንጥልጥል ላይ ያለ ይመስላል፡፡ የሆነው ሆኖ ጉዳዩ ያልተቋጨና መጨረሻውም ያልለየ በመሆኑ ሁሉም እውነቱንና መጨረሻውን ለማወቅ በመጠባበቅ ላይ ስለሆነና ጥሩው ከመጥፎው በአግባቡ ተለይቶ መጠየቅ ስላለበት ጉዳዩን የያዙት አካላት እውነቱን ሳይደብቁ ሁሉም ትምህርት ሊያገኝ በሚችልበት መንገድ ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡ ለነገሩ የውስጥ ኦዲት መምሪያ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ያደረገው የምርመራ ሪፖርት የነበረውን የቁጥጥር ሥርዓት መበላሸት ያጋለጠና የሥራ ሀላፊዎችንም ተጠያቂ የሚያደርግ ቢሆንም ሦስት ሠራተኞች ብቻ ተባረው ጉዳዩ ተዳፍኖ እንዲቀር የተፈለገ ይመስላል፡፡ የባንኩ ማኔጅመንት መስራት ያለበትን ስራ በጊዜው ሰርቶ ቢሆን ኖሮ ባንኩ ዛሬ እንደዚህ አይነት ውስብስብ ችግር ውስጥ ይገባ ነበር? አይመስለንም፡፡ በአጠቃላይ የባንኩ አሠራር እንደዚህ በተዝረከረከና ባልተቀናጀ ሁኔታ እየሰራ ነው የአገሪቱን ገንዘብ ሊያስተዳድርና ሊቆጣጠር የሚችለው? እንደ እሳት አደጋ መኪና እሳት ባየበት ቦታ እየሮጠ የእለቱን ችግር ብቻ ለመገላገል የሚሰራ፣ ራሱ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የተተበተበና የተዘፈቀ አመራር ትኩረቱን ሁሉ አሰባስቦ መሠረታዊ የገንዘብ ፖሊሲዎችን ማውጣትና በቂ የሆነ የቁጥጥር ሥራ ሊሰራ ይችላል? ከላይ እንደጠቀስነው ባጭሩ ቢያንስ ከዛሬ ሰባትና ስምንት አመታት ጀምሮ ማኔጅመንቱ መስራት ያለበትን ስራ ባለመስራቱ "ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ" እንደተባለው ስራውን በፕሮጀክት ለማሰራት ከመገደዱም በላይ ይሄ አልበቃ በማለቱ እንደገና ሌላ ኮሚቴ አዋቅሮ ጥናት እስከ ማስጠናት ድረስ አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ሊገባ ችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለሌላ ስራ የነበረበትን ጊዜና የሰው ሀይል ጨምሮ ባንኩ ለውሎ አበል፣ ለትርፍ ሰአት ክፍያ፣ ለነዳጅና ሌሎች ከስራው ጋር ለሆኑ ወጪዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ብር አውጥቷል፡፡ ሥራው በጊዜ ባለመሰራቱ ባንኩ ተጨማሪ ከ50 በላይ የኮንትራት ሠራተኞችን ቀጥሮ በማሰራት ላይ ይገኛል፡፡ ቢሆንም በተመሳሳይ መልኩ የቁጥጥር ሥርዓቱን በበቂ ቴክኖሎጂ ባለማደራጀቱ አሁንም በድጋሚ የብር ስርቆት በኮንትራት ሠራተኞች በመፈፀም ላይ እንዳለ ሪፖርት በመደረጉ ለጊዜው አንድ የኮንትራት ሠራተኛ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለች ሲሆን እነርሱ የቆጠሩትን ብር ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ ከተለያዩ መምሪያዎች የተውጣጡ ሠራተኞች አሁንም እንደበፊቱ ቅዳሜና እሁድ በትርፍ ሠዓት ክፍያ እንዲሰሩ መመሪያ ተላልፎ ሥራው ተጀምሯል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |