| ነዳጅን መደጎም የሚገባው ስንዴ... |
|
| Wednesday, 08 October 2008 | |
ነዳጅን መደጎም የሚገባው ስንዴ የነዳጅ ድጎማን መሻማት አልነበረበትም!የቤንዚን፣ የናፍጣና የኬሮሲን ዋጋ በአገራችን ሰሞኑን ጨምሯል፡፡ የተሰጠው ምክንያትም ለነዳጅ ይደረግ የነበረው ድጎማ ከውጭ ስንዴ ለመግዛት ለማዋል ስለአስፈለገ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሬ አቅማችን አነስተኛ መሆን ከነዳጅ ድጎማ ወይም ከስንዴ ግዥ አንዱን እንድንመርጥ ስለአስገደደንና የምግብ ነገር ቅድሚያ መስጠት ስለአስፈለገ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሬ አቅማችን ለምን ቀነሰ? የነዳጅ ዋጋ የመውረድ አዝማሚያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታየ፣ የእኛ ድጎማ መቀነስ ነበረበት ወይ? አጨማመሩስ ትክክል ነው ወይ? ኬሮሲን ዝቅተኛ የሕብረተሰባችን ክፍልም ስለሚጠቀምበት እዛ ላይ የተደረገው ጭማሪ ሌላው ጋ ማድረግ አይቻልም ነበር ወይ? ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎች በጭማሪው ዙሪያ ማንሳት ይቻላል፡፡ የአሁኑ አጀንዳችን ግን ይህንን ማንሳትና መተንተን አይደለም፡፡ መነሳት ያለበት ትልቁ ጥያቄ ነዳጅን መደጎም የሚገባው ስንዴ፣ ከነዳጅ ድጎማ መሻማት ነበረበት ወይ? መነሳት ያለበት የጊዜያዊ የዋጋ ከፍና ዝቅ ማለት ሳይሆን የፖሊሲ ጥያቄ ነው፡፡ የፖሊሲ ጥያቄውም ስንዴ ኢምፖርት ማድረግ ነበረብን ወይ? ስንዴን ኤክስፖርት የምናደርግ ወይስ ስንዴን ኢምፖርት የምናደርግ ሕዝቦች ነን መሆን ያለብን? በእኛ አስተያየት ስንዴ ነዳጅን መደጎም ነበረበት እንጂ፣ የነዳጅን ድጎማ መሻማት አልነበረበትም፡፡ ኢትዮጵያ የስንዴ ኤክስፖርተር እንጂ ስንዴን ኢምፖርት የምታደርግ አገር መሆን የለባትም፡፡ ስንዴ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ እንጂ የውጭ ምንዛሬን የሚቀራመት መሆን የለበትም፡፡ ታዲያ ለምን እንደዛ ሳይሆን ቀረ? መልሱ አጭር ነው፡፡ የፖሊሲና የአፈጻጸም ችግር! የመንግሥት ፍላጎት ኢትዮጵያ በምግብ ራስዋን እንድትችል ማድረግ እንደሆነ ይገባናል፡፡ ከተቻለም ኤክስፖርት የምታደርግ አገር እንድትሆን ማድረግም ፍላጎት እንዳለ እናውቃለን፡፡ ገጠርን ማዕከል ያደረገ፣ እርሻ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ነው ቢባልም ይህን ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ይህ ፍላጎትና እምነት ግን በፖሊሲ ተተርጉሞ በአፈጻጸም የሚታይና የሚረጋገጥ አልሆነም፡፡ ኢትዮጵያ በምግብ ራስዋን ለመቻልና ምግብ ኤክስፖርት ለማድረግ በመላው አገራችን ከጫፍ እስከ ጫፍ መዝነብ የለበትም፡፡ እያንዳንዱ የአገራችን ካሬ ሜትርም ለምና አምራች መሆን የለበትም፡፡ ለእርሻ የሚያመቹ የተወሰኑ በጣም ሰፋፊ አካባቢዎች ማልማትም እንኳን ኢትዮጵያን መላ አፍሪካን መመገብ በቻለ ነበር፡፡ ባሌ፣ አርሲ፣ ወለጋ፣ ጎጃም የሚገኙ የውሃና የልምላሜ ችግር የሌለባቸው አካባቢዎች በልዩ ጥናት፣ በልዩ ባጀትና በልዩ መንግሥታዊ ድጋፍ ቢለሙ ኖሮ ስንዴ ነዳጅን በደጎመ ነበር፡፡ ማልማት ስንል ግን ሁሉም ነገር ለአነስተኛ የገበሬ መሬት ይዞታና እርሻ በመተው ማለታችን አይደለም፡፡ አነስተኛ የገበሬ እርሻ እየለማ፣ ሰፋፊ መካናይዝድ እርሻ መኖር ይገባዋል፡፡ ንግዳዊ (ኮሜርሻል) እርሻ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሌላው ቀርቶ በደርግ ጊዜ የተጀመሩ ሰፋፊ የእርሻ ልማቶች ተጠናክረው ቢቀጥሉ ኖሮ ትልቅ ሚና በተጫወቱ ነበር፡፡ በመንግሥትም፣ በዓለም ባንክም፣ ብዙ እርዳታ ተደርጎላቸው፣ ብዙ ውጤት ያመጣሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረግ በምግብ ምርትና በኤክስፖርት ልዩ ትርጉም ሊኖራቸው በቻለ ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ አካሄድ ለምን ትኩረት እንደማይሰጠው ግልፅ ሊሆንልን አልቻለም፡፡ መንግሥት ከያዘው "ልማታዊ መንግሥት" አቅጣጫም አይጻረርም፡፡ ሰፋፊና መካናይዝድ ኮሜርሻያል እርሻዎች ለንግድ ተብለው ብቻ ሳይሆን የምግብ እጥረት ሲያጋጥም የሕዝብ ሕይወት ለመታደግም ዋስትና ይሆናሉ፡፡ ከአሜሪካና ከካናዳ ርዳታ እስኪደርስ ድረስ የሚጠፋ ሕይወትም አይኖርም፡፡ ላልተጠበቀ ረሃብና ድርቅም አስተማማኝ መከላከያና መጠባበቂያ ዋስትና ይሆናል፡፡ ሰፋፊ መካናይዝድ ኮሜርሺያል እርሻ ይስፋፋ ስንል አካሄዱ የግድ በመንግሥት ይካሄድ ማለት አይደለም፡፡ የግል ባለሃብቶች ሊገቡበት ይገባል፡፡ እንደ አበባውም ልዩ ማበረታቻ ያስፈልገዋል፡፡ እርሻ እንደ አንድ ትልቅ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተቆጥሮ ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብት በከፍተኛ ሁኔታ የሚበረታታ ሊሆን ይገባል፡፡ ምናልባት መንግሥት መቸ ተቃወምኩ ሊል ይችላል፡፡ ቁም ነገሩ ግን የመቃወምና አለመቃወም ሳይሆን በግልፅ የማበረታታትና አለማበረታታት ጥያቄ ነው፡፡ መንግሥት በግልፅና ፊት ለፊት ሰፋፊ መካናይዝድ ኮሜርሻል እርሻ እንደሚያበረታታና እንደሚደግፍ የአበባው አይነት ትኩረት እንዲሰጠው አላሰመረበትም፡፡ በግል ደረጃ ማስፋፋት ካልተቻለም መንግሥት ጠቃሚነቱን አይቶ ሊገባበት ይችላል፡፡ የግል እስኪገባበት ተብሎ የምግብ ነገር ችላ ሊባል አይገባም፡፡ መንግሥት ራሱም የምግብ ችግርን ለመፍታትና የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት በመንግሥት እጅ ሆነው ችላ የተባሉትን አጠናክሮ ሊያስተካክላቸው ይችላል፡፡ እንዲህ አይነቱ ነገር በቻይናም፣ በሕንድም የታየና የተሳካ ውጤት አስገኝቶ በቢሊየን የሚቆጠር ህዝባቸውን መግበው ምግብ ኤክስፖርት እያደረጉ ናቸው፡፡ በአገራችን ሱፐር ማርኬቶችም ይገኛሉ፡፡ ስንዴ እየገዛን ነው፣ ከነዳጅ ድጎማ ቀንሰን ለስንዴ ግዢ አውለነዋል የሚል አባባል በተሻለ ሁኔታ ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ ትገዛለች የሚለው ሞራልን የሚነካና አንጀትን የሚያሳርር ነው፡፡ መንግሥት ልዩ ትኩረት ይስጠው፣ እርሻን በዘመናዊ መልክ ያስፋፋ፤ ያጠናክር፡፡ ስንዴ እየገዛን ነው ከሚል አሳፋሪ ነገር ውጥቶ፣ ስንዴ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ሆኖ ነዳጅ የሚደጉምበትና ተትረፍርፎ ራሳችን በምግብ እንድንችል የሚያደርገንን ምዕራፍ ውስጥ ያሸጋግረን፡፡ ኢትዮጵያ ስንዴ ላኪ እንጂ ስንዴ ገዢና አስመጪ አገር አትሁን፡፡ |
|
| Last Updated ( Thursday, 09 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |