| ሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በኘሬዚዳንቱ... |
|
| Wednesday, 08 October 2008 | |
|
ሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በኘሬዚዳንቱ ንግግር ላይ ሞሽን ያቀርባሉ
በኃይሌ ሙሉ በፓርላማ መቀመጫ ያላቸው ሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኘሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ባለፈው ሰኞ ዕለት ለተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ የሥራ ዘመን መክፈቻ አስመልክቶ ያደረጉትን ንግግር በመቃወም የውሳኔ ሃሳብ (ሞሽን) እንደሚያቀርቡ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡ የኦፌዴን ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ብዙ ታላላቅ የአገር ጉዳዮች በኘሬዚዳንቱ ንግግር አለመዳሰሳቸውን ገልፀው ፓርቲያቸው መነሳት ነበረባቸው የሚላቸውን ጉዳዮች በሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ በሚካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ሞሽን እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል፡፡ "ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ የምትወጣበትን ቀን በናፍቆት ይጠብቃል" ያሉት አቶ ቡልቻ ሰው እየሞተና ንብረት እየወደመ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ኘሬዚዳንቱ ምንም አለማለታቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም "የተራበውን ወገናችን መመገብ ሳንችል ጦርነት ውስጥ ለረጅም ጊዜ መቆየታችን ተገቢ አይደለም" ብለዋል፡፡ አቶ ቡልቻ ያነሱት ሌላው ጉዳይ የትምህርት ጥራት ነው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት በየትምህርት ቤቱ በቂ የትምህርት መረጃ መፅሐፍት ባለመኖሩ በርካታ ተማሪዎች አንድን መፅሀፍ በየተራ ለመጠቀም ተገድደዋል፡፡ በቂ የትምህርት ቤት መፅሐፍ ለተማሪዎች ማቅረብ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት የኦፌዴን ሊቀመንበር የትምህርት ጥራት እንደ አንድ የአገር ጉዳይ ሆኖ መነሳት እንደነበረበት አመልክተዋል፡፡ በየክልሉ በብሔሮችና በጐሳዎች መካከል በሚካሄዱ ግጭቶች በርካታ ሰዎች ለሞት እንደሚዳረጉ የገለፁት አቶ ቡልቻ "የብሔሮች ግጭት መነሻ ምንድነው? መፍትሔውስ ምን መሆን አለበት?" የሚል ሀሳብ አለመነሳቱንና ኘሬዚዳንቱ አንድም ቃል አለመናገራቸውን እንደ ድክመት ወስደውታል፡፡ ኘሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ዙሪያ ምንም አለማለታቸውንም አቶ ቡልቻ ተችተዋል፡፡ እንደእርሳቸው እምነት በተለያዩ አካላት ብዙ ችግር እንደነበረበት በተገለፀው በ2000ው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ኘሬዚዳንቱ አንድ ነገር ማለት ነበረባቸው፡፡ የኢዴአፓ መድህን ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው ፓርቲያቸው በኘሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ንግግር ላይ ሞሽን ለፓርላማው እንደሚያቀርብና የሚቀርበውን ሞሽንም በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ተመካክሮ እንደሚወስን አስታውቀዋል፡፡ የኢዴኅህ ሊቀመንበር ኘሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው ፓርቲያቸው በኘሬዚዳንቱ ንግግር ላይ ሞሽን እንደሚያቀርብ ቢገልፁም በፓርላማ አሰራር ሞሽኑን አስቀድሞ ማሳወቅ ስለማይቻል ፓርቲያቸው የሚያቀርበውን የተቃውሞ ሀሳብ ለጊዜው ይፋ ማድረግ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀጣይ ማክሰኞ ዕለት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚቀርበውን ሞሽን (የውሣኔ ሃሣብ) ላይ ተወያይቶ ውሣኔ የሚያሳልፍ ሲሆን የነገ ሣምንት ሐሙስ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በኘሬዚዳንቱ ንግግር የመንግሥታቸውን አቋም ፓርላማ ቀርበው እንደሚያሳውቁ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |