| መቋጫ ያጣው የኢትዮ... |
|
| Wednesday, 08 October 2008 | |
![]() መቋጫ ያጣው የኢትዮ - ኤርትራ - "ቀዝቃዛ ጦርነት" በየማነ ናግሽ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጠቅላላ ጉባኤ 63ኛ መደበኛ ስብሰባ ባካሄደበት ባለፈው ሳምንት ከቀረቡት አጀንዳዎች መካከል አንዱ የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጉዳይ ነበር፡፡ ሁለቱም አገሮች በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው አማካኝነት ለጉባኤተኛው ባቀረቡት ሪፖርት ተወዛግበዋል፡፡ የኤርትራው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በድርጅቱና በአሜሪካ ላይ ያሰሙት ወቀሳ ዋነኛ ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ እርምጃ ባለመውሰዳቸው ነው፡፡ ሉዓላዊው የኤርትራ ግዛት በኢትዮጵያ ወታደሮች ቁጥጥር ሥር መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም ኢትዮጵያ በአሜሪካ ድጋፍ ሰጪነት ሶማሊያን መውረሯና ይህም እጅግ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ማስከተሉን ጠቅሰዋል፡፡ አሜሪካ በሱዳን የምታደርገውን ጣልቃገብነትም ሚኒስትሩ የተቃወሙ ሲሆን፣ በጅቡቲ ላይ ኤርትራ ወረራ ፈጸመች የሚባለው የአሜሪካ ፈጠራ ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ ይህ ሁሉ በቀጣናው በሽብርተኝነት ሽፋን የሚፈፀም መሆኑን ጠቁመው፣ የአሜሪካ ፖሊሲ ካልተቀለበሰ ችግሩ ከቁጥጥር ውጪ ይሆናል በማለት ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ያላትን ቁርጠኝነትን በሶማሊያ የከፈለችውን መስዋዕት በማንሳት አስረድተዋል፡፡ በሶማሊያ በሽግግር መንግሥቱና በዓማፂዎች መካከል ድርድር ተደርጎ ተቀባይነት ያለው ስምምነት ላይ እንዲደረስ በጥብቅ እየሰራች መሆኗን ያስገነዘቡት አቶ ስዩም፣ ስለ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መውጣት አለመውጣት ያሉት ነገር ባይኖርም፣ የድርጅቱ የፀጥታ ምክር ቤት በአስቸኳይ ሰላም አስከባሪ ወደ ሶማሊያ እንዲልክ፣ ካልሆነም የአፍሪካ ህብረት የሰላም ልዑክን (አሚሶም) እንዲያጠናክር አሳስበዋል፡፡ አቶ ስዩም፣ የኢትዮ-ኤርትራን የድንበር ጉዳይ አስመልክተው፣ "ከኤርትራ ጋር ያለንን ማንኛውም ውዝግብ በሰላማዊ፣ ህጋዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት ዝግጁ ነን" በማለት ጦርነት የኢትዮጵያ አማራጭ እንዳልሆነ ለጉባኤተኞቹ አስረድተዋል፡፡ ኤርትራ በ1985 ዓ.ም ነፃነቷን ካገኘች በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት ግንኙነት ፣መልካም፣ ቢመስልም በተለይ በኢኮኖሚ ተንታኞች ቅጥ ያጣ፣ መርህ አልባ ወዘተ. የሚል ትችት ይሰነዘርበታል፡፡ በሁለቱም አገሮች መካከል የነበረው የኢኮኖሚ ግንኙነት ይመራ የነበረው በሁለት ሉዓላዊ አገራት መካከል የሚደረግ ዓይነት ሳይሆን በአንድ አገር ወስጥ ካሉ ክልሎች ጋር የሚደረግ ግንኙነት ተመሳሳይ እንደነበር ተንታኞቹ ይናገራሉ፡፡ ቅርጽ አልባ የንግድ ልውውጥ፣ ስምምነትና መርህ የሌለው የንግድ ሂደት ነበር ይላሉ፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ተንታኞችም፣ ኤርትራ በእነዚህ ፣ወርቃማ፣ ዓመታት ከኢትዮጵያ በህገ ወጥ መንገድ በመዘበረችው ሃብት በቀጣናው ኃያልነቷን ለማረጋገጥ ስትራቴጂ ነድፋ ስትሯሯጥ እንደነበረች ይናገራሉ፡፡ ይህ "መልካም" የሚመስል ነገር ግን መርህና ስርዓት ያልነበረው የሁለቱም አገራት ግንኙነት ግን ከአምስት ዓመት በላይ የዘለቀ አልነበረም፡፡ ኤርትራ በ1989 ዓ.ም የራሷን ገንዘብ (ናቅፋ) ማሳተሟ የቆየው ግንኙነታቸው ላይ ተደምሮ ተጨማሪ ውዝግብ ማስነሳቱን ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ኤርትራ የራሷን ገንዘብ ስታሳትም ከኢትዮጵያ ብር ጋር ሊኖረው የሚችል ምንዛሬ አሁንም ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ህግ የተከተለና በራሳቸው ፍላጎት ብቻ የተቃኘ እንደነበር በብዙዎች ይነገራል፡፡ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሁኔታው ስላሳሰባቸው፣ ጠንከር ያለ ምላሽ መስጠት መጀመራቸውና ግንኙነታቸውም፣ ህግና ስርዓት እንዲኖረው መጠየቃቸው በአዲሷ ኤርትራ ባለስልጣናት ዓይን በመልካም አልታየም፡፡ በመሆኑም፣ ከንግድ ግንኙነታቸው ባልተለየ ሁኔታ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል የሁለቱም አገሮች ድንበር በግልጽ ተለይቶና ተስማምተውበት አልነበረም፡፡ እንደውም አንዳንድ ምንጮች እንደሚጠቁሙት፣ ጉዳዩ በትጥቅ ትግል ወቅትም በሁለቱም ፣ነጻ አውጪ፣ ድርጅቶች መካከል ውዝግብ አስነስቶ እንደነበርና "የጋራ ጠላት (ደርግ) እናስቀድም" በሚል የተላለፈ ውሣኔ እንደነበር ነው፡፡ ሌሎች የግጭት ተንታኞችም፡ ታሪካዊ ገጽታውን በማየት የኤርትራውያን የተሳሳተ የራስ ምስልና (Wrong self image) ለኢትዮጵያውያን ያላቸውን አመለካከት ለጦርነቱ ዋነኛ መስንኤ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ረዳት ፕ/ር መድኃኔ ታደሰ "የኤርትራና የኢትዮጵያ ጦርነት፣ መነሻውና መድረሻው" በሚለው መጽሀፋቸው ይህንን የኤርትራውያን የራስ ምስል ታሪካዊ አመጣጥና የቅኝ አገዛዝ ጣጣ በመተንተን ለግጭቱ መንስኤ ለየት ያለ የስነ ልቦና ገጽታ ይሰጡታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትን ጨምሮ አንዳንድ የቀጣናው የፖለቲካ ተንታኞችም የችግሩ መንስኤ፣ የኤርትራ መንግሥት የተንኳሽነት ባህሪ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ለዚህም የመንን፣ ሱዳንን፣ ጅቡቲን በመጨረሻም ኢትዮጵያን የኤርትራ መንግሥት መተንኮሱ በማስረጃነት ያስደግፋሉ፡፡ ይህንን የፖለቲካ ተንታኞቹም፣ ከአዲስ አገር ምስረታ (Nation Building) ፀባይ ጋር ያያይዙታል፡፡ የችግሩ መነሻ ያም ሆነ ይህ፣ በ1990 ዓ.ም ኤርትራ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ጦርነት በማወጅ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ የሁለቱም አገራት ዜጎች ሞት ያስከተለ ሁኔታ ዕልባት ሳያገኝ እነሆ 10 ዓመታት ሞልቶታል፡፡ በጦርነቱ ወታደራዊ ድል የቀናት ኢትዮጵያ፣ በዲፕሎማሲያዊ መስክ ግን አልተሳካላትም፡፡ ኤርትራ በበኩሏ መጀመሪያ ለሰላማዊ ድርድር ያቅማማች ቢሆንም፣ ያልታሰበ ወታደራዊ ሽንፈት ከገጠማት በኋላ በአልጀርስ ተኩስ አቁም ስምምነት ለመፈረም ወደ ኋላ አላለችም፡፡ ስምምነቱ የኢትዮጵያን ወታደራዊ ድል ግምት ያላስገባና የአገሪቱን ጥቅም የማያስጠብቅ እንደነበረ በብዙዎች ይተቻል፡፡ የአልጀርሱ ስምምነት "ይግባኝ የሌለውና የመጨረሻ" እንዲሆን ስምምነት ላይ ይደረስ እንጂ፣ የድንበር ኮሚሽኑ የሰጠው ውሳኔ ግን "ዘላቂ ሃሳብ" የሚያመጣ አይደለም በሚል በኢትዮጵያ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ በመሆኑም ውሳኔው ተፈጻሚ ከመሆኑ በፊት ሁለቱም መንግሥታት ድርድር እንዲያደርጉ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተዘጋጀው "ባለአምስት ነጥብ የሰላም ሂደት" በኢትዮጵያ ፓርላማ ፀድቋል፡፡ ይህ የሰላም ሃሳብ መካለል ከመካሄዱ በፊት ድርድር እንዲደረግ በኢትዮጵያ መንግሥት የተላለፈውን ውሳኔ፣ የኤርትራ መንግሥት ቢያጣጥለውም፣ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ተቀባይነት በማግኘቱ የድንበር ውሳኔው ተፈፃሚ እንዳይሆን ኢትዮጵያን ረድተዋል፡፡ ውሳኔው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተፈጻሚ እንዲሆን የምትፈልገው ኤርትራ፣ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ለኢትዮጵያ የድርድር ሃሳብ ድጋፍ መስጠቱ አስቆጥቷታል፡፡ በመሆኑም በተለይ ከአሜሪካ ጋር የነበራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተቋረጠ ሲሆን፣ ከሌሎችም ጋር ግንኙነቷ ተበላሽቷል፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር የነበረው ጊዜያዊ የደህንነት ቀጣና ጥሳ በመግባት ከአንሚ መተባበር ካቆመች ከርማለች፡፡ ይህ በተመድ የፀጥታ ምክር ቤት የተረጋገጠ ቢሆንም፣ ምክር ቤቱ የቃላት ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ያለፈ እርምጃ አልወሰደም፡፡ እንዲሁም፣ የድንበር ኮሚሽኑ ለችግሩ ምንም ዕልባት ሳያስገኝለት፣ የድንበር ውሳኔውን በካርታ ላይ አስቀምጦ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የተበተነ ሲሆን፣ በአካባቢው የነበረው የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ኃይል በበኩሉ ከሶስት ወራት በፊት ቀጣናውን ጥሎ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ ውሳኔው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተፈጻሚ እንዲሆን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጥር ማሳመን ያቃታት ኤርትራ፣ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የተለያዩ ስትራቴጂዎች ስትጠቀም መቆየቷን የኢትዮጵያ መንግሥት ይገልፃል፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ትጥቅ ያነሱ እንደ ኦነግና ኦብነግን በጀሌነት በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ በርካታ የሽብር ተግባሮች ፈጽማለች በማለትም የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ኤርትራን ይወነጅላል፡፡ ከሶማሊያ ጋር የማትዋሰነው ኤርትራ፣ የኢትዮጵያ ኃይልን ለማዳከምና ፀጥታዋን ለመረበሽ ከእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትና አልሻባብ ከተባለው የሶማሊያ አማጺ ቡድን እጅና ጓንት ሆና እየሰራች እንደነበር በተመድ ተቆጣጣሪ ቡድን ተረጋግጧል፡፡ ይህ የኤርትራ እንቅስቃሴ በአንድ በኩል የድንበር ችግሩን ወደ ሶማሊያ በመውሰድ የእጅ አዙር (የውክልና) ጦርነት እያካሄደች እንደሆነ፣ በሌላ በኩል በቀጣናው የኢትዮጵያን ኃያልነት ለመቀልበስ ያለመ እንደሆነ የአካባቢው የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ አንዳንድ የግጭት ተመራማሪዎች እንደሚሉት፣ እንደውም የሶማሊያ ቀውስ መፍትሄ በኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ውዝግብ ላይ የተንጠለጠለ ሆኗል፡፡ የሶማሊያ ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ሰላም በሁለቱም አገራት ግንኙነት የሚወሰን ሆኗል፡፡ በቅርቡ በጅቡቲ ላይ ትንኮሳ ያካሄደችው ኤርትራ፣ አገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የኢኮኖሚ ግንኙነት (በተለይ የወደብ አጠቃቀም) ስላላስደሰታትና በሶማሊያ ሽግግር መንግሥትና በሶማሊያ አማፂዎች መካከል ድርድር እንዲካሄድ በማድረጓ መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም የሁለቱም አገራት ሰላም ሳይመለስ በቀጣናው መረጋጋት አይኖርም የሚል የአንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች አባባል እውነታነትን የሚያመላክት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኦስማን ሳሊህ በዚሁ የተመድ ጉባኤ ባቀረቡት ሪፖርት ኢትዮጵያና አሜሪካ በአካባቢው ላለው አለመረጋጋት ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ በዓለም ግጭቶችና ሰብዓዊ ቀውሶች እየተባባሱ መምጣታቸውን የተናገሩት አቶ ኦስማን፣ ለዚህ ሁሉ ቀውስ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመንስኤነት ወንጅለዋል፡፡ ይሄም ዓለም በአንድ ኃያል አገር በመመራቷ ምክንያት መሆኑንና፣ ተመድም በዚሁ ኃያል መንግሥት የሚሽከረከር ደካማ ድርጅት መሆኑንም ወቅሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ በቅርቡ ድርጅታቸው ኢህአዴግ ባካሄደው ሰባተኛ ጉባኤ ወቅት "የኤርትራ ጉዳይ እስከመቼ እንዲህ ሆኖ ይቀጥላል?" በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ "ከአንድ የመንደር ጎረምሳ ጋር አተካራ አንገባም" በማለት፣ "ነገር ግን የልማት እንቅስቃሴያችንን የሚያስተጓጉል አንዳችም እንቅስቃሴ ከተደረገ ለምንወስደው እርምጃ አንደራደርም" ማለታቸው ይታወሳል፡፡ የኤርትራው ፕሬዚዳንት በበኩላቸው ጦርነት እንደማይፈልጉ፣ ሆኖም በህግ የተሰጣቸውን መሬት ለማግኘት ማንኛውንም መንገድ እንደሚጠቀሙ በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተኩስ ድምጽ ባይሰማም የሁለቱም አገሮች ወታደራዊ ሃይሎች በተቀራረበ ሁኔታ እንደሚገኙና ተመድም ሁኔታው እንደሚያሳስበው ገልጿል፡፡ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ በበኩሉ "ጦርነት አይቀሬ ነው" የሚል መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ አሁን በአካባቢው ያለው "ሰላምም ጦርነትም አልባ" ሁኔታ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ላይ ከባድ ተጽዕኖ እያሳደረ ሲሆን፣ በአገራቱ መካከል ምንም ዓይነት የአቋም መቀራረብ አይታይም፡፡ ይህ "ቀዝቃዛው ጦርነት" መጨረሻው ምን ይሆን? |
|
| Last Updated ( Thursday, 09 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |