Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow የዓለም የፋይናንስ ቀውስ
የዓለም የፋይናንስ ቀውስ E-mail
Wednesday, 08 October 2008
ImageImageImage- "የወለድ ገቢያችን ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል"
አቶ ብርሃኑ ጌታነህ
- "ከአበባ ንግድ የምናገኘውን ገቢ ቀንሶታል"
አቶ ፀጋዬ አበበ
- "በጥሩ ጊዜ አልጠቀመንም በመጥፎው ጊዜም አይጐዳንም"
አቶ ኤርሚያስ አመልጋ

በብርሃኑ ፍቃደ

በአሜሪካ የተከሰተው የገንዘብ ቀውስ ለአውሮፓውያንም እየተረፈ ይገኛል፡፡ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገሮች ማዕከላዊውን የአውሮፓ ባንክ በገንዘብ ለመደጐም መዘጋጀታቸውን የሚገልፁ መረጃዎች እየተደመጡ ነው፡፡

የገንዘብ ቀውሱ በፋይናንስ ሴክተሩ ሳይገደብ ወደ ኢኮኖሚውም እየተሻገረ መሆኑን በአሜሪካ የሚታዩ ኩነቶች ይጠቁማሉ፡፡ ብዙዎች ከሥራ ገበታቸው እየተፈናቀሉ የሚያገኙትም ገቢ እየተቋረጠ ይገኛል፡፡

የቀውሱ ጉዳይ በኢትዮጵያ ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖና ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት አስመልክቶ የህብረት ባንክ ፕሬዚዳንት፣ የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንትንና የኢትዮጵያ አበባ አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ሊቀመንበርን በተናጠል አነጋግረናቸዋል፡፡

የሕብረት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ጌታነህ እንደገለፁት በዓለም በተለይም በአሜሪካ፣ በእስያና አውሮፓ የደረሰው የገንዘብ ቀውስ ኢትዮጵያን ከሚመለከትባቸው ነጥቦች አንዱ የምንዛሪ መዋዠቅ እንዲከሰት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩ ነው፡፡ እርግጥ የምንዛሪ መዋዠቅ የገንዘብ ቀውሱ ባልተከሰተበት ጊዜም የሚያጋጥም ችግር ሲሆን ቀውሱ በዋና ምክንያትነት ሊጠቀስ የሚችልበት አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡

የምንዛሪው መዋዠቅ ወደ ውጭ በሚላኩና ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ዕቃዎች ዋጋ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ለአብነት አንድ የአሜሪካን ዶላር በቀውሱ ሳቢያ የነበረው የመግዛት አቅም የሚቀንስ ከሆነ ወደ ብር በሚቀየርበት ወቅት አነስተኛ መጠን ስለሚኖረው ተፅዕኖ ይፈጥራል፤ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢም ይቀንሳል፡፡ በዓለም የታወቁ ባንኮች ላይ የገንዘብ ቀውስ ተከሰተ ከተባለና ኢትዮጵያም የውጭ ምንዛሪ ልውውጡን በታዋቂዎቹ ባንኮች ሳቢያ የምታካሂድ ከሆነ ችግር መፈጠሩ አይቀርም ይላሉ አቶ ብርሃኑ፡፡

በሌላ በኩል ምንም እንኳ አሜሪካ አሁን የምትገኘው በገንዘብ ቀውስ ውስጥ ቢሆንም በተቃራኒው የዶላር የመግዛት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሆኑና "ኢትዮጵያ በዶላር የገንዘብ ልውውጥ ስርዓቱን ብታካሂድ በቀጥታ አትጐዳም" የሚሉት ደግሞ የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንትና የአክሰስ ካፒታል ዳይሬክተር ናቸው፤ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፡፡

የዓለም ኢኮኖሚ በሁለት ዋና ዋና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ይገለፃል፡፡ በፋይናንስ ኢኮኖሚና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ተግባሮች፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በኢኮኖሚ ረገድ ያላት ትስስር ደካማ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከሚፈጥሩ ምክንያቶች አንዱ በአገሮች መካከል የሚደረግ የንግድ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ምርቶችና አገልግሎቶች ወደ ውጭ ይላካሉ ወደ አገር ውስጥም ይገባሉ፡፡ የዓለም ኢኮኖሚ ሲያድግ የምንልካቸው ምርቶችና አገልግሎቶች ከፍተኛ ገቢ ሊያስገኙልን ካልቻሉና የኢኮኖሚ ትስስራችን ጥብቅ ካልሆነ ተጠቃሚ የመሆን እድላችን በጣም ጠባብ ነው፡፡ በሌላ በኩል ጥብቅ የኢኮኖሚ ትስስርና ተጠቃሚነት ያላቸው አገሮች የዓለም ኢኮኖሚ በማደጉ ሳቢያ ይጠቀማሉ፡፡ ቀውስ ውስጥ በሚገባበትም ወቅት የዚያኑ ያህል ተጐጂዎች ይሆናሉ፡፡ እስከ አሁን የተመዘገበው የወጪ ንግድ እንደሚያሳየው አገሪቱ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ገቢዋ ረገድ የምታገኘው ገቢ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህም ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ያለን ትስስር ደካማ መሆኑን ያሳያል፡፡ ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ማግኘቷ ይታወቃል፡፡ ይህ አሃዝ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አይን ሲታይ ከቁጥር አይገባም፤ ቢሆንም በየጊዜው እየጨመረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡  

በፋይናንሱ ዘርፍም ቢሆን የዓለም የፋይናንስ ገበያ ሲጐለብትና ሲያድግ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ አልነበረችም፡፡ በቅርቡ የተከሰተው ፋይናንስ ቀውስም ቢሆን ኢትዮጵያን ምንም ያህል እንደማይጐዳ አቶ ኤርሚያስ እምነት አላቸው፡፡ "አመዛዝነን ካየነው ከጉዳቱ ይልቅ የገንዘብ ቀውሱ የሚሰጠው የራሱ ጠቀሜታ ይኖረዋል" የሚሉት ኃላፊው የፋይናንስ ትስስር ውስጥ የእኛ ድርሻ የተገደበ ነው፡፡ የለንበትም፡፡ የኢትዮጵያ ፋይናንስ ሴክተር ለዓለም አቀፉ ፋይናንስ ዝግ ነው፡፡ የአገሪቱ ሕግ አንድ የውጭ አገር ዜጋ ኢንቨስተር በባንክና ኢንሹራንስ ዘርፍ እንዲሰማራ አይፈቅድም፡፡ ብድርም ይከለክላል፡፡ አሁን ባለው አሠራር ከባንክና ኢንሹራንስ አገልግሎት በስተቀር በአገሪቱ የአክሲዮን፣ የገንዘብ፣ የቦንድና የሌሎችም ዓይነት የካፒታል ገበያዎች የሉም፡፡ ስለዚህ በፋይናንስ ረገድ ከውጭው ዓለም ጋር ትስስር ባለመኖሩ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ወለድ መጠን መጨመርም ሆነ መቀነስ በቀጥታ የሚያሳድረው ተፅዕኖ አይኖርም፡፡ ከዚህ አንፃር በጥሩው ጊዜ አልተጠቀምንም፣ በመጥፎው ጊዜም የሚጐዳን አይሆንም፡፡ በውጭ አገሮች የተፈጠረው ቀውስ ዋነኛ ምክንያቱ የብድር መጥፋት ነው፡፡ የአሜሪካም ሆነ የአውሮፓ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀሰው በብድር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከውጭ ኢኮኖሚ በተለይ  ከንግድ ባንኮች ብድር አታገኝም፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ብድርም ሆነ ሌላ አገልግሎት የሚያገኙት ከመንግሥት ነው፡፡ ይህ በመሆኑ አሁንም ቀጥተኛ የቀውሱ በትር አይመለከተንም ባይ ናቸው፡፡

ዋናው ወይም መደበኛውን ኢኮኖሚ በሚመለከት ወደ ውጭ የምንላካቸው ምርቶች በበዙ ቁጥር እንጠቀማለን፡፡ ይህ ካልሆነና የምርት መጠናችን ከቀነሰ ደግሞ እንጐዳለን፡፡ የአሁኑ ቀውስ ከወጪ ንግድ የምናገኘውን ገቢ ሊቀንሰው ወይም እንዲጨምር ምክንያት የሚሆንበት አጋጣሚ የለም፡፡ ከኢትዮጵያ የሚላኩ ምርቶች አመዛኙን ለፍጆታ የሚውሉ ናቸው፡፡ በመጠንም ቢሆን በአነስተኛ ደረጃ ለውጭ ገበያ ስለሚቀርቡ እስካሁን ምንም የታየ ጉዳትና ከዋጋ አንፃርም የመቀነስ ሁኔታ የለም፡፡ በተለየ ሁኔታ ቀውሱ የአበባ ምርት ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተፅዕኖ ሊኖር ይችላል፡፡ በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ የመግዛት አቅም መዳከም ሲከሰት እንደ ቀድሞው ለአበባ የሚኖረው ፍላጐት ላይኖር ይችላል፡፡ የሚል ግምታቸውን አቶ ኤርሚያስ አስቀምጠዋል፡፡

የአበባን ዘርፍ በሚመለከት ያነጋገርናቸው አቶ ፀጋዬ አበበ የኢትዮጵያ አበባ አምራቾች ማህበር ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ከፍላጐት አንፃር እስካሁን የታየ ችግር ባይኖርም በቀውሱ ሳቢያ የተከሰተው የምንዛሪ መዋዠቅ ከአበባ ምርት የሚገኘው ገቢ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡ በዋናነት ለአውሮፓ ገበያዎች ከሚላከው የአበባ ምርት ከሳምንታት በፊት ይገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ቅናሽ አሳይቷል፤ ይህ የሆነው ደግሞ የዩሮ ምንዛሪ መጠን በማሽቆልቆሉ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በ15.40 ብር ይመነዘር የነበረው አንድ ዩሮ በአሁኑ ወቅት ወደ 13.22 ብር ዝቅ ብሏል፡፡ በሌላ በኩል የዶላር የመግዛት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ በዶላር የሚገዙ ዕቃዎች ላይ የሚወጣው ወጪ ከፍ እንዲል አስገድዷል፡፡ ለአብነት "በዩሮ ከተገኘው ገቢ ላይ ለአውሮፕላን ማጓጓዣ የሚከፈለው በዶላር በመሆኑ ከበፊቱ የበለጠ ወጪ በማስወጣት ገቢያችን ላይ ችግር አስከትሏል" ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል እስከ አሁን የምርት ወቅት ላይ የነበሩ በመሆኑ የፍላጐት መቀነስ ስለመከሰቱ መናገር እንደማይቻል አመልክተው ግዥ ይቀንሳል ወይም ይቆማል የሚል ስጋት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ቢሆንም ቀውሱ በገቢ ላይ ያስከተለው ተፅዕኖ ጠቋሚ መልዕክት እንዳስተላለፈ ገልፀዋል፡፡

በጥቅሉ በዋጋና አቅርቦት ላይ መጠነኛ ተፅዕኖ ቢኖረውም ዋናው የኢኮኖሚ አውታር ባለመሆኑ ቀውስ ውስጥ ይከተናል አሊያም ገበያ ያሳጣናል የሚል ስጋት እንደሌላቸው አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ይገልፃሉ፡፡ የቆዳ ምርትና ውጤቶችንም ሊነካካ የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር ቢችልም የወጪ ንግዱን ስጋት ላይ የሚጥል አይሆንም፡፡

ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችና አገልግሎቶችን በተመለከተ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ መሆንዋን የሚናገሩት አቶ ኤርሚያስ ከገቢ ንግዱ ዘርፍ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ነዳጅ ነው፡፡ በዓለም ላይ ያለው የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው እየቀነሰ መጥቶ አሁን ከ90 ዶላር በታች (900 ብር ገደማ) በበርሜል እየተሸጠ ነው፡፡ የነዳጁ ዋጋ ሲንር የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ሲያሽቆለቁል ለግዥ የሚወጣው የምንዛሪ መጠን ይቀንሳል፡፡ በሌላ በኩል ለፋብሪካ ግብዓትነት የሚውሉ ከውጭ የሚገቡ እቃዎችም ቢሆኑ በተለይ ኢትዮጵያ ገቢ የምታደርጋቸው ለመሠረተ ልማትና ለምርት የሚውሉ እቃዎች በመሆናቸው የእነዚህ እቃዎች ፍላጐትና ዋጋ በዓለም ገበያ ሲቀንስ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ያደርጋታል፡፡

ከወጪ ንግዱ ባልተናነሰ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ የምታገኝበትና ለኢኮኖሚው ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ የሚገኘው በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት የሚልኩት ገንዘብ (ሬሚታንስ ፔይመንት) ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለቱም ባለሙያዎችና ኃላፊዎች (አቶ ብርሃኑ እና አቶ ኤርሚያስ) ተመሳሳይ አቋምና አመለካከት አላቸው፡፡

አቶ ብርሃኑ የአሜሪካው የገንዘብ ቀውስ ብዙዎችን ከሥራ እያፈናቀለ እንደሚገኝ ገልፀው ከሚፈናቀሉት ሠራተኞች ውስጥ ኢትዮጵያውያንም ይገኙበታል፡፡ በመሆኑም ወደ አገራቸው የሚልኩት የውጭ ገንዘብ ይቀንሳል፡፡ አገሪቱም ታገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሪ አብሮ ይቀንሳል ብለዋል፡፡

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በበኩላቸው ጉዳቱ በአገርም በግለሰቦችም ላይ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡  

ኢትዮጵያ ይፋ በሆነ መልኩ ከ10 እስከ 10.2 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ ገቢ ውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ታገኛለች፡፡ ከወጪ ንግድ ያልተናነሰ ገቢ የሚያስገባው ይህ እንቅስቃሴ የሚመነጨው በአብዛኛው በተለያዩ የውጭ አገሮች የአገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው በሚሠሩ ዜጐች ነው፡፡ በዋናነት የዚህ ዓይነቱ ገቢ የሚመነጨው አሜሪካን አገር ኗሪ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን ነው፡፡ በአውሮፓና እስያ ከሚኖሩ ዜጐች ጋር ሲነፃፀር አሜሪካ የሚገኙት በገቢም በብዛትም የተሻሉ ናቸው፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ገቢ አግኝተው የሚኖሩት እዚያ ነው፡፡

የአሜሪካ ኢኮኖሚ ተዳከመ ማለት ደግሞ በተለይ በሆቴልና በሪል ስቴት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የጐላ ይሆናል፡፡ እነዚህ ሴክተሮች በቀውሱ ተመትተዋል፡፡ በኢንቨስትመንት በኩልም ማንኛውም ሥራ ያለው ሰው በብድር ቤት መግዛትና መሥራት የሚችልበት እድል ተፈጥሮለት ነበር፡፡ ይህ በመሆኑም ብዙ ኢትዮጵያውያን ቤት በዱቤ ገዝተው መኖር እንደጀመሩም ከአሜሪካ የሚገኙ መረጃዎችን ጠቅሰው አቶ ኤርሚያስ ያስረዳሉ፡፡

አክሰስ ካፒታል በተሰኘው ኩባንያቸው በኩል የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ 50 በመቶ ገደማ የሚሆነው የአዲስ አበባ የቤት ሽያጭ በዲያስፖራው የሚደረግ ነው፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ ነዋሪነታቸው በአሜሪካ ነው፡፡

ከዚህ በመነሳት ጥናት ቢደረግ በአዲስ አበባ የሚካሄደው የሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ሊነካካ የሚችልበት አጋጣሚ ስለመኖሩ ምንም ጥርጣሬ እንደሌላቸው ይገልፃሉ፡፡

በተለይ በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጐች አገር ቤት የሚኖሩ ቤተሰቦቻቸውን የሚደጉሙ ናቸው፡፡ በከተማው የሚታዩት ትንንሽ ኢንዱስትሪዎች በብዛት በባንክ ብድር ሳይሆን ከውጭ በሚመጣ ገንዘብ የሚከፈቱ፣ የሚቋቋሙ ናቸው፡፡

የአገራችንን ኑሮ ከሚደጉሙ ዋነኛ ምንጮች አንዱ የሆነው ይህ ገቢ ከአገሪቱ ባሻገር የግለሰቦችንም ኑሮ በዚህ መልኩ ችግር ውስጥ ይከታል፡፡ ገንዘቡን የሚልኩት ዜጐች ከሥራ ከተፈናቀሉ፣ በሚኖሩበት አገር ለሠሩት ቤትና ላፈሩት ንብረት ያለባቸውን ዕዳ እንዲከፍሉ ጫና ከመጣባቸው፣ ወደ አገር ቤት የሚላከው ገንዘብ ይቀንሳል፣ ይቋረጣል፡፡ ከውጭ በሚመጣ ገንዘብ እየተደጐመ የሚኖረው ቤተሰብ ችግር ውስጥ ይገባል ከተባለ ደግሞ ምክንያቱ በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ የተከሰተው የፋይናንስ ቀውስ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

በአሜሪካ የሚኖሩ የሜክሲኮ ዜጐች ሁኔታም ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ የገለፁት አቶ ኤርሚያስ፣ በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ከውጭ አገር ኗሪዎች ወደ ሜክሲኮ የሚላከው ገቢ 10 በመቶ ቀንሷል፡፡ ይህ ከስድስት ወር በፊት የነበረ መረጃን ዋቢ ያደረገ ነው፡፡ ይህ ገና በጅምሩ የሚታይ ሲሆን በሚቀጥሉት ጊዜያት የት ሊደርስ እንደሚችል መገመት ይቻላል፣

በኢትዮጵያም መረጃ አልተገኘም እንጂ ጥናት ቢደረግ ከተጠቀሰው ያላነሰ ማሽቆልቆል ሊከሰት እንደሚችል ያላቸውን ሥጋት አስቀምጠዋል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ አገራችን ላይ ሊከሰት የሚችለው ሌላው ተፅዕኖ የውጭ ምንዛሪን በውጭ አገር በሚያስቀምጡ ባንኮች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ነው፡፡ የውጭ ባንኮች የፋይናንሰ ቀውስ ውስጥ ሲገቡ ከተቀማጭ የሚገኘው ገቢ ይቀንሳል፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች ጥቅም በዚህ መልኩ ይነካል ያሉት አቶ ብርሃኑ የወለድ ገቢ በመቀነሱ ሳቢያ የባንኮች እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

የዓለም የፋይናንስ ቀውስ የታችኛውን ሕብረተሰብ ክፍል የኑሮ ሁኔታ ያሰጋ እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ኤርሚያስ ከውጭ ወደ አገር ከሚገባው ገንዘብ (ሬሚታንስ ፔይመንት) በቀር ድሃው ሕብረተሰብ ተጠቃሚ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ ለአብነት የነዳጅ ዋጋ ቀንሶ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማዳን ቢቻል የትራንስፖርት ሴክተሩ ሁሉንም ስለሚነካካ መጠነኛ እፎይታ በመፍጥር የኑሮ ውድነቱን ሊቀንስለት ይችላል ይላሉ፡፡

"በኢትዮጵያ የተፈጠረው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት በታችኛው የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ሕብረተሰብ ሕይወት አናግቷል፡፡ የአሁኑ ቀውስ ደግሞ ለእኛ ጥቅም የሚሰጥ ከሆነ የዋጋ ንረቱን በመቀነስ ሊረዳን ይችላል፡፡" ስለዚህ የኑሮ ጫና አይፈጠርበትም እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፡፡

የፋይናንስ ቀውሱ የእርዳታ መጠንን በመቀነስ ይጐዳናል የሚል እምነት እንደሌላቸው በመግለፅ ለጋሽ የሚባሉ አገሮችም የሚሰጡት እርዳታ ይቋረጣል ወይም ይቀንሳል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

በአጠቃላይ ከዓለም ኢኮኖሚ አንፃር ያለን ትስስር የተገደበ በመሆኑ ቀውሱ ያን ያህል ሥጋት ላይ የሚጥል አይደለም፡፡ ነገር ግን በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ የተከሰተው የገንዘብ ቀውስ ተገቢ የሆነ የባንክ አሠራር     (ፕሩዳንት ባንኪንግ) በመላላቱ የተነሳ በመሆኑ የቀውሱ መዘዝ ስጋት ላይ እንዳይጥለን ካስፈለገ ዋናው ተቆጣጣሪ ባንክ (ብሔራዊ ባንክ) በተገቢው መንገድ ባንኮችን የመቆጣጠር ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል የሚል አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ብርሃኑ ጌታነህ ናቸው፡፡

የፋይናንስ ቀውሱ በአሜሪካ ከ10 ትሪሊዮን ብር በላይ ድጐማ ቢደረግበትም አሁንም ስጋት ላይ መሆናቸውን ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ በቅርቡ አስታውቀዋል፡፡ መቼ እንደሚያበቃ በእርግጠኝነት መናገር እንደማይቻልም እየተነገረ ሲሆን የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ከፍተኛ ድጐማ ከሚደረግላቸው ተቋሞች አንዱ ነው፡፡ በሌላ በኩል እንደ ዋል ስትሪት ያሉ የአክሲዮን ገበያ ማዕከሎች ከጨዋታ ውጭ በመሆን የፈረሱበት ክስተት መፈጠሩን የዓለም መገናኛ ብዙሃን ከትናንት በስቲያ ዘግበዋል፡፡   
Last Updated ( Thursday, 09 October 2008 )
 
< Prev   Next >