Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow የኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር...
የኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር... E-mail
Wednesday, 08 October 2008
Imageየኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር - 31ኛ ከ48 ደሃ አገራት

በጌታቸው ንጋቱ

"በአፍሪካ መልካም አስተዳደር ካልሰፈነ የአፍሪካ የተፈጥሮ ሃብት ብክነት ይቀጥላል፡፡ ኢንቨስተሮችም አፍሪካን እንደፈሩ ይቀራሉ፡፡ ዜጐችም አካላዊና የፋይናንስ ጥበቃና ከለላ ያጣሉ፡፡ ነገር ግን የአፍሪካ መንግሥታት እነዚህን በመቅረፍ መልካም አስተዳደር ማስፈን ከቻሉ አፍሪካ ያላትን እምቅ ኃይል ማውጣት ትችላለች፡፡ ያለ መልካም አስተዳደር ሠላም የለም፡፡ ያለ ሠላም ኢንቨስትመንትና ልማት የለም"፡፡
ሞ ኢብራሂም

ሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን የኢብራሂም የመልካም አስተዳደር መለኪያ /Index/ ሠኞ ዕለት በሸራተን ሆቴል የ2ዐዐ8 ሪፖርቱን በይፋ አውጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር ደረጃም ከነበረበት ደረጃ ማዘቅዘቁን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በኢብራሂም ኢንዴክስ ሪፖርት መሠረት ከሠሃራ በታች ካሉ 48 ኋላ ቀርና ደሃ አገራት ውስጥ በመልካም አስተዳደር ኢትዮጵያ 31ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ አዲሰ የወጣው የ2ዐዐ8 የኢብራሂም ኢንዴክስ እንደሚያሳየው ባለፈው ዓመት የነበረው የኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር ደረጃ ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው ወርዷል፡፡ ኢትዮጵያም ለመልካም አስተዳደር በተሰጠው ውጤት ከ1ዐዐ ነጥብ 50.9 አግኝታለች፡፡ ይህም አገሪቱ ከ48 የሠሃራ በታች አገራት 31ኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል፡፡

በኢብራሂም ኢንዴክስ መለኪያ መሠረት ካሉት አምስት መመዘኛዎች በሦስቱ ኢትዮጵያ ከነበረችበት ደረጃ ወርዳ አስመዝግባለች፡፡ በሠላምና ፀጥታ፣ በሕግ የበላይነት፣ በግልፅነትና በሙስና እንዲሁም ሕዝብን በማሳተፍና በሠብዓዊ መብት ጥበቃ ኢትዮጵያ ከነበረችበት ደረጃ ወርዳለች፡፡ ኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት አስመዝግባ የተገኘችው የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድሎች በመፍጠርና በሠው ኃይል ልማት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የሠላምና ፀጥታ ሁኔታ በ2007 ከነበረበት 75.2 በ2008 ወደ 72.8 ከመቶ በማግኘት አሽቆልቁሏልል፡፡ ይህም አገሪቱ ከ48ቱ ደሃ የአፍሪካ አገራት 35ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡ በሕግ የበላይነት፣ በግልፅነትና በሙስና ኢትዮጵያ ከመቶ ነጥብ 49.1 በ2007 የነበራት ሲሆን ይህም በ2008 ወደ 47.9 ከመቶ ወርዷል፡፡ ደረጃዋም 31ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ሕዝብን በማሳተፍና በሠብዓዊ መብት አያያዝ ከ48 አገራት 37ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ኢትዮጵያ በ2007 ካስመዘገበችው 44.3 በመቶ ወደ 40.4 ዝቅ ብላለች፡፡

ኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት አስገኘች የተባለችበት የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድል መፍጠር በ2ዐዐ7 ከነበረችበት 40.4 በመቶ ወደ 40.5 በመቶ በ2008 በ0.1 ከመቶ ጨምራለች፡፡ ይህም አገሪቱን ከደሃዎቹ የሠሃራ በታች አገራት 25 ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡ በሰው ኃይል ልማትም ኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት ያስመዘገበች ሲሆን በዚህም ከነበረችበት 51.0 ወደ 52.7 ከመቶ ከፍ ብላለች፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላት ደረጃ 23ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ማሽቆልቆል የታየው ሕዝብን በማሳተፍና የሠብዓዊ መብት አጠባበቅ ላይ ሲሆን ይህም ከነበረበት ደረጃ 3.9 በመቶ ወርዷል፡፡ በሪፖርቱ መሠረት ኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት ያስመዘገበችው በሠው ኃይል ልማት ነው፡፡

በኢብራሂም ኢንዴክስ ሙሉ መሻሻል ያልታየበት የአፍሪካ አካባቢ የአፍሪካ ቀንድ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ምን እንደሆነ የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን የቦርድ አባል የሆኑት የቀድሞ የአፍሪካ ኅብረት ዋና ፀሃፊ ዶ/ር ሳሊም አሕመድ ሣሊም ሲያስረዱ "በአፍሪካ ቀንድ የመልካም አስተዳደር መሻሻል ያላሳየው በአካባቢው በተፈጠረው ያለመረጋጋት እና ግጭት ነው፡፡ ሶማሊያ እጅግ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ትገኛለች፡፡ የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ግጭትም አልተፈታም፡፡ ይህም የአፍሪካ ቀንድ መልካም አስተዳደር እንዳይሻሻል አድርጐታል" ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ብቸኛ መሻሻል ያሳየችው አገር ጅቡቲ ናት፡፡ ሶማሊያ በአፍሪካ በመልካም አስተዳደር ከ48 አገራት 48ኛ ደረጃ በመውጣት የመጨረሻ ቦታ ይዛለች፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ከጅቡቲ ቀጥላ የተሻለ መልካም አስተዳደር ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ ሥትሆን ኤርትራ ከኢትዮየጵያ ቀጥላ በሦስተኝነት ትገኛለች፡፡ ሶማሊያ ከአፍሪካ ቀንድም በመጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

በኢብራሂም ኢንዴክስ መሠረት ከሠሀራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ከ2/3ኛ በላይ የሚሆኑት የመልካም አስተዳደር ሥራቸው መሻሻል አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር ግን ከነበረችበት ደረጃ ማሽቆልቆል ብቻ ሳይሆን ከምርጫ 97 በኋላ ካለው የመልካም አስተዳደር የወረደ ነጥብ ባለፈው ዓመት ማስመዝገቧ አጠያያቂ ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ  31ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው 30ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠችው ጊኒ-ቢሣዎ በ1.0 በመቶ ነጥብ ተበልጣ ሲሆን ከኢትዮጵያ ቀጥሎ 32ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው በቅርቡ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባትና በወታደራዊ አገዛዝ ሥር የምትገኘው ሞሪታንያ ነች፡፡ ኢብራሂም ኢንዴክስ ለኢትዮጵያ 50.9 በመቶ በመስጠት በእነዚህ ሁለት አገሮች መካከል ሲያስቀምጣት የሮበርት ሙጋቤ አገር ዙምባብዌ ከኢትዮጵያ ሳትርቅ በ50.4 ከመቶ 33ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

በአፍሪካ ከፍተኛ የሠብዓዊ መብት ጥሠት ካለባቸው አገራትና በመልካም አስተዳደር እጦት ከሚሰቃዩት ሕዝቦች መካከል ኢትዮጵያ ተጠቅሳለች፡፡ በደረጃቸው ከኢትዮጵያ በታች ያሉት አገራትም እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ነገር ግን ለመሻሻል የሚችሉበት ሠፊ ዕድል መኖሩን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በአፍሪካ በመልካም አስተዳደር የመጀመሪያውን ቦታ የያዘችው ሞሪሺየስ ስትሆን በኢብራሂም ኢንዴክስ መሠረትም 85.1 በመቶ አስመዝግባለች፡፡ ከሞሪሽየስ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ የምትገኘው ሲሼልስ 79.8 በመቶ እንዲሁም ቦትስዋና በ74.0 በመቶ በሦስተኝነት ትከተላለች፡፡

ጐረቤት አገር የሆነችው መንግሥት አልባዋ ሶማሊያ ከ48 አገራት 48ኛ ደረጃ ላይ 18.9 በማግኘት ከኋላ ትመራለች፡፡ ከሶማሊያ በመቀጠል በ47ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ዴሞክራቲክ ኮንጐ 29.8 በመቶ በማግኘት ነው፡፡ ቻድ በ33.9 በመቶ 46ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ጐረቤት አገር የሆነች ሱዳን በ34.2 በመቶ 45ኛ ደረጃ ስትይዝ፣ ኬንያ በ59.1 በመቶ 17ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ኤርትራ በመልካም አስተዳደር ይዞታዋ ከኢትዮጵያ በ10 አገራት ርቀት ከ48 አገራት 41ኛ ደረጃ በማግኘት ተቀምጣለች፡፡

የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን በአፍሪካ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚሠራ ሲሆን ከአፍሪካ መሪዎች ስልጣን በራሱ ፈቃድ ለለቀቀ የሃገር መሪ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላርና የኢብራሂም የመልካም አስተዳደር ሽልማት ተሸላሚ ያደርጋል፡፡ በዚህም መሠረት የቀድሞውን የሞዛምቢክ ኘሬዚዳንት ዮአኪም አልቤርቶ ቺሳኖ የመጀመሪያ ተሸላሚ በማድረግ መርጧል፡፡

የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን መስራች የሆኑት ሱዳናዊው ሞ ኢብራሂም የ2ዐዐ8 የኢብራሂም ኢንዴክስ በይፋ ሲገለፅ በሸራተን አዲሰ ባደረጉት ንግግር በአፍሪካ ያሉት ችግሮች ሁሉ ዋነኛው መንስዔ የመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን እና የመልካም አስተዳደር ችግር ከተፈታ ሌሎቹን ችግሮች ለመፍታት ቀላል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የአፍሪካ መንግሥታት ለሪፖርታቸው ምን ዓይነት ምላሽ ሊኖራቸው እንደሚችል ተጠይቀው ሞ ኢብራሂም ሲመልሱም "የአፍሪካ መንግሥታት ሪፖርቱን መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ እኛ አፍሪካ መሻሻል እያሳየች ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡ ይህ ሪፖርት በከፍተኛ ጥንቃቄ የተሰራ ከመሆኑም በላይ በራሳችን በአፍሪካዊያኖች ለአፍሪካ የተሰራ ነው፡፡ ኔልሰን ማንዴላንና ኮፊ አናንን የመሳሰሉ የአሕጉራችን ታላላቅ ሰዎች በአፍሪካ መልካም አስተዳደር ለማስፈን የምናደርገውን ጥረት እየደገፉ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ሥራ የምንሰራው የራሴን ገንዘብ በመመደብ ነው፡፡ ሃብቴን ያገኘሁት ከአፍሪካዊያን ነው፡፡ ለአፍሪካዊያንም ገንዘቡን መመለስ እፈልጋለሁ፡፡ ገንዘቡን ለመመለስ ትክክለኛው አማራጭ ደግሞ በአፍሪካ ዋነኛ ችግር የሆነውን የመልካም አስተዳደር እጦት በመፍታት ነው መሆን ያለበት" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር በቁጥር ሲገለፅ
 ምድብ
2007 እ.ኤ.አ (ከመቶ)
2008 እ.ኤ.አ (ከመቶ)
የ2008 ደረጃ (ከ48 አገራት)
 ሠላምና ፀጥታ
 75.2 72.8
 35ኛ
 የሕግ የበላይነት፣ ግልፅነትና ሙስና  49.1 47.9 31ኛ
 የሕዝብ ተሳትፎና የሠብዓዊ መብት 44.3    40.4
 37ኛ
 የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድል መፍጠር 40.4
 40.5
25ኛ
 የሠው ኃይል ልማት 51.0 52.7
  23ኛ


የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን የዘንድሮውን ሪፖርት በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ለማቅረብ መምረጡን ሲያስታውቅ የቦርዱ ሊቀመንበር ሞ ኢብራሂም፣ የቦርድ አባላቱ የሆኑት የቀድሞ የአየር ላንድ ኘሬዚዳንትና የተባበሩት መንግሥታት የሠብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ዶ/ር ሜሪ ሮቢንሠን፣ የአፍሪካ ህብረት የቀድሞ ሊቀመንበርና የታንዛንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ሣሊም አሕመድ ሣሊም፣ የዓለም ባንክ የቀድሞ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና የኬኘታውን ዩኒቨርሲቲ ምክትል ቻንስለር የነበሩት ዶ/ር ማምፌላ ራምፔሌ ተገኝተው ስለቀረበው ሪፖርትና ሥለ ሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከቦርድ አባላቱ በተጨማሪም የዘንድሮውን ኢንዴክስ በመስራት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረከቱት የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የሆኑት ዶ/ር ሮበርት ሮትበርግ ተገኝተዋል፡፡

የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ሪፖርት ከኢትዮጵያ መንግሥት ምንም ዓይነት ምላሽ እስካሁን ያልተሰጠበት ቢሆንም እንደ ሞ ኢብራሂም ገለፃ ግን መንግሥታት ባይወዱትም ሊቀበሏቸው እንደሚገባ ነው፡፡ "እነዚህ ቁጥሮች በጥናት የተገኙ ናቸው፡፡ የተለያዩ ምንጮችን ተጠቅመን በከፍተኛ ልፋትና ጥንቃቄ ነው የሠራናቸው፡፡ ቁጥሮች እውነትን ሥለሚናገሩ ቆንጆዎች ናቸው፡፡ በዚህ ማንም መከፋት የለበትም፡፡ አሁን ካሉበት ደረጃ ራሳቸውን መንግሥታት እንዲያሻሽሉ መጠቆሚያ ይሆናል፡፡ እኛ ይህንን ሪፖርት የምንሰራው አገራት ያሉበትን ደረጃ አውቀው እንዲሻሻሉ እንጂ ለሌላ ለምንም አይደለም፡፡ እኛ የሲቪል ማኅበራት እንጂ ሥልጣን ፈላጊዎች አይደለንም፡፡ ይህ ሪፖርት ከሌሎች ሪፖርቶች የሚለየው በራሳችን በአፍሪካዊያን የተሰራ በመሆኑና ለአፍሪካ መሻሻል ከማንም በላይ ስለሚመለከተን ነው" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን እያሻሻለ እና በአገሪቱም መልካም አስተዳደር እያሰፈነ መሆኑን ቢገልፅም አገሪቱ አሁን ያለችበት ደረጃ አሳፋሪ ከሚባሉት የመጨረሻዎቹ ተርታ ላይ ነው፡፡ መጨረሻ አካባቢ መሆኑም ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ አገራት የመልካም አስተዳደር መሻሻል ቢያሳዩም ኢትዮጵያ ግን ከነበረችበት ዝቅ ብላለች፡፡

የሞ ኢብራሂም ኢንዴክስ በኢትዮጵያ ሙስና ከመቀነስ ይልቅ መስፋፋቱን ያመለክታል፡፡ በአገሪቱ የፀረ ሙስና ኮሚሽን የተቋቋመው ሙስናን ለማጥፋት ቢሆንም በአገሪቱ የሙስና ሥራዎች መብዛታቸውን የኢብራሂም ኢንዴክስ ያሳያል፡፡ በዚህም መንግሥት የፀረ-ሙስና ኮሚሽንን ሥራ ውጤታማነት መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ በኢትዮጵያ የእምባ ጠባቂ ተቋምና የሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ቢቋቋምም የሠብዓዊ መብት ጥሰት በመስፋፋቱ አገሪቱ በዚህ ረገድ ከመቶ 40.4 ብቻ ማስመዝገቧን የተደረገው ጥናት ያመለክታል፡፡ በአገሪቱ የሕግ የበላይነት እየተከበረ እንዳልሆነም ይኸው የኢብራሂም ኢንዴክስ ያመለክታል፡፡

በተለይ በምርጫ 97 ወቅት ከነበረው የመልካም አስተዳደር ይዞታ አሁን አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ የወረደ መሆኑ በአገሪቱ ልማትና መልካም አስተዳደር እያሰፈንኩ ነው ለሚለው የኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ የሚያቀርብ ነው፡፡

የሞ ኢብራሂም ኢንዴክስ በየዓመቱ ከሠሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ የአገራትን የመልካም አስተዳደር ለውጥ በመገምገም ሪፖርቱን በተከታታይ የሚያወጣ ሲሆን የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽንም ታላቅ ሥራ ለሰሩት ሽልማቱን መስጠቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ የዘንድሮው ተሸላሚም በቅርብ ቀናት ውስጥ ተለይቶ የሚሸለም ሲሆን የሽልማቱ ኮሚቴ መሪ ኮፊ አናን ናቸው፡፡
Last Updated ( Thursday, 09 October 2008 )
 
< Prev   Next >