| መደበቅ |
|
| Wednesday, 08 October 2008 | |
|
ፍቅራችሁን ደብቁ፤ ህመማችሁ መድኃኒታችሁም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም ፍቅር ለነፍስ ብርጭቆ ውስጥ እንዳለ ወይን ጠጅ ነው፡፡ የምታዩት ፈሳሽ ቢሆንም በውስጡ መንፈስ ተደብቋል፡፡
ችግራችሁን ደብቃችሁ ይህን ካደረጋችሁ ባህር ቢናወጥና ሰማይ ቢወድቅ እንኳን አንዳች አይደርስባችሁም፡፡ (ተስፋሁን ምትኩ እና ሀብታሙ ተስፋዬ፣ የጥበብ መንገድ"ትርጉም"፣ 1998) አምባገነናዊነትን ማፈራረስ የህብረተሰቡ ተቋማዊ ለውጥ እየተካሄደ ባለበት ወቅት፣ ተቃውሞና ትብብርን የመንፈግ እንቅስቃሴዎች እየጨመሩና እየጐለበቱ መሄድ አለባቸው፡፡ የዴሞክራሲያዊ ትግል መርህ ነዳፊዎች ማሰብ ያለባቸው በአገዛዙ ላይ ከሚደረጉ ውሱን የተመረጡ የተቃውሞ እርምጃዎች የዘለለና ጠንከር ያለ ሀገር አቀፍ ተቃውሞ ለማድረግ መዘጋጀትንም ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቱን ሀገር አቀፍ ህዝባዊ ተቃውሞ ለማዘጋጀትና ለማቋቋም፣ የተቃዋሚ ኃይላትንም ብቃት ለመገንባት በቂ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ምናልባትም ዓመታት ሊፈጅ ይችላል፡፡ በዚህ የዝግጅት ጊዜ ግን የተመረጡ ተቃውሞዎች ከአመርቂ የፖለቲካ ዓላማ ጋር በተከታታይ መካሄድ አለባቸው፤ በየደረጃው የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍልም ጠንክሮ መሳተፍ አለበት፡፡ ቆራጥነትና ሥርዓታዊነት የተሞላባቸው ፖለቲካዊ የተቃውሞ እርምጃዎች እየጐለበቱ ሲሄዱ የአምባገነናዊ አገዛዙ ውስጣዊ ድክመት እየጐላ መምጣቱ እያደር ገሀድ ይወጣል፡፡ (አሰፋ ኃይሌና ሌሎች፣ ከአምባገነን አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ"ትርጉም"፣ 1998) ክልክል ነው ማጨስ ክልክል ነው ማፍዋጨት ክልክል ነው መሽናት ክልክል ነው ግድግዳው በሙሉ ተሰርቶ በክልክል የቱ ነው ትክክል? ትንሽ ግድግዳና ትንሽ ኃይል ባደለኝ "መከልከል ክልክል ነው"፤ የሚል ትዕዛዝ አለኝ፡፡ (በእውቀቱ ስዩም፣ የ፣ሣት ዳር ሐሳቦች፣ 2000) ተጠርጣሪ ወይም በወንጀል ጥፋተኛ የሆኑ ሴቶችን ጉዳይ የሚያጣሩ የፖሊስ አባላት የሚመሩባቸው ታሳቢ መርሆዎች • ሴቶች ቃላቸውን ሲሰጡ፣ ሲታሰሩ ወይም ሲያዙ የአያያዙ ወይም የምርመራው ሂደት በሴት ፖሊስ ባልደረቦች ወይም በእነርሱ መሪነት ሊከናወን ይገባዋል፡፡ • ሴት ፖሊስ በተገኘችበት ካልሆነ፣ በቁጥጥር ሥር በዋለች ሴት እና በወንድ ፖሊስ መካከል አካላዊ መነካካት ሊኖር አይገባም፡፡ • በቁጥጥር ሥር በዋሉት ሴቶች ላይ የሚደረግ ምርመራ በአስቸኳይ፣ በጥንቃቄና ያለማዳላት መከናወን ይገባዋል፡፡ • በተቻለ መጠን ሴቶች በሴት የፖሊስ አባላት ሊጠበቁ ይገባል፡፡ • በቁጥጥር ሥር የዋሉ ወንዶችና ሴቶች፣ ተለያይተው ሊታሰሩ ይገባል፡፡ ሴት ታሳሪዎች በሴት የፖሊስ አባላት ሊፈተሹ ይገባል፡፡ • ለአረገዙ፣ ለሚያጠቡና ሕፃናት ልጆች ላሏቸው ታሳሪዎች የበለጠ ጥንቃቄ ሊደረግላቸው እና ከተቻለም የተለየ አገልግሎት እና አቅርቦቶች ሊያገኙ ይገባል፡፡ (ፍትህ ሚኒስቴር፣ ሰብዓዊ መብቶች ሕጎቹና አፈጻጸማቸው፣ 1999) "ምኒልክ ይሙት"" በ1928 ዓ.ም. አፄ ምኒልክ በሕይወት አልነበሩም፡፡ ካረፉ ሃያ ሁለት ዓመታት አልፈው ነበር፡፡ በነዚያ ሃያ ሁለት ዓመታት ውስጥ ሦስት ነገሥታት ቢቀያየሩም አንዳቸውም በኢትዮጵያ ምድር ላይ አሻራቸውን አልተውም ነበር፡፡ በየቦታው የሚታየው የምኒልክ አሻራ ነበር፡፡ ታላቁ ቤተ መንግሥት የተሠራው በእሳቸው ዘመን . . . ለመጀመሪያ ጊዜ የባቡር መሥመር የተዘረጋው በሳቸው ዘመን . . . የአራዳው ጊዮርጊስ ታቦት የቆመው በሳቸው ዘመን . . . የህትመት ሥራ፣ የቴሌፎንና የቴሌግራም አገልግሎት፣ የባንክ አገልግሎት፣ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና በርከት ያሉ ሌሎች ዘመናዊ ሥራዎች የተተለሙትና በሥራም ላይ የዋሉት በእሳቸው ዘመን ነበር፡፡ በ1928 ዓ.ም. የምኒልክ ትዝታ በሕዝቡ አእምሮ ውስጥ ሰፍኖ ይገኝ ስለነበረም የአዛውንቱ መሐላ ምኒልክ ይሙት ነበር፡፡ (ሣህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም፣ ባሻ ቅጣው፣ 1976) "ስነው" በኢትዮጵያ ውስጥ "ስነው" አይታይም፡፡ "ስነው" የሚለው ቃል አየሩ ለተለመደው ዝናብ በጣም በሚቀዘቅዝበት ጊዜ እንደ ባዘቶ ጥጥ ከሰማይ ብን ብን እያለ የሚወርደውን ለስላሳ ነጭ ብናኝ የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ ስነው በከፍተኛ ሁኔታ ሲወርድ፣ እይታን ይሸፍንና ለማየት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ለስላሳው ነጭ ብናኝ መሬት ላይ ይከማችና ተራሮችን፣ ዛፎችንና ቤቶችን ሳይቀር ሁሉንም አካባቢ በለስላሳው ነጭ ብርድ ልብስ ይሸፍነዋል፡፡ ስነው በጣም ጥልቅ ሊሆን ይችላልና ገና በአዲስነቱ ሳለ ያማረ ሆኖ ይታያል፡፡ አየሩ ሲቀዘቅዝ፣ ስነው ግግር ሊሆን ይችላል፤ ከዚያም ጠጣር ይሆንና ስለሚያንሸራትት በእርሱ ላይ መራመድ አደገኛ ነው፡፡ አየሩ ሲሞቅና ስነው ሲሟሟ ወደ ውኃነት ይለወጣል፡፡ አልፎ አልፎ የአየሩ ሙቀት መለዋወጥ ብዛት ያለው ስነው ከተራራው ጎን ተደርምሶ እንዲወርድ ያደርጋል፡፡ ይህ ናዳ ተብሎ ይጠራል፡፡ እየሟሟ ያለው ስነው በዚህ ዓይነት ኃይል ዛፎችን ሊነቃቅልና ቤቶችንም ሊያፈራርስ ይችላል፤ በዚህ ወቅት ተራሮች ላይ የሚወጣ ማንኛውም ሰው በስነው ውስጥ የመቀበር አደጋ አለበት፡፡ (ገበየሁ አየለ"ትርጉም"፣ አስደናቂው የይቅርታ ቅርስ፣ 1997) ዐፄ ተክለ ጊዮርጊስ ለፈረንሳይ ንጉሠ ነገሥት ለናፖሊዮን የፃፉት በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ አፄ ተክለ ጊዮርጊስ፡፡ ይድረስ እግዜር ከሰው መርጦ ካነገሠዎ ንጉሠ ነገሥት ናፑልዮን፡፡ እንዴት አሉ፤ ደህና አሉን፣ እጅጉን" እኔ የርስዎን ወዳጅነት እጅግ እፈልገዋለሁ፤ በረከትም ልሰድልዎ ወድጄ ነበር፡፡ ነገር ግን መንገዱ አልተመቸኝም፡፡ የፍቅር ወረቀት ብቻ መስደዴ የመላላክ መጀመሪያ እንዲሆን፣ የርስዎንም ፍቅር መፈለጌ ምልክት ይሆንዎ ብዬ ነው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ያከፉትን ሁሉ ከምክርዎና ከፍቅርዎ ጋራ በእግዚአብሔር ኃይል አቀናዋለሁ ብዬ አስቤአለሁ፡፡ እኔ ባገሬ ቆንስላዎ እንዲገባ፣ ያገርዎም ነጋዴ ገብቶ እንዲገበይ፣ እኔም የምፈልገው በርስዎ ፈቃድ እንዲሆንልኝ እወዳለሁ፡፡ ደጃች ካሳ አያቱ ላያቴ፣ አባቱ ላባቴ ተገዝቶ ታዞ ይኖር ነበረ፡፡ እርሱንም እኔ ሹሜ አገር ጠብቅ ብዬ ብተወው አምጦ አልታዘዝም አለ፤ አሁን ግን የምጠይቀው ነኝና አይፍረዱብኝ፡፡ ይህን መልክት በሌላ እጅ መስደዴ ሰውን ባላምን ነው፡፡ ከጌታችን ልደት በሺሕ ከስምንት መቶ ስድሳ ሁለት ዓመት፣ በዘመነ ማርቆስ ወንጌላዊ፣ በሐምሌ መጀመሪያ ቀን፡፡ (ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ ዐፄ ዮሐንስ እና የኢትዮጵያ አንድነት፣ 1982) ገ ራ ገ ር አጫሹ ባስከተለው ፍንዳታ ታሰረ አንድ ሲጋራ አጫሽ እየተንቀሳቀሰበት ባለው መኪና ውስጥ ይዞት የነበረውና የፍንዳታ ድምፅና መብራት የሚፈጥረው መሳሪያው በሲጋራ እንዲፈነዳ በማድረጉ በአሜሪካ ለእስር እንደተዳረገ ፓውቱኬት ታይምስ ዘግቧል፡፡ የ28 ዓመቱ ፍራንሲስ ስትራንኮ የታሰረው የሚፈነዳውን መሳሪያ በመያዙ ነው፡፡ እስሩን የፈፀመው ፖሊስ ዴቪድ ዮሴፍ በመኪና ውስጥ ፍንዳታ መከሰቱን ሪፖርት ተደርጎለት ግዳጁን እንደፈፀመ ተናግሯል፡፡ ፖሊሱ በተጠቆመበት ቦታ ሲደርስ ከመኪናዋ በርካታ ጭስና የፍንዳታ ሽታ እንዳጋጠመውም ገልጿል፡፡ አሽከርካሪው ስትራንኮ መሳሪያዎቹ የፈነዱበት በድንገት እንደሆነ አመልክቷል፡፡ በፍንዳታው ምንም ዓይነት ጉዳት ያልደረሰበት ስትራንኮ ፍንዳታው በድንገት ሲከሰት ሲጋራ እያጨሰ እንደነበር ግን ለፖሊስ አልካደም፡፡ ዘገባው በርካታ ነዋሪዎች ፖሊስ ከስፍራው ከመድረሱ በፊት አሽከርካሪው የሚፈነዱ መሳሪያዎችን ከመኪናው ላይ እየወረወረ ሲጥል እንዳዩ መናገራቸውን ጠቁሟል፡፡ ሰውየው የሚስቱን ፓስፖርት በላ አንድ የሩሲያ ዜጋ የቀድሞ ሚስቱን ፓስፖርት በጉዞአቸው ወቅት ከበላ በኋላ ለእስር መዳረጉን አናኖቫ ዘግቧል፡፡ የሩሲያ ፖሊስ የ31 ዓመቱን ኢቫን ቮሎኮቭን በኒዝኒኖቭጎሮድ በቁጥጥር ስር ያዋለው የቀድሞ ሚስቱን የአናን ፓስፖርት ከቀዳደደ በኋላ ቁርጥራጮቹን በሙሉ ከበላ በኋላ ነው፡፡ የፖሊስ ቃል አቀባይ "ጥንዶቹ በቅርቡ ቢፋቱም የሚኖሩት በአንድ ቤት ጣሪያ ስር ነው፡፡ ባልየው የቀድሞ ሚስቱን ፓስፖርት ማውደም የፈለገው ሴትየዋ በቤቱ የመኖር ህጋዊ መብት እንዳላት የሚያሳይ ብቸኛ ይፋዊ ሰነድ በመሆኑ ነው" ብሏል፡፡ ቮሎኮቭ ይፋዊ ሰነድን በማውደምና በህይወት ላይ ስጋት በሚጥል ባህሪ ተከሷል፡፡ ፓርቲ አሳዳጁ ከእንግሊዝ ሙኒክ ለመድረስ 2 ሺህ ፓውንድ ከፈለ ከእንግሊዙ ፖርትስማውዝ ከተማ ተነስቶ የቢራ ፌስቲቫል ወደሚደረግበት የሙኒክ ከተማ ጀርመን ያለውን 740 ማይል (1184 ኪሎ ሜትር) ለመድረስ አንድ ፓርቲ (ድግስ) አሳዳጅ እንግሊዛዊ፣ ለታክሲ ነጂው ወደ 2 ሺህ ፓውንድ የሚጠጋ ገንዘብ መክፈሉን ዴይሊ ሚረር ዘግቧል፡፡ የታክሲ ሹፌሩ ሚክ ሆጋን፣ በ3ዐዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኘው ዴቭ ወደ ሙኒክ ስለመሄድ በጉጉት ሲያወራ እየቀለደ መስሎት እንደነበርና በኋላ ላይ ግን ወደ ሙኒክ ሊያደርሰው የሚችለው የመጨረሻው አውሮኘላን ስላመለጠው መሆኑን ሲያስረዳው እንዳመነው ገልጿል፡፡ የ3 ልጆች አባት የሆነው ሚክ ሙኒክ ለመድረስ 1950 ፓውንድ እንደሚያስፈልግ ለዴቭ ሲነግረው ዴቭ ያለማመንታት ገንዘብ የታጨቀ ቦርሳ እያሳየው መስማማቱንም ተናግሯል፡፡ ለሚክ ስራው በጣም አትራፊ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን ሙኒክ ለመድረስ ፈረንሳይ፣ ቤልጂየምና ሉክሰንበርግን ለማቋረጥ 17 ሰዓታት ፈጅቶበታል፡፡ ሚክ "ይህ ዓይነት ሥራ በየቀኑ ለመስራት የምትመኘው፣ ነገር ግን በአጋጣሚ ብቻ የምታገኘው ነው" ብሏል፡፡ የጠፉ ፔንጉኖች በብራዚል አየር ኃይል ተገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፔንጉኖች (ርግብ መሰል) ጠፍተው ከቆዩ በኋላ ከተገኙበት የብራዚል ጠረፍ በብራዚል አየር ኃይል አማካይነት ወደ ትውልድ ቀያቸው ወደ ደቡብ አትላንቲክ ውቅያኖስ መመለሳቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ምንም እንኳን በየዓመቱ ፔንጉኖች ከቀዝቃዛው ደቡብ ወደ ሞቃታማው ሰሜን ከፓታጎኒያ አቅራቢያ በመነሳት ምግብ ፍለጋ መጓዛቸው አዲስ ባይሆንም የዘንድሮው የጉዞ ርቀት ባለስልጣናቱን አስገርሟል፡፡ አንዳንድ ፔንጉኖች እስከ 3000 ኪሎ ሜትር ርቀት እንደተጓዙ የጠቆመው የቢቢሲ ዘገባ ባለሙያዎች ክስተቱን በአሳ የምግብ አቅርቦት ዙሪያ ከተፈጠረ ያልተለመደ እጥረት ጋር እንዳገናኙት ገልጿል፡፡ በርካታ ፔንጉኖች በአየር ለውጡና በሰው ሰራሽ ብክለቱ የተነሳ የብራዚልን ጠረፍ ያጥለቀለቁት ሲሆን የሃገሪቱ አየር ኃይል ከተለመደ ተግባሩ ባሻገር ፔንጉኖችን እንዲያጓጉዝ አስገድዶታል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |