| የሕዝብና ቤት ቆጠራ የመጨረሻ... |
|
| Wednesday, 08 October 2008 | |
የሕዝብና ቤት ቆጠራ የመጨረሻ ውጤት ለኮሚሽኑ ቀረበበታምሩ ጽጌ የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ በመላው አገሪቱ ያካሄደውን የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሥራ አጠናቆ ውጤቱን ትናንት መስከረም 27 ቀን 2001 ዓ.ም ለሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን አስረከበ፡፡ ከሶማሌና አፋር ክልሎች በስተቀር በግንቦት ወር 1999 በሁሉም ክልሎች 81ሺ መምህራንን አሰማርቶ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሥራውን ማከናወኑንና ሁለቱን ክልሎች በህዳር ወር 2001 ዓ.ም ቆጥሮ ማጠናቀቁን የጽህፈት ቤቱ ፀሐፊና የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳሚያ ዘካሪያ በተለይ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልፀዋል፡፡ በም/ጠ/ሚኒስትርና የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር በአቶ አዲሱ ለገሰ ሰብሳቢነትና የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት፣ የትምህርት፣ የማስታወቂያ፣ የአቅም ግንባታ፣ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የማዕከላዊ ስታስቲክስና ሌሎች መ/ቤት ተወካዮች በአባልነት ለሚገኙበት የሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን በትናንትናው ዕለት ጠቅላላ ሪፖርቱን ማቅረባቸውን የተናገሩት ወ/ሮ ሳሚያ፣ ሥራው በተቀላጠፈና በአጭር ጊዜ መድረሱ እንዳስደነቃቸው ገልፀዋል፡፡ "ቆጠራው ከተካሄደ ከዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ይፋ ማድረጊያ ጊዜው ለምን ተጓተተ?" በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ "የሕዝብና ቤት ቆጠራው በተቀላጠፈና በአጭር ጊዜ ነው የተጠናቀቀው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት አዳዲስ ቴክኖሎጂ (እስካኒግ ማሽን) በመጠቀማችን ነው፡፡ እንኳን በእኛ አገር ባደጉ አገሮችም ቢሆን የሕዝብና ቤት ቆጠራ ከአንድ ዓመት በታች ቀድሞ ይፋ አይደረግም፡፡ በእኛ አገር ቀድሞ በነበሩት ቆጠራዎች እንደምናደርገው የቅድሚያ ጥናት ውጤት ይፋ ያደርጋል፡፡ አሁን ግን አዲስ ቴክኖሎጂ በመጠቀማችን ወደ ኮምፒዩተር ስናስገባ የሚፈጀውን ጊዜ በማስቀረቱ ያንን ሳናደርግ አጠቃላይ ውጤቱን በአንድ ዓመት ውስጥ አጠናቀን ለሚመለከተው አካል (ለኮሚሽኑ) አስረክበናል" በማለት ወ/ሮ ሳሚያ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ወደ ኋላ ዘግይተው ቆጠራ የተካሄደባቸው አፋርና ሶማሌ ክልሎች መሆናቸውን የገለፁት ዳይሬክተሯ፣ በአፋር ክልል በታሰበው ወቅትና ጊዜ ቆጠራው መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡ በሶማሌ ክልል ቆጠራውን ለማካሄድ ከ20 ቀናት በላይ እንደወሰደባቸው በሌሎቹ ክልሎች ቆጠራውን ለማጠናቀቅ አስር ቀናት ብቻ እንደበቃቸው የተናገሩት ወ/ሮ ሳሚያ የተመደበው በጀት ባለመብቃቱ የሶማሌ ክልል መንግሥት አምስት ሚሊዮን ብር መደጎሙንም አስታውቀዋል፡፡ በሁለቱ ክልሎች ለተደረገው ቆጠራ ከድሬዳዋ፣ ከሐረሪ፣ ከደቡብ እና ከአዲስ አበባ የተውጣጡ ዘጠኝ ሺህ መምህራን መሳተፋቸውን ወ/ሮ ሳሚያ ገልፀዋል፡፡ የኤጀንሲው ውጤት የተቀበለው ኮሚሽኑም ተወያይቶበት በቅርብ ቀን ለፓርላማ በማቅረብ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡ |
|
| Last Updated ( Thursday, 09 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |