| የተገፋ ባለ ታክሲ |
|
| Wednesday, 08 October 2008 | |
|
ታክሲ ከለላ የለውም፡፡ ብዙው ግን ባለ ከለላ ነው፡፡ መጠጊያ አለው፤ ምሽግ ይዟል፡፡ የመከላከያ ወረዳውን ያጠናክራል፡፡ ባለሥልጣኑ፣ በከለላ ይኖራል፤ ነጋዴው የባለሥልጣን ግንብ ገንብቷል፡፡ ምሽጉን ያደላደለ ከመከላከል ወደማጥቃት ይሸጋገራል፡፡
ያለ ባለሥልጣን ከለላ የሚኖር ደሃና ባለ ታክሲ ብቻ ነው፡፡ ለታክሲ ከለላ መሆን የሚፈልግ የለም፡፡ እንደተንጦለጦለ፣ ማንም ደረቱን የነፋ ሁሉ እንደገላምጠው፣ የተንቀዥቃዥች ሁሉ እንደተውረገረገችበት እንዲኖር የተፈረደበት ይመስላል፡፡ ከለላ ማለት፣ የባለሥልጣን ከለላ ነው፡፡ ደረጃው ምንም ይሁን ምን፣ ዘመነኛን፣ ጊዜው የሳቀለት ሹምን፣ ያልተደገፈ "ወግድ" እንደተባለ ነው፤ በካልቾ እንደተጠለዘ ነው፡፡ ቢናገር የማይደመጥ፣ ሲያፈጥ ሲውል ለአይን የማይሞላ፣ መብቱን ለማስከበር ለምን ሲል "ምን አባትህ ልትሆን" የሚባል ነው፡፡ የታክሲ ሾፌር ቁጥር ከነዚህ ውስጥ ነው፡፡ አገልግሎታችን የሚፈልጉ፣ ሥራችንን የሚወዱ፣ ግን ከለላ ሊሆኑን አይፈልጉም በምሽት የሚወዱን ባለመኪናዎች በብርሃን ይሸሹናል፡፡ ተሩዋሩጠው የሚፈልጉን የቀን ደንበኞቻችን፣ ደመወዛቸውንና ሥልጣናቸውን ይነግሩናል እንጂ ምሽግን እንዲሆኑን በዘዴ ብንለምናቸውም አያዳምጡንም፡፡ ሽጉጣቸውን ያሳዩናል እንጂ መጠጊያ እንዲሆኑን አይፈቅዱም፡፡ ሥራችንን እንደጨው ተፈልጎ፣ እኛ ግን ተገፍተን ስንዋትት አናሳዝንም? ለነገሩ የሚያዝን ልብ ያለው ስንት ሰው ነው? አንዳንድ ጊዜ ሳስበው የዱሮ አዝማሪና የአሁን ባለታክሲ ይመሳሰሉብኛል፡፡ ሌላው ሲፈልጋቸው የሚንገበገብላቸው፣ እነሱ ሲፈልጉ ግን የሚገፉ፡፡ አንድ ቀን የባለ ታክሲም ቀን ይመጣ ይሆን? መጠጊያ በማጣታችን፣ ምሽግ ሊሆነን የሚፈልግ ስለሌለም መንገላታት ደርሶብናል፡፡ "ብታምኑም ባታምኑም በቁም ሞተናል" ባልልም ተደፍረናል፤ ተንቀናል፡፡ የስንቱን ባለሥልጣን ምስጢር እና ጉድ ደብቀን እንዳልያዝን ለጥቅም ሲሆን እንገፋለን፡፡ ባለታክሲ ይጋፋል፡፡ ፍቅሩ ቀርቶ ፀቡ ከመጣ፣ ብዙ ጉድ እንደምናወጣ መርሳት ሞኝነት ነው፡፡ ሥራ ስናቆም አገሪቱ ከዳር እስከ ዳር እንደምትናወፀው ምስጢር እናወጣለን ያልን ለትም መንግሥት እንደሚንቀጠቀጥ ለምን ይረሳዋል፡፡ አንድ ቀን ከሳሪስ ወደ ስታዲየም ላዳዬን በዝግታ እነዳለሁ፡፡ በደህናው ቀን የወጣልን ስም አልለቀቅ ብሎን እንጂ ባለታክሲ ይንቀዠቀዣል፤ የሚባለውን ርሱት፡፡ ስም አንድዬ ከወጣ የማይነሳ ሆኖ ነው እንጂ የትኛው መንገድ ነው እንዲህ የሚያስሮጠው እና ቀስ ብዬ እየነዳሁ ጎተራ ጋር ስደርስ የቀበጠ ባለሥልጣን ገጨኝ፡፡ አለቅድሚያው ተክለፍልፎ ከሐዲዱ ላይ ገጨኝ፡፡ ደግሞ ቁጣው በሱ ብሶ ያለጠለጠ ፊቱን በቀሰም እንደተነፋች ዶሮ እያሳበጠ አፈጠጠብኝ፡፡ ሜክአፕ እንደተቀባች ሴት ወይዘሮ ፊቱን አቅልቶ የሞጨሞጨ ዓይኑን ሰካብኝ፡፡ የምታብረቀርቅ መኪናው በመነካቷ ተናደደ፤ ሁኔታው ለምን እኔ እዚህ ስደርስ ቆመህ እጅ አትነሳም የሚል መሰለኝ፡፡ በሸቅሁ፡፡ ባለሥልጣን መሆኑን እርግጠኛ ባልሆንም ግን በልምድ እንደማውቀው ባለሥልጣን ወይም ከለላ ያለው ነጋዴ መሆኑ ገብቶኛል፡፡ ቢገባኝም ተናደድሁ፡፡ ምንም ድሃ ብሆን ወኔዬ እንዲከዳኝ አልፈቅድም፡፡ የድሃ ዋና ገንዘቡ ወኔው ነው፡፡ "ወግድ" ማለት አለበት፡፡ ለማ ብሎ ተዋርዶ ይኖራል? ሥልጣን የለው፤ ገንዘብ የለው፤ ስለዚህ ወግድ ማለት አለበት፡፡ መኪናዬን አቁሜ ተስፈንጥሬ ወጣሁ፡፡ ወፍራሙ ሰውዬ ሰውነቱን ከላይ እስከታች ያሰረውን ሞራውን እየጎተተ መጣ፡፡ የስድብ መዓት አወረደብኝ፡፡ ያን የመሰለ የስድብ ቃል ለመማር ባለሥልጣን መሆን የሚጠይቅ እስኪመስለው ድረስ ተንጣጣብኝ፡፡ ሽጉጥ ለማውጣት እንደሚፈልግ ሁሉ ወገቡን ይዳብሳል፡፡ አልደነገጥሁም ለ"ክብሩ" የተገባ ዘለፋ ወረወርሁ፡፡ አልፈራሁትም፡፡ ለምን እፈረዋለሁ? አያቴ "በሬሳዬ እነቅለዋለሁ" የሚሉት ትዝ አለኝ፡፡ ቢገድለኝ ቢያንስ አንድ ሰሞን ይጨነቃል፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች ደግሞ መጨነቅ እንደሚገድላቸው አውቃለሁ፡፡ እንደነዚህ አይነት ሰዎች ፍርሃታቸው አያድርስ ነው፡፡ ለእንደኔ አይነቱ ድሃ፣ ለብቻቸው ይፎክሩ እንጂ አለቆቻቸውን፣ ከለላዎቻቸውን፣ ሲናገሩዋቸው ቀርቶ ሲያይዋቸው እንኳ በቁማቸው ብርክ እንደሚይዛቸው አውቃለሁ፡፡ አንድ ጋዜጣ ከፃፈበትማ አበቃለት "ነፍስ ገዳዩ እገሌ" የሚል ርዕስ ለጋዜጣ ወሬ ይመቻል፡፡ የዛሬ ጋዜጠኞች፣ ደግሞ አንድዬ ፅፈው አይበቃቸውም፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ የሚመራው ድርጅት አቶ እገሌ በቦርድ ሊቀመንበርነት ይመሩታል፤ ብለው ያክሉበታል፡፡ ወይም ነፍሴ ገዳዩ የእገሌ ወዳጅ ነበር፤ ብለው ያወጣሉ፡፡ ያን ጊዜ ምሽጉም ይሰበራል፤ መከላከያ ወረዳው መፍረስ ይጀምራል፡፡ ስህተቱ የሱ እንደሆነ ነገርኩት፡፡ ትራፊክ ፖሊስ ካልመጣ መኪናዬን እንደማላንቀሳቅስ ዛትኩ፡፡ ከንፈሩን ወደጎን ሸርምሞ የሽሙጥ ሳቀብኝ፡፡ ስልኩን አወጣ ደወለ፡፡ አነጋገሩ ትዕዛዝ ይመስላል፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ በአይናቸው ብቻ አፈር የሚያስግጡ በመኪና ከተፍ አሉ፡፡ ሊመቱኝ ከጀሉ፡፡ አዝኜ ዝም አልኩ፡፡ ትራፊክ ፖሊስ መጣ፡፡ የኔ መንጃ ፈቃድ ተወሰደ፡፡ ሰውዬው ከአክብሮት ጋር እንዲሄድ ተደረገ፡፡ እኔ ግን ወደ ትራፊክ ጽ/ቤት፡፡ አዲዮስ ባለታክሲ፡፡ እስከዛሬ ድረስ ያ የትራፊክ ፖሊስ የመከረኝ ከልቤ ውስጥ ቀርቷል፡፡ ስለሕጋዊነት፣ ስለበደል በንዴት እየጦፍኩ ስጮህ እጅግ በረጋ አንደበት "መኖር ይሻልሃል፡፡ ከኖርህ ሁሉንም ታያለህ" አለኝ፡፡ መኖር? መኖር? ልጅና ቤተሰብ የሌላቸው እንዴት ታደሉ፡፡ ለማጣራት ጊዜ አልፈጀብኝም፡፡ ዱካው የጠፋ ወንጀለኛ በባለታክሲ ጥቆማ እንደሚያዝ ፖሊስ ጠይቁ፡፡ ስለዚህ ሰውዬው ማን እንደሆነ ደረስኩበት፡፡ ሥራ አስኪያጅ ነው፡፡ ከለላዎቹን እነማ እንደሆኑ ሳውቅ ግን ራሴን በሁለት እጆቼ ይዤ ቀረሁ፡፡ ባለታክሲን የሚንቀው ባለሥልጣንና ቱጃር ብቻ አይምሰላችሁ፡፡ ራሱ ባለታክሲውም ፌንታ ይሰራበታል፡፡ ሌባን ሌባ እንደሚሰርቀው፣ ባለታክሲውንም ባለታክሲው ይገፋዋል፡፡ ባለሥልጣን ላይ በባለስልጣን እንደሚያሴረው፣ ባለታክሲም ለባለታክሲ ክፉ ይሆናል፡፡ ድሃ በድሃ ላይ እጁን እንደሚያነሳ ሁሉ ባለታክሲም በባለታክሲ ላይ ይጨክናል፡፡ ይኸን ማረጋገጥ ከፈለጋችሁ ወደ ቦሌ አየር ማረፊያ ኑና እዩ፡፡ እዚያ ማቆሚያ ለማግኘት "ከለላ" ያስፈልጋል፡፡ ባለብጫዎቹ ቦታ ተመድቦላቸዋል፡፡ በእነሱ ቦታ እኛ ባለ ላዳዎቹ ድርሽ አንልም፡፡ ሃላፊዎቹም እንዳንደርስባቸው አዘዋል፡፡ እኛ ግን ከፍለን ለምንቆምበት ቦታ ሌሎቹ እንዳይመጡብን የሚከላከልልን የለም፡፡ በኛ ላይ የሚሰራ ደንብ ለኛ አይሰራም፡፡ ለኃላፊዎቹ አመለከትን፡፡ ዘወር በሉ አሉን፡፡ ከለላ አላበጀንም፡፡ ይበለን፡፡ ምሽግ ለመስራት ለምን አንሞክርም? ሁሉም ቢሆን "ጠላት ለማጥቃት" ዘዴ አድርጎ የሚጠቀምበት ምሽግ ማፍረስ ሳይሆን ምሽግ መገንባት" ነው፡፡ ግን የምሽግ ብዛት ውጤት የለውም፡፡ ባለታክሲዎች የምንኖረው እንዲህ እየሆን ነው፡፡ የነዚህን መሰል 1000 ምሳሌዎች ልነግራችሁ እችላለሁ፡፡ ትርፉ ግን ንዴት ነው፡፡ ለባለታክሲ በንዴት ለይ ንዴት የሚጨምር እንጂ ብስጭትን የሚያቃልልለት አይመጣለትም፡፡ ለመብት ስንከራከር የቤንዚን ዋጋ ይጨመርብናል፡፡ ምን ልንሆን እንችላለን? በክፍያው ስንነጫነጭ የጤፍና የስንዴ ዋጋ ጣራ ይነካብናል፡፡ ለነገሩ የግል ታክሲ ጨጓራ ድርብ ድርብ በመሆኑ ቶሎ አይታመምም፡፡ ውስጠኛው ጨ"ራችን እስኪበሳ ባለታክሲዎች እንታገላለን፡፡ ግን ማሸነፋችንን አላውቅም፡፡ ምነው ፖለቲካ ባታናግሩኝ፡፡ ወደ ሰንጋ ተራዬ" |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |