| ቃሊቲ ብረታ ብረት በ3ዐ ሚሊዮን... |
|
| Wednesday, 08 October 2008 | |
![]() አቶ ማቴዎስ አሰሌ - ከ 132 ሚሊዮን ብር በላይ ሽያጭ አከናወነ በዳዊት ታዬ ቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ እያደገ ከመጣው የኮንስትራክሽን ግንባታ ጋር በተያያዘ የሚያስፈልገውን የተለያዩ ብረታ ብረት ምርቶች ለማሳደግ በ30 ሚሊዮን ብር የማስፋፊያ ግንባታ ሊያካሂድ ነው፡፡ በ2000 በጀት ዓመት ከ132 ሚሊዮን ብር በላይ ሽያጭ ማከናወኑን አስታወቀ፡፡ የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቴዎስ አሰሌ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት በአገር ውስጥ ካለው የገበያ ፍላጐትን መሠረት በማድረግ ፋብሪካው ከሚያመርታቸው ምርቶች ውስጥ እንደ ቱቦና ኤጋ የቆርቆሮ ክዳን ያሉ ምርቶች መጠንን ለማሳደግ ማስፋፊያ ኘሮጀክት ለመገንባት አስፈላጊው ጥናት ተጠንቶ ለመንግሥት ቀርቧል፡፡ ከ3ዐ ሚሊዮን ብር በላይ ይፈጃል፤ ተብሎ የሚገመተውን የማስፋፊያ ኘሮጀክት በተያዘው የበጀት ዓመት ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው የማስፋፊያ ኘሮጀክቱ ጥናት የቀረበለትም አካል ግንባታውን ለመጀመር የሚያስችል አዎንታዊ መልስ የሰጠ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት የግንባታ ማረጋገጫውን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ፋብሪካው ባለፈው ቅዳሜ ባከበረው የደንበኞችና የሠራተኞች ቀን ክብረ በዓል ላይ እንደተገለፀውም በ2ዐዐዐ በጀት ዓመት ፋብሪካው ያካሄደው ሽያጭና ያገኘው ትርፍ በፋብሪካው ታሪክ ውስጥ እስካሁን ያልተመዘገበ ነው፤ ተብሏል፡፡ ፋብሪካው በበጀት ዓመቱ 8 ሺህ 102 ቶን ልዩ ልዩ ምርቶችን ለማምረት አቅዶ 8 ሺህ 905 ቶን በማምረት የእቅዱን 110 በመቶ ማሳካቱን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ በሽያጭ ረገድም 73.61 ሚሊዮን ብር የሚሆን ምርት ለመሸጥ ታቅዶ ሊሸጥ የቻለው 132.27 ሚሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል፡፡ ይህም የእቅዱን 180 በመቶ እንዲሆን ማድረጉንና በበጀት ዓመቱ የተከናወነው ሽያጭ ከፍተኛ በመሆኑም 18.85 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል፡፡ እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ በበጀት ዓመቱ ውስጥ ፋብሪካው ያተርፋል፤ ተብሎ በእቅድ ተይዞ የነበረው 13.5 ሚሊዮን ብር በመሆኑ የትርፍ እቅዱ 140 በመቶ እንዲሆን አድርጐታል፡፡ ፋብሪካው በበጀት ዓመቱ ካመረተው ምርት ውስጥ ከ5ዐ በመቶ በላይ የሚሆነውን ምርት የገዙት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የሚገኙት የቤቶች ኘሮጀክት ጽ/ቤቶች ናቸው፡፡ በዓሉ በተከበረበትም ወቅት ቀዳሚ ደንበኞች አድርጐ የሸለመው የአዲስ አበባና የክልል የቤቶች ኘሮጀክት ጽህፈት ቤቶችን ነው፡፡ ከቤቶች ኘሮጀክቶች ሌላ ከ35 የሚበልጡ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎችና ሌሎች መስሪያ ቤቶች ተሸልመዋል፡፡ የፋብሪካው ዋነኛ ተልእኮ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በጥራ" በተወዳዳሪ ዋጋ በሚፈለገው መጠንና ጊዜ ለደንበኞች በማቅረብ በዘርፉ መሪ ድርጅት ሆኖ መቀጠል መሆኑን ያመለከቱት ሥራ አስኪያጁ እቅዳቸውን ከግብ ለማድረስ እንደሚጥሩ ገልፀዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ፋብሪካው ከፍተኛ የተባለውን ውጤት ያስመዘገበ ቢሆንም ይህንን ለማግኘት ችግሮች አጋጥመው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ በተለይም የኤሌክትሪክ ኃይል በፈረቃ መቋረጡ ለቤቶች ልማት ኘሮጀክትና ለሌሎችም ደንበኞች ምርቶቹን በወቅቱ ለማቅረብ እንቅፋት ሆኖ ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ በዓለም የብረት ዋጋ መጨመር አስቀድመው የተገቡ ውለታዎች ላይ ኪሣራ እንዳያደርስ ጥንቃቄና የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ፋብሪካው በሚፈልጋቸው ጥሬ እቃዎች ላይ ከ40 እስከ 60 በመቶ የሚሆን ጭማሪ ታይቶ እንደነበር የገለፁት አቶ ማቲዎስ ይህም ሆኖ ምርት ሳይቋረጥ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጭማሪ ሳቢያ ሊፈጠር የሚችለውን ኪሣራ ለመቋቋም በአጭር ጊዜ ወጪ ቆጣቢ በሆነ የአመራረት ስልት ተጠቅመው ችግሩን ተቋቁመናል ብሏል፡፡ የብረት እጥረት ለኮንስትራክሽን እንቅስቃሴው ችግር እንዳይፈጠር የታሰበ ጉዳይ እንዳለ ጠይቀናቸው በሰጡት መልስም የብረት እጥረት ኮንስትራክሽኑ ላይ ችግር እንዳይፈጥር የብረታ ብረት ልማት ምርት ማእከል ባለቤትነት አንድ ጥናት አጥንቶ ለማፅደቅ ለመንግሥት ለማቅረብ የቀየሰው ስትራቴጂ መኖሩን ጠቁመው ይህ ስትራቴጂ ተግባራዊ እንዲሆን ከፍተኛ የሆነ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ ስትራቴጂው በአገር ውስጥ የብረትን ማእድን አጥንቶ ለማምረት የሚያስችለው አሠራር በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ተግባራዊ በማድረግ ከአገር ውስጥ የጥሬ እቃ ምርት ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚል እምነት አላቸው፡፡ እስከዚያው ግን ለብረታ ብረት ምርት የሚሆኑ ጥሬ እቃዎችን ከውጭ መግዛት ግድ ይሆናል፡፡ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶችን በተመለከተም አቶ ማቴዎስ እንደገለፁት "የኢትዮጵያ ጥራትና ደረጃዎች በዚህ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ገልፀናል፡፡ ከውጭ አገር የሚገቡ ምርቶች የጥራት ደረጃቸውን ያሟላሉ አያማሉላም የሚለውን ለመቆጣጠር የሚያስችል መመዘኛ አልወጣም፡፡" በብረታ ብረት ምርቶች ላይ የደረጃ መመዘኛ ካለመውጣቱ የተነሳ ቁጥጥር አይደረግበትም ያሉት አቶ ማቲዎስ ይህንን መመዘኛ ለማወጣት በብሔራዊ ደረጃ አንድ ኮሚቴ ተዋቅሮ በአሁኑ ጊዜ በመስራት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡ በጣም ዝቅተኛ የሆኑ ጥራትና ደረጃ ያላቸው ምርቶች ወደ አገር በመግባታቸውም ተጠቃሚዎች ብዙን ጊዜ በደንብ መለየት ስለማይችሉና ዋጋውን ብቻ በመመልከት ስለሚገዙ በኮንስትራክሽን ግንባታ ላይ ተፅእኖ እያሳረፉ መምጣታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ባሳለፍነው ቅዳሜ በተከበረው የደንበኞችና የሠራተኞች ቀን ላይ እያንዳንዱ የፋብሪካው ሠራተኛ የሜዳሊያ ሽልማት ተሰጥቷል፡፡ ይህንን በተመለከተ እንደገለፁትም የቤት እጥረትን ለማስወገድ መንግሥት እየወሰደ ካለው እርምጃ አኳያ በአዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች የቤቶች ኘሮጀክት ጽ/ቤቶች ለሚያካሂዱት ሥራ እቅዳቸውን ለማሳካት በርትቶ መስራት የነበረባቸው በመሆኑ መብራት በሚቋረጥበት ወቅት እቅዳችንን የሚያስተጓጉል ስለነበር ከሠራተኛው ጋር ተወያይተን ተከታታይ የእረፍት ቀናትን በነፃ እንሰራለን በማለታቸው ከእቅድ በላይ ሊመረት ችሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ለተገኘው ውጤት የእያንዳንዱ ሠራተኛ ተሳትፎ ስለነበረበት ሜዳሊያው እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ በዓሉ በተከበረበት ወቅት የመንግሥትና የልማት ድርጅቶችና የኘራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ በየነ ኃ/መስቀል የተገኙ ሲሆን በእለቱ ባደረጉት ንግግርም ፋብሪካው ያስመዘገበው ወጤት ለሌሎች አርአያ የሚሆን ተግባር እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ በ1960 ዓ.ም. በጣሊያናዊው ሲኞር ሪሶ ስኘራንዶ እና በሌሎች የአገር ውስጥ ባለድርሻዎች በ5ዐዐ ሺህ ብር መነሻ ካፒታል የተመሠረተ ሲሆን በ1968 ዓ.ም. በደርግ ተወርሶ ቆይቷል፡፡ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ማቋቋሚያ በአዲስ መልክ በ9.67 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንዲቋቋም የተደረገ ሲሆን በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ካፒታሉ 148.5 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ |
|
| Last Updated ( Thursday, 09 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |